የህዳሴው ግድብ ተስፋና ስጋት | ጤና እና አካባቢ | DW | 29.07.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የህዳሴው ግድብ ተስፋና ስጋት

ከስድስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤለክትሪክ ሀይል ያመነጫል የተባለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ከሰሞኑ ተጠናቋል።ይህ ዜና ከግማሽ በላይ የኤለክትሪክ መብራት ለማያገኘው የሀገሪቱ ህዝብ አስደሳችና ተስፋ ሰጪ ነው።የአፈርና የውሃ ጥበቃ ባለሙያዎች ግን ስጋት አላቸው።ስጋታቸው ምን ይሆን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:29

ግድቡ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዟል

ከስድስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤለክትሪክ ሀይል ያመነጫል የተባለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ከሰሞኑ ተጠናቋል።ይህ ዜና ከግማሽ በላይ የኤለክትሪክ መብራት ለማያገኘው የሀገሪቱ ህዝብ አስደሳችና ተስፋ ሰጪ ነው።የአፈርና የውሃ ጥበቃ ባለሙያዎች ግን ስጋት አላቸው።ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁን  የህዳሴ ግድብ መገንባቷን ተከትሎ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ግብፅ ግድቡ  የወንዙን የውሃ ፍሰት ይቀንሳል በሚል እስካሁን ድረስ መቋጫ ባለገኘ  ውዝግብ ትገኛለች።በሌላ በኩል  ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት እተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  በራስ አቅም የሚገነባ  በመሆኑ የገንዘብ እጥረትም ሌላው ተግዳሮት  ሆኖ ቆይቷል።በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሚታየው የሰላም እጦትና  አለመረጋጋትም የግድቡን ስራ ባያስተጓጉልም ተፅኖ ማሳደሩ አልቀረም ። ያም ሆኖ  ኢትዮጵያ በነዚህ   ችግሮች መሀልም ሆና ከስድስት ሺህ  ሜጋዋት  በላይ ሀይል ያመነጫል ተብሎ የሚጠበቀውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የዉሃ ሙሌት የመጠናቀቁ ዜና ያለፈው ሳምንት ሀምሌ 15 ቀን 2012 ዓ/ምተበስሯል።

ይህ ዜና እንደ ዓለም ባንክ የዚህ ዓመት መረጃ መሰረት  ከጠቅላላ የህዝብ ብዛቷ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የኤለክትሪክ መብራት የማያገኝባት ኢትዪጵያ፤ ህዝቦቿን አስፈንድቋል።ትልቅ ተስፋም አሳድሯል።ይህ ተስፋ ግን  በአንዳንድ ባለሙያዎች ዘንድ ስጋት የተቀላቀለበት ነው።በአሜሪካን ሀገር ዳላስ ከተማ በተፋሰስ ልማት ዘርፍ በመስራት ላይ የሚገኙት የአፈርና የውሃ ጥበቃ  ባለሙያ  ዶክተር ታከለ ምትኩ ከነዚህ መካከል አንዱ ናቸው።« ውሃዉ እጅግ የደፈረሰ ነው።ይህ ማለት ብዙ ደለል አለው ማለት ነው።«በማለት ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ።

እንደ  የኢትዮጵያ  የዉሃና የመስኖ ልማት ምንስቴር መረጃ በሰሞኑ የመጀመሪያው ዙር  የውሃ ሙሌት ግድቡ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይዟል።የግድቡ ከፍተኛና አስፈላጊው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር  ሲሆን ይህንን የውሀ  ውሃ መጠን በግድቡ ውስጥ ለመያዝ ደግሞ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ያስፈልጋል።እንደ ባለሙያው በእነዚህ የሙሌት አመታት በአፈር መሸርሸር ሳቢያ ወደ ግድቡ አላስፈላጊ አፈር ገብቶ ደለል እንዳይፈጠር ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። ያ ካልሆነ እንደ ባለሙያው  ሱዳንና ግብፅን በመሳሰሉ ከዚህ ቀደም ግድብ በገነቡ  የተፋሰሱ ሀገራት ተመሳሳይ የደለል ችግር አጋጥሞ እንደነበረው ገልፀው በኛ ሀገርም የግድቡን እድሜና ሀይል የማመንጨት አቅም ይቀንሳል የግድቡን መካኒካል መሳሪዎችም ይጎዳል ብለዋል። ላለፉት አስር ዓመታት በግንባታ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ከሦስት አራተኛው በላይ መጠናቀቁን መንግስት ሲገልፅ ቆይቷል።ግድቡ ተጠናቆ ሥራ ሲጀመር በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ከመሆኑ በላይ  250 ኪሎ ሜትሮችን የሚያካልል ቦታን በውሃ በመሸፈን ሰው ሰራሽ ሀይቅም ይፈጥራል።በዚህም ግድቡ ከሚያመነጨው የኤለክትሪክ ሀይል በተጨማሪ ሀገሪቱን የአሳ ምርት ተጠቃሚ ያደርጋታል።ይሁን እንጅ የደለል ችግር ይህንን የዓሳ ምርትም አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል  ዶክተር ታከለ ያስረዳሉ።

የህዳሴው ግድብ ለተፋሰሱ ሀገራት ከሚሰጠው ጥቅም አንዱ 86 በመቶ ወደ ግብፅና ሱዳን ግድቦች የሚገባውን ደለል የሚያስቀር መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።ነገር ግን ይህ ደለል በኢትዮጵያ ሊለሙ በሚችሉ  ቦታዎች እንጅ በግድቡ ውስጥ መቅረት ስለሌለበት፤ ኢትዮጵያ ችግሩን ቀድማ በመገንዘብ መፍትሄ መሻት አለባትም ይላሉ።በተለይ  ይህ ወቅት ከግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡና በተቋማት ዘንድ መነቃቃት የተፈጠረበትና ለጉዳዩ ትኩረት የተሰጠበት  ጊዜ በመሆኑ ለአባይ ወንዝ ገባር በሆኑ  በየ አካባቢው በሚገኙ ትንንሽ ወንዞች ላይ ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግ መንግስት ችግሩን በማስረዳት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራት አለበት።በተፋሰሱ አካባቢ ተገቢውን ጥናት በማድረግም በተለይ በግብርና በኢንደስትሪና በግንባታ ስራዎች ላይ የሚታየው የአፈር መሸርሸርም ከፍተኛ በመሆኑ በነዚህ ዘርፎች ላይ በማተኮር  አፈሩ ከቦታው ሳይነሳ ማስቀረት፣ ሁለተኛው ዘዴ ደግሞ ወደ ግድቡ ሳይደርስ መንገድ ላይ አፈርን ከውሃ መለየት ናቸው።«ሶስተኛው መንገድ ደግሞ አንዴ አባይ ከገባ በኋላ መጥረግ ነው።እሱ ደግሞ ሌላ ግድብ መስራት ይሻላል።ውድና አድካሚ ስራ ነው።ስለዚህ የሚሻለው ገና ሳይነሳ አፈሩን መያዝ ነው።ለዚህ ደግሞ አዲስ አያስፈልግም።እንደ ኮንሶ አካባቢ ያሉትን በአፈርና ዉሃ ጥበቃ በታሪክ የምንሰማው ተሞክሮ አለ ገበሬዎች የሚወስዱት።»  የኢትዮጵያ ምርታማነት ለዘመናት ለምና ርጥበታማ በሆኑ የደጋ አካባቢዎች ላይ ብቻ ተመስርቶ በመቆየቱ በአሁኑ ወቅት ያለው አማራጭ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ መጠቀም መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።በአካባቢ ደንና  የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን «ሬድ ፕላስ» የተባለ የአየር ንብረት ለውጥ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪና የደንና የስነ ምህዳር ሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አይተብቱ ሞገስ በዚህ ይስማማሉ።ነገር ግን የውሃ ሀብትን መጠበቅና ማልማት ከደን ልማት ጋር መተሳሰር አለበት ይላሉ።ይህ ልማት ውጤት እንዲኖረው ደግሞ በባለሙያ እንዲመራ ይሻሉ።

የአሜሪካ የፌደራል የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ መሰረት አንድ ግድብ ሊፈርስ ወይም እንዲበላሽ ከሚያደርጉ ስምንት ነገሮች ውስጥ  የአፈር ደለል በዋናነት የሚጠቀስ ነው።ይህ ችግር ለአፈርና ውሃ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ በቂ ትኩረት በማይሰጡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ችግሩ የጎላ ሊሆን ይችላል።ያ በመሆኑ የአፈርና ውሃ ሀብት መራቆትና መመናመን የግብርና ምርትን  በመቀነስ ከሚያሳድረው ተፅዕኖ በተጨማሪ በርካታ ሀብትና ጉልበት የፈሰሰበትን ግድብ ሊያሳጣን ይችላል ማለት ነው።ስለሆነም በባለሙያዎቹ ምክር መሰረት በቀሪዎቹ  የሙሌት አመታት የአፈርና የውሃ ጥበቃን እንዲሁም የደን ሽፋንን ማሳደግ የአፈር ደለል በግድቡ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ሊቀንሰው ይችላልና ቢታሰብበት መልካም ነው።

 

ፀሐይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic