የሉተር ተሀድሶ 500ተኛ ዓመት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 07.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የሉተር ተሀድሶ 500ተኛ ዓመት 

ጀርመናዊው የቀድሞ የካቶሊክ መነኩሴ በኋላም የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መሥራች ዶክተር ማርቲን ሉተር የካቶሊክ እምነት የቀኖና ስርዓቶችን በይፋ የተቃወሙበት እና የተሃድሶ እንቅስቃሴ የጀመሩበት 500ተኛ ዓመት ባለፈው ሳምንት በመላ ጀርመን ተከብሯል። የፕሮቴስታንት መሠረት በሆነችው በጀርመን ግን የእምነቱ ተከታዮች ቁጥር ክፉኛ አሽቆልቁሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:13 ደቂቃ

በጀርመን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ቁጥር ተመናምኗል

ቪትንበርግ ፣በምሥራቅ ጀርመኑ የዛክሰን አንሀልት ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ውስጥ የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ናት። ኤልበ በተሰኘው ወንዝ ዳር የተቋረቆረችው ይህች ከተማ የዛሬ 500 ዓመት በካቶሊክ ሃይማኖት የቀኖና ስርዓት ላይ በተነሳ ተቃውሞ እና ተቃውሞውን በተከተለው የተሀድሶ እንቅስቃሴ  ትታወቃለች። የያኔው የካቶሊክ መነኩሴ ማርቲን ሉተር በጎርጎሮሳዊው ጥቅምት 31 ፣ 1517 የቤተክርስቲያኗን የቀኖና ስርዓቶች በመቃወም ተሃድሶ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ስርዓቶች በዝርዝር ያሳወቁበትን ጽሁፍ ለህዝብ ይፋ ያደረጉት በዚህች ከተማ ነበር።

የሥነ መለኮት መምህር እና በኋላም የተሀድሶው መሪ ዶክተር ሉተር በቪትንበርግ ከተማ ማዕከል በሚገኘው «የመላ ቅዱስን ቤተክርስቲያን» በር ላይ ትችታቸውን ያሰፈረበትን ጽሁፍ መለጠፉቸው ይነገራል። መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው ከፍተኛ ትምህርታቸውን ጀርመን የተከታተሉ የስነ መለኮት ምሁር ናቸው። የሉተር ተቃውሞ ምን እንደነበር እና ተከታዮችን እንዴት ማፍራት እንደቻለ ያስረዳሉ። በዚህ ተቃውሞ ምክንያት ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተወገዱት ሉተር የፕሮቴስታንት ወይም ወንጌላውያንን ቤተ ክርስቲያን መሠረቱ። በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ በመላው ዓለም ከ800 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች አሏት። ይሁን እና መሪጌታ ዳዊት እንደሚሉት ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሄደ እንጂ በአንዴ የተገኘ ውጤት አልነበረም። 

በአሁኑ ጊዜ ሉተር የተሀድሶ እንቅስቃሴ በጀመረባት በበቪትንበርግ ከተማም ይሁን በሌሎች የጀርመን ከተሞች የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ቁጥር ተመናምኗል። 48 ሺህ አምስት መቶ ነዋሪዎች ካሏት የተሀድሶው የትውልድ ስፍራ ቪትንበርግ የፕሮቴስታንቶች ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ 12 በመቶ ብቻ ነው። በከተማዋ ቤተ ክርስቲያኖች በሚካሄዱ የፀሎት ስርዓቶች ላይ የሚገኙትም ቁጥር አነስተኛ ነው። እንዲያውም ከስርዓቱ ተካፋዮች አብዛኛዎቹ ከተማዋን ለመጎብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች ናቸው።

በዚህች ከተማ ውስጥ የሚገኘው ሉተር አዘውትረው ያስተምሩባት የነበረው እና የመጀመሪያው የፕሮቴስታንት የፀሎት ስርዓትም የተካሄደባት የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የጎብኚዎች መስህብ ናት። ቪትንበርግ ዘንድሮ 500ተኛውን ዓመት የሉተር ተሃድሶ ዐውደ ርዕዮችን ጨምሮ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብራለች። ቤንያሚን ሃስልሆርን በከተማይቱ የተዘጋጀው ልዩ ዐውደ ርዕይ ሃላፊ ናቸው። ሉተራዊነት እያበቃ ይሆን? የተሰኘ መፀሀፍ የጻፉ ፕሮቴስታንት የስነ መለኮት ምሁር ናቸው። የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ቁጥር መቀነስ እጅግ ያሳስባቸዋል። «እድሜዬ 31 ዓመት ነው። ቤተክርስቲያን ሁሌም የሚመጣ ሰው ብዙ አላውቅም። ቤተክርስቲያን ጥለው የወጡ ብዙ ሰዎች አውቃለሁ። ወላጆቻችን እና ቅድመ አያቶቻችን ሲሞቱ ማን ቤተ ክርስቲያን እንደሚመጣ በእውነት አላውቅም። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ከቀጠለ የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ወደፊት በጣም ትንሽ ቡድን ይሆናል።»

