የለገጣፎ ጩኸትና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 22.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የለገጣፎ ጩኸትና የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ

የለገጣፎ የቤት ማፍረስ ተግባር እና የኦዲፓ መግለጫ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን እያነጋገረ ነው። በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ሕገ-ገወጥ በሚል መፍረሳቸው የሳምንቱ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ሰፊ መነጋገሪያ ኾኗል። የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በፌዴራሊዝሙ አልደራደርም ማለቱም ሌላኛው ዐቢይ መነጋገሪያ ነበር። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:17

«በአጭር ትውስታ ብቻ ነው የምንበረግገው»

በየሳምንቱ አንዳች የመነጋገሪያ ርእስ የማያጣው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ አኹን ደግሞ የለገጣፎ የቤት ማፍረስ ተግባር እና የኦዲፓ መግለጫ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን እያነጋገረ ነው። መብራት እና ኤሌክትሪክ በመንግሥት ገብቶላቸው ከኹለት ዐሥርተ-ዓመታት በላይ ከኖሩበት ቤታቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የለገጣፎ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው በርካቶችን አስቆጥቷል። ነዋሪዎቹ ቤታቸው ሕገ-ወጥ ነው ተብሎ ከመፍረሱ በፊት መሬቶቹን ሲያሻሽጡ የነበሩ ሕገ-ወጦች ምን ተደረጉ? የሚል ጥያቄም አስነስቷል። የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ «ODP» በፌዴራሊዝሙ ላይ እንደማይደራደር መግለጡ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ተጨማሪ የመነጋገሪያ ርእስም ኾኗል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ትጥቅ እየፈታ ወደተዘጋጀለት ጊዜያዊ የጦር ሰፈር መግባቱም አወያይቷል። 

በለገጣፎ ቤቶች መፍረሳቸው

«የሚያድግ ልጅ አይጥላህ፤ ለገጣፎ» ይላል የማዳም ደመቂያ አጭር የትዊተር መልእክት። ከመልእክቱ ጋር ፎቶግራፍም ተያይዟል። የብረት ግቢ ያለው ዘመናዊ ሕንጻ ጣራ ላይ የቆሙ ሰዎች ይታያሉ። እግቢው በራፍ ላይ ሰዎች ተሰብስበው ጣራ ላይ ያሉትን ይመለከታሉ። ከእነዚህ ሰዎች በስተቀኝ አንድ ትንሽ ልጅ ጣሪያው ላይ ያሉትን ሰዎች ይመለከታል። ጣራያው ላይ የቆሙት ጣሪያውን ለማፍረስ ነው።

ብሬቤስት በሚል የትዊተር ስም የቀረበ ሌላ ጽሑፍ  ደግሞ፦«ለገጣፎ ላይ የሆነው ግፍ» ሲል ይንደረደራል። ከጽሑፉ ጋር ፎቶግራፍ ተያይዞበታል።  ፎቶግራፉ ላይ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ሕጻናት ከፊት ከኋላ ደግሞ አዋቂዎች ተስብስበው ይታያሉ። መልእክቱ እንዲህ ይቀጥላል፦ «ህፃናት ከት/ቤት ሲመለሱ ተወልደው ያደጉበት ቤት፤ በመሬት ወራሪዎች በልማት ስም ፈርሶ ጠበቃቸው። ይህ ሁሉንም የሠው ልጅ ይመለከታል።»

ዳግም አ መኮንን በትዊተር ገጹ የቢቢሲ አማርኛ ድረ-ገጽ ዘገባ ላይ ከወጣ ጽሑፍ የተወሰነውን ቀንጭቦ አቅርቧል። «ሚስቴ ከወለደች ሦስት ቀኗ ነዉ» ሲል ይንደረደራል ጽሑፉ። «ከቤት ተባርራ ጎዳና ላይ ነች። ቤቱን ሲያፈርሱት እባካችሁ ሚስቴ ከወለደች ሦስት ቀኗ ነዉ ትንሽ ታገሱኝ ስል 'ምን አገባኝ ከእኔ አልወለደች' ሲል አንደኛው ምላሽ ሰጠኝ።» እያለ ይቀጥላል የዳግም የትዊተር መልእክት።

ዳግም ያያያዘው የቢቢሲ የድረ-ገጽ ጽሑፍ፦ አቤቱታ አቅራቢው ወደተለያዩ የመንግሥት አካላት ቢያቀኑም ሰሚ ማጣታቸውን ይገልጣል። «አቤቱታ አቅራቢዎቹ በመቀጠል ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ቢያመሩም "ጉዳያችሁን እዛዉ ጨርሱ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ጉዳይ ጣልቃ አይገቡም" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸዉ ለቢቢሲ ተናገረዋል» ይላል ጽሑፉ።

ጦማሪ አቤል ዋበላ፦«በአጭር ትውስታ ብቻ ነው የምንበረግገው። ሊያስበረግገን የሚገባው የሚጠብቀን፣ በደኅንነት የሚያኖረን ስርዓት አለመገንባታችን ነው። ለገጣፎ የሆነውን ነገ እንረሳዋለን። 12,000 ዜጎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ የት እንደወደቁ የሚያስታውስ አይኖርም» ሲል ጽፏል።

ሜሮን ኤስ ዱሞ መልእክቷን ያሰፈረችው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የትዊተር መልእክትንም አያይዛለች።  ጎዳና ላይ የወደቁ ልጆችን ሰብስበው መጠለያ እንደሰጧቸው፤ በዚያም ኩራት እንደተሰማቸው ይጠቅሳል ከሦስት ሳምንት በፊት የተጻፈው የምክትል ከንቲባው መልእክት። ይኽን የትዊተር መልእክት ያያዘችው ሜሮን በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤታቸው በመፈናቀላቸው የምክትል ከንቲባው ፌሽታ እጅግ «ፈጠነ» ስትል ትቀጥላለች። «ከጎረቤትዎ ያሉት ከንቲባ 12 ሺህ ቤቶችን እየደረመሱ ነው። እያንዳንዱ ቤት አምስት ሰው ቢኖረው፤ 60 ሺህ አዲስ ተፈናቃዮች እየመጡሎት ነው። እናም የኩራት ወቅት ሳይኾን የእፍረት ነው» ብላለች። አውራሪስ ዲ አሰፋ ደግሞ፦«እያንዳንዱን ቤት ለመገንባት 400 ሺህ ብር ቢያወጣስ?» ሲል ይጠይቃል። እናም፦ «እንግዲህ የለገጣፎ ከተማ 6,3 ቢሊዮን ብር ወደ አመድ ቀየረች ማለት ነው» ሲል ስሌቱን አስፍሯል። «ይኽ ሁሉ ታዲያ እንደ ከንቲባዋ ከኾነ ለአረንጓዴ ስፍራ ተብዬ ነው» ሲል ምሬቱን በጽሑፍ ገልጧል። 

የማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ላይ የሚንሸራሸር ጽሑፍ፦ ቤቶቹ በለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር የፈረሱት ሕገወጥ በመኾናቸው እንደኾነ ይገልጣል። ቤቶቹ ለዓመታት መብራት እና ኤሌክትሪክ ገብቶላቸው አንዳንዶቹ ግብር እየከፈሉ ቆይተው ሕገወጥ በሚል ከማፍረስ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ማቅረብ ይገባ ነበርም ብለዋል። አብርሃም በትዊተር ጽሑፉ፦ «በለገጣፎ እና በዚያ አካባቢ ያለውን መሬት ሲባጎ እየወጠሩ እንደ ዳቦ ሸንሽነው ሲቸበችቡ የነበሩትን የኦህደድ አመራሮችን ተጠያቂ ሳታደርግ ሕግ ማስከበር በሚል ሰበብ እልፎችን መድረሻ ሲያጡ ለሕግ ያለህ የተዛነፈ እይታ ፈጦ ይወጣል» ብሏል።

«እንዴት አደርሽ እማማ ኢትዮጵያ ሕግ እያስከበርሽ ነው አሉ እስኪ በነካ እጅሽ እዛው ለገጣፎ CCDን ካድሬዎችሽን መሬት ሲያሻሽጥ የከረመውን ባለስልጣኖችሽን ገበሬውን እያጭበረበረ መሬቱን ሲያሸጥ የኖረውን ደላላሽን እንዴት አደርክ በይልኝ» የከበቡሽ ጽሑፍ ነው።

«ይኽ በለገጣፎ እየኾነ ያለው አሳዛኝ ኹኔታ ነው» የብሩክታይት ዓለማየሁ አጭር መልእክት ነው። ነጭ የሹራብ ቆብ ያደረጉ ዐይነ ሥውር ሰውዬ እያነቡ መውደቂያ ማጣታቸውን ለሚጠይቃቸው ጋዜጠኛ ሲናገሩ የሚያሳይ የተንቀሳቃሽ ምስል አብራ አያይዛለች።  

«ኦዴፓ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን የያዘች ይመስል የንፁሀን ዜጎችን ቤት በሕገወጥነት ስታፈርስ ትንሽ እንኳ እፍረት አይሰማትም!?» ይኼ ደግሞ የአማር ቢን ያስር መልእክት ነው። «ለገጣፎ ስለንፁሀን ዝምአልልም» የሚል ሀሽ ታግም አለው።

የለገጣፎ ጉዳይ ወደተባበሩት መንግሥታት ዘንድ መድረሱም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴw መልእክቶች ይጠቁማሉ። አቤቶ ሮቤል በሚል የትዊተር ስም የቀረበው የእንግሊዝኛ መልእክት ይኽንኑ ይጠቅሳል። «ለገጣፎ ከሚገኘው መኖሪያቸው በግዳጅ የሚባረሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ረዳት አልባ ኢትዮጵያውያን ካሳሰቧችሁ የተባበሩት መንግሥታት በቂ የቤት አቅርቦት ልዩ መልእክተኛን ያግኙ» በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣኗን የትዊተር አድራሻ አስፍሯል።

ላይላኒ ፋራህ ይባላሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣኗ፦ በለገጣፎ 12 ሺህ ቤቶች የማፍረሱ ጉዳይ ምርመራ እየተደረገበት እንደኾነ የሚገልጥ ጽሑፍ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ይገኛል። አንዳንድ የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ከ20 ዓመታት በላይ የቆዩ ቤቶችን በ7 ቀናት ማስጠንቀቂያ ማፍረሱ ከፖለቲካ ጋር የተገናኘ ነው ሲሉ ጽፈዋል።

እሸቱ ሆማ ቄኖ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዲህ ሲል ይጠይቃል፦ «ለገጣፎ ግን የራሱ የሆነ ማስተርስ ፕላን አለው ወይ??? ካለው/ከነበረው ግሪን ኤርያው ላይ 20 ዓመት ሰዎች ቤት ሠርተው ሲኖሩበት ከንቲባው የት ነበሩ??? እንጠያየቅ» ይላል።

«በፌዴራሊዝሙ ድርድር የለም»

ሌላው በሳምንቱ አነጋጋሪው ርእሰ-ጉዳይ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር «ODP» በፌዴራሊዝሙ ላይ እንደማይደራደር መግለጡ ነው። የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት የህዝብ አስተያየት እና ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታየ ደንደአ፦ «ሕገ-መንግሥቱ እስካልተስተካከለ እና በሥራ ላይ እስከሆነ ድርስ መከበር አለበት፤ ፌዴራሊዝም ለሀገሪቱ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ ላይ ድርድር» እንደማይኖር ለዲ ደብሊው ተናግረዋል።  

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር «በፌዴራሊዝሙ» እንደማይደራደር የገለጡበት ጽሑፍ ከፓርቲው ዓርማ ጋር በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በስፋት ተሰራጭቷል። የሺሀሳብ አበራ፦ ዘለግ ባለው የፌስቡክ ጽሑፉ፦«ህዋኃት እና ኦዴፓ ሁለቱም በብሄር ፌዴራሊዝሙ እንደማይደራደሩ በተመሳሳይ ሰዓት ገልፀዋል፡፡ በተለይ ኦዴፓ በአዲስ አበባ ጉዳይ እና የአፋን ኦሮሞ ቋንቋን ጉዳይ እንደሚሰራ በፖለቲካ ቋንቋ አሳውቋል» ሲል ጽፏል።

«ከፀሀይ በታች የማንደራደርበት ጉዳይ የለም። " ሲሉ የነበሩ ዛሬ " ፌዴራሊዝሙ ለድርድር አይቀርብም::" ወደ ማለት ተቀይረዋል:: የተደበቀ ማንነት የሚገለጠው ቀስ በቀስ ነው!» የኤፍሬም ኪዳኔ የፌስቡክ ጽሑፍ ነው።

ኦነግ ትጥቅ መፍታቱና ጦር ሠፈር መግባት መጀመሩ

ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር መሣሪያ ተማዞ የነበረው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በሀገር ሽማግሌዎች አግባቢነት ወደ ጊዜያዊ ጦር ሰፈር መግባት መጀመሩ በርካቶችን «እፎይ» አስብሏል።

«የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከመንግሥት ጋር በደረሰው ስምምነት መሰረት ከአንድ ሺህ በላይ የሠራዊት አባላትን ወደ ካምፕ ማስገባቱ ተገለፀ። ይህ ተግባር እስከ የካቲት 14 እንደሚቀጥልም ተገልጿል»  የሚል መልእክት በማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ተሰራጭቷል።  ኦነግን በተመለከተ ከተሰጡ አስተያየቶች  የተሰጡትን እናቅርብ። ያላቸው መልስ፦ «...ኦነግ ወደ ጫካ ሲሄድም በወተት ተሸኘ ። ወደ ከተማ ሲመለስም በወተት ተቀበሉት። እግረ እርጥብ ይሉሀል እንዲ ነው ። መታደል ነው ። ሽፍትነትም ገድ አለው» ሲል ጽፏል።

«ጥያቄ አለኝ» በማለት የሚንደረደረው እዮራም ጉግሳ ነው። «ኦነግ እና ኦዴፓ ሲታረቁ ኦነግ ከአስራ ስምንት በንኮች ዘረፈ የተበለውን ገንዘብ መልሶ ነው ወይንስ በግርግር አረሳስተውን? የአገር ሐብት ከዘረፈ ወንበዴ ጋር ዝም ብሎ ለመታረቅስ ኦዴፓ ምን ሥልጣን አለውሲል በጥያቄ ተሰናብቷል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic