የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ትዕይንት | ኤኮኖሚ | DW | 06.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ትዕይንት

የጀርመን ሰሜናዊት ከተማ የሃኖቨር ዓለምአቀፍ የኢንዱስትሪ ትዕይንት ባለፈው ዕሑድ በይፋ ተከፍቶ እየተካሄደ ነው።

default

በዘንድሮው ትዕይንት ላይ ዋነኛዋ ተባባሪ ፈረንሣይ ስትሆን በጥቅሉ ከ 65 ሃገራት የመጡ ከስድሥት ሺህ የሚበልጡ አምራቾች የሥራ ውጤቶቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ። ወቅቱ የምርት መኪናዎችን የሚያመርተው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ካለፉት ዓመታት የኤኮኖሚ ቀውስ እያገገመ የመጣበት ሲሆን የትዕይንቱ ተሳትፎም አንዲሁ ከአሥር ዓመታት ወዲህ የላቀው መሆኑ ነው። የሃኖቨሩ ትዕይንት በጃፓኑ የአቶም ሃይል ጣቢያ አደጋ ሳቢያ በአማራጭ ኤነርጂ ላይ በሚደረገው ክርክር መጋረዱም አልቀረም።

የጃፓኑ የፉኩሺማ አቶም ጣቢያ አደጋ ምን ያህል የሃሣብ ለውጥን እንደጠየቀ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ባለፈው ዕሑድ በሃኖቨሩ ትዕይንት ላይ ያሰሙት ያሰሙት መክፈቻ ንግግር አመልክቷል።

“ከታዳሽ የኤነርጂ ምንጮች ዘመን ላይ ለመድረስ ከፈለግን ድፍረት ያስፈልገናል። አዲስ አስተሳሰብ፤ እንዲሁም አዲስ አቅጣጫ መያዝም ቁርጠኝ’ነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። እና እኔም በዚሁ መንፈስ ሁሉንም፤ በተለይም የጀርመን ኢንዱስትሪንና ሕዝቡንም በዚህ በኩል እንዲተባበር እጋብዛለሁ። ታዳሽ ኤነርጂ እፈልጋለሁ ያለ አስፈላጊውን መዋቅር ለማቆምም ዝግጁ መሆኑ ግድ ነው”

ይህ ጥሪ በትዕይንቱ ላይ የብዙዎችን ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ የቀረ አይመስልም። መድረኩም ተስማሚው ነበር ለማለት ይቻላል። የሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ኤግዚቢሽን ወይም ትዕይንት ከስድሥት አሠርተ-ዓመታት በላይ በዓለምአቀፍ ደረጃ ቀደምቱ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ የምርቶችና የአዳዲስ ጽንሰ-ሃሳቦች መከሰቻ መድረክ ሆኖ ቆይቷል። ኤግዚቢሽኑ በወቅቱ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒኩን መስክ የመሳሰሉ 13 የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቁልፍ የቴክክኖሎጂ ጥበቦች የሚታዩባቸውን ክፍሎች በስሩ የጠቀለለ ነው። የዘንድሮው ትዕይንት እስከፊታችን አርብ የሚዘልቅ ሲሆን ከዓለም ዙሪያ የመጡት 6,500 ኩባንያዎች የተሃድሶ ውጤቶቻቸውን ሲያቀርቡ ይሰነብታሉ።

የሃኖቨሩ ትዕይንት የሚካሄደው በአውሮፓ እንደገና የፊናንስ ቀውስ አደጋ እያሰጋ ባለበት ሰዓት ነው። ኤውሮን በድጋፍ ከውድቀት ለማዳን ጥረት መደረጉ የተሰወረ ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ የኤኮኖሚውን ዘርፍም ብርቱ ፈተና ላይ ሊጥል ይችላል። ይሁንና በሌላ በኩል ሰሞኑን በሃኖቨሩ ትዕይንት ላይ እንደሚታየው የተሳታፊዎቹ ኩባንያዎች ስሜት ጨርሶ ስጋት የተዋሃደው አይደለም። ይህ ደግሞ የሃኖቨሩ ትዕይንት ዘንድሮም ተሥፋ ሰጭ የኤኮኖሚ ዕድገት መለኪያ ሆኖ መታየቱን የሚያመለክት ነው። የተሳታፊው ቁጥር ባለፈው ዓመት ካቆለቆለ በኋላ ዘንድሮ መልሶ መጨመሩ የጀርመንን የኤግዚቢሽን ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ቮልፍራም ፍሪችን ጭምር በጣሙን ነው እፎይ ያሰኘው።

“በዚህ ዓመት 400 ኩባንያዎች ተመልሰው መጥተዋል። ከነዚሁ ግማሹ ደግሞ የውጭ ሃገራት ናቸው። ይህም የሚያሳየው ከሃገራት ክልሎች ባሻገር የዘለቀ የዕድገት ተሥፋ መኖሩን ነው”

በዘንድሮው ዝግጅት በመላው 13 ተናጠል የትዕይንት ዘርፎች ውስጥ ቁልፍ ርዕስ ሆኖ የሚገኘው የኢንዱስትሪ ምርቶችን ብቃት ከፍ የማድረጉ ጉዳይ ነው።

“በዘንድሮው የኢንዱስትሪ ትዕይንት ትልቁ ርዕስ ስማርት-ኤፊሸንሲይ፤ ማለት ዕውቀት የተመላው የሰከነ ብቃት ነው። ኩባንያዎቹ ከቀውሱ በኋላ በውስጥ ራሳቸውን ለማጠናከር ብቁ የሚያደርጉ ሞዴሎችንና መንገዶችን በመፈለግ ላይ ነው ያሉት። ይህ ነው ሰፊ ውይይት የሚደረግበት ሆኖ የሚሰነብተው”

የኢንዱስትሪው ዘርፍ ባልደረባ ሃርትቪግ-ፎን-ዛስ አያይዘው እንደሚሉት ኤነርጂ በአግባብ ጥቅም ላይ የሚውልበትን ሁኔታ ለማሟላት የሚደረጉ ተሃድሶዎችም የዚሁ አንድ አካል ናቸው። ታዳሽ የኤነርጂ ምንጮች፣ የኤነርጂ ብቃት፣ የአካባቢ አየር ጥበቃ፤ እነዚህ ሁሉ በፊናንሱ ቀውስ ወቅት ወደ ኋላ የተገፉ ጉዳዮች ነበሩ። ሆኖም የጃፓኑ የፉኩሺማ የአቶም ጣቢያ አደጋ በወደፊቱ የኤነርጂ አቅርቦት ላይ እንደገና አዲስ ውይይት እንዲስፋፋ ነው ያደረገው። ታዲያ የሃኖቨሩ ትዕይንትም ዘንድሮ በዚሁ ዘርፍ ላይ ብዙ ማተኮሩና ብዙ የሚታዩ ነገሮችን ይዞ መቅረቡ አልቀረም።

“በዚህ ዓመትም እርግጥ የተሃድሶው መስክና የኤነርጂው ዘርፍ ታላቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው። የሃኖቨሩ ትዕይንት በኤነርጂ ጉዳይ በሚያደርገው ጠንካራ ትኩረት የተነሣ በዓለም ላይ በዚሁ የቴክኖሎጂ መስክ ታላቁ ትዕይንት መሆኑ የሚታወቅ ነው”

ትኩረቱ ደግሞ ታዳሽ ኤነርጂን የማምረቱንና የማሰራጨቱን ያህል በአቶም ሃይሉ የወደፊት ዕጣ ላይም ነው። በመሆኑም ሁሉም የአቶም ሃይል ጣቢያዎች፤ እንዲሁም ቀደምቱ የነፋስ፣ የጸሃይና የባዮ-ኤነርጂ ዘርፎች ሁሉ የተሃድሶ ውጤቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል። በትዕይንቱ ላይ አንዱ አዲስ ነገርም የወደፊቱ ብቁ የኤነርጂ አጠቃቀም ራዕይ ክፍል ነው። የመፍትሄውን ዘርፍ “ሜትሮፖሊታን-ሶሉሺንስ” ብለውታል። ለምሳሌ በብልህነት በተዘረጋ መረብ አማካይነት ወደፊት የታላላቅ ከተሞች የኤነርጂ ስርጭት እንዴት ሊቀናበር እንደሚችል ይታያል።

የከተሞችን ዕድገት ካነሣን በተለይም ለታላላቅ ከተሞች መዋቅራዊ ችግሮች መፍትሄ መሻቱ ዘንድሮ በሃኖቨሩ ትዕይንት ላይም ጎልቶ ነው የሚታየው። በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ይበልጥ እየጨመረ የሚሄድ ነው። እና ከተሞችም ይበልጥ እየተለቁ ሜጋ፤ ማለት ግዙፍ ከተሞች መሆናቸው ቀጥሏል። ለግንዛቤ ያህል እነዚህ ግዙፍ የሚባሉት ከተሞች ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባቸው ናቸው። እና የኤነርጂና የውሃ አቅርቦቱ ከሕዝቡ ብዛት ዕድገት ተታጥሞ ባለማደጉ እነዚህ ከተሞች ከባድ ፈተና ላይ መውደቃቸው አልቀረም።

ችግሩ ደግሞ የአየር ብክለትን፣ የኤነርጂ ብክነትንና የቁሻሻ ክምር ችግርን ያስከትላል። ሊዚህም ነው የኢንዱስትሪው ዘርፍ አዲስ ምላሽ የሚጠይቅ መስክ እየሆነ የመጣው። በመሆኑም በሃኖቨሩ ትዕይንት ላይ የተለያዩ ኩባንያዎች የመፍትሄ አቅጣጫ ማሳየታቸው አልቀረም። ለነገሩ ቆሻሻ ቆሻሻ ብቻ አይደለም። በውስጡ ብዙ ኤነርጂንም የሚይዝ ነው። ግን ባለፉት አሠርተ-ዓመታት በታየው ቆሻሻን የማቃጠል ዘይቤ ብዙ ኤነርጂ ሲባክን ነው የኖረው። እናም አሁን በትዕይንቱ አዲስ ቴክኖሎጂ በአጋዥነት ቀርቧል።

“ቆሻሻውን እንዳለ አናቃጥለውም። እ’ንዲከፋፈል ነው የምናደርገው። ጠቃሚውን ነገር ከቆሻሻው በመለየት ከዚሁ ከቀረው ነገር ነዳጅ እናገኛለን። ይህም ቆሻሻው እንዳለ በቀጥታ እ’ንዲቃጠል አይደረግም ማለት ነው። በአንጻሩ ለሌሎች መሣሪያዎች በተተኪ ሃይልነት የምንጠቀመትን ነዳጅ ነገር ነው የምንፈጥረው”

ከቆሻሻ ኤነርጂ መፍጠር! የዚህ ቴክኖሎጂ አራማጆች በዛሬው ጊዜ የመሣሪያቸው ተፈላጊነት እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠብቃሉ። የታላላቅ ወይም እጅግ ግዙፍ ከተሞች የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ፍላጎት እያደገ እንደሚሄድ ሁሉ ማለት ነው። የጀርመኑ የኤሌክትሮኒክ ኩባንያ ዚመንስ ለምሣሌ የወደፊቱን መኖሪያ ቤት ሞዴል ለትዕይንት አቅርቧል። በዚህ መንገድ የተረፈው ሃይል እንደገና ወደ መረቡ እንዲመለስ ይደረጋል።

ኩባንያው እንደሚገምተው በዓለም ላይ አርባ በመቶው ኤነርጂ ወይም ሃይል በስራ ላይ የሚውለው በሕንጻዎች አኳያ ነው። በነገራችን ላይ ዚመንስ ኩባንያ አሁን የራሱን የከተሞችና የመዋቅር ዘርፍ ማነጽ ጀምሯል። የኩባንያው ባልደረባ ሽቴፋን ዴኒግ እንደሚያስረዱት ከሆነ ዓላማውም፤

“ዚመንስ ዘለቄታ ለሚኖራቸው ከተሞች ግንቢያ ያለውን የመዋቅራዊ መፍትሄ ከፍተኛ ፍላጎት ይገነዘባል። ይህንን ፍላጎትም ለማርካት እንፈልጋለን። በዚህ ዘርፍ ፍላጎቱ ከአማካይ መጠን በላይ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው የራሳችንን የቴክኖሎጂ መፍትሄ የሚያራምድ ዘርፍ ለመክፈት የተነሳነው። ዓላማችን የሕንጻዎች፣ የትራንስፖርትና የኤነርጂ ብቃት መፍትሄ ማቅረብ ነው”

በዓለም ላይ ዛሬ 900 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ ንጹህ የመጠጥ ውሃ የማግኘት ዕድል የለውም። ውሃን የማጣራቱ ጉዳይም ታዲያ በሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት አንዱ የአዲሱ መስክ መነጋገሪያ ርዕስ ነው። ግን በማደግ ላይ ባሉ ሃገራት የሚገኙት ግዙፍ ከተሞች ይህን ውድ የቴክኒኖሎጂ ጥበብ ከናካቴው ሊጠቀሙ ይችላሉ ወይ? ይህም የዓለም ባንክን ባልደረባ አድሪያና-ዴ-አጊናጋን ጨምሮ በርካታ ባለሙያዎችን በትዕይንቱ አኳያ እያነጋገረ ያለ ጉዳይ ነው።

”እርግጥ እነዚህ የቴክኖሎጂ ዘዴዎች በጣም ውድ እንደሆኑ እናውቃለን። ለዚህም ነው የዓለም ባንክ ክሊን-ኢንቨስትመንት-ፈንድ የሚል የገንዘብ ድጋፍን ያዘጋጀው። ይህም የሚፈጠረው ወጪ የተጠቃሚውን አቅም ካለፈ በድጎማ ተግባር ላይ እንዲውል ይደረጋል”

የሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት በፍጻሜው እንደተለመደው በርካታ የንግድ ውሎች የሚፈረሙበት ሲሆን ቢቀር በዚህ በጀርመን የኤኮኖሚው ዕድገት ተሥፋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉ የሚጠበቅ ነው። በታዳሽ የኤነርጂ ቴክኖሎጂ የተራመደችው ጀርመን በተለይም በዚህ ዘርፍ በሚታየው የተሃድሶ ግፊት ወይም ፍላጎት የገበያ ተጠቃሚ መሆን ለመቻሏም አንድና ሁለት የለውም።

መስፈን መኮንን

ሂሩት መለሰ