በጎርጎሮሳዊው 1990  37 በመቶው የጀርመን ዜጋ ፕሮቴስታንቶች ነበሩ። አሁን የቤተክርስቲያኗ የተመዘገቡ አባላት ቁጥር 27 በመቶ ብቻ ነው። ከ8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከ1990 ወዲህ ወይ ሞተዋል አለያም ቤተ ክርስቲያኑን ለቀው ሄደዋል የሚል ግምት ነው ያለው። ይህ ማለት ደግሞ ቤተ ክርስቲያኑ ገቢ እያጣ ነው። በጀርመን በቤተክርስቲያን የተመዘገበ ማንኛውም አባል ለቤተክርስቲያኑ የውዴታ ግዴታ የሆነውን ክፍያ ይፈጽማል። ይህንንም ገንዘብ መንግሥት ከሠራተኞች ደሞዝ እየቆረጠ በገቢ ቀረጥ ክፍል አማካይነት ለሚመለከታቸው አብያተ ክርስቲያናት ያስተላልፋል። የአባላት ቁጥር አነሰ ማለት ገቢውም ይቀንሳል ማለት ነው።

የቪትንቤርግ ቅድሥት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፓስተር ዮሐንስ ብሎክ ችግር አሁንም እየተሰማን ነው ይላሉ።«በአሁኑ ጊዜ የገንዘብ ማነስ ያስከተለው ተጽእኖ ክፉኛ እየተሰማን ነው። ምክንያቱም ከባልደረባችን አንዱ በመሰናበቱ በሁለት ፓስተሮች ብቻ ነው አገልግሎት የምንሰጠው። ወደፊት በቋሚነት የሚያገለግሉ ተቀጣሪዎች ቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ ነው። እናም የእምነቱ ተከታዮች በጥቂት የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች እና ፓስተሮች ብቻ ነው አገልግሎት የሚያገኙት። »

ለምዕተ ዓመታት የጀርመን ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያን እና ፓስተሮችን ለማግኘት ርቀው መሄድ አልነበረባቸውም። አሁን ግን እየተለወጠ ነው። ቤተ ክርስቲያኖች እየተዘጉ ነው። የፓስተሮችም ቁጥር ይቀንሳል ተብሎ ነው የሚገመተው። ለምሳሌ ሁለቱ የቪትንቤርግ ፓስተሮች የሚያገለግሉት በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ብቻ አይደለም። በሌሎች ቤተክርስቲያናትም ጭምር እንጂ። የቤተክርቲያኗ ሰበካ ጉባኤ አባላት ቁጥር 3800 አካባቢ ነው። ሆኖም ቄስ ዮሐንስ ብሎክ እንደሚሉት እጅግ አሳሳቢው የወደፊቱ ነው።«ወደፊት የፀሎት ስነስርዓት ቤት ወደሚካሄድበት ደረጃ እያመራን ነው። ክርስትና ወደ ትላላቅ ከተሞች የተሰበሰበ ይመስለኛል። የእኛ ቁጥር እያነሰ ነው የሚሄደው። እንደሚመስለኝ ለህዝቡ የምንሰጠውን አገልግሎት ማጠናከር አለብን። ምናልባት ጭንቀቱ እና ብዙው ሃላፊነት ስለሚቀልልልን በመጠኑ ደስተኛ ነን።»

የቪትንበርግዋ ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ የተለያዩ ትርዒቶችን እና ዝግጅቶችን በማቅረብ ነዋሪዎችን ለመሳብ ይጥራል። ይሁን እና ቪትንቤርግ እና ሌሎችም የጀርመን ከተሞች  ዋነኛ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የነበሩበት ዘመን ግን እስከ ወዲያኛው የቀረ ይመስላል። ጀርመን ለ17 ዓመታት የኖሩት የስነ መለኮት ምሁር እና በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የኑርንበርግ ቅድሥት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መሪ ጌታ ዳዊት ከፋያለው እንደሚሉት በጀርመንም ሆነ በሌሎች የአውሮጳ ሀገራት ቁጥራቸው የተመናመነው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ብቻ አይደሉም። በጀርመን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም የሉተር ተሀድሶ መነሻ ቪትንበርግ ግን አሁንም በአገር ጎብኝዎች መስህብነትዋ እንደቀጠለች ነው። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic