1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህወሓት አመራሮች ክፍፍል እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈጠረ ውዝግብ ሥጋት ፈጥሯል

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2016

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አመራሮቹን ለውዝግብ የዳረገውን ጉባኤ ሲያጠናቀቅ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሊቀ-መንበርነታቸው ቀጥለዋል። አቶ አማኑኤል አሰፋ ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው አቶ ጌታቸው ረዳን ተክተዋል። ጉባኤውም ይሁን ውጤቱ ግን በምርጫ ቦርድ እውቅና አልተሰጠውም። የፖለቲካ መሪዎችና ነዋሪዎች የተፈጠረው ውዝግብ አስግቷቸዋል።

https://p.dw.com/p/4jeM0
የህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል
ለሰባት ዓመታት ገደማ ህወሓትን የመሩት ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው የፓርቲያቸው 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠናቀቅ በሊቀ-መንበርነታቸው ቀጥለዋል።ምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትን ከምክትል ሊቀመንበርነት አሰናብቶ ተጠቀቀ-ከዚያስ?

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ በከፍተኛ አመራሮቹ መካከል በተፈጠረ ክፍፍል ኃይለኛ ውዝግብ ውስጥ ተዘፍቋል። በህወሓት ሊቀ-መንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው አንድ ክንፍ ባካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ሥራ አስፈፃሚ፣ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት መርጧል። ጉባኤው በሰባተኛ ቀኑ ሲጠናቀቅ ደብረፅዮን ገብረሚካኤልን ሊቀ-መንበር አድርጎ መርጧል። አቶ አማኑኤል አሰፋ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን በመተካት ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነዋል።

ጉባኤውም ሆነ ምርጫው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ባያገኝም ውጤቱ ግን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን ከህወሓት አመራር ገፍቶ አስወጥቷል። በእርግጥ አቶ ጌታቸው፣ የህወሓት የቁጥጥር ኮሚሽን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጉባኤው "ህጋዊ አይደለም" የሚል አቋም አላቸው።

ህወሓት በአመራሮቹ መካከል የከፋ መቃቃር ሲያጋጥመው የአሁኑ የመጀመሪያ ባይሆንም ትግራይ ከደም አፋሳሽ ጦርነት በቅጡ ሳታገግም የተከሰተ መሆኑ ግን ሥጋት የፈጠረ ጉዳይ ነው። ይኸ ሥጋት ደግሞ በመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ ይንጸባረቃል።

ሁለት ዓመት በዘለቀው ጦርነት የተሳተፈው ዮሐንስ ክፍሎም በሁለቱ የህወሓት አመራር ቡድኖች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል “የትግራይ ህዝብን ወደ አደጋ የሚያስገባ” እንደሆነ ሥጋት አለው። ልዩነቱ “የትግራይ ህዝብ ዋጋ የከፈለበትን እና ልጆቹ የሰጠበትን ትግል ዋጋ የሚያሳጣ እና ወዳልተፈለገ መንገድ የሚመራ ነው” የሚለው ወጣቱ ዮሐንስ “ከንቱ የስልጣን ሽኩቻ” በማለት ይገልጸዋል።

የትግራይ ተዋጊዎች
ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከኤርትራ ወታደሮች እና ከአማራ ኃይሎች ጋር በተደረገው ጦርነት የተሳተፈው ዮሐንስ ክፍሎም በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት “የትግራይ ህዝብን ወደ አደጋ የሚያስገባ” እንደሆነ ሥጋት አለው።ምስል YASUYOSHI CHIBA/AFP

መከፋፈሉን “የሚያሳዝን እና የማንጠብቀው ነው” የሚለው ዳንኤል ለምለም “ህዝባችን ወደ ቀዬው እንኳን ሳይመለስ፣ በርካታ ችግሮች ሳይፈቱ አመራሩ እንዲህ ሆኖ ስታየው ያሳፍራል” ሲል ይወቅሳል። ዳንኤል “ካለፈው መጥፎ ጊዜ የባሰ ነው እየመጣ ነው” የሚል ሥጋት አለው።

እነ ማን ናቸው?

በሐውልቲ ሰማዕታት አዳራሽ የተካሔደው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና አልተሰጠውም። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም አልተሳተፉም። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከፍተኛ የፓርቲው ባለሥልጣን ያልተሳተፉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥር 19 መድረሱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከጉባኤው ራሳቸውን ያገለሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በስብሰባው እንዲሳተፉ ጥሪ ቢቀርብላቸውም አልተቀበሉም። ጠቅላላ ጉባኤው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የቁጥጥር ኮሚሽን በፓርቲው ሕገ-ደንብ መሠረት የሥልጣን ጊዜያቸው በማብቃቱ በህወሓት ሥም ፖለቲካዊ ሥራዎች ማከናወን እንደማይችሉ ወስኗል።

ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጉባኤው ሲጀመር ባሰሙት ንግግር “በፓርቲያችን ውስጥ ተፈልፍሎ ፓርቲያችንን ለመበተን እየሰራ ያለ የጥፋት ቡድን ያደረገው እና እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በየሰዓቱ እየፈጠረ ያለው መደነጋገር ሁኔታዎች ከመጥፎ ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋግረዋል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጉባኤ ባካሔደው የህወሓት የአመራር ቡድን ውስጥ ከደብረፅዮን በተጨማሪ በፓርቲው ውስጥ ረዘም ላሉ ዓመታት ግንባር ቀደም የነበሩ ፖለቲከኞች ይገኛሉ። ከህወሓት ጉምቱ አመራሮች አንዱ የሆኑት ዶክተር አዲስዓለም ባሌማ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ዓለም ገብረዋሕድ በዚሁ ቡድን ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በ14ኛው ጠቅላላ ጉባኤ
ጠቅላላ ጉባኤ ባካሔደው የህወሓት ክንፍ (ከግራ ወደ ቀኝ) አቶ ዓለም ገብረዋህድ፣ ዶክተር አብርሀም ተኸስተ፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር፣ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና ዶክተር አዲስዓለም ባሌማን የመሳሰሉ ከፍተኛ አመረar,oce ይገኛሉ። ምስል Million Haileselassie/DW

ዶክተር ደብረጽፅዮን በሕዳር 2009 አቶ አባይ ወልዱን ተክተው የህወሓትን መሪነት ሲረከቡ በምክትልነት የተመረጡት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር በዚህ ቡድን ውስጥ ይገኛሉ። ይኸ ቡድን የኢትዮጵያ የገንዘብ እና የኤኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር አብርሃም ተከስተ እና ለረዥም ዓመታት የኢትዮጵያን የደሕንነት መሥሪያ ቤትን የመሩት አቶ ጌታቸው አሰፋን ጭምር ያካትታል።

አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሁለት ከፍተኛ የጦር አዛዦችን ጨምሮ ከፌድራል መንግሥቱ፣ የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ኃይሎች ጋር ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 የተካሔደውን ጦርነት የመራው “የትግራይ ሴንትራል ኮማንድ” አብዛኞቹ አባላት በዚህ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ ጌታቸው አሰፋ፣ ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር እና ዓለም ገብረዋሕድ የዕዙ አባላት ነበሩ። ዕዙ ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ እና ጄኔራል ታደሰ ወረደን የሚያካትት ነው። የህወሓት አመራር ለሁለት ሲከፈል ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ያካተተው የትግራይ የጸጥታ መዋቅር ገለልተኛ እንደሚሆን አስታውቋል። 

ይሁንና ክፍፍሉ እንዲ በጉልህ ሳይወጣ  በህወሓት ላይ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ በደረሰበት ጊዜ የጦሩ ከፍተኛ አዛዦች በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ወጥተው "ህወሓት በአለፈው የትጥቅ ትግልም ሆነ አሁን በክልሉ ከፍተናኛ የመሪነት ሚና የተጫወተና በመጫወት ላይ ያለ ድርጅት ነው፤ ለዚህ ተግባሩ ሓወልት ሊሰራለት የሚገባ ድርጅት ነው" በማለታቸው ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል።

በጉባኤው ሳይሳተፍ የቀረው ሁለተኛ ጎራ እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ሁሉ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ በኃላፊነት የተሾሙ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሚገኙበት ነው። መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን የመሳሰሉ ግዙፍ ኩባንያዎች በሥሩ የሚያስተዳድረው የትግራይ መልሶ ማቋቋም ድርጅትን (EFFORT) ከዚህ ቀደም በኃላፊነት የመሩት በየነ መክሩ በዚህኛው ጎራ ተካተዋል።

የትግራይ ክልል ምክረ ቤት አፈ-ጉባኤ የነበሩት ሩፋኤል ሽፋረ፣ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረ ሕይወት፣ የትግራይ ጤና ቢሮ ኃላፊ ሆነው የሠሩት ዶክተር ሐጎስ ጎደፋይ፣ የትግራይ ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኤ ሓለፎም በሁለተኛው ምድብ ከተካተቱ መካከል ይገኙበታል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ
14ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ የተቃወሙት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከህወሓት ምክትል ሊቀመንበርነታቸው ተሽረዋል። ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP

የሁለተኛው የህወሓት ቡድን መሪ ተደርገው እየተቆጠሩ ያሉት አቶ ጌታቸው ባለፈው ቅዳሜ ከትግራይ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጠቅላላ ጉባኤ ያካሔደው የህወሓት አመራር “የትግራይን ሕዝብ ዳግም ወደ አደጋ የሚከት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” ሲሉ ከሰዋል።

አቶ ጌታቸው “የህዝብ የሰላም ፍላጎት ወደጎን በመተው ለጊዜው ማን መሆኑ በግልፅ ከማይታወቅ እና እነሱ ደጀን ይሆነናል ያሉት የውጭ ኃይል ተማምነው፥ ያለ የሆነ ዝግጅት፣ የተወሰኑ ግለሰቦች ጠባብ ፍላጎት ሲባል የትግራይ ህዝብን ዳግም ወደ አደጋ ለመዳረግ የሚደረግ እንቅሰቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው” ሲሉ ተናግረዋል።

የ14ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ “ይኸ አገላለጽ ትክክል አይደለም” ሲሉ የአቶ ጌታቸውን ክስ አስተባብለዋል። ፓርቲያቸው “በትግራይ ሕዝብ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት እና በተቋማዊ አሰራር” እንደሚያምን የገለጹት አቶ አማኑኤል “ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ ፖለቲካዊ መንገድ ይፈታሉ ብለን እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል።  

አቶ ጌታቸው ግን 14ኛው የህወሓት ጉባኤ በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ሥምምነት “ባለቤት አልባ ሊያደርግ” እንደሚችል ሥጋት አላቸው። በጉባኤው መክፈቻ ባሰሙት ንግግር ደብረፅዮን “ህወሓት ከፈረሰ የፕሪቶርያው ሥምምነት አይኖርም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ተቀስቅሶ ብርቱ ሰብአዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ ያስከተለውን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት የገታው የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት በፌድራል መንግሥት እና በህወሓት የተፈረመው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በሐላላ ኬላ
በፕሪቶሪያ ከተፈረመ ግጭት የማቆም ሥምምነት በኋላ የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ግንNUነት የመሻሻል አዝማሚያ ቢያሳይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም ከትግራይ ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት “አሁንም ጦርነት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ” ብለው ነበር።ምስል Ethiopian Broadcasting Corporation

በኋላ አልነገረንም እንዳትሉ

ሥምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚሩት የፌድራል መንግሥት እና ህወሓት ግንኙነታቸውን ቀስ በቀስ እያደሱ ቢሔዱም መፍትሔ ያልተበጀላቸው ጉዳዮች ብዙ ናቸው። ፌድራል መንግሥቱ እና ህወሓት ግጭት የማቆም ሥምምነቱን ወደ ተሟላ የሰላም ሥምምነት ለመቀየር የሚያደርጉት ፖለቲካዊ ውይይትም በሚገባው ልክ አልተራመደም። በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው መተማመንም ጥያቄ የሚነሳበት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከዚህ ቀደም ከትግራይ ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረጉት ውይይት “አሁንም ጦርነት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ” ብለው ነበር። “ጦርነት ይፈልጋሉ” ብለው የከሰሷቸው ሰዎች “ይብቃችሁ ሊባሉ ይገባል” ያሉት ዐቢይ “በኋላ አልነገረንም እንዳትሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ማካሔድ ያለበት በምርጫ ቦርድ ከተመዘገበ በኋላ እንደሆነ አስገንዝበው ነበር። ዐቢይ “ምርጫ ቦርድ ካልተቀበለው ህወሓትን፤ ሕጋዊ ፓርቲ ካላለው በምርጫ ሊሳተፍ አይችልም። መንግሥት ሊሆን አይችልም። ምን ማለት ነው? ተመልሰን ደግሞ ጦርነት እንገባለን ማለት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

ህወሓት “በአመጻ ተግባር ተሰማርቷል” በሚል ጦርነት በተቀሰቀሰ በወራት ልዩነት በጥር 2013 ያጣውን ሕጋዊ ምዝገባ ለማስመለስ የሚያደርገው ጥረት ከፌድራል መንግሥቱ እና በፓርቲው ውስጥ ውዝግብ የፈጠረ ጉዳይ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓርማ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ለህወሓት ባለፈው ነሐሴ 3 “የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ የምዝገባ ሰውነት ማረጋገጫ” ቢሰጥም ተቀባይነት አላገኘም። ምስል Ethiopian National Election Board

በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ባለፈው ነሐሴ 3 ቀን 2016 “የክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲ በልዩ ሁኔታ የምዝገባ ሰውነት ማረጋገጫ” ሰጥቷል። ህወሓት ግን የተሠረዘው ወደነበረበት እንዲመለስ እንጂ እንደ አዲስ መመዝገብ አይፈልግም። የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ምዝገባ “በፕሪቶሪያ ሥምምነት ላይ ያልተመሠረተ” ያለው ህወሓት የምዝገባ ማረጋገጫውን አልተቀበለም።

የፌድራል መንግሥት ግን “የህወሓት የሕግ ሰውነት አግባብ ባለው ሕግ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሠራር መሠረት ብቻ እልባት ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ” ነው የሚል አቋም አለው። የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ባለፈው ሣምንት “የህወሓት የሕግ ሰውነት እና የምዝገባ ጉዳይ በተመለከተ በፕሪቶሪያ ሥምምነት ውስጥ የወሰደው የተለየ ኃላፊነት ወይም ግዴታ አልነበረም” ብሏል።

የሕግ ባለሙያ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፕሪቶሪያውን ሥምምነት ተግባራዊ ማድረግ ነበረበት ሲሉ ይሞግታሉ። “በፌድራል መንግሥቱ ውስጥ ያሉ ማናቸውም ተቋማት የፕሪቶሪያውን ሥምምነት ማክበር እና እንዲከበር የማድረግ፤ መፈጸም እና እንዲፈጸም የማድረግ ግዴታ አለባቸው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዶክተር ደብረፅዮንም ሆኑ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሯቸው ቡድኖች በህወሓት ምዝገባ ረገድ የአካሔድ እንጂ የአቋም ልዩነት የላቸውም። ሁለቱም የህወሓት ሕጋዊ ምዝገባ ወደነበረበት እንዲመለስ ይፈልጋሉ።

ተቃዋሚዎች ምን ይላሉ?

የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር ዶክተር ደጀን መዝገበ ግን ከህወሓት እውቅናም ሆነ ከጠቅላላ ጉባኤ ጋር የተያያዘ ውዝግብ ወደ ሕዝብ መሸጋገር የለበትም ሲሉ ይሞግታሉ። ዶክተር ደጀን መዝገበ በመቐለ ሦስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት መግለጫ “የአንድ ፓርቲን ሕጋዊ ሰውነት ለማግነት የሚደረግ ጉባኤ ፓርቲውን እና የፓርቲዎች ሕጋዊነትን የሚመለከት የፌድራል ተቋም አለ። እነሱ የሚጨርሱት እንጂ ከፓርቲው እና ከዚያ ተቋም ውጪ ወደ ሕዝብ የሚመጣ ምንም አይነት ሁኔታ መኖር እንደሌለበት እናምናለን” ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ሕዝብም “ተመልሰን ወደ ጦርነት እንዳንገባ ሥጋት አለው፤ እኛም አለን” የሚሉት ዶክተር ደጀን “ይኸ ሥጋት ትግራይ ካለው ከህወሓት ብቻ የሚመነጭ ሳይሆን ይኸንን ከትግራይ ህዝብ ጋር አጣብቆ የማየት አባዜ ያለበት የኢትዮጵያ ፖለቲካም ጭምር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) እና የሳልሳይ ወያነ ትግራይ አመራሮች
የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) አመራሮች የህወሓት አመራሮች የውስጥ ክፍፍል ወደ ትግራይ ሕዝብ ተሻግሮ ችግር ሊፈጥር እንደማይገባ አሳስበዋል። ምስል Million Haileselassie/DW

ህወሓት ያካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ ውጤት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና ባያገኝም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር እጣ ፈንታ ላይ የሚወስን ነው። የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር 14 የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች፣ 4 የትግራይ ሠራዊት ወታደራዊ መኮንኖች፣ 5 ምሁራን እና 2 የታላቋ ትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ (ባይቶና) አባላትን ያቀፈ ነው። አቶ ጌታቸው በመጋቢት 2015 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት በህወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቅራቢነት ነው።

የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀ-መንበር አቶ አሉላ ኃይሉ የህወሓት የውስጥ ችግር ጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ሥጋት አላቸው። “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቋቋም በፕሪቶሪያ ውልም ቢሆን አካታች እንዲሆን ተጽፎ እያለ በሙሉ በሙሉ የህወሓት ሲደረግ” ዋናው ስህተት እንደተፈጠረ ይተቻሉ። አቶ አሉላ አሁን ፓርቲው የገጠመው ችግር ሲመጣ “መንግሥትንም ይዞ ይወድቃል” ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት በጸደቀ ደንብ የተቋቋመው በመጋቢት 2015 ነው። አስተዳደሩ አካታች ቢባልም ከተቃዋሚዎች መቀመጫ ያገኘው ግን ባይቶና ብቻ ነው። የባይቶና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሴፍ በርኸ “የተተከለው ጊዜያዊ አስተዳደር የህወሓት ስለሆነ፤ ህወሓት ደግሞ በፓርቲው ጉዳይ ላይ ስለተጠመደ፤ ትግራይ ከአመራር ወይም ከአስተዳደር ውጪ ሆናለች ብለን ነው  የምናስበው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ግዛቶች ተረስተዋል፤ ሕዝቡ ኬንዳ ላይ ተጥሎ ያለው። ስለዚህ መንግሥት ያስፈልጋታል፤ አስተዳደር ያስፈልጋታል” የሚሉት አቶ ዮሴፍ “ሁሉንም ፖለቲካ ኃይሎችን ያካተተ ምክር ቤት ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር መቋቋም አለበት” በማለት ይሞግታሉ። 

በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት በአቶ ጌታቸው ምትክ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ አዲስ ፕሬዝደንት ሊመርጥ እንደሚችል ይጠበቃል። በጠቅላላ ጉባኤ ያልተሳተፉ የህወሓት አመራሮች ውሳኔውን እንዴት ይቀበሉታል? የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትስ ምላሽ ምን ይሆናል? በመጪዎቹ ቀናት የሚታይ ይሆናል።

ሚሊዮን ኃይሥላሴ

እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር