የሁዋንታናሞ 10ኛ ዓመት፤የአፍቃኒስታኑ ቅሌት | ዓለም | DW | 16.01.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሁዋንታናሞ 10ኛ ዓመት፤የአፍቃኒስታኑ ቅሌት

የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች፥ ሰላይ-ገራፊዎች በተጠርጣሪ አሽባሪዎች ላይ የፈፀሙት ግፍ-በደል፥ለአስረኛ ዓመት ሲያከራክር አሽባሪን ሊያጠፋ፥ ሠላም ዴሞክራሲን ሊያሰርፅ አፍቃኒስታን የዘመተዉ የአሜሪካ ጦር ባልደረቦች አስከሬን ላይ እየሽኑ ሲያላግጡ የተነሱት የቪዲዮ ፊልም በዓለም ናኘ

default

16 01 12


«ሁዋንታናሞ ካሁን በሕዋላ አንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ ይዘጋል።»


የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ።ጥር ሃያ-ሁለት 2009-ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።የአሜሪካኖች የግፍ ማዕከል ግን አስረኛ-አመቱ።የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች፥ ሰላይ-ገራፊዎች በተጠርጣሪ አሽባሪዎች ላይ የፈፀሙት ግፍ-በደል፥ለአስረኛ ዓመት ሲያከራክር አሽባሪን ሊያጠፋ፥ ሠላም ዴሞክራሲን ሊያሰርፅ አፍቃኒስታን የዘመተዉ የአሜሪካ ጦር ባልደረቦች አስከሬን ላይ እየሽኑ ሲያላግጡ የተነሱት የቪዲዮ ፊልም በዓለም ናኘ።የሁዋንታናሞ ማጎሪያ ማዕከል አስረኛ ዓመት፥ የአሜሪካ ወታደሮች ጋጠወጥነት መሠረት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።

ወይዘሪት ኮንዳሊሳ ራይስ-የፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የፀጥታ ጉዳይ አማካሪ ከነበሩበት-የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ይዘዉ-የዚያን ቀን ያሉትን እስካሉበት ድረስ፥ያሉትን እያሉም መንግሥታቸዉ እዚያ ደሴት የሚፈፅም-የሚያስፈፅመዉን «አያዉቁም ነበር» ማለት በርግጥ አሳሳች ነዉ።ግን አሉት።መጋቢት ሁለት ሺሕ ስድስት።

«መላዉ ወንድ እና ሴት በክብርና በነፃነት መኖርን ይሻሉ፥መኖር ይገባቸዋልም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሠብአዊ መብት ደንብን ገቢር ማድረግና አስተማማኝ ዲሞክራሲን በመላዉ ዓለም መገንባት ለትዉልድ የሚከናወን ምግባር ነዉ።ግን ሊዘገይ የማይችል አስቸኳይ ምግባር ነዉ።»

አሽባሪዎችን ለማጥፋት፥ እና ራይስ «መዘግየት የማይገባዉ ያሉትን ሠብአዊ መብት ለማስከበር፥ ዲሞክራሲን ለማስረፅ» አፍቃኒስታን የዘመተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር የማረካቸዉ፥ ወይም የአሜሪካ ሰላዮች በጥርጣሬ የያዟቸዉ የመጀመሪያዎቹ ሃያ ሰዎች ሁዋንታናሞ የታጎሩት፥ ራይስ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ከመያዛቸዉ ብዙ ቀድመዉ ነበር።የካቲት አስራ-አንድ 2002።

እርግጥ ነዉ ራይስ ሥለ መላዉ ዓለም ሰዉ ሰብአዊ ክብር ከመናገራቸዉ በፊት፥ መከላከያ ሚንስትር ዶናልድ ራምስፌልድ እዚያ ማጎሪያ ጣቢያ ያሰጎሯቸዉን ሰዎች «የመጥፎዎች መጥፎ» በማለት ከሰዉ የመቆጠራቸዉንም ክብር አጠያቀዉ፥ አጣጥለዉትም ነበር።ከመከላከያ ሚንስትራቸዉ ቀጥለዉ፥ ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ቀድሞ የተናገሩት ግን የሁለቱም አለቃ ነበሩ።ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የካቲት 14 2005።«ግርፋትን አናበረታታም።ግርፋት እንዲፈፀም አዝዤ አላዉቅም።በጭራስ አላዝም።የዚች ሐገር እሴት፥ ማለት ግርፋት የሕይወታችን ክፍል አይደለም።»የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት መግለጫ ለሰብአዊ መብት እና ለፍትሕ ተሟጋቾች፥ ማን ያርዳ የቀበረ-ማን ይናገር የነበረ አይነት ያሰኘዉ።እሱ ማሕር አረር ይባላል።እዚያ ነበር።«ሠነድ ሰጡኝ።እዚያ ሠነድ ዉስጥ የዓል-ቃኢዳ አባል እንደሆንኩ ፅፈዉበታል።የፃፉት አብዛኛዉ ብርቱ ሚስጥር በሚሉት መረጃ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ነግረዉኛል።ለኔ ግን ምንም የገለፁልኝ ነገር የለም።»

የዓለም ብችኛ ሐገር ልዕለ- ሐገር መሪ፥ ለሰብአዊ መብት፥ ለዲሞክራሲ፥ ለሰዎች እኩልነት የሚፋለመዉ ጦር ጠቅላይ አዛዥ ግን እዚያ ድብቅ ማጎሪያ ሰፈር የሚፈፀመዉን ግፍ በደል-ዳግም ካዱ።እንዲያዉም ተቆጥጠዉ-ሕጋዊ ነዉ አሉ።

«ሁሉም ነገር የተፈፀመዉ በሕጉ መሠረት ነዉ።አንገርፍም።»

ካናዳዊዉ ማሕር አረር መስከረም-ሁለት ሺሕ ሁለት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲወርድ፥ ፀረ-ሽብር ሥለሚባለዉ ሁለንተናዊ ዘመቻ-ዉጊያ ከበቂ በላይ በተደጋጋሚ በመስማቱ የዘመቻዉ ዓላማ የገባዉ መስሎት ነበር።የያኔዉ የሰላሳ-ዓመት ወጣት ኋላ እንደተናገረዉ ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብረዉ ፀረ-ሽብር ዘመቻ በዓል-ቃኢዳና የዓል-ቃኢዳ ተባባሪ ቡድናትና በቡድናቱ አባላት ላይ ያነጣጠረ ነዉ ብሎ ያምን ነበር።

ከካናዳ ብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በመቶ የሚቆጠሩ የተለያዩ ሐገራት ዜጎች ሥለ መታገታቸዉም ብዙም የሚያዉቀዉ ነገር አልነበረም።እና ኒዮርክ ገባ።ጆን ኤፍ ኬኔዲ አዉሮፕላን ማረፊያ። አዉሮፓላን ለመቀየር መሳፈሪያዉን እያንጋጠጠ ሲያማትር አጅሬዎች ተቀበሉት።የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት ባልደረቦች።ብዙም አልቆየ-እያንከለከሉ እስከዚያ ድረስ ብዙም ከማያዉቀዉ ማጎሪያ ደሴት ከረቸሙት።

«የመጀመሪያዎቹ ቀናት መላዉ ሰዉነቴ በሽቦ ገመድ ክፉኛ ሲገረፍ ነዉ ያለፉት።በተለይ ወገቤ፥ ጀርባዬ፥ ዳሌዬ በጣም ነዉ የተቀጠቀጡት ።ያልደረሰበት ሥቃዩን ሊያዉቀዉ አይችልም።ሥቃዩን መግለፅ አይቻልም። የተፈፀመብኝ ግፍ አካላዊ ብቻ አይደለም።ሥነ-ልቡናዊም ጭምር እንጂ።እኔን ማቆያ ክፍል ዉስጥ አስቀምጠዉ በሌሎች ላይ ጠንካራ ምርመራ ያደርጉ ነበር።እዚያ ቁጭ ብዬ የሚሰቃዩቱን ሰዎች የሲቃ-ጩኸት እሰማ ነበር።»

የኮባዉ ደሴት ሁዋንታናሞ የጦር ሰፈርነቱን እንጂ የሚደረግ የሚፈፀምበትን ብዙም የሚያዉቀዉ አልነበረም። በአንድ ወቅት ስምንት መቶ ግድም የነበሩት የሁንታናሞ ታጋቾች ለረጅም ጊዜ ከዉጪዉ ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበራቸዉም።ፍርድ ቤት አልቀረቡም።ዘመድ-ወዳጅ፥ ጠበቃ፥ ገለልተኛ ሐኪም እንዲጎበኛቸዉ እንኳን አልተፈቀደላቸዉም ነበር።የቀይ መስቀል ባልደረቦች እንኳን እንዲጎበኟቸዉ የተፈቀደላቸዉ ከብዙ ዉጣ ዉረድ፥ ከተደጋጋሚ ልመና በሕዋላ ነበር።

አሳሪዎቻቸዉ የሚያለብሷቸዉ ብርቱካናማ ቱታ፥እስከ አንገታቸዉ የሚጠለቅላቸዉ መሸፈኛ-እና እግር ከወርች የሚቀየዱበት እጀ ሙቅ በመላዉ የግፍ-ስቃይ ምልክት ከሆነ በሕዋላ ግን የመከላከያ ራምስፌልድ የመጥፎች መጥፎ ይዞታ በነበረበት አልቀጠለም።የሰብአዊመብት ተሟጋቾች፥ የፍትሕ-እኩልነት ተቆርቋሪዎች ያደረጉት አለም አቀፉ ዘመቻ ሰበብ ምክንያት ሆኖ ኢትዮጵያዊዉ ቢኒያም መሐመድን ጨምሮ ብዙዎቹ ተጠርጣሪዎች ቀስ በቀስ ከዚያ ማጎሪያ ሠፈር ተለቀቅዋል።

ራምስፌልድ በበላይነት የሚመሩት ጦር ባልደረቦች ኢራቅ አቡ-ግራይብ እስር ቤት የፈፀሙት ሌላ ግፍ እና የሁዋንታናሞዉ ሰቆቃ-ራምስፌልድን ከስልጣን ካስወገዱ ዋና ዋና ምክንያቶቹም የሚጠቀሱ ናቸዉ። ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ ሥልጣን በያዙ በሁለተኛዉ ቀን ያን የግፍ፥ ስቃይ ሰቆቃ አብነት እንዲዘጋ የወሰኑትም የገደፈዉን የሐገራቸዉ ክብር-ስም ለማስመለስ ነዉ-ብለዉ ነበር።

እርግጥነዉ ሁዋንታናሞ ዉስጥ ታጉረዉ ከነበሩት ስምንት ያሕል ተጠርጣሪዎች አብዛኞቹ ተለቀዋል።አንድ መቶ ሰባ-አንዱ ግን ዛሬም እዚያዉ ናቸዉ።ኦባማ ሥልጣን ሲይዙ አመት ባልሞላ ጊዜ ሊዘጉ የወሰኑበት ማጎሪያ ሰፈርም እንደነበረ ነዉ።ሁዩማን ራይትስ ዋች የተሰኘዉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ባልደረባ አንድሪያ ፕራሶዉ እንደሚሉት ታጋቾቹ እስካሁን ፍርድ ቤት ቀርበዉ ሊበይንባቸዉ በተገባ ነበር።«ወንጀል ፈፅመዋል የሚል ክስ የተመሠረተባቸዉ እስረኞች ሊበየንባቸዉ ይገባል።የአሜሪካን ሕግ ከጣሱ አሜሪካ ዉስጥ፥ የሌላ ሐገር፥ ለምሳሌ የአፍቃኒስታንን ሕግ ከጣሱ አፍቃኒስታን ዉስጥ ሊፈርድባቸዉ ይገባል።አለበለዚያ መለቀቅ አለባቸዉ።»

ግን አልሆነም። ምክንያቱ አንዳዶች እንደሚሉት ከፖለቲካ ይልቅ የሕግ አተረጓጎም ልዩነት ሊሆን ላይሆንም ይችላል።ትክክለኛዉ ምክንያት ምንም ሆነ ምን የኦባማ መስተዳድርን ተአማኒነት በጅጉ ምሸርሸሩ አልቀረም።የዛሬ አስር አመት ከአፍቃኒስታን በተጋዙ ታጋቾች የተከፈተዉ ሕገ-ወጥ ማጎሪያ ጣቢያ አለመዘጋት በሚያነጋግርበት መሐል ሰሞኑን አፍቃኒስታን የዘመተዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ባልደረቦች የፈፀሙት ፀያፍ ምግባር አደባባይ ወጣ።

የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ባሕር ወለድ ጦር ባልደረቦች የታሊባን ደፈጣ ተዋጊ ነዉ ተብሎ በሚጠረጠር አስከሬን ላይ ሽንታቸዉን ሲሽኑ የሚያሳይ የቪዲዮ ፊልም በተለያዩ ድረ-ገፆች ተለጥፏል። የወታደሮቹ ድርጊት ለትልቂቱ ሐገር ጦር አሳፋሪ፥ ለሌላዉ የሌላ ጥያቄ፥ ጥርጣሬ ሰበብ-ምክንያት ሆኗል።

አፍቃኒስታን የሰፈረዉ የዉጪ ጦር ቃል አቀባይ ሌትናንት ጄኔራል አድሪያን ጄ ብራድሻዉ ተቀባይነት የለዉም ይላሉ።

Protest in Brüssel gegen Gefängnis in Guantanamo

ተቃዉሞ ሰልፍ

«በቅርቡ በሕዝብ አምደ-መረቦች የተለጠፉ ቪዲዮዎች የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች በደፈጣ ተዋጊዎች አስከሬን ላይ አጅግ አሳፋሪ ምግባር ሲፈፅሙ ያሳያል።በየሞተ ጠላት ይሁን ወዳጅ አስከሬንን ክብር ማሳጣት ፍፁም ተቀባይነት የለዉም።ተጣማሪዉን ጦር ደረጃ በምንም መንገድ አይወክልም።»

የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚንስትር፥ የዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና ሌሎች ባለሥልጣናትንም ተመሰሳሳይ ነገር ብለዋል።ወንጀለኞችን ለፍርድ ሊያቀርቡም ቃል ገብተዋል።የአሜሪካ ወታደሮች አቡ ግራይብ እስር ቤት፥ የታሰሩ ሰዎችን ማሰቃየት-ማንገላታታቸዉ እንደተጋለጠ ያኔ ከነበሩት የዋሽንግተን ሹማምንት ተመሳሳዩን ሰምተን ነበር።የሁዋንታናሞዉ ግርፋት-ግፍ ሲጋለጥም እንዲሁ።

ግፍ ጥቂት የበታች የጦር መኮንኖች ወይም ተራ-ወታደሮች ፍርድ ቤት ቀረቡ ከመባል ባለፍ ወንጀሉን ያስፈፀሙት፥ እንዲፈፀም ያዘዙት፥ ወይም ወንጀለኞችን መቆጣጠር የነበረባቸዉ ባለሥልጣናትን የጠየቀ አይደለም፥ ሊጠይቅ ያቀደ መንግሥት፥ ተቋምም የለም።ካለም መኖሩ አይታወቅም።እና ሕገ-ወጡ ፀያፍ ምግባር አሁን መልኩን ቀይሮ አፍቃኒስታን ተደገመ።

የወታደራዊ ጉዳይ ባለሙያ ሰባስትያን ጁንገር እንደሚሉት አስከሬን ላይ የሸኑት ወጣት ወታደሮች የፈፀሙት ከፖለቲከኞቻቸዉ ከሰሙት ብዙ የተለየ አይደለም።«እነዚ ሰዎች ገና የአስራ-ዘጠኝና የሃያ አመት ወጣቶች ናቸዉ።ለአስር አመታት የፖለቲካዉን ንግግር (መግለጫ) እየሰሙ ነዉ ያደጉት።»

ታዲያ ተጠያቂዉ ማነዉ-ነዉ?።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic