የሄይቲው የምድር ነውጥ፣ ስባሪው ኮከብ «አፖፊስ»ና ዝካሬ-ቅጣው፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 13.01.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የሄይቲው የምድር ነውጥ፣ ስባሪው ኮከብ «አፖፊስ»ና ዝካሬ-ቅጣው፣

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ የሄይቲው የምድር ነውጥና ምድራችንን ያሠጋል የተባለው «አፖፊስ» ሥባሪ ኮከብ፣ እንዲሁም አንድ ዝካሬ ይኖረናል።

default

በካራይብ ባህር ፣ ከዶሚኒካን ሪፓብሊክ በስተምዕራብ የምትገኘው ሀገር ሄይቲ ትናንት በ Richter መለኪያ 7,0 የደረሰ ኃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ንጧት፣ ከ 200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች፣ ህይወታቸውን ሳያጡ እንዳልቀሩ ታውቋል፤ ምናልባትም አንድ ሺና ከዚያ በላይ የሚሆን ህዝብ በተደረመሱ ህንጻዎች ሥር ተቀብረው ሊሆን ይችላል ተብሎም ተሠግቷል። የነውጡ ማዕከል፣ ከመዲናይቱ ከ Port au Prince በስተደቡብ ምዕራብ 15 ኪሎሜትር ገደማ ራቅ ብሎ 8,3 ኪሎሜትር ጥልቀት ያለው ቦታ ሲሆን ፣ ነውጡም አግድሞሻዊ እንደነበረ የአሜሪካና የፈረንሳይ የምድር ነውጥ ተመራማሪ መ/ቤቶች አስታውቀዋል። በምዕራቡ ንፍቀ ክብብ እጅግ የደኸየች አገር መሆኗ የሚነገርላት ሄይቲ፣ ጠንካራ መሠረት በሌለው የቤት አሠራርና የተቀላጠፈ የአስቸኳይ ሁኔታ እርዳታ ማቅረቢያ ዘዴ ጉድለት ሳቢያ፣ አደጋውን የከፋ አድርጎታል። ብዙዎቹ የጥንት ህንጻዎች፣ ቤተ-መንግሥቱ ሳይቀር ፈራርሷል። አደጋው ከደረሰ በኋላ ፣ወዲያው በመዲናይቱ ባረፈው ከማያሚ፣ፍሎሪዳ የገባው አኤሮፕላን ተሣፋሪዎች፣ በአኤሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ያዩት ሁኔታ አስገርሟቸው እንደነበረ ነው የገለጡት።

«በእርግጥ የመሰለን ህንጻው ባንድ የሆነ ነገር እንደተመታ ነው። ግን፣ የምድር ነውጥ ነበረ። አደጋው ከደረሰ በኋላ ነው የመሬት መንቀጥቀጥ አጋጥሞ እንደነበረ ለመገንዘብ የቻልነው። »

እሳተ-ገሞራ፣ የምድር ነውጥ፣ የባህር ወለል ነውጥ የሚያስከትለው አደገኛ የውቅያኖስ ማዕበል(ሱናሚ)በምድራችን ላይ አልፎ- አልፎ ብርቱ ጥፋት ያስከትላሉ። የእሳተ-ገሞራ ክሥተት ፣ የፍጥረተ-ዓለም አንዷ አካል፣ ፕላኔታችን ፣ ከተፈጠረች 4,54 ቢሊዮን ዓመት ገደማ እንደሚሆን የሚነገር ሲሆን፣ ላይዋ ይቀዝቅዝ እንጂ ፣ ውስጧ፣ ምንጊዜም፣ የእሳትነት ባህርይ እንዳልተለየው ነው የምንገነዘበው። በምድራችን፣ የሚኖሩ ነፍሳት፤ በፕላኔታችን ግለትና ርደት ብቻ አይደለም ለጥፋት የሚዳርግ አደጋ የሚደቀንባቸው። ከፕላኔቶች ፣ ከዋክብትና ጨረቃዎች አንጻር፣ ከግንባታ ውጭ ፣ እንደ ትርፍ የካብ ድንጋይ የሚታዩት ሥብርባሪ ከዋክብትም አሥጊ መሆናቸው አይታበልም። የአሜሪካው የበረራና የኅዋ ምርምር ድርጅት (NASA)ከጊዜ በኋላ አቃሎ የተመለከተው የሥባሪ ኮከብ «አፖፊስ» አደጋ፣ በሩሲያውያን ሳይንቲስቶች አመለካከት አሳሳቢ ሆኖ ነው የተገኘው። እናም ሩሲያውያኑ ጠበብት፣ በ26 ዓመታት ውስጥ ከምድራችን ጋር ሊላተም ይችላል የተባለውን ሥባሪ ከከብ እንዴት አድርጎ መግታት ይቻል ዘንድ ፣ ምሥጢራዊ ምክክር እንደሚያደርጉ ከወዲያኛው ሰሞን፣ ነበረ ያስታወቁት። የሩሲያ የኅዋ ተመራማሪ ድርጅት ኀላፊ አናቶሊ ፐርሚኖቭ ፣ ሥባሪው ኮከብ፣ እ ጎ አ፣ በ 2036 ዓ ም፣ ከፕላኔታችን ጋር ሊጋጭ እንደሚችል በመጠቆም፤ በመቶ ሺ የሚቆጠር ህዝብ ህይወት እስኪጠፋ ከመጠበቅ፤ አሁን፣ ያወጣ-ያውጣ፣ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ወጪ በማድረግ፣ አደጋውን መግታት የሚቻልበትን መላ መሻት ነው የሚበጀው ይላሉ። በግምት 350 ሜትር ያህል ወርድ ያለው ሥባሪ ኮከብ እንደሚወረወር ድንጋይ ምድራችንን ከመታ የፈረንሳይን ያህል ሥፋት ያለው ቦታ ምድረ-በዳ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ሊከተል የሚችለውን ብርቱ አደጋ በማሰብ፣ ከሩሲያ ሌላ፣ የአውሮፓው ኅብረት ፣ ዩናይትድ እስቴትስና ቻይናን የመሰሰሉ አገሮች ጠበብት በመምከር አንድ ዓለም አቀፍ ፕሮጀክት መንደፍ ሳይኖርባቸው አይቀርም። ፐርሚኖቭ፣ «የኑክልየር ቦንብ ማፈንዳት አያስፈልግም፤ በፊዚክስ የተፈጥሮ ህግ መላ እንዲገኝ ነው የምንጥረው» ብለዋል። የአሜሪካው የኅዋ ድርጅት NASA ባለፈው ጥቅምት እንደገለጠው ከሆነ፣ በ 2036 ዓ ም፣ ሊደርስ የሚችለው አደጋ በአመዛኙ ሊያጋጥም እንደማይችል፣ ስሌቶች ይጠቁማሉ። እ ጎ አ ሚያዝያ 13 ቀን 2036 ዓ ም፤፣ በሥባሪ ከከብ «አፖፊስ» ሊደርስ ይችላል የተባለው አደጋ ፣ በተከታታይ ጥናቶች ጥቆማ መሠረት ከ 45,000 አንድ እጅ ሊያጋጥም እንደሚችል የተተነበየለት አደጋ አሁን ከሚልዮን 4 ገደማ ያህል ቢሆን ነው፣ -- የ NASA መግለጫ እንደሚለው!

RIA Novosti የተሰኘው የሩሲያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፣ እ ጎ አ በ 2029 ከአንዳንድ ሰው ሠራሽ ሳቴላይቶች ይበልጥ ቀረብ በማለት ፣ ከምድራችን 30 ሺ ኪሎሜትር ብቻ ርቆ የሚወነጨፈው ሥባሪ ኮከብ፣ የምኅዋሩን አቅጣጫ በመለወጥ፣ ከዚያ በኋላ፣ 7 ዓመት ቆይቶ፣ ከፕላኔታችን ጋር ሊላተም ይችላል።

ኢትዮጵያውያን ዕድሉን ካገኙ፣ የሚያበረታታቸው ሁኔታ ካለ፣ ለሀገር ልማት ዐቢይ አስተዋጽዖ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከቶውንም አያጠራጥርም። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ አቅራቢያ በዘመኑ የአላማያ ኮሌጅ ምሩቃን፣ የነበሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ፣ በግብርና ተሠማርተው ባበረከቱት አስመስጋኝ አስተዋጽዖ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሽልማት ለማግኘት መብቃታቸው አይዘነጋም።

ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን፣ በሁመራ ሰፊ ልማት በመዘርጋት ላገሪቱ ሰፊ የውጭ ምንዛሪ ያስገኙ የነበሩት፣ በዚያው ዘመን እንደነበረ የሚታውስ ነው። ሀገርን በግብርና ማልማት ለኢትዮጵያውያን እንግዳ ነገር አይደለም። አሁንም ቢሆን ገንዘብንና ዕውቀትን ሥራ ላይ በማዋሉ ረገድ ተቀዳሚው ጥሪ መቅረብ የነበረበት ሁኔታዎችም መመቻቸት የነበረባቸው በውስጥም በውጭም ለሚኖሩ የአገሪቱ ተዋላጆች ነበር።

በመጨረሻ፣ ሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ለግንባታ ወይም ለልማት፣ ከሚለው ጽንሰ ሐሳብ በመነሣት፣ በዚህ፤ መሬት ለልማት ወይስ ለባዕዳን ቅርምት? እየተባለ ክርክር እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ከ 4 ዓመት በፊት በዛሬዋ ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የትልቁን ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ዶ/ር ቅጣው እጅጉ ራእይ እናስታውሳችሁ። የሳይንስና ሥነ ቴክኒክ ዕውቀት እንዲሁም ወረት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ፣ በ 5 እና 10 ዓመት ውስጥ፣ ደረጃ በደረጃ፣ በምን ዓይነት አቅድ አገርን ከውድቀት ማንሳት እንደሚችሉ በህይወት በነበረበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር።----

(ድምፅ)----

ተክሌ የኋላ፣

አርያም ተክሌ