የሁሉንም ተሳትፎ የሚሻዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ | ጤና እና አካባቢ | DW | 15.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የሁሉንም ተሳትፎ የሚሻዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ

በእኛ የክረምት በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ደግሞ የበጋ ወራት ሲቃረብ አንስቶ በኅዳር እና ታኅሳስ ወር ወደተረኛዉ ክረምት ወቅቱ እስኪሻገር ድረስ የጀርመንን መልክዓ ምድር ለተመለከተዉ በደንና በልምላሜ የታጀበ አረንግዴ ሆኖ ነዉ የሚከርመዉ። በክረምት ይህችን ሀገር የጎበኘ ምነዉ የቅጠል ዘርም የለባት ብሎ መገረሙ አይቀርም።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:52
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:52 ደቂቃ

የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ዋነኛዉ ርምጃ ነዉ፤

ጀርመን ታዲያ እንደኢትዮጵያ ለቁጥር የሚያታክት የብዝሃ ሕይወት ስብጥር የላትም።  ያላቸዉን ግን በወጉ ይዘዉት ደኑንም ለመናፈሻ እና ለዓይን ማረፊያ አድርገዉ ሲመለከቱ፤ ያኔ ለኢትዮጵያ « ዙሪያሽ ሁሉ ለምለም» እያሉ ያቀነቀኑት ወገኖቻችን ቢያይዋት በእንዴት ያለ የቅኔ ዉበት ያዜሙላት ይሆን ብለዉ ለአፍታም ቢሆን ያስባሉ። ጀርመንም ብትሆን ግን ዛሬ የሚታየዉ ገጽታዋ ላይ ለመድረስ ብዙ መጓዟ እሙን ነዉ። 

በቅርቡ ለአደጋ ተጋልጠዋል ተብለዉ ትኩረት ከተደረገባቸዉ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ስሙ የወጣዉ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በተመ የትምህርት፤ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበዉ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1978ዓ,ም ነዉ። ይኸዉ ፓርክ በጎርጎሪዮሳዊዉ 1996ዓ,ም ለአደጋ የተጋለጡ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ዉስጥ ገባ። በያዝነዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2017 ሐምሌ ወር ደግሞ ከዚህ ስጋት ነፃ መሆኑን ሰማን። ፓርኩን ለአደጋ ካጋለጡት መካከል ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር፤  የግጦሽ መሰማሪያ መሆኑ እና የተሽከርካሪዎች መተላለፊያ መሆኑ በዋነኛነት ተጠቅሰዋል። በብዝሃ ሕይወት የደረጀዉ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክም ሆነ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙ ሌሎች ፓርኮች ካሉበት ስፍራ ርቀዉ ለሚገኙ አካባቢዎች ሁሉ የሚተርፍ በረከት እንዳላቸዉ ነዉ አቶ ያለም ሰዉ አደላ በኢትዮጵያ የአካባቢ እና የደን ምርምር ኢንስቲትዩት የአካባቢ ብክለት አያያዝ ምርምር ክፍል ዳይሬክተር የሚያስረዱት።

«ይኼ የስሜን ተራሮች ፓርክ በሀገሪቱ ዉስጥ ከሚገኙ ወደ ሃያ አካባቢ ፓርኮች አሉ እጅግ ዉብ የሆኑ እና የተለያዩ እጽዋትን አእዋፍን እንዲሁም የዱር እንስሳትን የያዘ ፓርክ ነዉ። እንዳልሽዉም በባዮዳይቨርሲቲ ረገድ በጣም ትልቅ አስተፅኦ ያለዉ ነዉ፤ እንደዉም አሁን ትላልቅ ምርምሮች ሁላ የሚናገሩት የስሜን ተራሮች ፓርክ የብዝሃህይወት አስተዋፅኦ እስከ ሰሃራ በረሃ ዉስጥ ድረስ ሁላ የተለያየ ተጽዕኖ እንዳለዉ የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ፤  እናም በጣም ትልቅ ፓርክ ነዉ፤ ይኼም ብቻ አይደለም በሀገሪቱ ጥሩ ጥሩ ፓርኮች አሉ ተመሳሳይ አይነት አስተዋጽኦ ያላቸዉ። ለምሳሌ የባሌ ናሽናል ፓርክን ብንወስድ በአፋር በቦረና በሱማሌ አካባቢ ያሉ ችግሮችን የመቆጣጠር እና የመወሰን አቅም እንዳለዉ የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ። እና እንደዚህ በብዝሃ ሕይወት የደረጁ አካባቢዎችን መጠበቅ ትልቁ ሥራ ነዉ ማለት ነዉ።»

ለመሆኑ ዩኔስኮ አንድ የተፈጥሮ ሃብት ክምችት ያለበት ፓርክ ወይም አካባቢ ለአደጋ ተጋልጧል ብሎ ጥንቃቄ እንዲደረግለት ማሳሰቢያ የሚሰጠዉ ምን ሲሆን ነዉ? አቶ ያለም ሰዉ፤

«በመሠረቱ ዩኔስኮ ይሄን ሲያደርግ ያደጋ ቀጠና ዉስጥ ገባ ሲል፤ ሁለት እንትኖች አሉት ለተፈጥሮ ቁሶች ብሎ ዩኔስኮ ያስቀመጣቸዉ መርሆዎች አሉ። ምን ሲሆን ነዉ ወደዚህ ዝርዝር ዉስጥ የሚገባዉ? ለሚለዉ የተረጋገጠ ለአደጋ ተጋልጧል የሚል እና ሊጋለጥ ይችላል የሚል ሁለት ክፍሎች አሉት። በtl,ይ በመጀመሪያዉ ሲወስን አደጋ ዉስጥ ገብቷል ብሎ ሲያስብ በዋነኛነት እነዚህ የተለያዩ ኣጽዋቶች ሊሆኑ ይችላሉ፤ የዱር እንሳስት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ቁጥራቸዉ በፊት ከነበራቸዉ እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ ሲቀንስ አንደኛዉ መገለጫዉ ነዉ፤ ተፈጥሯዊ ይዞታቸዉንም ሲያጡ እና የሳይንሳዊ አስተዋጾኦዋቸዉም በሰዉ ልጅ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ሲጎዳ አንደኛዉ የሚያስቀምጡት ምክንያት ነዉ። እንዲሁም የሰዎች (ያዉ እዚህ ታዳጊ አገር ከፍተኛ ችግር ነዉ ያለዉ ኑሮዉን ራሱ ደግፎ ለመኖር በእርሻዉ በምኑ በምኑ ይገባል) እነዚህ እነዚህ ሲሆን ዩኔስኮ አንድ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበን ወደለአደጋ የተጋለጠ መዝገብ ዉስጥ ይወስደዋል።»

ይህ ካለበት አካባቢ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ መሆኑ የሚነገርለት የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዉስጡ ለዓለም ብርቅዬዎቹን እነ ቀይ ቀበሮን፤ እነ ዋልያን እና ሌሎችንም ግዙፍ አጥቢ እንስሳት በቤትነት በማስተናገዱ ይታወቃል። ለአደጋ መጋለጡ ይፋ ሲደረግም በዉስጡ ከመታደን ተርፈዉ ይኖሩ የነበሩት የዋልያዎች ቁጥር ከ150 እስከ 250 ደርሶ እንደነበር፤ ቀበሮዎቹ ደግሞ ከ18 እስከ 21 ገደማ እንደነበሩ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ማሩ ቢያድግልኝ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። አሁን ደግሞ የዋልያዎቹ ቁጥር ከአንድ ሺህ በላይ መድረሱን፤ የቀበሮዎቹም ከ150 ከፍ ማለቱን አስረድተዋል። የስሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ አደጋ ላይ ከሚገኙ የዓለም ቅርሶች ዝርዝር ዉስጥ እንዲወጣ በመንግሥት ከተወሰዱ ርምጃዎች በዋናነት በፓርኩ ዉስጥ ለግጦሽ ከብቶች መሰማራታቸዉ መቀነሱ፤ በከፍተኛ ወጪ የተሠሩ ፓርኩን አቋርጠዉ የሚሄዱ መንገዶች መቅረት፤ ከምንም በላይ ደግሞ ሰዎች በፓርኩ ዉስጥ የነበራቸዉን እንቅስቃሴ መግታት ይጠቀሳሉ። የተፈጥሮ ሃብት ላይ ጉዳት ለማድረስ የሰዎች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል። በዚህ ረገድም የአካባቢ ተፈጥሮን ለመጠበቅ የሚደረገዉ ጥረት በተለይ ለአዳጊ ሃገራት ቀላይ እንዳልሆነ ነዉ አቶ ያለምሰዉ የሚናገሩት።

«በታዳጊ ሃገራት ያለዉ ከፍተኛ ድህነት የቱንም አይነት ፖሊሲ ቢወጣ ምንም አይነት መመሪያዎች ቢኖሩም በቀላሉ እነዚህን ችግሮች መፍታት ይቻላል ማለት አይደለም። ያም ስለሆነ ብዙ ጊዜ ይወሳሰባል። እንደምታዉቂዉ እነጀርመን የእናንም ጣቢያ ያለበት ምን ያህል ዝርያ አላቸዉ ብትይ በእጽዋት እንኳ ከ10 ከ 20 ዝርያ በላይ የበለጠ የላቸዉም። ለዛች ለ 10 ---20 እፅዋት ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሰጥተዉ ነዉ ሲንቀሳቀሱ የምታይዉ። እንደኢትዮጵያ ያሉ ደግሞ የብዝሃ ሕይወት መነሻ እና ክምችት ያለባቸዉ ቦታ ስትሄጂ ድህነቱ እራሱ ተጽዕኖ ያደርሳል ማለት ነዉ እነዚህ ሃብቶች ላይ።  የተትረፈረፈ ነገርም አለኝ ብሎ ሲታሰብ አንዱ መሠረታዊ ችግር ይሆናል ነገሮችን ትኩረት አለመስጠት። በተለይ ይሄ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል አይነት ነዉ የሚሆነዉ። እንግዲ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት እንደ ሀገር ፖሊሲዎች አሉ፤ ኢትዮጵያም የፈረመቻቸዉ የዓለም አቀፍ ስምምነቶች አሉ፣ መንግሥትም እየወሰደ ያለዉ ትልልቅ ኃላፊነቶች አሉ። እና ለአደጋ የሚጋለጡበትን እና በተለይ በዉስጡ ያሉ እፅዋትም ሊሆን ይችላል የዱር እንስሳት ሊጠፉ ከሚችሉበት ሁኔታ መታደግ የሚያስችሉ አካሄዶችን መከተል ነዉ።»

የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያ ዉስጥ ክፉኛ የተጎዱ አካባቢዎች ተፈጥሯቸዉ እንዲያገግም በተወሰዱ ርምጃዎች አበረታች ዉጤት መገኘቱ ይነገራል። ለዚህ ዉጤት ደግሞ ሀገሪቱ ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ያወጣችዉ መመሪያ እና የፈረመቻቸዉ ዓለም አቀፍ ዉሎች ብቻቸዉን የፈየዱት ነገር አለ ብሎ መገመቱ ይከብዳል። ከምንም በላይ ኅብረተሰቡን የማስተማር እና የማንቃቱ ሥራ ትልቅ ሚና ይኖረዋል። የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት ለሚለዉ አሁንም አቶ ያለምሰዉ፤

«ጥሩ እንግዲህ ግንዛቤ የመጀመሪያዉ ትልቁ መሣሪያ እሱ ነዉ የሚመስለኝ። በተለይ ከአካባቢ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ስናስብ ግንዛቤ ነዉ የመጀመሪያዉ ትልቁ ነገር መሆን ያለበት ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ምንም አይነት ፖሊሲ ብናወጣ ፣ ምን አይነት ቴክኒዎሎጂዎች ቢኖሩን ያን መቀበል የሚችል ማኅበረሰብ ፤ ቴክኒዎሎጂ ሲመጣ ለራሱ ጥቅም መሆኑን መረዳት ማገናዘብ የሚችል፤ ቴክኒዎሎጂዉን መጠቀም የሚችል ማኅበረሰብ ያስፈልጋል፤ ግንዛቤዉ ማለት ነዉ። በአፍሪቃ እና በተለይ በታዳጊ ሃገራት የአካባቢ ርዕስ ሲነሳ ትልቁ ነገር ምንድነዉ ከትልልቅ ከተማሩ ፣ ኃላፊነት ቦታ ላይም ካሉ ሰዎችም ጭምር ያለ አንድ ችግር ይመስለኛል ግንዛቤ፤ ምክንያቱም የአካባቢ ጉዳዮችን እንደቅንጦት የማየት ሁኔታዎች ይኖራሉ። አካባቢ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደቅንጦት አድርገዉ የሚያስቡ የሥራ ኃላፊዎች፤ ትልልቅ ዉሳኔ ሰጪ ቦታ ላይ የተቀመጡ ይኖራሉ። ፖሊሲዉ እጅግ ጠንካራ ሆኖ እንደሀገር ቢቀመጥ እንኳን ያ ግንዛቤ መፈጠር አለበት ማለት ነዉ።  አሁን ብዙዎቹን የእኛን ሀገር ከአካባቢ  ጋር የተገናኙ ፖሊሲዎች ብታያቸዉ በይዘት ምንም አይነት ችግር የለባቸዉም፤ ትልቁ ችግር ግን ግንዛቤዉ ማን ጋር ነዉ ስንል ሕዝቡ ጋር ብቻ አይደለም ችግሩ ያለዉ። ፖሊሲዎች ከሚያወጡ ከሚያስፈጽሙም አካል ጋር ነዉ ያለዉ።»

እንደእሳቸዉ እምነትም ይህን የተመለከተዉ የግንዛቤ ትኩረት በትምህርት ዉስጥ ሁሉ ተካቶ ቢሰጥ መልካም ይሆናል። ምክንያቱም ዘላቂ በሆነ መልኩ እዉቀቱን ወደ ኅብረተሰቡ ማስረጽ የሚቻለዉ በትምህርት ነዉና። 

«ትምህርት ቤቶቻችን በመጽሐፎቻቸዉ ላይ የእንደዚህ አይነት ቦታዎች አስፈላጊነት በብዙ መልኩ ሊማሩት ይገባል። ከታች ከአንደኛ ክፍል ጀምሮም ሊሆን ይችላል፤ በሚገባቸዉ ደረጃ ምን ማለት ነዉ የእነዚህ ቦታዎች እንደ ሀገር መኖር? ሳይንሳዊ ጥቅሙ ሊሆን ይችላል፣ የማኅበረሰባዊ ጥቅሙ ሊሆን ይችላል፤ ኤኮኖሚያዊ ጥቅሙ ሊሆን ይችላል፣ ፖለቲካዊ ጥቅሙ ምን ማለት ነዉ የሚለዉ በሰፊዉ ግንዛቤ መፈጠር አለበት። በዋነኛነት ለዚህ ትልቁን ሚና ይጫወታሉ የምለዉ መገናኛ ብዙሃን (ሚዲያዎች) ናቸዉ። ሚዲያዎች የሀገሪቱን ሁሉንም ጥግ ይደርሳሉ ትኩረት ሰጥተዉት የእነዚህ ጥቅም ማስረዳት ይቻላል። ኅብረተሰቡን ለማስተማርም ተጨባጭ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ትናንት የባህላዊ መድኃኒቶችን ከየጓሯቸዉ ዛሬ እነዛ አሉ ወይ? ትናንት ከብቶቻቸዉ ሲታመሙ ቅንጥስ አድርገዉ አንድ ቅጠል አሽተዉግተዋቸዉ የሚድኑ ከብቶች ዛሬ ያን ማድረግ ይቻላል ወይ? ለኅብረተሰቡ ራሱ ማስተማሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከአካባቢዉ እየወሰዱ መልሶ ማኅበረሰቡን ማንቃት ያስፈልጋል።»

በልቶ የማደርን እንጂ ለተፈጥሮ አካባቢ ትኩረት የመስጠቱ ነገር በአህጉር ደረጃም ችግር  መሆኑን አፅንኦት የሰጡት የተፈጥሮ አካባቢ ተቆርቋሪ እና የዘርፉ ባለሙያ አቶ ያለምሰዉ እዉነታዉ ሲታይም ከባድ መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም። ያም ቢሆን ግን ለምሳሌ ኢትዮጵያ በጤናዉ ረገድ ሲታይ እስከ እታች ኅብረተሰቡ ድረስ የደረሰዉ የጤና ኤክስቴንሽን ስልትን ለአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ ግንዛቤ መፍጠሪያ መቀጠቀም እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

አካባቢ እና ደን ሀብት ላይ ትኩረት ከመስጠት አንፃር ኢትዮጵያ ዉስጥ በዋነኛነት ራሱን ችሎ  የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መቋቋሙ አንድ ነገር መሆኑን አቶ ያለምሰዉ ይጠቅሳሉ። የኢትዮጵያ የአካባቢ ፣ የደን እና የአየር ንብረት ለዉጥ ሚኒስቴር። በዚህ መሥሪያ ቤት ሥርም ሁለት ትልልቅ የምርምር ተቋማት አሉ። ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸዉእና ብዙ የሰዉ ኃይል ተቀጥሮላቸዉ ፖሊሲዎች ወጥተዉ ምርምሮች እንደሚካሄዱም አዉስተዋል። እኛ ጋር ያለ ችግር ግን ይላሉ፤

«እኛ ምንድነዉ በዚህ በተፈጥሯዊ ነገር ብቻ አይደለም ይኼ ባህላዊ በሆነዉ ነገር ላይ ስታይ ዝም ብለሽ (እኔ በግሌ ሁሌም የሚከነክነኝ ነገር ስለሆነ ነዉ) ያለንን ነገር ነዉ ችላ የምንለዉ፤ እንደዉም እንደዉም ግለጸዉ ካልሽኝ ናፋቂ ነን። ያላየነዉን ነዉ የምናፍቀዉ። የኖርንበትን ያሸተትነዉን ፤የዳንንበትን የታከምንበትን ሁሉ አንፈልገዉም። እናም ይመስለኛል ይሄ ግንዛቤ ሲሰራ እንደማኅበረሰብ ንቃተ ሕሊናችን በሁሉም ዘርፍ መሆን አለበት። ምናልባት ጀርመን የምታዉቂዉ ነዉ የግንዕዝ ቋንቋን የሚያስተምሩ ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። እንደዉ ግዕዝ በጣም ለጀርመን ምን አድርጎለት ይሆን? ብዬ አንዳንዴ ስጠይቅ ለራሴም የሚገርሙኝ ነገሮች አሉ። እናም ያለንን ማወቅ ያስፈልጋል ምንድን ነበረን? እሱን ስናዉቅ ነዉ ወደመሬት ሁሉንም ማዉረድ የምንችለዉ። እኛ ያሉን የብዝሀ ሕይወት ሃብቶች በእጽዋት፣ በእንስሳት፣ በአዕዋፍ ስናየዉ ትልቅ ነዉ። ይኼም በዓለም በተለያዩ የሳይንስ መድረኮችም ይታወቃል። ከአንድ እስከ ስምንት እና እስከ አስር ባሉ የብዝሃ ሕይወት ክምችት ካለባቸዉ ሃገራት አንዱ የእኛ ሀገር ነዉ።»

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በብዝሃ ሕይወት ሀብታቸዉ የበለፀጉ ከሚባሉት ሃገራት ተርታ ብትሰለፍም ዛሬ በአንዳንድ አካባቢ ለወትሮዉ ለምች መድኃኒትነት የሚቆረጡት እጽዋት ጠፍተዉ፤ ሰዎች ለዚሁ ህመም ሃኪም ቤት መሄድ መገደዳቸዉ ነዉ አቶ ያለምሰዉ ያመለከቱት።   

አሁን ከደን እና የአየር ንብረት ሚኒስቴር የሚወጡ መረጃዎች የሀገሪቱ የደን ሽፋን እየተሻሻለ መምጣቱን እንደሚያመለክቱ ነዉ ባለሙያዉ የገለጹልን። ሆኖም ግን ያላሉ ካወደምነዉ የደን ሀብት ገና ይሄ ነዉ የሚባል በቂ መጠን ዳግም መሸፈን እንዳልተቻለ ግን ያሳስባሉ። ለዚህም ደግሞ እንደ አንድ ችግር ያነሱት ያንዱ ሴክተር ከሌላዉ ጋር ያለመናበብ መሆኑን ነዉ የተናገሩት።

የኢትዮጵያን እና የጀርመንን የደን ይዞታ ከሽፋን አኳያ ማወዳደር እንደሚከብድ የገለፁልኝ አቶ ያለምሰዉ አደላ፤ አካሄዳችን ያለንን ከመጠበቅ ይልቅ ወደማጥፋት የሚያመራ ይመስላል እና ሁሉም ሊያስብበት እንደሚገባ በማሳሰብ ነዉ የተሰናበቱን።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic