የሁለት ሐገራት ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 12.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሁለት ሐገራት ምርጫ

የጋምቢያ አሸናፊዎች ተሸናፊዎችን ሲያስፈራሩ፤ ጋናዎች ተሸናፊዎችን ያመስግኑ ነበር።ጋናዎች ከተሸናፊዎች ጋር ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ እንደሚመክሩ ሲያስታዉቁ፤ የጋምቢያ ምርጫ ዉጤት የወለፊንድ ባረቀ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:38
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:38 ደቂቃ

የሁለት ሀገራት ምርጫ

ታሕሳስ 1 2016 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያዉያን አቆጣጠር ነዉ) ጋምቢያዎች የወደፊት ፕሬዝደንታቸዉን መረጡ።በሳምንቱ፤ ጋናዎችም።የምርጫዉ ሒደት-ዉጤት፤ አንድነት-ተቃርኖዉ ያፍታ ዝግታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።ጋምቢያ።መልከዓ ምድራዊ ካርታዋን ትኩር ብሎ ያየ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች ሽኩቻ ዉጤት መሆንዋን ለማወቅ ሌላ ምርምር አይጠይቀዉም።ካርታዉን ከባሕሩ ወደ ምድሩ ሲመለከቱ በቀድሞዋ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ሴኔጋል ላይ ያረፈ የአንድ እግር ፈለግ

ትመስላለች።ወይም አካሉን ባሕር ዉስጥ ደብቆ መላሱን ሴኔጋል ላይ የጎለገለ---ሰዉ ወይም እንስሳ።

በተቃራኒዉ ይመልከቷት። ሴኔጋል እንደ እናት ጋምቢያ እንደ ሕፃን። ሴኔጋል ራስዋን ደረቷ ላይ አስደግፋ፤ እግሯን ባሕሩ ዉስጥ ነክራ፤ የተቀረ አካሏን በሁለት ክንዶችዋ ታቅፋ የምታጥባት ሕፃን ትመስላለች። ጋምቢያ።  ትንሽ ናት።ሁለት ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ሐገር።

ጋና፤ በቆዳ ስፋትም፤ በሐብትም፤ በሕዝብ ብዛትም ጋምቢያን ከአስር ጊዜ በላይ ታጥፋታለች።የቀድሞዋ የወርቅ ጠረፍ ጎልድ ኮስት የ26 ሚሊዮኖች ሐገር ናት።

ከብዙ ልዩነታቸዉ ጋር ብዙ ይመሳሰላሉ።ሁለቱም የምዕራብ አፍሪቃ ሐገራት ናቸዉ።ሁሉቱም አትላንቲክን ይዋሰናሉ።ሁለቱም የብሪታንያ ቅኝ ተገዢዎች ነበሩ።ጋና ቀደም፤ ጋምቢያ ከተል ብለዉ ሁለቱም በ1960ዎቹ ከቅኝ ገዢያቸዉ ነፃ ወጡ።

ሥለ

ነፃነት ገድል-ድል ታሪካቸዉ ሲያወሩ ጋናዎች ክዋሚ ንኩሩማን ይዘክራሉ።ጋምቢያዎች ዳዋዳ ካሪባ ጃዋራን።የመፈንቅለ መንግሥት ታሪክ ሲወሳ ግን ይለያያሉ።የጋናዎች ረዘም፤ደገምገም ያለ ነዉ።ደግሞም ደም አፋሳሽነቱ ይደምቃል።

ጋናዎች በመፈንቅለ መንግሥት፤ በአመፅ ሁከት ሲተራመሱ ጋሚቢያዎች በየአምስት ዓመቱ እንዴ መሪ-እና እንደራሴዎቻቸዉን «እየመረጡ» ቀዝቃዛዉን ጦርነት ዘመን ተሻገሩ።በሁሉም ምርጫ የሚያሸንፈዉ ግን ዳዋድ ጃዋራ የሕዝብ ዕድገት ያሉት ፓርቲያቸዉ ነበር። የጋምቢያ ሕዝብ በጣሙን ጦር ሐይሉ ብዙ ዘግይቶ ከጋና እና ከብዙዎቹ የአፍሪቃ ሐገራት የተማረዉን ገቢር አደረገ።መፈንቅለ መንግሥት። 1994።ደም ግን  አልፈሰሰበትም።

የመጀመሪያዉን መፈንቅለ መንግስት የመሩት መቶ አለቃ ያሕያ አብዱል አዚዝ ጄሙስ ጁንኩንግ ጃሜሕ የትሺቱ ሐገር ሁለተኛ መሪ ሆኑ።የበቀደሙን ምርጫ የጠሩም እሳቸዉ ናቸዉ።

                               

«ከዚሕ በፊትም ግልፅ አድርጌያለሁ።ምርጫ ከጀመርን ጀምሮ ያለናንተ ይሁንታ ይሕቺን ሐገር አልገዛም።ምርጫዉን አላጭበረብርም፤ዉጤቱን ለመቀበል አላንገራግርምም።ምክንያቱም ይሕ ከመላዉ ዓለም በጣም ግልፅና የማይጭበረበር ምርጫ ነዉ።ሥርዓታችን ልዩ ነዉ።ምርጫ እንዲደረግ የወሰነዉም የሚመራችሁን ሰዉ ማንነት የምትወስኑት እናንት የጋምቢያ ሕዝብ በመሆናችሁ ነዉ።ከዚሕ ቀደም ተናግሬያለሁ።ተቃዋሚዬ በአንድ ድምፅ እንኳን ቢበልጠኝ ምርጫዉ ነግልፅ እስከሆነ ድረስ ዉጤቱን እቀበላለሁ።»

 

የምርጡኝ ዘመቻዉ፤ የተፎካካሪዎች አሰላለፍ፤ የድምፅ አሰጣጡ ሒደትም ታዛቢዎች እንደመሰከሩት የጋምቢያም፤ የጋናም ተመሳሳይ ነበር።ነፃ እና ፍትሐዊ።እንደ ምርጫዉ ጊዜ ሁሉ ዉጤቱ ቀደሞ የታወጀዉ ግን ከባንጁል ነበር።

                             

«ከተሰጠዉ ድምፅ 263,200ዉን ድምፅ በማግኘት አዳማ ቦሮዉ የጋምቢያ ሪፐብሊክን በፕሬዝደትነት

እንዲያገለግሉ መመረጣቸዉን አስታዉቃለሁ።»

የጋምቢያ አስመራጭ ኮሚሽን የበላይ ሐላፊ።አዳማ ቦሮዉ ፖለቲካ እንደሚያዉቁ የሚያዉቅ አልነበረም።እንድም ጊዜ የመንግሥት ሥራ ወይም ሥልጣን ይዘዉ አያዉቁም።በዕድሜ ከፕሬዝደንት ያሕያ ጃሜሕ ጋር በወራት ይበላለጣሉ።

ጃሜሕ ቤተ መንግሥት የገቡበትን ስምንተኛ ዓመት ሲያከብሩ ፖለቲካ የማያዉቁት የዕድሜ አቻቸዉ ያሁን ተቀናቃኛቸዉ ወደ ብሪታንያ ተሰደዱ።የድሮ የሐገራቸዉ ቅኝ ገዢዎች ያሉ፤ያደረጓቸዉ ወይም ያደረጉላቸዉ አይታወቅም።ግን ወደ ሐገራቸዉ ተመለሱ።

በምርጫዉ፤ ሰባት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወክለዉ እንደሚወዳደሩ ሲያዉጁ ግን የብሪታንያ መገናኛ ዘዴዎች ልክ እንደ ዶናልድ ትራምፕ ቤት እያሰሩ የሚሸጡ የተዋጣላቸዉ ነጋዴ እያሉ ያሞጋግሷቸዉ ገቡ።ድላቸዉ ሲታወጅ ደግሞ ከትራምፕ በላይ አስደናቂ ዉጤት እያሉ አደነቋቸዉ።

የፖለቲካ ተንታኞች ባሮዉን፤ የ22 ዓመቱን አምባ ገነን ገዢ ያንበረከኩ፤ የማይደፈረዉን የደፈሩ እያሉ አወደሷቸዉ።አንቶኒ ታባልን የመሳሰሉትማ ከአሜሪካዉ ምርጫም ይበልጣል እስከማለት ደረሱ።

                           

«ትንሺቱ፤ 22 ዓመት በአምባገነን የብረት ጡንቻ ስትገዛ የኖረችዉ ጋምቢያ ያስተናገደችዉ ምርጫ በቅርቡ ዩናይትድ ስቴትስ ከተደረገዉ ምርጫም የበለጥ ሽግግር ነዉ የሚመስለዉ።ሙሉ በሙሉ ጥሩ ተስፋ አለኝ።»

ፕሬዝደት ያሕያሕ ጃሜሕም የምርጫዉን ዉጤት ተቀበሉት።ሰዉዬዉ ለጠላቶቻቸዉ ምሕረት የላቸዉም ይባላሉ።ግብረ-ሰዶማዉያንን አይወዱም።የምዕራባዉያንን መርሕ ባደባባይ በማጋለጥ፤ በመዝለፍ፤ መሳደብ የሚበልጥ እና በቅርቡ ዘመን የሚቀድማቸዉ ከነበረ።አንድም ሙዓመር ቃዛፊ፤ ሁለትም ሁጎ ሻቬዝ ነበሩ። ሁለቱም ሞተዋል።

በዚሕም ምክንያት የጃሜሕ ሽንፈት የባሮዉ ድል ብቻ አይደለም። የምዕራባዉያን፤ ጃሜሕን የሚጠሉ ዜጎቻቸዉ፤ ለዉጥ የፈለጉ ምናልባትም የአዳማ ባሮዉን ትኩረት መሳብ የሚሹ ሁሉ እንጂ። ሁሉም ጨፈረ።

በፌስታ ፈንጠዝያዉ መሐል ጋምቢያዊዉ አንጋፋ ድምፃዊ ጃሊብ ኩያቴሕ ባንድ ወቅት ሐገሬን ስጠራ አፍሬ ነበር አለ።«አንድ ታንዛኒያዊ የየት ሐገር ሰዉ ነሕ አለኝ።ጋምቢያዊ ነኝ አልኩት።ዉዉ-- ጋምቢያን አልወዳትም አለኝ።ለምን ስለዉ፤ አምባገነን መሪ ነዉ ያላችሁ ብሎ መለሰልኝ።በጣም አፈርኩ።»

የባሮዉ ድል የሱም ድል ሆነ።አዲስ ዘፈን አቀነቀነ።አስጨፈረም።

                          

ባንጁል የ22 ዓመት ገዢዎችዋን አንገት አስደፍታ አሸናፊዎችን ሥታስቦርቅ አክራ የምርጫ ዉጤትዋን አወጀች።አሸናፊዉ። የተቃዋሚዉ አዲሱ የአርበኞች ፓርቲ (NPP) ዕጩ ናና አኩፎ-አዶ።አኩፎ አዶ ከዚሕ ቀደም ሁለቴ ተወዳድረዉ ተሸንፈዉ ነበር።አሁን በሥልጣን ላይ ያሉትን ፕሬዝደንት ጆን ድራማኒ ማሐማን በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት አሸነፉ።54 ለ44 በመቶ በሆነ ድምፅ።

የአኩፎ አዶ ደጋፊ አድናቂዎች በተገኘዉ ዉጤት መፈንደቅ፤ መቦረቃቸዉ አልቀረም።ሐቅ፤ ተገቢም ነዉ።ፍንደቃ ቡረቃዉ ግን እንደ ጋምቢያዎች ተሸናፊዉን በማዉገዝ፤መዝለፍ፤መወረፍ ላይ ያተኮረ አልነበረም።ጥንቃቄ የተሞላበት፤  ምክር፤ ማስጠንቀቂያ አዘል ብጤም ጭምር እንጂ።

                       

«ለወደፊቱ ፕሬዝደንት ያለኝ መልዕክት አንድነት እንፈልጋለን።ከምርጫ በኋላ በዉጤቱ የማይደሰቱ ሰዎች አሉ።ስለዚሕ አዲሱ መሪ በጋራ ሆነን እንድንታገል የሚያስተባብረን መሆን አለበት።ጥንቅሬያችን አንድነታች ነዉ።»

ይሕ ነዉ ልዩነቱ።ያም ሆኖ ሁሉም ተመሳሳይ መልዕክት ወይም አቋም አለዉ ማለት አይደለም።ጋና፤ ጋምቢያ፤ ናጄሪያ ሆነ ኢትዮጵያ ለመጥፎ-ይሁን ለጥሩ፤ የአብዛኛዉን ሕዝብ አስተሳሰብ የሚቀርፁ፤ የሚቀይሱ፤ አቅጣጫ የሚያመለክቱትም አንድም መሪዎቹ፤ ሁለትም አዋቂዎቹ ናቸዉ።

ለፖለቲካ እንግዳ የሆ

ኑት የጋምቢያዉ ተመራጭ ፕሬዝደንት አዳማ ቦሮዉ ግን ከዉጪም፤ከዉስጥም የሚጎርፍላቸዉን አድናቆት፤ ከተቀናቃኛቸዉ የሰሙትን ሽንፈትን የመቀበል መልዕክት በጥንቃቄ ማጤን፤ ማስተንተን የቻሉ ወይም የፈለጉ አይመስሉም።አሸናፊነታቸዉ በታወጀ በሳልስቱ  የ22 ዓመቱን ገዢ ያስጠነቅቁ፤ ያሳሰቡ፤ለማዘዝም ይንጠራሩ ገቡ።በሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞቹን መፍታት አለበት አሉ።

                      

«ይሕ ጥሩ እርምጃ ይመስለኛል።ይሕን ካደረጋችሁ ሥልጣን ስትለቁ ጥሩ የንግድ ምልክት ትታችሁ ትሔዳላችሁ።ይሕንን ሳይዘገዩ ማድረጉ ጥሩ ነዉ።ለመንግሥት ያለኝ ምክር ይኽ ነዉ።»

ነጋዴ አይደሉ።የንግድ ምልክትን አልረሱም።ሰዉዬዉ በዚሕ አለማቆማቸዉ እንጂ ክፋቱ። በስልጣን ላይ ያለዉን መንግስት ባለሥልጣናት ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡ ዛቱ።ጋምቢያ በጃሜሕ ዘመን የገባባቻቸዉን ዓለም አቀፍ ዉሎች ዳግም እንደሚያጤኑት አስታወቁ።

«ጃሜሕ አሁንም ሥልጣን ላይ መሆናቸዉን ዘነጉት መሰለኝ» አሉ የባንጁል ነዋሪ።

«የሐገሪቱ ጦር ሐይል ጠቅላይ አዛዥ መሆናቸዉን ዘነግተዉታል።» አከለ።«ይሕ  ዘለፋ ነዉ።እሳቸዉን፤ ሚንስትሮቻቸዉን፤ ጦሩን በሙሉ መዝለፍ ነዉ።»የጋምቢያ አሸናፊዎች ተሸናፊዎችን ሲያስፈራሩ፤ ጋናዎች ተሸናፊዎችን ያመስግኑ ነበር።ጋናዎች ከተሸናፊዎች ጋር ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማድረግ እንደሚመክሩ ሲያስታዉቁ፤ የጋምቢያ ምርጫ ዉጤት የወለፊንድ ባረቀ።

የ22 ዓመቱ ገዢ፤ ተቀናቃኛቸዉ በአንዲት ድምፅ ቢበልጣቸዉ እንኳን ዉጤቱን ለመቀበል ቃል የገቡት  ጃሜሕ የምርጫዉን ዉጤት ዉድቅ አደረጉት።ቅዳሜ።«ጋምቢያዉያን ሆይ፤ የምርጫዉን ዉጤት ሙሉ በሙሉ እንደማልቀበለዉ አስታዉቃለሁ።በዚሕም ምክንያት ምርጫዉን ከነሙሉ ሒደቱ ዉቅድቅ አድርጌዋለሁ።ዳግም ምርጫ ይደረጋል።ምክንያቱም ጋምቢያዊዉ በሙሉ ድምፅ መስጠቱን ማረጋገጥ አፈልጋለሁ።»

ይሕ ነዉ የጋና-ጋምቢያ ሰፊ ተቃርኖ።ይሕ ነዉ ትንሺቱ ሐገር ትልቅ ድቀት።እንዴት ይፈታ ይሆን? 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic