የሁለቱ ትላልቅ ከተሞች ምርጫ | ኢትዮጵያ | DW | 17.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የሁለቱ ትላልቅ ከተሞች ምርጫ

አዲስ አበባ ከድሬዳዋ መሻልዋ እርግጥ ነዉ።ግን ቁሻሻ መድፊያ መሙላት መጉደሉን የሚቆጣጠርላት  አስተዳደር አጥታ ቁሻሻ ከመልቀም ያልተላቀቁ ምስኪን ነዋሪች በቁሻሻ ክምር ያለቁባት፤ ሕጋዊ መኖሪያ ቤት በማጣታቸዉ እንደነገሩ ጎጆ ያቆሙ ነዋሪዎችዋ በዘመቻ ቤቶቻቸዉን የሚያፈርስ አስተዳደር የተመሰራተላት ርዕሠ-ከተማ ናት።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:54

የድሬዳዋ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤታዊ ምርጫ መራዘም

አዲስ አበባ ያዉ አዲስ አበባ ናት።የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የምጣኔ ሐብት ርዕሠ-ከተማ፤ ከኒዮርክ እና ዤኔቭ ቀጥሎ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ዲፕሎማቶች መቀመጫ ከሁሉም በላይ በ1999 በተደረገዉ የህዝብ ቆጠራ መሠረት የ3ሚሊዮን ሕዝብ አንዳዶች ከአራት ሚሊዮን ይበልጣል ይላሉ መኖሪያ ናት።እሷን ዊኪፔዲያ እንደፃፈዉ፤ ኦሮሞዎች የመድሐኒት ሜዳ፤ ሶማሌዎች የዲር ጦር መትከያ ይሏታል። አማሮች ደግሞ ባንድ የታሪክ አጋጣሚ አዲስ ወይም አዲሷ ሐረር ብለዋትም ነበር።ድሬዳዋ።አራት መቶ ሺሕ የሚጠጋ ነዋሪ አላት።ሁለቱም የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሥልጣኔ ጀማሪ፤ የኢንዱስትሪ ማዕከል፤የምጣኔ ሐብት ሞተር፤ ናቸዉ።ለድሬዳዋ ግን ነዋሪዎችዋ እንደሚሉት ነበር-መባሉ ነዉ እዉነቱ።ሁለቱም ለኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግሥት ተጠሪ በሆነ መስተዳድር የሚተዳደሩ ናቸዉ።ዘንድሮ መደረግ የነበረበት የሁለቱ የምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ባለፈዉ ሳምንት ተራዘመ።                                            

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈዉ ሳምንት ጉዳዩን በይፋ እስካነሳዉ ድረስ፤ የገዢዉ ይሁን፤የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች፤ነፃ ይባሉ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች፤ የግል ይሁኑ የድርጅት ተቋማት በሁለቱ ትላልቅ ከተሞች ምርጫ ሥለመደረግ አለመደረጉ ያሉት ነገር የለም።ብለዉም ከነበር መራጩ ሕዝብ አልሰማቸዉም።

እርግጥ ነዉ ኢትዮጵያን ላለፉት ሰወስት ዓመታት ግራ ቀኝ ያላጋዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ፤ ግጭት እና ዉጥረት የሐገሪቱን ፖለቲከኞች ትኩረት በመሳቡ የሁለቱን ከተሞች አስተዳደር፤ ምርጫ እና ሒደቱን ለማጤን ጊዜ አልነበራቸዉም መባሉ ያስኬድ ይሆናል።ይሁንና ሕዝብን ለተቃዉሞ ያሰለፈ፤ ያሳደመ፤ ለሞት፤ለጉዳት እና እስራት የዳረገዉ የፍትሕ፤የዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት ጥያቄ መሆኑ አይካድም።ኢትዮጵያን በፖለቲካ ይሁን በምጣኔ ሐብቱ የሚዘዉሩት የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎች የመምረጥ አለመምረጥ መብትም እኒያ ሕዝብን ለተቃዉሞ ያሳደሙ ጥያቄዎች አካል መሆናቸዉ አያከራክርም።

ታዛቢዎች እንደሚሉት ሁለቱን ከተሞች የሚያስተዳድረዉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ

ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና የሚቆጣጠራቸዉ ተቋማት የሁለቱን ከተሞች ምርጫን ርዕሥ-ያላደረጉት ሕዝብ ያነሳባቸዉን ጥያቄዎች እስከሚያዳፍኑ ይላሉ።ሌሎች ደግሞ ገዢዉ ፓርቲ እና ተቋማቱ ግፊት ካልተደረገባቸዉ በፈለጉበት ጊዜ ማንሳት እና መጣል የሚችሉትን ጉዳይ  ርዕሥ የሚያደርጉበት ምክንያት የለም ባዮች ናቸዉ።

ገዢዉ ፓርቲ ችላ ያለዉን ጉዳይ የሕዝብ ጉዳይ ማድረግ የነበረባቸዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነበሩ።በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛዉ የተቃዋሚ ፓርቲ እንደራሴ የነበሩት አቶ ግርማ ሠይፉ ግን አጭር አስተያየት አላቸዉ።ምን ተቃዋሚ አለ የሚል።

የድሬዳዋዉ ነዋሪ አቶ መሳይ ተክሉ እንደሚሉት ደግሞ ምርጫዉ እንዲራዘም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወሰነ በኋላ እንኳ ሥለተራዘመበት ምክንያት፤ ምርጫዉ እስኪደረግ ከተማይቱን ሥለሚያስተዳድረዉ ባለሥልጣን ወይም አካልም ሆነ፤ ከተማይቱን ሥለሚያስዳድርበት ደንብ ለከተማይቱ ሕዝብ ያስረዳ ወገን የለም።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈዉ ሐሙስ ባሳላፈዉ ዉሳኔ መሠረት ለዘንድሮ ተይዞ የነበረዉ የሁለቱ ከተሞች አስተዳደሮች የምክር ቤት አባላት እና ለተጓደሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ የሚደረገዉ በመጪዉ ዓመት ነዉ።የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ለምክር ቤቱ አባላት እንደነገሩት ምርጫዉ ጊዜ እንዲራሰም ካስገደዱት ምክንያቶች አንዱ የፀጥታ መደፍረስ ነዉ።                           

የድሬዳዋዉ መምሕራን ማሕበር ሊቀመንበር እና የቀድሞዉ የከተማይቱ ምክር ቤት አባል መምሕር አበበ ታምራት እንደሚሉት ግን ድሬዳዋ ሰላም ናት።አቶ መሳይም ለምርጫዉ በቂ ዝግጅት አልተደረገም ካልተባለ በስተቀር  የፀጥታ ችግር ለድ

ሬዳዋ ምክንያት ሊሆን አይችልም።                                          

አዲስ አበባ ግን፤ የቀድሞዉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደራሴ አቶ ግርማ ሰይፉ እንደሚሉት ሠላም የለም።ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተገዛች አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን በመሳሰሉ ከተሞች ምርጫ ማድረግ አይቻልም።-አቶ ግርማ እንደሚሉት።የምርጫዉ ጊዜ መራዘሙንም አቶ ግርማ ይደግፉታል።ምክንያታቸዉ ግን ፀጥታ እስኪከበር ወይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስኪነሳ የሚል ብቻ አይደለም አይደለም።                                    

አቶ ግርማ «እኛ» ሲሉ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ማለታቸዉ ነዉ።ይሁንና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫዉ ጊዜ ያራዘሙት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እንዲዘጋጁ ጊዜ ለመስጠት አይደለም-አንድ።የማራዘሙ ሐሳብም ተቃዋሚዎች «ለመንግሥት ያደረ ከሚሉት ምርጫ ቦርድ ቀረበ እንጂ ከተቃዋሚዎች አይደለም።-ሁለት።ሰወስተኛ አቶ ግራም ተቃዋሚ የለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዉስብስብ ችግሮች የሁለቱ ትላልቅ ከተሞችም ችግሮች ናቸዉ።የኢትዮጵያ መንግስት እና ደጋፊዎቹ በተደጋጋሚ እንደነገሩን የሐገሪቱ ምጣኔ ሐብት በየአመቱ በሁለት አሐዝ መንቻረር ከጀመረ አስር ዓመት አልፎታል።የድሬዳዋ ከተማ ዕድገት ግን የቁልቁሊት ነዉ።ነዋሪዎችዋ እንደሚሉት አዲስ የተዘረጋዉ አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋር የሚያገናኘዉ የባቡር መስመር፤ በከተማይቱ የሚገነባዉ የኢንዱስትሪ ማዕከል (ፓርክ) የተቀዛቀዘዉን የከተማይቱን ምጣኔ ሐብት ለማነቃቃት ይረዳ ይሆናል።                                      

