የሊማዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የሊማዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ

የዛሬ አምስት ዓመት ኮፐንሃገን የተካሄደዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ጉባኤ ብዙ ተብሎለትና ብዙ ተጠብቆበት ካለ ዉጤት መጠናቀቁ ብዙዎችን ግራ ያጋባ ብቻ ሳይሆን ተስፋም ያስቆረጠ መስሎ ነበር።

በወቅቱ በተለይ የአየር ንብረት ለዉጥ ለሚያስከትላቸዉ መዘዞች የተጋለጡ በኢንዱስትሪዉ ያላደጉ ሃገራት ተሰሚነታቸዉ ከፍ ብሎ የግዙፍ እንዱስትሪዎች ባለቤቶች የሆኑ መንግሥታት የፖሊሲ ለዉጥ ሊያደርጉ የሚያስችል የፖለቲካ ዉሳኔ ያስወስናሉ የሚለዉ ግምት የአፍሪቃ መሪዎች ፓሪስ ላይ ካካሄዱት የግል ዉይይት በኋላ ባልተጠበቀበት አቅጣጫ መጓዙ ብዙ የተባለበትና በአንድ ጎራ የተሰለፉ የመሰሉትን የከፋፈለ አጋጣሚ ሆኖ ማለፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነዉ።

ከኮፐንሃገኑ ጉባኤ በኋላ በየደረጃዉ በተለያዩ ቦታዎች ጉባኤዉ ዓመቱን ጠብቆ ቢካሄድም ይህ ነዉ የሚባል ተጨባጭ ዉጤት ሳያስገኝ ቆይቷል። እንዲያም ሆኖ አሁንም የአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ የመነጋገሪያ አጀንዳነቱ እንዳልተዘጋ ባለፈዉ ሳምንት ሊማ ፔሩ ላይ የተጀመረዉ ዓመታዊ ጉባኤ ግልፅ አድርጓል።

ከዘንድሮዉ ጉባኤ ቀደም ብሎም በመካከላቸዉ ባለዉ ፉክክር ምክንያት የበካይ ጋዞች ቅነሳ ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት ሲሆኑ የከረሙት ዩናይትድ ስትቴትስና ቻይና ከዚህ በፊት ያደርጉት የነበረዉን ወደጎን በማለት ከባቢ አየርን የሚበክለዉን አደገኛ ጋዝ ለመቀነስ በሚካሄደዉ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የመሳተፍ ፈቃደኝነትን ማሳየታቸዉ እንደአዎንታዊ ምልክት ተወስዷል።

በመካሄድ ላይ የሚገኘዉ 20ኛዉ የአየር ንብረት ለዉጥን የተመለከተዉ ጉባኤ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ጉባኤዎች የሚለይባቸዉን ነጥቦች የዘረዘሩት ኢትዮጵያዊዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ተሟጋች አቶ አየለ ከበደ በተለይ የኮፐንሃገኑን ጉባኤ ለማነፃፀሪያነት በማንሳት አዎንታዎ ነገሮች እንዳሉ ነዉ የሚናገሩት፤

ጉባኤ በተጀመረ በሳምንቱ ከባቢ አየርን በከፍተኛ ሁኔታ እየበከሉ የሚገኙ ሃገራት ብክለቱን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸዉ አዉስትራሊያ አመልክታለች። የአዉትራሊያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጁሊ ቢሾፕ ኢንዱስትሪዎቻቸዉ ከባቢ አየርን በጣም እየበከሉ የሚገኙ ሃገራት ኃላፊነቱ በእነሱ ትከሻ መሆኑን ሊያዉቁት ይገባል ነዉ ያሉት። ፤

ያ ካልሆነ ግን ሌሎች ሃገራት በየበኩላቸዉ ብክለቱን ለመቀነስ የሚያደርጉትን ጥረት ቢተዉት እንደሚሻልም ተናግረዋል። እሳቸዉ እንደሚሉትም እነዚህ ሃገራት ብክለቱን ለመቀነስ የሚያደርጉት ጥረት ከባቢ አየርን በከፍተኛ ሁኔታ የሚበክሉት ሃገራት ምንም ለዉጥ ሳያደርጉ ከቀጠሉ ቸልተኝነታቸዉ የእነሱን ልፋት ዋጋቢስ እንደሚያደርገዉ ግልፅ አድርገዋል። ይህ እንዳይሆን ግን የበለፀጉትና በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት በመጠኑ ካደጉት እና ከድሀ ሃገራት ሳይፎካከሩ በሚበክሉት መጠን ልክ ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል። 23 ሚሊዮን ኗሪ ያላት ሀገራቸዉ በድንጋይ ከሰል በሚመነጭ ኃይል ተጠቃሚ ስትሆን ከባቢ አየርን የሚበክል አደገኛ ጋዝ ከሚለቁ ሃገራት አንዷ ናት። ይህን የተገነዘበዉ የሀገራቸዉ መንግሥትም የብክለት መጠኑን በአምስት በመቶ ለመቀነስ መዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።

ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ በሳይንሳዊ መረጃዎች መሠረት የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ ማድረግ እስከተቻለ ድረስ የተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ነዉ የተስማማዉ። እንዲያም ሆኖ የአየር ንብረት ብከላዉ እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት የታለመዉን እንኳ ማሳካት እንደማይቻል ምልክምት መታየት መጀመሩን በጀርመኑ የፖትዳም የአየር ንብረት ለዉጥ ተፅዕኖ ምርምር ተቋም ፕሮፌሰር የሆኑት ሽቴፋን ራሃምሽቶርፍ ይናገራሉ።፤

«የአየር ንብረት ለዉጥ ተከስቷል፤ የሰዎችንም ህይወት እየጎዳ ነዉ። ይህም የሆነ በተከሰተዉ መጠነኛ የመሬት የሙቀት መጠን መጨመር ነዉ ይኸዉም ከአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ያነሰ ማለት ነዉ። እናም ይህን ለዉጥና ሂደት ማስቆም ካልቻልን ወደሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ እና ከዚያ በላይም ከፍ ማለታችን አይቀርም። በዚህም በሰዉ ልጅ ኑሮ ታሪክ ከተለመደዉ በላይ እናልፍና ከቁጥጥር ዉጭና አደረገኛ ዉሃዎችን ለመጋፈጥ እንገደዳለን።»

የዘርፉ ምሁራን ወደከባቢ አየር የሚለቀቀዉ የበካይ ጋዞች መጠን ትርጉም ያለዉ ቅነሳ ካልተደረገበት በቀር የዓለም የሙቀት መጠን በቅርቡ እስከአራት ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ ሊል እንደሚችል ነዉ የሚያሳስቡት። አሁን በእጅ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ከፍ ሳይል እንዲቆይ ለማድረግ በቀጣይ አስር ዓመት ዉስጥ በጣም ቀንሶ በያዝነዉ ምዕተ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ዓለም ከካርቦን ነፃ የምትባልበት ደረጃ መድረስ ይኖርባታል። ይህን እዉን ለማድረግም ከፔሩዉ የአየር ንብረት ጉባኤ አዎንታዊ ዉጤት እንደሚጠበቅ ነዉ የመንግሥታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ጉዳይ ኃላፊ ክርስቲና ፍጎርስ ያመለከቱት።፤

«ሃገራት በሙሉ በየበኩላቸዉ በመጪዉ ዓመት ሊያደርጉ የሚችሉትን አስተዋፅኦ ጠረጴዛዉ ላይ ያስቀምጣሉ ብለን እንጠብቃለን። ሆኖም ለዚያ የሚሰጠዉ ቀነ ገደብ እስከ መጋቢት 2015ዓ,ም ብቻ አይደለም። እናም ሊደረግ የሚቻለዉን ያመላክታሉ ብለን ነዉ የምንጠብቀዉ፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ሃገራት በአሁኑ ወቅት የየራሳቸዉን የቤት ሥራ እየሠሩ ነዉ። ማለትም ብሄራዊ መመዘኛ በማስቀመጥ ምን ማድረግ እንደሚችሉ፤ ከፖለቲካ፣ ከማኅበራዊና ኤኮኖሚ ፤ እንዲሁም ከቴክኒክ አኳያ እነሱ ለመፍትሄዉ ማድረግ የሚችሉትን አስተዋፅኦ ይመለከታሉ። ሆኖም እስከሚመጣዉ ዓመት ድረስ የመጨረሻዉ ቁጥር አይታወቅም።»

በትናንትናዉ ዕለት በጉባኤዉ የሚሳተፉ የላቲን አሜሪካን ሰባት ሃገራት 20 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስከመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020ዓ,ም ድረስ በደን ለማልበስ ቃል መግባታቸዉ ተሰምቷል። ወደከባቢ አየር የሚለቀቀዉን ካርቦን ዳይኦክሳይድ በዛፎቹ ለመምጠጥ ለታቀደዉ ፕሮጀክትም ባለሃብቶች 365 ሚሊዮን ዶላር ሥራ ላይ ለማዋል በበኩላቸዉ ቃላቸዉን ሰጥተዋል።፤

ከአየር ንብረት ጉባኤዉ በተጓዳኝ የቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኮስታ ሪካ፣ ኤኳዶር፣ ጓቲማላ፣ ሜክሲኮና ፔሩ የግብርና እና የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮች ባካሄዱት ስብሰባ ደን ለማልማት ያሳለፉት ዉሳኔ እግረ መንገዱንም የአፈርን መከላት እንደሚታደግም ተገልጿል። የደን ሃብቷ መራቆቱን ይፋ ያደረገችዉ ፔሩ 3,2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዛፎች ለመሸፈን መዘጋጀቷን ስታመለክት፤ ሜክሲኮ በበኬሏ 8,5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ለማልበስ መቁረጧን አስታዉቃለች። በጉባኤዉ ቆይታ በተለይም ባለፈዉ ቅዳሜና ትናንት ሰኞ 17 በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት በየበኩላቸዉ ሊቀንሱ ያሰቡትን የበካይ ጋዞች መጠን እንዲያሳዉቁ በጉባኤዉ ተሳታፊ ሌሎች ሃገራት እንደሚጠየቁ ነዉ የተገለፀዉ። በሊማዉ ጉባኤ ከሚካሄዱ ዉይይቶች በመነሳትም የሚወሰኑ ዉሳኔዎች ዘመኑ ያበቃለትን የኪዮቶ ስምምነት ሊተካ የሚያስችል አዲስ ዉል በመጪዉ ዓመት ፓሪስ ላይ ለመድረስ ያስችላሉ የሚለዉ ግምት እየተሰማ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic