የሆርስት ከለር «የገና ሥጦታ» ለአፍሪቃ | የጋዜጦች አምድ | DW | 23.12.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የሆርስት ከለር «የገና ሥጦታ» ለአፍሪቃ

«ርጉዞች የሚረዱበት አንድ ማዕከል ስጎበኝ ጣሳዋን ሰጡኝ» አሉ የጀርመኑ ፕሬዝዳንት-ሆርስት ከለር ላነጋገራቸዉ ጋዜጠኛ።«መስፈሪያ ነች።ሃያ ሴንቲ ሜትር ያሕል ጥልቀት አላት።» ቀጠሉ ፕሬዝዳንቱ።«አንድ ጣሳ አጃ ለአንዲት ነብሰጡር የሳምንት ቀለብ ነዉ።» እያሉ።

ከለር በአፍሪቃ ሕብረት

ከለር በአፍሪቃ ሕብረት

ነጋሽ መሐመድ

«ከፅፈት ጠረጴዛቸዉ የማትለይ አንድ የፕላስቲክ ጣሳ አለች።»-ይላል ባለፈዉ ህዳር ማብቂያ የተነበበዉ የጀርመን ጋዜጣ-Die Zeit። «የአለም ገንዘብ ድርጅት የበላይ በነበሩበት ጊዜ የዛሬ አራት አመት አፍሪቃን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲጎበኙ ነዉ-ከማሊ ያመጥዋት።ከአፍሪቃ።የአፍሪቃዉያንን ድሕነትና ረሐብ ለማስታወስ።» አከለ ጋዜጣዉ። የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ሆርስት ከለር-በጣሳዋ የሚያስታዉሱ-የሚያስቧትን አፍሪቃን በቅርቡ ዳግም አይዋት።የአስር ቀን ጉብኝታቸዉ ለራስዋ ለጀርመን ጨምሮ ለትላልቆቹ ሐገሮች የፖለቲካ አስተንታኞች-ለመገናኛ ዘዴዎችም የጠዋት ማታ ርዕሥ አልነበረም።አፍሪቃ-በጣሙን አስር ቀን ያሳለፉባቸዉ አራቱ ሐገራት ግን ጉብኝቱና ዉጤቱን ጀርመን እንደሐገር፣ ፕሬዝዳንቷ እንደ መሪ በገና ዋዜማ ለየሕዝባቸዉ እንደ ሰጡት የገና ስጦታ ቢያዩ፣ ቢንከባከቡት ተገቢ ነዉ።በብዙ ምክንያት።-----

ዓለም በቀን ሰማንያ ሚሊዮን በርሚል ነዳጅ ዘይት ትጠጣለች።በየጊዜዉ እየናረ የመጣ፣ እንደናረ የሚቀጥለዉን የአለም የነዳጅ ጥማት በግማሽ የሚያረካዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ-ሠላምም፣ ዲሞክራሲም እንደራቀዉ ነዉ።የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ሪቻርድ ኒክሰን «የነፃዉ ዓለም ሕልቅት» ያሉት፣ የዓለም ነዳጅ ዘይት የማይነጥፍ ጎተራ በተለይ እስራኤል እንደ ሐገር ከተመሠረተች-ከ1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በማይነጥፍ ሁከት፣ በማያባራ ጭቆና ብዝበዛ እንደተዘፈቀ ዘመን-ሸኝቶ ዘመን ለመቀበሉ፣ ወደፊት በእስካሁን ጉዞዉ ለመቀጠሉ ሥጋትም-አያሌ ወገኖች አያሌ ምክንያት ይሰጣሉ።