መምሕር አበበ ታምራት ናቸዉ።ግን ያዉ ተስፋ ነዉ።ድሬዳዋን ከኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከላት አንዷ፤ ከትላልቅ የንግድ  መናኸሪያዎች ግንባር ቀደሟ፤ ሥልታዊቱ ዘመናይቱ ከተማ የድሮ ሐብት ዉበቷ ትዝታ ከሆነ አመታት ተቆጥረዋል።ነዋሪዎችዋ እንደሚሉት የድሬዳዋ ዘመናይ ኢንዱስትሪ አብነት ይባል የነበረዉ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ፈርሷል።የሲሚንቶ ፋብሪካዋ እየተንገዳገደ ነዉ።

የድሮዎቹ ትላልቅ የቡና ላኪ ኩባንዮች የሉም ወይም ወደትንሽነት አድገዋል።ቁልቁል።ነባሩ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር እያጣጣረ ነዉ።ቻንድሪስ ሥጋ ፋብሪካ፤ ድሬዳዋ ዱቄት ፋብሪካ፤ የለስሳ ፋብሪካ ወይም ማከፋፋይ አሉ ሳይሆን ነበሩ እንበል።መምሕር አበበ ያክሉበታል።                          

ለከተማይቱ ቁልቁል ማደግ ምክንያቱ ብዙ ነዉ።ዋናዉ ግን የፌደራሉ እና የከተማይቱ አስተዳደር የማስተዳደር

ብቃት ማነስ፤ ሙስና ወይምትኩረት መንፈጋቸዉ እንደሆነ ብዙ ነዋሪዎችዋ ይናገራሉ።አቶ መሳይ ግን የፌደራል መንግስትም፤ ባለሐብቶችም ትኩረት አልሰጧትም ባይ ናቸዉ።አዲስ አበባ ከድሬዳዋ መሻልዋ እርግጥ ነዉ።ግን ቁሻሻ መድፊያ መሙላት መጉደሉን የሚቆጣጠርላት  አስተዳደር አጥታ ቁሻሻ ከመልቀም ያልተላቀቁ ምስኪን ነዋሪች በቁሻሻ ክምር ያለቁባት፤ ሕጋዊ መኖሪያ ቤት በማጣታቸዉ እንደነገሩ ጎጆ ያቆሙ ነዋሪዎችዋ በዘመቻ ቤቶቻቸዉን የሚያፈርስ አስተዳደር የተመሰራተላት ርዕሠ-ከተማ ናት።

የኢትዮጵያ መንግሥት በየአመቱ እስከ አስራ-አንድ ከመቶ አደገ የሚለዉ ምጣኔ ሐብት ለርዕሰ ከተማይቱ ነዋሪ ንፁሕ ዉኃ ለማጠጣት እንኳን አልበቃም ወይም ከእድገቱ የገኘዉ ገቢ የገባበት አይታወቅም ወይም የለም።የኤሌክትሪክ መብራት ብርቅ ነዉ።የምግብ ሸቀጥ ዋጋ፤ ቤት ኪራይ አለቅጥ ንረዋል።ትራንስፖርት እንዲሁ።

አቶ ግርማ የአዲስ አበባ መስተዳድር ባለሥልጣናት የሕዝቡን ችግር ለማቃለል እየሰሩ አይደለም ይላሉ።ችግሩም ጠንቷል።ችግር የጠናባቸዉን የሁለቱ ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮቻቸዉን ለመምረጥ ቢያንስ አንድ ዓመት መጠበቅ ግድ አለባቸዉ።ምርጫዉ እስኪደረግ ድረስ ሁለቱን ከተሞች የሚያስተዳድረዉ ወገን ማንነት ላሁኑ አይታወቅም።የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤም እስከምርጫዉ ድረስ ከተሞቹን የሚያስተዳድረዉ ወገን ማንነት ገና ለወደፊቱ በምክክር ይወሰናል ነዉ ያሉት።ያነጋገርናቸዉ የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎች እንደሚገምቱት ግን አሁን በስልጣን ላይ ያሉት አስተዳዳሪዎች እስከሚቀጥለዉ ምርጫ ድረስ  የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ መቀጠላቸዉ አይቀርም,።አስተዳዳሪዎቹ ለሕዝቡ አልሰሩም።ግን የያዙትን ሥልጣን እንደያዙ ይቀጥላሉ።ድቅም አይደል? 

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች