የህዳሴዉ ግድብና የተፋሰሱ ሀገራት ዉይይት | ኢትዮጵያ | DW | 05.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የህዳሴዉ ግድብና የተፋሰሱ ሀገራት ዉይይት

በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረዉ አለመረጋጋት የተነሳ ለወራት ተቋርጦ የነበረዉ የኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን ዉይይት በዛሬዉ ዕለት በካርቱም  መጀመሩ ተሰምቷል። ዉይይቱ ሶስቱ መሪዎች ባለፈዉ ጥር አዲስ አበባ ባደረጉት ስብሰባ ባሳለፉት ዉሳኔ መሰረት መሆኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታዉቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:27

« በሶስቱ ሀገራት ህዝቦች የልማት ትስስር ላይም ዉይይት ይካሄዳል።»አቶ መለስ ዓለም


 ዉይይቱ በሀገራቱ መካከል ያለዉን የመተማመን መንፈስ ለማዳበርና ህዝቦችን በተለያዩ ልማቶች ለማስተሳሰር  ያለመ መሆኑም ተመልክቷል ።
ኢትዮጵያ  በአባይ ወንዝ ላይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረች ሰባት አመታት ተቆጥረዋል።የየግድቡ ግንባታ አብዛኛዉን ሀገሪቱን ህዝብ  በአንድ ዓላማ ያሰለፈ ቢሆንም ከታችኛዉ ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ከግብፅ የሚነሳዉ ስጋትና ተቃዉሞ አሁንም ድረስ መቋጫ አላገኜም።ግብፅ የኢትዮጵያን የአባይ ዉሃ ተጠቃሚነትና ልማት እንደማትቃወም በተደጋጋሚ ብትገልፅም በሌላ በኩል  ወንዙ የህልዉና ጉዳይ ነዉ በሚል በግድቡ ያላትን ስጋት ስትገልፅ ቆይታለች። ይህንን ስጋትና አለመተማመን ለማስወገድ ሌላኛዋን የወንዙ ተጠቃሚ ሀገር ሱዳንን ጨምሮ 3ቱ ሀገራት በተለያዩ ጊዜያት ዉይይት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን የመጨረሻዉ ስብሰባ የተካሄደዉ ያለፈዉ ጥር ወር በአዲስ አበባ ከተማ ነበር።ከዚህ ዉይይት በኋላ በኢትዮጵያ በተፈጠረዉ አለመረጋጋት የተነሳ ዉይይቱ ለወራት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን  በዛሬዉ ዕለትም በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም  የሀገራቱ  ዉይይት መጀመሩን የአትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።


እንደ አቶ መለስ ገለጻ ዉይይቱ የሀገራቱ መሪዎች ባለፈዉ ጥር ባካሄዱት ስብሰባ በተላላፈ ዉሳኔ መሰረት የቀጠለ ሲሆን ከህዳሴዉ ግድብ ባሻገር የሶስቱን ሀገራት ህዝቦች በልማት የማስተሳሰር አላማ አለዉ።«ካርቱም ላይ ተጀምሯል።የኢፌዲሪ የዉጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየዉ፣ የዉሃ ሃብት ሚንስትርሩ ኢንጅነር ዶክተር ስለሽ አሉበት ሌሎችም ባለሙያዎች ካርቱም ይገኛል።አሁንም እንደቀጠለ ነዉ።በመግባባት መንፈስ እየተካሄደ ነዉ።ያኔ የአዲስ አበባዉ ስብሰባ ሲካሄድ የግብጹ ፕሬዝንዳትና ሌሎችም ሁለቱም መሪወች ያስተጋቡት መልዕክት ነበር።ሶስት ሆነን እንደ አንድ መስራት ይገባናል የጋራ ፍላጎት አለን ፤የጋራ ጥቅሞች አለን ። ህዝቦቹም ያላቸዉ ግንኙነት የትናንትና የትናንት ወዲያ አይደለም።ለዘመናት አንድ ላይ የኖሩ ናቸዉ።በህዝቦቹ መካከል ያለዉ ግንኙነት ከህዳሴ ግድቡ በላይ ነዉ። በሚል የመግባባት መንፈስ በወንድማማችነት መንፈስ እየተካሄደ ያለ ዉይይት ነዉ።» በማለት ነበር አቶ መለስ የገለፁት።
በሱዳን እየተካሄደ ያለዉ የ3ቱ ሀገራት ዉይይት  የአባይ ዉሃ የአለመግባባት ምንጭ ከመሆን ይልቅ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት መዋል ላይ ያተኮረ ቢሆንም ሌላኛዋ የተፋሰሱ ሀገር ሱዳን በቅርቡ በተናጠል ከግብፅ ጋር ካደረችዉ  ዉይይትና ከግብፅ ተለዋዋጭ አቋም የተነሳ ዉይይቱ የተለዬ መልክ ሊኖረዉ ይችላል የሚል ግምት አሳድሯል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በኢትዮጵያ  የዉጭ ግንኙነት ስትራቴጅካዊ ጥናት ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ  አቶ አበበ አይነቴ ግን  የግብፅና የሱዳን አለመግባባትም ይሁን የተናጠል  ዉይይት ከድንበርና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዘ በመሆኑ ይህንን ችግር መፍታታቸዉ ለሶስትዮሽ ዉይይቱ ጥቅም እንጅ ጉዳት የለዉም ይላሉ።

«ያላቸዉ አለመግባባት ከዓባይ ዉሃ ጋር በተያያዘ አይደለም ።የራሳቸዉ የድንበር ጉዳይ ነዉ።እንደተባለዉ ግብፅና ሱዳን የነበራቸዉን ችግርና በተወሰነ ደረጃ ተቋርጦ የነበረዉን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ተነጋግረዉ ፈተዋል።ሱዳንና ግብፅ ያንን ችግር ተነጋግረዉ መፍታታቸዉ አጠቃላይ ለዉይይቱ ጠቃሚ ነገር ነዉ እንጅ የሚሆነዉ፤አሉታዊ ነገር ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።ስለዚህ ሁለቱ ሀገሮች ያላቸዉን ልዩነት መፍታታቸዉ ለሶስትዩሽ ዉይይቱ ጠቃሚ ነገር ነዉ የሚሆነዉ እንጅ አሉታዊ ሚና አይኖረዉም።»
ሀገራቱ ከሚያደርጉት ዉይይት በተጨማሪ ቀደም ሲል  ግድቡ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ የሚያሳድረዉን ተፅዕኖ  በተመለከተ  ቢ አር ኤልና አርቴልያ በተባሉ ሁለት የፈረንሳይ  ኩባንያወች ጥናት እንዲያደርጉ  ስምምነት ደርሰዉ ነበረ።ያም ሆኖ ግን  ባለፈዉ ህዳር ኩባንያወቹ  ባቀረቡት ቴክኒካዊ ዘገባ ላይ ግብፅ አለመስማማቷን ገልፃለች። በታህሳስ 2017 ም የዓለም ባንክ ከሶስትዮሽ የቴክኒክ ኮሚቴዉ  ዉስጥ እንዲሳተፍና እንዲያዳራድር ሀሳብ አቅርባለች ።ምንም እንኳ በኢትዮጵያና  በሱዳን  በኩል ተቀባይነት ባያገኝም ።ከዚህ በግብጽ ተለዋዋጭ አቋም የተነሳም እስካሁን በተካሄዱ ዉይይቶች ጠብ ያለ ነገር የለም ሲሉ የሚተቹ አሉ።ተመራማሪዉ አቶ አበበ አይነቴ ግን ይህንን አይቀበሉትም ግብፅ የቱንም ያህል የአቋም መዋዠቅ ብታሳይም በኢትዮጵያ በኩል የታየዉ  ቁርጥ አቋም ግብፅ ወደ ድርድር እንድትመጣ ማድረጉን ነዉ የሚገልፁት። ለዚህም ማሳያ አላቸዉ።

« በግብፅ በኩል የአቋም መዋዠቅ እንደተጠበቀ ሆኖ  አንዱ ማሳያ ግን በሶስትዮሽ ዉይይቱ ችግሩ መፈታት አለበት በሚለዉ አቋም ላይ እና በሁሉም ደረጃ ለመነጋገር ያለዉ ዝግጁነት ያሳዩበት ከጥቂት ቀናት በፊት በተፈጠረዉ ፖለቲካዊ ሁኔታ ምክንያት የህዳሴዉ ግድብ የሶስትዮሽ ዉይይት ችግር ላይ ናችሁ እና ይራዘም ወይም ወደ ወደፊት ገፋ ማድረግ እንችላለን የሚለዉ መልዕክት መተላለፉ አንዱ ግብፅ በዉይይትና በድርድር ጥቅሟን ለማስጠበቅ ፍላጎት እና ተነሳሽነት እያሳየች ለመሆኑ አመላካች ነዉ።» ነበር ያሉት።
እንደ አቶ አበበ ገላፃ በግብፅ በኩል ያለዉ የአቋም መለዋወጥ በወንዙ ላይ ለዘመናት ከነበራት የበላይነት እንዲሁም  የግብፅ መንግስት፤ ሙህራንና የመገናኛ ዘዴዎች  በግድቡ ላይ ከሚያራምዱት የተለያዬ አቋም የሚመነጭ ነዉ። ያም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት የግብፅ መንግስት  የተፋሰሱ ሀገራት የወንዙን የጋራ ተጠቃሚነት መብት  በመጠኑም ቢሆን እየተረዳ መሆኑን ገልፀዋል።
በጎርጎሮሳዊዉ ሚያዚያ 2011 የተጀመረዉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ እስካሁን  64 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በመጭወቹ  3 ዓመታት  ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic