1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተባባሰው የህዋሓት ውዝግብ

ሰኞ፣ ኅዳር 2 2017

በሃይማኖት መሪዎች አሸማጋይነት ወደ ንግግር ተመልሰዋል ተብለው የነበሩ የህወሓት ሁለት ቡድኖች ወደሌላ ፍጥጫ ገብተዋል። የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ጉባኤ ያደረገው የህወሓት ቡድን መፈንቅለ መንግሥት እያካሄደ ነው ሲል ከሷል።

https://p.dw.com/p/4mtIP
የህወሀት ሰንደቅ
በሃይማኖት መሪዎች አሸማጋይነት ተገናኝተው፥ በልዩነቶቻቸው ላይ ለመነጋገር ተስማምተዋል ተብለው የነበሩት ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ዳግም ወደ ከረመው ውዝግብ የተመለሱ መስለዋል። ፎቶ ከማኅደርምስል Million Haileyessus/DW

የህዋሀት የተባባሰው ውዝግብ

 

ባለፈው ሳምንት በሃይማኖት መሪዎች አሸማጋይነት ተገናኝተው፥ በልዩነቶቻቸው ዙርያ ለመነጋገር ተስማምተዋል ተብለው የነበሩ ሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ዳግም ወደ ከረመው ውዝግብ የተመለሱ ይመስላሉ። ትናንት እሑድ መግለጫ ያወጣው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፥ ሕገወጥ ጉባኤ አደረገ ያለው ህወሓት ከቆየው የመንግሥት ሥራዎች የማደናቀፍ ተግባሩ ተሻግሮ፥ ይፋዊ መፈንቅለ መንግሥት ወደ መፈፀምና ፍፁም ስርዓት አልበኝነት ወደ ማስፈን ተሸጋግሯል ብሏል። ለዚህም በመቐለ ከተማ አስተዳደር እና በትግራይ ሰሜን ምዕራብ እንዲሁም ማእከላዊ ዞኖች እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ማሳያ ናቸው ሲል ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት «ከትግራይ ሠራዊት ጋር ተግባብተናል፣ ከላይ እስከታች የመንግሥትን መዋቅር ለመቆጣጠር ጨርሰናል» እያለ ሰፊ ማደናገሪያ በማሰራጨት ላይ ተጠምዷል ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የከሰሰ ሲሆን ይህ ግን «አጉል ተስፋ» ሲል አጣጥሎታል።

መግለጫው እንደሚለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ህወሓት ለማዳን በሚደረግ ጥረት ከማንኛውም አካል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ ለመነጋገር ዝግጁ ናቸው ያለ ሲሆን ይሁንና በሥልጣን ክፍፍል ጉዳይ ግን ወደ ድርድር እንደማይቀርብ አቋሙ አስታውቋል። በዚህ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርያቀረበውን የመፈንቅለ መንግሥት ክስ አስመልክቶ በደብረፅዮን ከሚመራው የህወሓት ቡድን ምላሽ ለማግኘት በህወሓት ፅሕፈት ቤት ተገኝተን እንዲሁም በስልክ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይሁንና ህወሓት ከዚህ በፊት ይሰጣቸው በነበረ መግለጫዎች በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የሚገባውን የሥልጣን ድርሻ እንደሚጠይቅ ሲገልፅ ቆይቷል። በአንፃሩ ደግሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተቆጣጠረው ኃይል የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመፈፅም እየሠራ አይደለም፣ ፍላጎቱ የሥልጣን ጊዜውን ማራዘም ነው ሲል ሲወቅስ ይሰማል። በቅርቡ በሰሜን ምዕራብ ዞን አድያቦ በተደረገ «ሕዝባዊ» የተባለ የውይይት መድረክ የተናገሩት የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ «በጊዜያዊ አስተዳደሩ ያለው ኃይል ሥልጣን የማራዘም ፍላጎት አለው» ሲሉ ከሰዋል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሰባት ሲቪል ተቋማት ቅዳሜ እና እሑድ ካካሄዱት ስብሰባ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ፥ የህወሓት መሪዎች ክፍፍል የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በሙሉእነት እንዳይተገበር ዕንቅፋት ሆኖ ይገኛል ነው ያሉት።

የፅላል ሲቪል ማኅበረሰብ ምዕራብ ትግራይ አመራር አቶ ዳኒኤል ነጋሽ «የትግራይ ፖለቲካዊ መሪዎች በተለይም የህወሓት አመራሮች፥ ካለፈው ድክመታቸው እና ውድቀታቸው ሳይማሩ በእልህ እና በእኔነት መንፈስ ወደሌላ ቀውስ እየተጎዙ» እንደሆኑ በመጠቆም የተፈጠረው ቀውስ በውይይት መፍትሄ እንዲፈለግለት ጥሪ አቅርበዋል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