የእስራኤል የሐይል እርምጃ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሥለአካባቢዉ የምትከተለዉ መርሕ፣ አካባቢዉ እንደተተራመሠ፣ በሙሥና በተዘፈቁ፣ ነገስታት፣ በሐይል ሥልጣን በያዙ አምባገነኖች እንደተገዛ፣ አሸባሪዎች እንደተፈለፈሉበት፣ ሐይማኖት አክራሪዎች እንደበቀሉበት ለመቀጠሉ ዋና ምክንያት የሚያደርጉ ትንሽ አይደሉም።የቅኝ ገዢዎችን አገዛዝ፣ የምሥራቅ ምዕራቦችን ሽኩቻ፣የአረብ ብሔረተኞች ያሰረፁትን አስተሳብ የሚወቅሱም አሉ።እስላማዊ አብዮተኞች የቴሕራንን ቤተ-መንግሥት በቆጣጠሩ ማግሥት ዩናይትድ ስቴትስ ላይ ደርቶ የነበረዉን-እስልምናና ሙስሊምን እንደ ኋላ ቀር፣ አክራሪ፣ አሸባሪ የማየቱን እሳቤ ኒዮርክና ዋሽንግተን በአሸባሪዎች ከተጠቁ ወዲሕ ያቀጣጠሉት ወገኖች ደግሞ እስልምናና ሙስሊሞችን መወንጀሉ አምሮባቸዋል።


ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ያ! የነዳጅ ባሕር-በደም እንደ እንደጨቀየ ነዉ።ፕሬዝዳንት ሐሪ ኤስ ትሩማን የእስራኤልን ሐገርነት ካፀደቁበት፣ ሪቻርድ ኒግሰን በ1970ዎቹ መጀመሪያ ነዳጅ ዘይት ላለመሸጥ ያደሙ ሐገራትን ለመዉረር እከተዘጋጁበት፣ ጂሚ ካርተር የኢራንን አብዮተኞች ለማስወገድ ከሞከሩበት፣ ሮናልድ ሬገን በኢራቅ በኩል ኢራንን እስካስወጉበት፣ ሊቢያን እስከመቱበት፣ ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ቀዳማዊ ኢራቅን ካስወጉበት፣ ቡሽ ዳግማዊ እስካስወረሩበት ድረስ የዋሽንግተን ሹማምንት በመካከለኛዉ ምሥራቅ የወሰዱት እርምጃ የተከተሉትም መርሕ ለአካባቢዉ አይደለም ነዳጅ ዘይት ለሚጠማዉ አለም የፈየደዉ ነገር የለም።

የተቀረዉ አለም ለሠላም ዲሞክራሲ መጥፋት የሚሰጡ ምክንያቶችን አጢኖ የአረብ እስራኤሎችን ጠብ ለማብረድ፣ የሁለቱን ወገኖች አቋም ለማረቅ፣ የዩናይትድ ስቴትስን መርሕ ለማስተካከል ወይም ሌላዉን ምክንያት ለማስወገድ የሚገባዉን ያሕል አለመጣሩ-የሕይወት፣ የሐብት፣ የጊዜ ዋጋ እንዲከፍል አስገድዶታል።መካከለኛዉ ምሥራቅ ከሠላም ዲሞክራሲ እንደራቀ የመቀጠሉ ሥጋት ደግሞ ነዳጅ ቢጠማዉ እንደከበረ መቀጠሉ የሚያጠራጥረዉን አለም አማራጭ የነዳጅ ምንጭ እንዲፈልግ ያራዉጠዉ ይዟል።አፍሪቃ ከአማራጮቹ አንዷ ሆናለች።

ዮኮስ የተባለዉ የሩሲያ ነዳጅ አምራች ኩባንያ ንብረት ሐራጅ መቅረቡ ለትላልቆቹ ሐገራት ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች «ሠበር ዜና» በሆነበት ሠሞን የጀርመን ፕሬዝዳንት የአፍሪቃ ጉብኝት የጎላ ርዕሥነት ሥፍራ ማጣቱ-የፕሬዝዳንቱ ሥልጣን ከሥነ-ሥርአት ነክ ጉዳዮች ያለመራቁ፣ አለያም አፍሪቃ ከችግር ትርምሷ ሌላ-የሚባልላት ነገር ሥለሌለት-ሊሆን ይችላል።አፍሪቃ ግን ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ አማራጭ የነዳጅ ዘይት ምንጭ ለማግኘት ያለመዉ ሩጫያ አንዷ ኢላማ መሆንዋ-ሊያጠራጥር አይገባም።

ዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኮሊን ፓወልና ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ሐቻምና ተከታትለዉ አንጎላ፣ ጋቦን፣ ሴኔጋል፣ ናይጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ቦትስዋናንና ሌሎችም የአፍሪቃ ነዳጅ አምራች፣ ነዳጅ ዘይት ለማመለስ የሚጠቅሙ ሥልታዊ ሐገራትን መጎብኘታቸዉ አፍሪቃ ከአማራጩ ሽሚያ አንዷ ምናልባትም ግንባር ቀደምዋ መሆንዋን ጠቋሚ ነዉ።

ፈረንሳይ ከዳርፉሩ ተሰደዉ ቻድ ለሠፈሩ ሱዳናዉያን ርዳታ የሚያቀርቡ ወገኖችን ደህንነት የሚጠብቅ ጦር-ከማንም ቀድማ አዝምታለች።የኮትዲቫርን ሠላም ለማስከበር ሠራዊት አስፍራለች።የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሐገራት ጉባኤን ከፓሪስ ይልቅ ዋጋ ዱጉ ላይ ጠርታለች።ፕሬዝዳንት ዣክ ሺራክ አልጀሪያን ጎብኝተዋል።ሊቢያንም።ሁሉም ለየሐገራቱ ሠላም በማሰብ፣ የቅኝግዛት ዉርስን ለመጠበቅ፣ወይም ከየሐገራቱ ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማጠናከር የተደረገ አይደለም ማለት አይቻልም።የሱዳን፣ የቻድን፣ የአልጀሪያን፣ የሊቢያን ነዳጅ ዘይት፣ የኮትዲቩዋርና የቡርኪናፋሶን ሥልታዊነት ለሚያስተነትን ደግሞ የተደረገዉ ሁሉ አፍሪቃን እንደአማራጭ የነዳጅ ዘይት ምንጭ ከማየት አይደለም ማለት ያሳስታል።

በያዝነዉ አመት የጣሊያን (ሁለቴ) የብሪታንያ፣ የጀርመን መሪዎች ከዣክ ሺራክ ቀድመዉ ሊቢያ ተመላልሰዋል።የጀርመንና የብሪታንያ መሪዎች አዲስ አባባ ነበሩ።ዳርፉርን ያልረገጠ የሐብታሞቹ ሐገራት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የለም ወይም ጥቂት ነዉ።የፀጥታዉ ምክር ቤት በታሪኩ ከሰወስት በስተቀር አይድሮጎት የማያዉቀዉን ሥለሱዳን ለመምከር ናይሮቢ ድረስ ወርዷል። የተደረገዉ በሙሉ ለአፍሪቃ ሠላም፣ ለህዝቦችዋ እድገት በመጨነቅ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል።-መካከለኛዉ ምሥራቅን ሙሉ በሙሉ ባይተካ የሚያካክስ ነዳጅ መፈለግ-ካልተነገረዉ አንዱ አለመሆኑን የሚስረግጥ ምክንያት ግን የለም።

---------------------

«ርጉዞች የሚረዱበት አንድ ማዕከል ስጎበኝ ጣሳዋን ሰጡኝ» አሉ የጀርመኑ ፕሬዝዳንት-ሆርስት ከለር ላነጋገራቸዉ ጋዜጠኛ።«መስፈሪያ ነች።ሃያ ሴንቲ ሜትር ያሕል ጥልቀት አላት።» ቀጠሉ ፕሬዝዳንቱ።«አንድ ጣሳ አጃ ለአንዲት ነብሰጡር የሳምንት ቀለብ ነዉ።» እያሉ።

የሥልሳ አንድ አመቱ የምጣኔ ሐብት ሊቅ ፖላንድ ተወለዱ።በ1943።የሶቬት ሕብረት ቀዩ ጦር ሮማንያን ሲቆጣጠር ወላጆቻቸዉ ከሰባት ታላላቆቻቸዉ ጋር ከሮማንያ ወደ ፖለንድ መሰደዳቸዉን ያወቁት ገና ልጅ እያሉ ነበር።ቀዩ ጦር ፓላንድን እንደተቆጣጠረ እሳቸዉ-አስረኛ የተቀላቀሉት ቤተሰብ ወደ ላይፕዚሽ-ምሥራቅ ጀርመን ተሠደደ።ከፍ ሲሉ እንደገና ወደ ባደን ቩርተምበርግ ሔዱ።ያሁኑ ፕሬዝዳንት።

ከለርና የተከተሏቸዉ የጀርመን ባለሥልጣናት የአፍሪቃ ጉብኝት ያልተነገረ ምክንያት ከሳቸዉ በፊት አፍሪቃን እንደጎበኙ---መሪዎች ሁሉ አፍሪቃን እንደ አማራጭ የነዳጅ ምንጭ ለመያዝ ያለመ አይደለም ማለት ያሳስት ይሆናል።ገና ከልጅነት፣ ጦርነትን እሸሹት፣-ችግር ሥደትን ኖረዉት፣ ረሐብ ድሕነትን አፍሪቃ አይተዉት-በጣሳም እያስታወሱት ማወቃቸዉ ሥልጣን ከያዙ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጉብኝታቸዉ አፍሪቃን መምረጣቸዉ የግል ምክንያታቸዉ አይደለም ማለትም አይቻልም

የተነገረ-ያልተነገረዉም ምክንያት ምንም ሆነ ምን ሴራሊዮን ተጀምሮ ቤኒን ቀጥሎ፣ ኢትዮጵያ አሠልሶ ጅቡቲ ባሳረገዉ ጉብኝት ከየሐገራቱ መሪዎች ጋር ያደረጉት ዉይይት፣ ያስተላለፉት የሠላምና የልማት መልዕክት የገቡት ቃልም ለአፍሪቃ እጅግ መጥቀሙ አያከራክርም።ጀርመን ከእርስ በርስ ጦርነት በማገገም ላይ ላለችዉ ሴራሊዮን ባለሙያዎች እድትረዳ ግፊት ለማድረግ ፕሬዝዳንቱ ቃል ገብተዋል።አብረዋቸዉ የተጓዙት የጀርመን ባለሥልጣን ለቤኒን ከአርባ ሚሊዮን ዩር በላይ ብድር ለመስጠት ተስማምተዋል።ኢትዮጵያ ካለባት ዕዳ ሥልሳ ሰባት ሚሊዮኑን ዩሮ ሠርዘዋል።

ሆርስት ኮለር ባለፈዉ ሐሙስ በርሊን እንደገቡ የአለም ሰወስተኛ፣ የአዉሮጳ አንደኛ ሐብታም፣ ሐገራቸዉ ለአፍሪቃ የምትሰጠዉ ርዳታ በትምሕርትና ሥልጠና ላይ እንዲያተኩር መጠየቃቸዉ በመንግሥታቸዉ በአዉሮጳ ሕብረትም መርሕ ላይ የሚያሳርፈዉ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።ሀሳባቸዉ ተቀባይነት ካገኘ አፍሪቃን ከድሕነት፣ ረሐብና በሽታ ለማላቀቅ የሚሰጠዉ ጥቅም እጅግ ነዉ።

ፕሬዝዳንቱን ተከትለዉ አፍሪቃን የጎበኙት የጀርመን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ ወይዘሮ ክርስቲን ሙለር አፍሪቃ በሚሻሸለዉ የፀጥታዉ ምክር ቤት ሁለት መቀመጫ እንዲኖራት ጠይቀዋል።ጥያቄዉ ተቀባይነት ይኑረዉ አይኖረዉ አይታወቅም።ለፍሪቃዉያን ግን ጩኸታቸዉን የሚጋራ አንድ ትልቅ ሐገር ለማግኘታቸዉ ዋቢ ነዉ።

ሆርስት ከለር፣ሌሎቹም የበለፀጉት ሐገራት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች ወይም ባለሐብቶች አፍሪቃ መመላለሳቸዉ ለየራሳቸዉ ጥቅም ሊሆን ይችላል።ለየጥቅማቸዉ ያደረጉና የሚያደርጉት ሁሉ አፍሪቃን ከጠቀመ፤ ግን ጥቅሙ ለአፍሪቃዉያን እንዲሆን መጣር የአፍሪቃ መሪዎች ፈንታ ነዉ።