የሃናዉ የቀኝ ጽንፈኛ ጥቃት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.02.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የሃናዉ የቀኝ ጽንፈኛ ጥቃት 

የሃናዉን ዘረኛ ጥቃት የጀርመን መሪዎች በጥብቅ ቢያወግዙትም ፤ወደፊትም እርምጃዎች ይወሰዳሉም ቢሉም የውጭ ዜጎችን ስጋት ግን አላስቀሩም። በተለይ በሃናው ጥቃት ከተገደሉት አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች መሆናቸው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ስጋት እንዲጨምር ማድረጉን በጀርመን የሙስሊሞች ምክር ቤት አስተባባሪ ቃል አቀባይ ዘኬርያ አልቱግ ተናግረዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:29

የሃናዉ የቀኝ ፅፈኛ ጥቃት

ጀርመን ውስጥ ባለፈው ሳምንት ሃናው በተባለችው ከተማ በውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ግድያ ላይ የሚሰማው ውግዘት ቀጥሏል።ቀኝ ጽንፈኛ እንደሆነ በተጠረጠረ ግለሰብ የተፈጸመው ይኽው ግድያ በውጭ ዜጎች ላይ ስጋት አሳድሯል፤መንግሥትንም ቀኝ ጽንፈኞችን ችላ በማለት አስወቅሷል። የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ነበር ቀኝ ጽንፈኛ እንደሆነ የተነገረው የ43 ዓመት ጎልማሳ ሃናው በተባለችው በሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ውስጥ ከፍራንክፈርት ወጣ ብላ በምትገኘው ከተማ በአመዛኙ ወጣት የሆኑ የ9 የውጭ ዜጎችን  ህይወት ያጠፋው።ግለሰቡ በዚያው እለት የ72 ዓመት እናቱንና ራሱንም ገድሏል።በከተማዋ በሚገኙ ሁለት የሺሻ ቤቶች ውስጥ  በምሽት ተኩሶ ከገደላቸው እድሜያቸው ከ21 እስከ 44 ዓመት ከሆነው የጥቃቱ ሰለባዎች መካል 5ቱ የቱርክ ዜጎች ናቸው።የተቀሩት ደግሞ አንድ በትውልድ  ቦስንያ ሄርዜጎቪናዊ በዜግነት ጀርመናዊ ፣አንድ አፍጋናዊ ጀርመናዊ ።አንድ ሮማንያዊ እና አንድ ቡልጋሪያዊ ናቸው። በጥቃቱ የተገደሉት በሙሉ የውጭ ዜጎች መሆናቸው ጥቃቱ ሆነ ተብሎ በውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸመ ዘረኛ ጥቃት መሆኑን ግልጽ አድርጎታል።  የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ከጥቃቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ይህንኑ አረጋግጠዋል።
«በሃናው የተፈጸመው በግልጽ ዘረኝነት ያነሳሳው የሽብር ጥቃት ነው።ይህ ከቫልተር ሉብከው ግድያ እና ከሀለው ሙክራብ ጥቃት ቀጥሎ ጀርመን ውስጥ በጥቂት ወራት ውስጥ የተፈጸመ ሦስተኛው የሽብር ጥቃት ነው። »

የሩቁን ትተን የቅርብ ጊዜውን  ጥቃት ወደ ኃላ መለስ ብለን ስንመለከት በዚህ ዓመት በጥቅምት ወር ሀለ በተባለችው ከተማ በሚገኝ የአይሁዶች ሙክራብ ላይ በተፈጸመ ዘረኛ ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል።ከዚያ በፊት ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ጀርመን ለሚገኙ ስደተኞች ድጋፍ ያደርጉ የነበሩ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት ፓርቲ በምህጻሩ CDU አባል እና ካስል የተባለችው ከተማ አካባቢ አስተዳዳሪ ቫልተር ሉብከ በመኖሪያ ቤታቸው በቀኝ ጽንፈኛ ተተኩሶባቸው ተገድለዋል።የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሀናውን ጥቃት ባወገዙበት መግለጫቸው  አሁንም በጀርመን ህብረተሰብ ውስጥ አለ ያሉትን ዘረኝነትን ክፉኛ ኮንነዋል።
«ዘረኝነት መርዝ ነው። ጥላቻ መርዝ ነው። ይህ መርዝ ደግሞ በማህበረሰባችን ውስጥ አለ።ለበርካታ ወንጀሎችም ተጠያቂ ነው።  «በህቡዕ የሚንቀሳቀሰው ብሔራዊ ሶሻሊስት» በምህጻሩ NSU ብሎ በሚጠራው ቡድን ከተፈጸሙት ወንጀሎች አንስቶ ቫልተር ሉብከ እስከተገደሉበት እንዲሁም እስከ ሃለው ግድያ ድረስ።»

ከጥቃቱ በኋላ በቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት ሊፈጸምባቸው ይችላሉ ተብለው የሚያሰጉ ቦታዎች ላይ  የፖሊስ ጥበቃ እንደሚጠናከር የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኽርስት ዜሆፈር ቃል ገብተዋል።የሃገሪቱ ፌደራል ፖሊስም በዚህ ረገድ እገዛ ለሚያሻቸው የፌደራል ግዛቶች ድጋፍ እንደሚያደርግም  ተናግረዋል።
«በመላ ጀርመን ለጸጥታ ጥበቃ የሚሰማሩ ፖሊሶችን ቁጥር እንጨምራለን።ለጥቃት የተጋለጡ አካባቢዎች ላይ ቁጥጥር እናደርጋለን።በተለይ መስጊዶች ላይ።ዝርዝር ሥራው በፌደራል መንግሥት ደረጃ  እየተካሄደ ነው።የፌደራል ፖሊስ በሚችልበት ቦታ ለምሳሌ በሰው ኃይል እና በመሣሪያ የፌደራል ክፍለ ግዛቶችን ይደግፋል። በባቡር ጣቢያዎች በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በድንበር አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ቁጥር እንደሚጨምር ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።»
የዛሬ ሳምንቱን የሃናዉን ዘረኛ ጥቃት የጀርመን መሪዎች በጥብቅ ቢያወግዙትም ፤ወደፊትም እርምጃዎች ይወሰዳሉም ቢሉም የውጭ ዜጎችን ስጋት ግን አላስቀረም። አሁን በሃገሪቱ የቀጠለው

የቀኝ ጽንፈኞች ጥቃት  ስጋቱን አባብሶታል።ጀርመን ተሰደው የሚኖሩት ብቻ ሳይሆን እዚህ ተወልደው ያደጉ እና የተማሩ የጀርመን ዜግነት ያገኙ  የውጭ ዝርያ ያላቸው ሰዎች በሃገሪቱ በሚፈጸሙ ዘረኛ ጥቃቶች ምክንያት ፍርሃት እንዳደረባቸው ይናገራሉ።በተለይ በሃናው ጥቃት ከተገደሉት አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች መሆናቸው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ስጋት እንዲጨምር ማድረጉን በጀርመን የሙስሊሞች ምክር ቤት አስተባባሪ ቃል አቀባይ ዘኬርያ አልቱግ ተናግረዋል።
«ከጥቆቶቹ በስተቀር ከተገደሉት ሁሉም ማለት ይቻላል ሙስሊም ወይም የውጭ ዝርያ ያላቸው ናቸው።ስለዚህ  ምንም እንኳን ዛሬ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ መስጊዶች  ለፀሎት ቢሰበሰቡም በጣም እንደተሸማቀቁ እና ደህንነት እንደማይሰማቸውም በርግጠኝነት መረዳት ይቻላል።»
ከዚህ በመነሳትም በጀርመን የሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎች በመስጊዶች ለሙስሊሙ ጥበቃ እንዲደረግ ጠይቀዋል።ይህ ዓይነቱ ስጋት ያደረባቸው ጀርመን የሚኖሩ  ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ የውጭ ዝርያ ያላቸው ሰዎችም ጭምር ናቸው።ቦን የሚገኝ የአንድ የሺሻ ቤት ባለቤት መህዲ ኤ ዛዴህ እንደሚለው በሺሻ ቤቶች እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት ነበረው።የዚህም ምክንያቱ በጥቂት ዓመታት በግልጽ እየታየ የሄደው ቀኝ ጽንፈኝነት ነው።

«ይህ እንደሚደርስ እጠብቅ ነበር። ጀርመን ውስጥ ከ2014 አንስቶ በጀርመን ብቻ አይደለም በመላው አውሮጳ ወይም በምዕራቡ ዓለም ወደ ቀኝ ማዘንበል ተከስቷል።መጀመሪያ ላይ እንደቀልድ ነበር የወሰድኩት።በኋላ ላይ ግን በማህበረሰቡ ውስጥ መንጸባረቅ ጀመረ።በህብረተሰቡ ብቻ አይደለም ፖለቲከኞችም መሰል አቋም ይዘው ብቅ ማለት ጀመሩ።አሁን ደግሞ የተለመደ ሆኗል።» 
ቀኝ ጽንፈኞች በህቡዕም በግልጽም በሚንቀሳቀሱባት በጀርመን የውጭ ዜጎች ጥላቻ አፍጦ የወጣው ስደተኞች በብዛት መግባት ከጀመሩበት ከጎርጎሮሳዊው 2015 ወዲህ ነው።ከዚያ በኋላ በውጭ ዜጎች ላይ ጥላቻ የሚነዙ ፓለቲከኞች እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረዋል። የውጭ ዝርያ ያላቸው ሰዎች ጀርመን መግባታቸውን በመቃወምና ጥላቻንም በመንዛት ግንባር ቀደሙን ቦታ የሚይዙት « አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ፓርቲ ፖለቲከኞች ናቸው።ፓርቲው በ2017 በተካሄደው ምርጫ የፌደራል ጀርመን ምክር ቤት ውስጥ መግባት ችሏል። ስደተኞች በብዛት ወደ ጀርመን የገቡበትን አጋጣሚ ፓርቲው ለህዝብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ተጠቅሞበታል። በጀርመንኛው ምህጻር AFD የተባለው የዚህ ፓርቲ መጠናከር ከሚያሰጋቸው  መካከል መህዲ አንዱ ነው።
« እኔ አሁን ሺሻ ቤት መገኘቴ አያሳስበኝም። ይልቁንም የወደፊቷ ጀርመን እኔን ታሳስበናለች። ምክንያቱም አማራጭ ለጀርመን AFD ሁሌም እየተጠናከረ ነው።የዘረኝነት አይደለም የአስተሳብ

ልዩነት ነው የሚለውን አልቀበለም። እኔ ግን ይህን ፤ጥቅል ጥላቻ እንጂ ስለ ሌሎች ዜጎች ያለ አመለካከት ነው ብዬ አልቀበልም። በተለይ የጀርመንን ታሪክ ወደ ኃላ መለስ ብለን ስንመለከት የናዚ ጀርመን ፓርቲ ከትንሽ ነበር የተነሳው።ምናልባት ማንም እስከደረሰበት ጥግ ድረስ ይደርሳል ብሎ የገመተ አልነበረም።»
አቶ አንቅሳዊ ምስጋናው በፍራንክፈርት ከተማ ለስደተኞች ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ የፍርንክፈርት አካባቢ ነዋሪ ናቸው።ጥቃቱ በተለይ ከህብረተሰቡ ጋር ተዋህደው የሚኖሩ በርካታ የውጭ ዜጎች በሚገኙባት በሃናው መፈጸሙ ያልተጠበቀ አስፈሪ እና አሳሳቢም መሆኑን ተናግረዋል።አደጋው በግልም ቢሆን ያሰጋቸው እንደነበርም ገልጸዋል።
ድምጽ 
አቶ አንቅሳዊ የቀኝ ጽንፈኞች እንቅስቃሴ መንግሥት እወስደዋለሁ ባላቸው ቁጥጥሮች እና ጥበቃዎች ብቻ ይገታል ብለው አያስቡም።በርሳቸው አስተያየት እነዚህ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም።በርሳቸው አመለካከት ቀኝ ጽንፈኞችን ችላ በማለት የሚወቀሰው መንግሥት ትኩረቱን እነርሱን በማዳከም ላይ ሊያደርግ ይገባል።መንግሥት ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡም የመፍትሄው አካል መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic