የሁዋንታናሞ ወህኒ ቤትና የእሥረኞቹ ዕጣ-ፈንታ፣ | ዓለም | DW | 22.01.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሁዋንታናሞ ወህኒ ቤትና የእሥረኞቹ ዕጣ-ፈንታ፣

ትናንት የመጀመሪያውን የሥራ ቀን፣ ብዙ ጉዳዮችን በትጋት በማከናወን ያሳለፉት ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ፣በዛሬው ዕለት የሥራ ውሎአቸው፣ በሁዋንታናሞ የሚገኘው በአሸባሪነት የተጠረጠሩ ሰዎች የሚገኙበት እሥር ቤት፣

default

በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲዘጋ የሚያደርግ አዋጅ ያወጣሉ፣ በእሥረኞቹ ላይ የሚካሄደው ምርመራም ሆነ የፍርድ ሂደትም፣ በሚመጡት 120 ቀናት እንዲገታ ትእዛዝ እንዲተላለፍ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዖባማ፣ የአገራቸው ጦር ከኢራቅ በሚወጣበት የጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም በአሸባሪነት ላይ የሚካሄደውን ትግል በማስመልከትም ልዩ ትኩረት ማድረጋቸው አልቀረም። በባራክ ዖባማ የሚንስትሮች ም/ቤት፣ የኃይል ምንጭ፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የሀገር ውስጥ ጥበቃ፣ የበጀት፣ የወታደር ጡረተኞች ጉዳይና የመሳሰሉት ሚንስትሮች ሹመት ፣ በተባበሩት መንግሥታት አገሪቱን የሚወክሉት አምባሳደር ሹመት ጭምር ወዲያው በም/ቤቱ የጸደቀ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሂልሪ ክሊንተንም ቢሆን ጥቂት ዘግየት ይብል እንጂ በብዙኅን ድጋፍ ጸድቋል። የገንዘብ ሚንስትራቸው፣ Timothy Geithner ለዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) 4 ዓመት በሠሩበት ወቅት የሚከፈል 34,000 ዶላር የጡረታ የቀረጥ ክፍያ ባለማሟላት ስህተት ፈጽመዋል ተብለው በሴኔቱ የፋይናንስ ኮሚቴ መስቀልኛ ጥያቄ አይሎባቸዋል። የህግና ፍትኅ ጉዳይ ሚንስትሩ ኤሪክ ሆልደርም ሹመት የሚጸድቅበት ጌዜም፣ ከሁዋንታናሞ እሥረኞች መርማሪዎች የወደፊት ዕጣ ጋር በተያያዘ፣ በሴኔቱ የፍትኅ ጉዳይ ኮሚቴ፣ ሪፑብሊካውያኑ አባላት ያቀረቡአቸው አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ እስኪገኝላቸው፣ በአንድ ሳምንት መዘግየቱ ታውቋል።

በአሸባሪነት ተጠርጥረው በሁዋንታናሞ የሚገኙት እሥረኞች ቁጥር ቤት በአሁኑ ጊዜ 250 ገደማ ይሆናል። ከአ,ዚህመካከል 60 ገደማ ከሞላ ጎደል አበሳ እንዳልተገኘባቸው በመገለጡ፣ የሚቀበላቸው ተቀብሎም እንደገና የማያሥራቸው፣ ቁም ስቅልም የማያሳያቸው ተቀባይ ሀገር ካገኙ ወዲያው ሊለቀቁ እንደሚችሉ ነው የሚነገረው። የጀርመን ሰብአዊ መብት ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ወ/ሮ Hertha Däubler-Gmelin

በመጀመሪያ ኀላፊነት ያለጻቸው ራሳቸው አሜሪካውያን ናቸው ይላሉ።----

«በመጀመሪያ አሜሪካውያን ሰዎቹን ተቀብላ ማስተናገድ አለባት። ሁዋንታናሞ ላይ እሥር ቤት አቋቁማ ወደዚያ በመውሰድ በደል ፈጽማባቸዋለችና!ሰለዚህ ኀላፊነት አለባቸውና ይህን መወጣት ይኖርባቸዋል። አሁን አንዳንዶቹ እሥረኞች፣ በአሜሪካውያን ላይ ብርቱ ጥላቻ ሳላለብን በአነርሱ አገር አንኖርም ካሉ፣ ተመሳሳይ ቁም ስቅል ማሳያ እርምጃ ሊፈጸምብን ይችላል በሚል ሥጋት ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስ የማይችሉ ወይም የማይፈልጉ ከሆነም፣ ሌላ ተቀባይ አገር ይገኝ እንደሁ መፈለግ ይኖርበታል። »

ፕሬዚዳንርት ባራክ ዖባማ፣ ሁዋንታናሞን ለመዝጋት በመጀመሪያ መወሰናቸው፣ የትክክለኛ ውሳኔ አንድ እርምጃ መሆኑን ሁሉም እየመሠከረላቸው ነው። በሁዋንታናሞ የሰብአዊ መብት የረገጡ ወደፊት ለፍርድ እንዲቀርቡ የጠየቁም አሉ።

ኦስትሪያዊው የዓለም አቀፍ ህግ ባለሙያና የተባበሩት መንግሥታት፣ የቁም ስቀል ማሳያ እርምጃዎች ጉዳይ አጥኚ መልእክተኛ ማንፍረድ ኖቫክ፣ እንዲህ ይላሉ።

«ከባራክ ዖባማ በተጨማሪ የምጠብቀው፣ ባለፉት ጊዜያት የተሠሩ ስህተቶችን፣ የተፈጸሙ የግፍ እርምጃዎችንም ችላ ሳይሉ እንዲመረመሩ፣ ምናልባትም እስከመጨረሻው ክትትል እንዲያደረጉባቸው ነው።»

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ መሆኑ የሚነገርለት የአፍጋኒስታን የሰብአዊ መብት ድርጅት ኀላፊ ላል ጉል ላል፣

«ሁዋንታናሞ ማለት፣ የዓለም አቀፍና የአሜሪካ ህግጋት የተጣሱበት ቦታ ነው። የኦባማ አስተዳደር በአገሪቱ ላይ የሚሠነዘረው ነቀፌታ እንዲገታ ከፈለገ፣ እሥረኞችን ለአገራቸው መንግሥታት ማስረከብ ፣ በኢራቅና በአፍጋኒስታን የሚገኙ እሥር ቤቶችንም መዝጋት ይኖርበታል» ብለዋል። አፍጋኒስታን ውስጥ፣ በዩ ኤስ አሜሪካው ዋና ምሽግ ፣ በባግራም፣ ላል እምደሚሉት አሁን 600 ያህል እሥረኞች ይገኛሉ። እ ጎ አ በ 2002 ዓ ም በተቋቋመው የሁዋንታናሞ እሥር ቤት ከ 200 በላይ አፍጋኒስታውያንና 68 ፓኪስታናውያን የተለቀቁ ሲሆን አሁንም ቢሆን በዛ ያሉ አፍጋኒስታውያንና 5 ፓኪስታናውያን በአጠቃላይም 250 ያህል በአሸባሪነት ተጠርጥረው የተያዙ እሥረኞች ይገኛሉ።

Quellen-DW,RTRs,DPA

►◄