የህይወትን ሥረ መሠረት ለማወቅ፤ በየዘርፉ የሚደረግ ምርምር፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 24.02.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የህይወትን ሥረ መሠረት ለማወቅ፤ በየዘርፉ የሚደረግ ምርምር፣

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ የህይወትን ሥረ-መሠረት ለማወቅ ፤ በየብስ ፤ በባህርና በኅዋ የሚደረገውን ምርምር እንዳስሳለን።

default

ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ሞስኮ አቅራቢያ በተዘጋጀ ፣ «ማርስ 500» በተሰኘ 180 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው እስቱዲዮ መሰል ልዩ በምድር ላይ በተሠራ የኅዋ ጣቢያ ፤ ወደ ማርስ በሚላኩ ጠፈርተኞች ላይ በዚያው በማርስ አደጋ ቢደርስ አንዱ ለሌላው ምን ዓይነት ህክምና ማድረግ እንደሚችል ፣ የጠፈር ልባሳቸውን እንደለበሱ ልምምዱን በተሣካ ሁኔታ አከናውነዋል። ጠፈርተኞቹ በተጠቀሰው ጣቢያ ውስጥ ከውጭው ዓለም ተገልለው እስካሁን 8 ወራት አሳልፈዋል። ማርስ ደርሶ ለመመለስ 520 ቀናት ገደማ ስለሚወስድ ፣ ለጉዞ ዝግጅት የሚያደርጉት ጠፈርተኞች እስከሚመጣው ዓመት ኅዳር ወር ድረስ፤ በዚያ የምርምር ጣቢያ ውስጥ ይቆያሉ። ከዚያው ከሩሲያ፤ ቻይና «ዪንግሁዎ-1» የተሰኘችውን 110 ኪሎግራም የምትመዝነውን የጠፈር መንኮራኩሯን በመጪው ኅዳር ወር ወደ ማርስ ታመጥቃለች። የመንኮራኩርዋ ተልእኮ፤ የማርስን አካል ፣ በተለይም በታሪኳ አንድ ጊዜ በሽበሽ የነበረው ውሃ እንዴት ተንኖ እንደጠፋ መመርመር ይሆናል። ቻይና ከሶቭየት ኅብረትና ዩናይትድ እስቴትስ ወዲህ በኅዋ ላይ ሰፊ ትኩረት በማድረግ ሰፊ ትኩረት በማድረግ የ 3 ኛነቱን ሥፍራ ይዛለች። በአሁኑ ጊዜ ሞስኮ አቅራቢያ በሚገኘው ለማርስ ጎዞ የዝግጅት ምርምር በሚካሄድበት ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙት ጠፈርተኞች መካከልል አንዱ ዋንግ ዩ የተባለው ቻይናዊ ነው።

ከዚህ ሌላ ዩናይትድ እስቴትስ በኅዋ ባሠማራችው ኬፕለር ቴሌስኮፕ አማካኝነት ፤ ፀሐይና ጭፍሮቿ በሚገኙበት ፤ ፍኖተ- ኀሊብ በሚሰኘው የኅዋ ክፍል 50 ቢሊዮን ያህል ፕላኔቶች ሳይገኙ እንደማይቀሩ የሥነ-ፈለክ ጠበብት ጠቁመዋል። ከእነዚህ መካከል 500 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ህይወት ያለው ነገር ሊገኝባቸው እንደሚችልና በፀሐዮቻቸው ዙሪያ ፤ የሚገኙበትን አካባቢ ማመላከት እንደማያዳግት ነው ፣ ጠበብቱ አክለው የገለጹት። ከ 3 ሳምንት ገደማ በፊት የአሜሪካው የጠፈር ምርምር መሥሪያ ቤት ፣ 1,235 ፕላኔቶች ፣ ከእነዚህም መካከል 68ቱ በመጠን ከእኛዋ ምድር ጋር እንደሚመሳሰሉና ፤ ከ 156,000 በላይ በሚሆኑ ከዋክብት (ፀሐዮች) ዙሪያ ምኅዋራቸውን ጠብቀው እንደሚሽከረከሩም ነው የሚነገረው። 590 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎበት የተሠራውና ቢያንስ ለ 3 ዓመት ከመንፈቅ ኅዋ ውስጥ የምርምር ተግባሩን እንዲያከናውን አሜሪካ ሃቻምና ያመጠቀችው ኬፕለር የተሰኘው የኅዋ ቴሌስኮፕ፣ 4,5 ሚሊዮን ገደማ ከዋክብት በሚገኙበት የፍኖተ-ኀሊብ ከፊል ነው እንዲያተኩር የተደረገው። እጅግ ዘመናዊ የተሰኙትን ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ ካሜራዎችን እንዲያነጣጥሩ የሚያደርገው ኬፕለር መንኮራኩር፣ በተለይ ከ 100,000-150,000 ብዛት ባለቸው በዙሪያቸው ፕላኔቶች በሚሽከረከሩባቸው ከዋክብት ላይ ይሆናል ይበልጥ ተልእኮውን እንዲያሳካ የሚፈለገው።

በፈረንሳይና እስዊትስዘርላንድ ድንበር ፤ በትኅተ-ምድር የተደራጀው የአውሮፓውያን የኑክልየር ምርምር ጣቢያ (CERN) በበኩሉ፤ ከ 10 ሳምንታት ዕረፍት በኋላ በሚመጣው ወር ፣ «ላርጅ ሓድረን ኮላይደር » በሚሰኘው ፣ የአቶምን ኢምንት ቅንጣቶች በሚጨፈልቀው ዐቢይ መግነጢሳዊ መሣሪያ ምርምሩን ይጀምራል።

ፍጥረተ ዓለም ፤ አሁን በሚገኝበት ሁኔታ እንዴት ሊገኝ ቻለ? ዝነኛው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አይንሽታይን እ ጎ አ በ 1905 ዓ ም የቀመረውን ልዩ የ «ሪላቲቢቲ» ነባቤ-ቃል መሠረት በማድረግም ይሆናል፣ CERN የወደፊቱን የምርምር ዘርፍ የሚያካሂደው። «ጥቁር ጉድጓዶች » (ብላክ ሆልስ)እንዴት ሊከሠቱ ቻሉ? እንዲሁም የ «ሂግስ ቅንጣት» ወደፊት ላቅ ያለ የምርምር ትኩረት የሚደረግባቸው ይሆናሉ። ይህም እስካሁን የተያያዙ ከሚባሉት 4 ዘርፎች፤ ርዝማኔ ፤ ስፋት(ወርድ) ጥልቀትና ጊዜ ባሻገር ጎን ለጎን

የተዘረጉ ፍጥረተ ዓለማትንም ይዳስሳል። ጥቁር ጉድጓዶች ማለት የከሠሙ ከዋክብት ናቸው። እነርሱም ለሰዎች በታወቀው የፍጥረተ ዓለም (ዩኒቨርስ ) ክፍል፣ በዛ ያሉ የተጫፈሩ ከዋክብትና ፕላኔቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚታዩ ናቸው። በጥቁር ጉድጓዶች፤ የስበቱ ኃይል (ግራቪቲ) እጅግ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ የተነሣ፣ ብርሃንን ሳይቀር ሰልቅጦ ነው የሚያስቀር። ይሁንና ሳይንቲስቶቹ ይህን በሚገባ ለማወቅ ገና ሰፊ ምርምር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይስማሙበታል። የግዙፍ ቁስ አካል ምንጭ ምንድን ነው? የሂግስ ቦሰን ቅንጣት ወይም የእግዚአብሔር ቅንጣት ስለሚሰኘው ፣ ከ 13,7 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ከግዙፉ ፍንዳታ በኋላ፣ ለተዘረጋው ፍጥረተ-ዓለም መነሻ ነው የሚባለውን ቅንጣት ለማግኘትና በትክክል ለማረጋገጥ እስካሁን ያልተቻለና ምርምር የሚካሄድበት ጉዳይ ነው።

21 የአውሮፓ መንግሥታት የሚሳተፉበት የኑክልየር ምርምር ጣቢያ ተግባር፣ ታላላቅ መንግሥታት ማርስን ለማሰስ የሚያደርጉት ዝግጅት፣ በከርሠ ምድር ለምሳሌ ያህል በአንታርክቲካና በደቡብ አፍሪቃ እጅግ ጥንታዊ የሆነ ፈሳሽ ውሃ ባህርይ ለማወቅ የሚደረገው ምርምር ፣ ሁሉም፣ የህይወትን አመጣጥ፣ የፍጥረትን አጀማመር ለማወቅ የሚደረግ ጥረት ክፍል መሆኑን ነው የምንረዳው።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ፤ ከ ዩናይትድ እስቴትስ፣ ካናዳ፣ ጀርመንና ደቡብ አፍሪቃ የተውጣጡ፣ ዓለም አቀፍ ጠበብት፣ ዊትዋተርስራንድ በሚገኘው የወርቅ ማዕድን 3 ኪሎሜትር ጥልቀት ላይ ሁለት ቢልዮን ዓመት ያስቆጠረ የተቋረ ውሃ ለማግኘት በቅተዋል። ውሃው ምድር ስትፈጠር የነበሩ የመጀመሪያዎቹ በቀላሉ በዓይን የማይታዩ የነፍሳት ዓይነት እንደተገኙበት ፤ ውሃው ራሱ በዛ ያለ የ«ኒዎን» ጋዝ የተከማቸበት መሆኑ ነው የተነገረው።

ከክፍለ-ዓለማቱ ሁሉ እጅግ ቀዝቃዛ በሆነውና ክረምት ከበጋ በበረዶ እንደተሸፈነ በሚገኘው አንታርክቲካ፣ 15 ሚሊዮን ዓመት የሆነውን ከበረዶ ቁልልም ሆነ ከበረዶ ተራራ ሥር የሚገኘውን ምሥጢር ለማወቅ የሩሲያ ሳይንቲስቶች ሠርሥረው 3,750 ሜትር ጥልቀት ሳይደርሱ እንዳልቀሩ ፣ በደቡባዊው የምድር ዋልታ፣ አቅራቢያ የሚገኘው የሩሲያ ቮስቶክ የምርምር ጣቢያ ኀላፊ አሌክሴይ ቱርክዬ አስታውቀዋል። በቅዝቃዜ የዓለም ክብረ-ወሰን ፤ 89,2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የተመዘገበው በዚያ ነው። ሩሲያውያኑ ሳይንቲስቶች እንዳሉት፤ የሐይቁ ጥልቀት ፕላኔታችን ፣ ከበረዶ ዘመን በፊት ፣

ህይወት ያላቸው ነፍሳት ፣ እንዴት ሊገኙ እንደቻሉ ፍንጭ ሳይሰጥ አይቀርም። ያን በመሰለ ብርቱ ቅዝቃዜ፣ የሚገኝ ህይወት ፤ በማርስና «አውሮፓ» በምትሰኘው የጁፒተር ጨረቃም ተመሳሳይ ሁኔታ መኖሩን ሊጠቁም እንደሚችልም ነው ተመራማሪዎቹ በተጨማሪ ያስረዱት።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