የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ትዕይንት | ኤኮኖሚ | DW | 10.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ትዕይንት

በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው ዓመታዊው የሃኖቨር የኢንዱስትሪ ትዕይንት በዚህ በጀርመን ካለፈው ሰኞ ወዲህ እየተካሄደ ነው።

የሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት ለጀርመን ብቻ ሣይሆን ከዚያ ባሻገርም የኤኮኖሚ ዕድገት አዝማሚያ መለኪያ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በዘንድሮው ትዕይንት ከ 62 ሃገራት የመጡ ከ 6,500 የሚበልጡ ኩባንያዎች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውን ይዘው በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በትዕይንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግማሽ የሚበልጡት ምርት አስተዋቂዎች ከውጭ ሃገራት ሲሆኑ አብዛኞቹ የመጡትም ካለፈው ዓመት የትዕይንቱ ተባባሪ ከቻይና ነው። ይህም የሃኖቨሩን ትዕይንት ዓለምአቀፍ ባሕርይ ይበልጥ የጠነከረ ያደርገዋል። በነገራችን ላይ የዘንድሮዋ ተባባሪ አገር ሩሢያ ስትሆን የትዕይንቱ ሃላፊ ዮኸን ኩክለር እንደሚያስረዱት ለዚህ መመረጧም ያለ ምክንያት አይደለም።

«ሩሢያ በመጀመሪያ ደረጃ እንደ አንድ የቡድን-ስምንት ዓባል መንግሥት በኤኮኖሚ ታላቅ አገር ናት። ሁለተኛ በኤነርጂ ተሃድሶ ረገድ እንበል እንደ ጋዝ አቅራቢ አገር ሚናዋ ከፍተኛ ነው። በሶሥተኛ ደረጃ ደግሞ ሩሢያ የራሷን ኢንዱስትሪ በዘመናዊ መልክ ለማስፋፋት ትፈልጋለች። እና በዚህ በኪል ከጀርመን ልምድ በመማር መካከለኛ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለማነጽ ነው የምትሻው»

በሌላ በኩል በሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት ዋዜማና አሁን በሂደቱ እንደሚታየው የኤኮኖሚ ዕድገቱ ተሥፋ ዘንድሮ ለዘብ ያለ ነው። እርግጥ ይህ ከጊዜው ሁኔታ አንጻር ብዙም የሚያስደንቅ አልሆነም። ጊዜው በኤኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ብዙ ጥርጣሬ የሰፈነበትና በራስ አለመተማመን የተጫነው እንደመሆኑ መጠን ጠንከር ያለ የኤኮኖሚ ዕድገት መተንበዩን ለዘርፉ ማሕበራት ቀላል አላደረገውም።

በመሆኑም ለምሳሌ ያህል ሃያሉ የጀርመን ኢንዱስትሪዎች ፌደራል ማሕበር ለጀርመን ለያዝነው ዓመት የተነበየው የ 0,8 ከመቶ ዕድገት ብቻ ነው። ይሁንና የኢንዱስትሪው ማሕበር መሪ ኡልሪሽ ግሪሎ እንደሚሉት በመሠረቱ የአውሮፓ የዕድገት መንኮራኩር ስትባል የቆየችው ጀርመን በተሻለ ሁኔታ ላይ መገኘት ነበረባት።

«ለነገሩ የበለጠ መራመድ እንፈልጋለን፣ አለብን፣ እንችላለንም። ይሄ ትክክለኛ ነገር ነው። እናም በመሠረቱ ተሥፋ የማልቆርጥ በመሆኔ ቢቀር በአንድ ከመቶ ማደግ አለብን ባይ ነኝ። ይህ ደግሞ ግሩም በሆነ ነበር። ግን ገቺ ነፋስ በአቅጣጫችን እየነፈሰ ነው። ስለዚህም ያሰብነው ሊሰምር የሚችለው ተጨማሪ ቀውስ ካልተከሰተ፤ እንበል የኤውሮን ቀውስ እንደነገሩ መቆጣጠር ከቻልን ብቻ ነው። የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በኤነርጂ ዋጋና ሌሎች ሁኔታዎች ካገዝን ነው። በዚህ ሁኔታ ብቻ ጥቂት የበለጠ ለማደግ እንችላለን። ግን እስቲ ሁሉንም በዓመቱ መጨረሻ እንመልከተው። በበኩሌ ሰለ አንድ በመቶና ከዚያም በላይ ዕድገት እንደምናዋራ ተሥፋ አደርጋለሁ»

ይህ ተሥፋ የሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንት በተከፈተበት ዕለት በየውይይቱ ሲሰነዘር ተሰምቷል። ለምሳሌ የጀርመን መኩራሪያና መለያ አርማ የሆነው አንድ ሚሊዮን ተቀጣሪዎች ያሉት «ማሺነንባው» የምርት መኪናዎች አምራች ዘርፍ ከሌሎች ሲነጻጸር ቀውሱን በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም ችሏል። በዓለም ዙሪያ ብዙ ኮንትራቶችን በማግኘት ዋነኛው የስራ መስክ ፈጣሪ ሞተር እንደሆነም ነው የቀጠለው።

እርግጥ በወቅቱ በተለይም በአገር ውስጡ ገበያ አዳዲስ ገብዪው እየቀነሰ መጥቷል። በመሆኑም ቀጣዩን ሁኔታ በተመለከተ ለምርት መኪናው አምራች ኢንዱስትሪ ማሕበር ፕሬዚደንት ለቶማስ ሊንድነር ከተሥፋና በትዕግስት ከመጠበቅ ሌላ ምርጫ አልተገኘም።

« ጉዳዩ የበረዶ ዝላይን መሰል ነው። በመጀመሪያ መንደርደርን፤ ከዚያም ጠንክሮ መዝለልን ይጠይቃል። እርግጥ መጪው የዓመቱ ሁለተኛ አጋማሽ ከመጀመሪያው የተሻለ እንደሚሆን ተሥፋ እናደርጋለን። ግን ሁኔታው በወቅቱ በጣም የተወሳሰበና ሂደቱ ጎልቶ የማይታይ መሆኑ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ለተሥፋ መቁረጥ አንዳች ቦታ አይኖርም»

ለዚህም ነው ማሕበሩ በኤኮኖሚ ዕድገት ትንበያው እንደጸና መቀጠሉን የሚመርጠው። በምርት ረደድ ሁለት ከመቶ ዕድገት ይጠብቃል። በያዝነው ዓመት ጥሩ ጅማሮ አድርገው ከሚገኙት መካከል በቀደምትነት የኤሌክትሮ-ኢንዱስትሪው ዘርፍ ኩባንያዎች ይገኙበታል። ዘርፉ በወቅቱ በተለይም ይበልጥ የኢንዱስትሪ መሣሪያዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማስተሳሰር ተግባር ላይ አተኩሮ ነው የሚገኘው። የትዕይንቱ አዘጋጆች ይህን ኢንቴግሬትድ-ኢንዱስትሪ፤ የኢንዱስትሪ መሣሪያዎች ትስስር ይሉታል። እንደ ኤሌክትሮ-ኢንዱስትሪው ማሕበር መሪ እንደ ፍሪድሄልም ሎህ ከሆነ ይህ በተለይ ለጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት በጣሙን በጅቷል።

«የጀርመን የኤኮኖሚ ዕድገት ምሥጢር የቴክኖሎጂዋ ፈጣንነትና የተሻለ ሆኖ መገኘት ነው። እና እንደ ጀርመን በምርት መኪና አምራችነት ጠንካራና ውስብስብ የቴክኖሎጂ ዘዴዎችን በተመለከተም ከሌሎች አገሮች የላቅን ለመሆናችን አሁን ማመሣከሪያውን ማቅረብ መቻል ይኖርብናል። በሰባኛዎቹ ዓመታት CIM Computer Integreted Manufacturing ማለትም ከኮምፒዩተር የተዋሃደ የአመራረት ዘዴ ጀምረን ይህ በሚገባ አልሰመረልንም። ዛሬ እርግጥ የኤሌክትሮኒኩ ቴክኖሎጂ ሁኔታ ከያኔው ብዙ የተሻለ ነው። ይህም ተሥፋችንን የላቀ ያደርገዋል። ግን ጊዜ እንደሚፈጅ አውቀን መቀበልም አለብን»

የዘንድሮው የሃኖቨር ትዕይንት የሚካሄደው «ኢንቴግሬትድ-ኢንዳስትሪይ» በመረብ የተሳሰረ ኢንዱስትሪ ወይም ሁሉም ነገር እርስበርሱ የተሳሰረበት ቴክኖሎጂ የሰፈነበት፤ እንዲሁም «ኢንዱስትሪ 4,0 ወይም አራተኛው የኢንዱስትሪ ዓብዮት በሚሉ የተሃድሶ መርሆዎች ላይ ተመስርቶ ነው። ይሄው የትስስር ዘዴ የኤነርጂ ፍጆትን ለምሳሌ በ 15 ከመቶ በላይ ለመቀነስ አስችሏል። በምርት መኪናዎችና በያንዳንድ አካላቸው መካከል ያለው የኤሌክትሮኒክ ትስስር መጠናከር የምርት ተግባርን ለማቀላጠፉም ጥርጥር የለውም።

እርግጥ ባለሙያዎች እንደሚገምቱት ኢንዱስትሪ 4,0 የተሰኘ የኢንዱስትሪ ዓብዮት የደረሰበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ከ 2025 ዓ-ም በፊት መገልገያ አዲስ ዘዴ ለመሆን መብቃቱ ያጠራጥራል። ገና የሚጎሎ መስፈርቶች አሉ፤ የኤሌክትሮኒኩ ቴክኖሎጂ የደህንነት ችግሮችም ገና መፍትሄ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ሊሣካ የሚችለው ፌስቶ የተሰኘው የአውቶማቲክ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሃላፊ ኤበርሃርድ ፋይት እንደሚሉት አጠቃላይ ትብብር ሲኖር ብቻ ነው።

«በኢንዱስትሪ 4,0 ረገድ ትብብር መኖሩ ሲበዛ ግድ ነው። ምክንያቱም ኢንዱስትሪ 4,0 ቴክኖሎጂ አቅራቢዎችን ብቻ ሣይሆን ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማትን፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ ፌስቶን የመሳሰሉ ኩባንያዎችን ጭምር ይጠቃልላል። ለምሳሌ ያህል በውጭ የሚገኙ ቅርንጫፍ ኩባንያዎቻችንንም ከዚህ ቴክኖሎጂ እናስተሳስራለን። ይህ በጀርመን የተያዘው ጥረት በዓለም ላይ ተመሳሳይ የማይገኝለት ነው። በእሢያ እንኳ የለም። እናም በዚሁ ትብብራችንን፣ ቴክኖሎጂንና ቴክኒካዊ ዕርምጃችንን ለማዳበር ትልቅ ዕድል ነው ያለን»

እርግጥ ይህን መሰሉ ዘይቤ በእሢያ ገና ባይኖርም የቻይና የምርት መኪና ኢንዱስትሪ እጅግ በታላቅ ዕርምጃ ወደፊት እየገሰገሰና እየደረበ ነው የመጣው። ይህን የጀርመን ኩባንያዎችም ያውቁታል። ሆኖም በኢንዱስትሪ ቬንቲሌተር ምርት በዓለም ላይ ቀደምት የሆነው ኬባንያ የ ebm ሃላፊ ራይነር ሁንድስዶርፈር እንደሚሉት ጉዳዩ ለፍርሃቻ ምክንያት አይደለም።

«ፍርሃቻ የለንም፤ ግን አክብሮት!ተፎካካሪዎቻችንን በየትኛውም የዓለም ክፍል ይሁኑ መናቅ የለብንም። እኔ ለስራ ባልደረቦቼ የምነግራቸው ፍርሃቻ እንደሌለን ነው። እኛም እነሱም በውሃ ነው የምንቀቅለው። ታዲያ እንዴት ለዓመታት የያዝነው ልምድ እያለን ከኛ ሊሻሉ ይችላሉ። ምን ጊዜም ከነርሱ ርካሽ ልንሆን አንችልም። እንደማይሆንም እናውቃለን። ግን የተሻልን ለመሆን መሞከር አለብን። አንድ አዲስ ምርት ከኤነርጂ አጠቃቀምና ከብቃት አንጻር ከቀድሞው መሻል ይኖርበታል። በዚህ መሠረተ-ዓላማ በመመራት ወደፊትም በዓለም ገበያ ላይ ድርሻችንን ይዘን ለመቀጠል እንደምንችል ነው የማምነው። ከማንም ጋር ይሁን፤ ከቻይና ተፎካካሪዎቻችን ጋር ጭምር»

በነገራችን ላይ ቻይና ምን ያህል እንደተራመደች በሃኖቨሩ የኢንዱስትሪ ትዕይንትም ለመመልከት ይቻላል። ከ 700 በሚበልጡ ኩባንያዎቿ ለትዕንቱ ከቀረቡት የውጭ አምራቾች ታላቋ ሆና ነው የምትገኘው።

መሥፍን መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic