የሁለቱ ሱዳን መንግሥታት ስምምነት በተንታኝ እይታ | አፍሪቃ | DW | 08.01.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሁለቱ ሱዳን መንግሥታት ስምምነት በተንታኝ እይታ

የሱዳን ፕሬዚደንት ኡማር ሀሰን አልበሽርና የደቡብ ሱዳን አቻቸው ሳልቫ ኪር ባለፈው ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባ ባደረጉት ስብሰባ ባሳለፍነው የመስከረም ወር የፈረመቱን ስምምነት ያለምንም ቅድሜ ሁኔታ በአፋጣኝ ለመተግበር ተስማምተዋል። ሀገራቱ ካላቸው ተነሳሽነት አኳያ የስምምነቱ ተግባራዊነት አጠራጣሪ መሆኑ ይነገራል።

ደቡብ ሱዳን ነጻ ሆና ራሷን ማስተዳደር ከጀመረች ወዲህ በሁለቱ ሱዳኖች መካከል እንደገና የተከሰተው የድንበር ውዝግብ እስካሁን መፍትሔ አላገኘም። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ለውዝግባቸው ፍጻሜ ለማስገኘት በአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪነት ባለፈው መስከረም ወር በአዲስ አበባ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። ሆኖም ግን ስምምነቱን ለመተግበር የተደረገ ጥረት አልነበረም። ለስምምነቱ መጓተት ዋና ምክንያት የሆነችው ሰሜን ሱዳን ነች ይላሉ በበርሊን የዓለም አቀፍ እና ጸጥታ ተቋም የሱዳን ጉዳዮች አጥኚ ዶክተር አኔቴ ቬበር።

«ይህን ጉዳይ ያወሳሰቡት የሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ-ሰሜን በሱዳን ሕዝብ ነፃ አውጪ ንቅናቄ- ደቡብ ትጥቅ ሲፈታ ብቻ ነው የነዳጅ ዘይቱ ኤክስፖርት ሊጀመር እና ነዳጅ ዘይቱም ከደቡብ ሱዳን በሱዳን በኩል እንደገና ሊያልፍ የሚችለው የሚለውን ቅድመ ግዴታ እንደገና ያስቀመጡት ሰሜን ሱዳን ወይም ኦማር በሺር ናቸው። እና ይህ ይመስለኛል ለስምምነቱ አለመተግበር ባለፉት ጊዚያት እና አሁንም ዋና መሰናክል የሆነው።»

ይህ የአልበሽር ክስ ቀድሞውኑ በስምምነቱ ሂደት ውስጥ መፍትሄ ሊያገኝ ይገባው ነበር። በዚህ ምክንያት ተጓቶ የቆየው ጥረት እንዲፋጠን ሁለቱ መሪዎች ባሳለፍነው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ ተገናኝተው መስማማታቸው መልካም ቢሆንም ስምምነቱ ተግባራዊ ስለመሆኑ ግን ዶክተር አኔቴ ቬበር ጥርጣሬ አላቸው፣

18.07:2008 DW-TV Quadriga Annette Weber

ዶክተር አኔቴ ቬበር

«ቢያንስ መነጋገሩን መቀጠል ይፈልጋሉ። ግን እውነተኛ ተነሳሽነትን አላየንም። ያየነው ነገር ቢኖር ቀነ ቀጠሮውን ማስረዘምና ስለተግባራዊነቱ ተስፋን መሰነቅ ብቻ ነው። ተጨባጭ የሆነ የጊዜ-ገደብና በቀጣይነት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ያካተተ ዝርዝር እቅድ የላቸውም።»

ሁለቱ ሀገራት ዳግም ለመወያየት የአንድ ሳምንት ቀጠሮ ይዘዋል። በቀጣዩ የአፍሪቃ ህብረት የጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለመወያየት የወሰኑት ሀገራቱ ምናልባት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ይስማማሉ ተብሎ ይታሰባል። እውነተኛ የሆነ የጋራ መፍትሔ እስካልተገኘ ድረስ በሀገራቱ መካከል ያለው መተነኳኩዎስና ጠብ አጫሪነት ይቀጥላል ይላሉ ዶክተር ቬበር። ሆኖም ግን የአፍሪቃ ህብረት አባል መንግስታት የሁለቱን ሱዳኖች ችግር ለመፍታት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ሁለቱን ሀገራት ወደ ስምምነቱ ተፈጻሚነት የሚያደርጉትን ጉዞ ሊደግፍ እንደሚችል ይገምታሉ።

«የአፍሪቃ ሀገራት፤ የአፍሪቃ ህብረትና ሌሎች ክልላዊ ድርጅቶች እጅግ በጣም ሲሳተፉና ከልባቸውም ሲሲሩ ቆይተዋል። ይህና ያቀረቡዋቸው ሀሳቦች ሁለቱ ሱዳኖች ትንሽ ወደ ፊት እንዲራመዱ መርዳት መቻል ነበረባቸው። ምክንያቱም ባለፈው መስከረም ሁለቱ ወገኖች የፈረሙት ስምምነት ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆንበትን መንገድ ያመላከተ ነበር። ያ ግን አሁን ተገቷል። »

የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጉዳይ ምናልባት በሁለቱ ሀገራት ድርድር መፍትሔ የማያገኝ ከሆነ በዓለም አቀፍ ዳኝነት መፍትሔ የማግኘቱ እድልም የጠበበ መሆኑ ይነገራል። ግጭቶች በወረቀት ላይ መፈታት ቢችሉም ሌሎች በርካታ ጉዳዮች ከበስተጀርባው አሉ ይላሉ ዶክተር አኔቴ ቬበር « በነኚህ ሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግጭት ከምንገምተው በላይ ብዙና የተወሳሰበ ነው። ዓለም አቀፍ ዳኝነት ምናልባት ከመፍትሔ መንገዶች ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል። ግን ቀጣይነት ያለው መፍትሔ አይሆንም። »

በዚሁ ምስራቅ አፍሪቃ ክልል የሚገኙ ኤርትራና ኢትዮጵያም ቢሆኑ በመካከላቸው ለተፈጠረው የድንበር ባለቤትነት ውዝግብ በዓለም አቀፍ ዳኝነት ታይቶ ውሳኔ ቢሰጥበትም እስካሁን ድረስ ግን ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። የሱዳንና የደቡብ ሱዳንም ችግር ለመፍትሔው ወደ ዓለም አቀፍ አካላት ከመመልከት ይልቅ ከውስጥ መፍትሔ ለሚያገኝበት ጥረት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ይነገራል።

ኢሳቅ ሙጋቢ

ገመቹ በቀለ

አርያም ተክሌ