1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ሪፖርት

ሰለሞን ሙጬ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 10 2017

የተሰጠው የሥራ ዘመን ሊጠናቀቅ ሦስት ወራት የቀሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእስካሁን የሥራ ሂደቱን በጥንቃቄ ሙምራቱን እና ሕዝቡ ሰላም እንደሚፈልግ መመልከቱን አስታወቀ። ኮሚሽኑ የአጀንዳ ባሰባሰበባቸዉ ክልሎች በአብዛኛው ተመሳሳይ አጀንዳ መቅረባቸውንና የፍትሕ፣ የማንነት፣ የአሥተዳደር ወሰን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አስታውቋል።

https://p.dw.com/p/4n9oh
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስል Seyoum Getu/DW

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥራ ሪፖርት 

የተሰጠው የሥራ ዘመን ሊጠናቀቅ ሦስት ወራት የቀሩት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የእስካሁን የሥራ ሂደቱን በጥንቃቄ ሙምራቱን እና ሕዝቡ ሰላም እንደሚፈልግ መመልከቱን አስታወቀ። ከትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በስተቀር የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር ባከናወነባቸው ክልሎች በአብዛኛው ተመሳሳይ አጀንዳ መቅረባቸውንና የፍትሕ፣ የማንነት፣ የአሥተዳደር ወሰን ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን አስታውቋል። ኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ይራዘም አይራዘም በሚለው ጉዳይ ላይ ምንም አስተያየት እንደሌለው፣ ይህ ኃላፊነት የምክር ቤቱ መሆኑንም ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ገልጿል። በትጥቅ ከመንግሥት ጋር የሚዋጉት ጉዳዮቻቸውን ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ እና እንዲደራደሩ ለማገዝ መንግሥት ዋስትና እንዲሰጥ ጠይቆ በጎ ምላሽ ማግኘቱን የገለፀው ኪሚሽኑ የማደራደር ሥልጣን ግን እንደሌለው ተናግሯል።

መንግሥት ለምክክሩ "አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር" በተደጋጋሚ ሲጠይቅ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ ዘጠኝ ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን ማጠናቀቁን አስታውቋል። ከትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በስተቀር ሌሎች አካባቢዎች አጀንዳ ከማስገባት በተጨማሪ ለዋናው የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውንም ለይተዋል ተብሏል። ከመላው ሀገሪቱ 4000 ተወካዮች የሚሳተፉበት ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መቼ እንደሚጀመር በግልጽ ባይነገርም "የኢትዮጵያ ሕዝብ እየመከረ ነው፣ ምክክር ተጀምራል" ሲሉ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ ተናግረዋል። የሰላም ሁኔታ ሥራቸውን አደናቅፎት እንጂ አሁን ሥራቸውን አጠናቀው ማስረከብ የነበረባቸው ወቅት እንደነበርም ለምክር ቤቱ አብራርተዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም "በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ መግባባት ላይኖር እንደሚችል" ይልቁንም በረጅም ጊዜ ለትውልድ የሚተላለፉ እና በዚህ ምክክር ሊፈቱ የማይችሉ ሀገራዊ አጀንዳዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል። የሥራ ኃላፊው መንግሥት "አንድ ጊዜም ቢሆን ጣልቃ ገብቶብን አያውቅም" ሲሉም ለፓርላማው ገልፀዋል። 

ከምክር ቤቱ አባላት በኮሚሽኑ ላይ የአካታችነት፣ የገለልተኝነት፣ የግልጸኝነት፣ የተዓማኒነት ጥያቄዎች ቀርበውለታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኮሚሽኑ ምን ይጠብቅ የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነር ኂሩት ወልደ ሥላሴ ነፍጥ አንስተው የሚዋጉት ከመንግሥት ጋር እንዲነጋገሩ ከመጋበዝ የዘለለ ኃላፊነት እንደሌለን ሊታወቅ ይገባል ብለዋል። ለተነሳው የተዓማኒነት ጥያቄም "የሠራነው ነገር ላይ ያጠፋነው ግዙፍ የሆነ ጉዳይ አለ ዎይ?" ሲሉ ሥራቸውን በጥንቃቄ መምራታቸውን ገልፀዋል። ሌላኛው ኮሚሽነር አምባሳደር ሙሐሙድ ድሪር የሚቀርቡ አጀንዳዎች እስከምን ድረስ መሄድ አለባቸው? የሕዝቡን የብዛት አንድነት የሚፈታቱኑ እንዳይሆኑ ኮሚሽኑ ምን ማድረግ ይገባዋል ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ "እኛ ዳኝነት አንሰጥም" ሕዝብ ነፃ ሆኖ አጀንዳ እያቀረበ ነው ብለዋል። በዛሬው የምክር ቤቱ ውሎ እስካሁን ለምክክር ኮሚሽን የቀረቡ አጀንዳዎች 75 በመቶ የሚሆኑት ተመሳሳይ መሆናቸው እና በዋናነትም የፍትሕ፣ የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንን የሚመለከቱ መሆናቸው፣ ሲጨመቁ ከአሥር የማይበልጡ መሆናቸው ተነግሯል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ ከውጭ ደጋፊዎች 13.5 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ማግኘቱን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ለበጎ ሀገራዊ ዓላማ በሚል የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ. ም ነበር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሀሳብ አመንጪነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

እሸቴ በቀለ