ዝክረ-አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት፤ 250ኛ ዓመት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 11.09.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ዝክረ-አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት፤ 250ኛ ዓመት

መስከረም በጠባ የመጀመሪያው ቅዳሜ ነበር ወደዚህ ዓለም ብቅ ያለው። ሣይንቲስት ብቻም አልነበር። መጻዒውን ተንባይ፤ ሀገር አሣሽ፤ ተመራማሪ እና ገድለኛም ጭምር እንጂ፤ ጀርመናዊው የተፈጥሮ ሳይንስ ጠቢብ አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት። የተፈጥሮ አሳሹ ሳይንቲስት እነሆ! ቅዳሜ መስከረም 3 ቀን፣ 2019 ዓ.ም ከተወለደ 250ኛ ዓመቱ ይታሰባል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:30

አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት ማን ነው?

መስከረም በጠባ የመጀመሪያው ቅዳሜ ነበር ወደዚህ ዓለም ብቅ ያለው። ሣይንቲስት ብቻም አልነበር። ሀገር አሣሽ፤ ተመራማሪ እና ገድለኛም ጭምር እንጂ፤ ጀርመናዊው የተፈጥሮ ሳይንስ ጠቢብ አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት። የተፈጥሮ አሳሹ ሳይንቲስት እነሆ! ቅዳሜ መስከረም 3 ቀን፣ 2019 ዓ.ም ከተወለደ 250ኛ ዓመቱ ይታሰባል። በተለይ በደቡባዊ አሜሪካ ሃገራት ይኽ ጀርመናዊ ሣይንቲስት ስሙ ዛሬም ድረስ በስፋት ይወሳል። በስሙ ተራራዎች፤ በርካታ ከተሞች፤ እንስሳት እና አጽዋት ተሰይመውለታል። በስሙ አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት የምርምር ተቋምም ተመስርቶለታል። ሌላው ቀርቶ ጨረቃ ላይ የሚገኝ አንድ ሥፍራ የዚሁ ጠቢብ ስያሜን ይዞ የሑምቦልት ቀለበት (Catena Humboldt)ተብሎ ተሰይሟል። 

አሌክሳንደር ፎን ሑምቦልት፦ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር መስከረም 3 ቀን፣ 1769 ዓ.ም ይኽችን ዓለም ሲቀላቀል፤ በዘመኑ ፕሩስያ በጀርመንኛው ፕሮይሰን የሚባለው ግዛት በጀርመኖች ቁጥጥር ስር ነበረች። ፕሩስያ የተመሰረተችው ለመቶ ዓመታት በተደረጉ ጦርነቶች ድል እና ሽንፈት ተፈራርቆባት ነው። በወቅቱ 132.000 ነዋሪዎችን ይዛ ቤርሊን የፕሩስያ መዲና ኾና አገልግላለች። ታዲያ ከነዋሪዎቿ ሩብ ያኽል የሚጠጋው ወታደር ቤት የገባ ነበር። በዚያው ዘመን የብሪታንያዋ መዲና ለንደን 750.000 ነዋሪዎቿን አቅፋ የተንደላቀቀ ኑሮ የሚገፉ ማኅበረሰቦችን ስታስተናግድ ቤርሊን የወታደር ቃጣና ነበረች ማለት ይቻላል። ወዲህ ከባሕር ማዶ ደግሞ ኢትዮጵያ የያኔዋ አቢሲንያ ዘመነ-መሣፍንት የሚንደረደርበት ጊዜ ነበር።

የአሌክሳንደር ሁምቦልት አባት በጦሩ ውስጥ ረዳት አዛዥ እስከመኾን ደርሰው ከኦስትሪያ ጋር ለሰባት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ተፋልመዋል። ከዚያ በኋላ በቤተመግሥት የአልጋ ወራሿ ሊጋባ ኾነው አገልግለዋል። አሌክሳንደር ጆርጅ ሑምቦልት ሹመቱን ካገኙ ከኹለት ዓመት በኋላ በ46 ዓመታቸው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1766 ዓም ፈት የነበረችውን የ25 ዓመቷ ማሪ ኤልዛቤት ኮሎምቦን አገቡ። አዲስ ቤት ሠሪዎቹ መጀመሪያ ታላቅየው ቪልሔልምን በኹለተኛ ዓመቱ ደግሞ ታናሽየው አሌክሳንደር ሑምቦልትን ወለዱ።

አሌክሳንደር እና ወንድሙ ቪልሔልም ሑምቦልት የመንግሥት ትምህርት ቤት ፈጽሞ ረግጠው ዐያውቁም። ይልቁንስ አባታቸው እንደሞቱ የ11 እና የ9 ዓመት ወንድማማቾቹን በሞግዚትነት በተረከቡት ጎትሎብ ዮሐን ክርስቲያን ኩንትስ ስር ትምህርታቸውን ለዐሥር ዓመታት በሚገባ ተከታትለው በርካታ ነገሮችን መቅሰም ችለዋል።  ያኔ ቤርሊን አንዳችም መካነ አዕምሮ ስላልነበራት አሌክሳንደር ሑምቦልት ከቤርሊን አቅራቢያ ፍራንክፉርት አን ደር ኦደር ላይ ወደሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ተልኮ ለስድስት ወራት ትምሕርቱን ተከታትሏል። ከዚያም ሌላ የግል መምህር ተቀጥሮለት ለአንድ ዓመት ያኽል የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከቤቱ ኾኖ ተከታተለ። በዚያ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ፊዚክስ፤ ሒሳብ፤ የግሪክ ቋንቋ፤ ስዕል እና ሥነ-እጽዋትን ማጥናት ችሏል። ወደ ሳይንሱ ዓለም ገና በለገ ዕድሜው የተሳበው አሌክሳንደር ሑምቦልት አንድን ነገር ሲያጠና ከብዙ አቅጣጫዎች መቃኘት መቻሉ ይወደስለታል።

ኮሎምቢያዊው ሥነ-ሕይወት ተመራማሪ እና የተፈጥሮ ጥበቃ አራማጁ ፈርናንዶ ትሩኺዮ፦ የዘመናችን ተመራማሪዎች እንደ አሌክሳንደር ሑምቦልት ሁለገብ ከመኾን በአንዲት ነገር ላይ ማተኮራቸው የከነከናቸው ይመስላል።

«በዚህ ዘመን ኹለ-ገብ የተፈጥሮ አጥኚዎችን አጥተናል። ልክ እንደ ሑምቦልት ሁሉ እያንዳንዱን ነገር ከተለያየ የምርምር መስክ አንጻር መተንተን የሚችሉ ሰዎችን አጥተናል። ሑምቦልት የከርሰ-ምድር ተመራማሪ ነበር፤ እጽዋትንም በጥልቀት አጥንቷል። ርእደ-መሬት ላይም ተመራምሯል። እኛ ግን አኹን አንድ ነገር ላይ እጅግ የሚያተኩር ሳይንስ ነው የምንከተለው። በአንድ ሞሎኪዩል፤ በአንድ አይነት ዝርያ ላይ ነው የምናተኩረው። ሑምቦልት የነበረው አይነት ኹሉን አቀፍ ምርምር ጠፍቶብናል።»

አሌክሳንደር ሑምቦልት የሳይንሳዊ ምርምር ጽሑፉን በመጸሐፍ ያሳተመው ገና የ21 ዓመት ወጣት ሳለ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1790 ነበር። የመጀመሪያ መጽሐፉም በራይን ዙሪያ ስላጠናው ጥቁር ድናጋይ የሚያትት በ126 ገጾች የተዋቀረ ጥናታዊ ጽሑፍ ነው።

አሌክሳንደር በሕይወት ዘመኑ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ ዐያውቅም። ኾኖም ግን የሰላ አዕምሮው ነገሮችን በተለያዩ መንገዶች ለመተንተን የማይተኛ ነበር።  ሐምቡርግ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የምጣኔ ሐብት ከፍተኛ ተቋም ገብቶ አፍታም ሳይቆይ ወደ ዛክሰን ግዛት አቀና። እዚያም ፍራይቡርግ ውስጥ በማዕድን ቁፋሮ እና ጥናት ዝነኛ በነበረው አካዳሚ ውስጥ ገብቶ ለአንድ ዓመት የሚሰጠውን ትምህርት በስምንት ወራት አጠናቆ ወጣ። ወዲያም በፕሩሲያ የማዕድን ተቆጣጣሪነት ሥራ ተቀጠረ። በዘመኑ የወርቅ፤ የብር፤ የብረት እንዲሁም ጨውና ሰልፈር ማዕድናት ለፕሩስያ ግዛት ከፍተኛ የገቢ ምንጮች ነበሩ። ስለነዚያ ማዕድናት ምርምር እያደረገ የማዕድን ቁፋሮ ትምህርት ቤት በማቋቋም የመማሪያ መጽሐፍ አሳትሟል።

በድንገት ኅዳር 18 ቀን፣1796 ዓም የአሌክሳንደር ሑምቦልት እናት ከዚህ ዓለም ተለዩ።  አሌክሳንደር ሑምቦልት፤ ታላቅ ወንድሙ ቪልሔልም ሑምቦልት እንዲሁም በእናታቸው በኩል ሌላኛው ወንድማቸው ሐይንሪሽ ፍሬድሪስ ሉድቪግ ፎን ሆልዌደ ሐብታም ኾኑ። በዓመት 400 ታለር ያገኝ የነበረው አሌክሳንደር በውርስ 90.000 ታለር ተቆጥሮ ተሰጠው። በተጨማሪም መሬት እና ሕንጻም ደረሰው። ሥራውን ርግፍ አድርጎ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅም በነፃነት አውሮጳን አሠሰ።  ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ወስጥም አንድ ሳይንሳዊ ተቋም ገዛ። እዚያም ወደፊት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አሠሳ ባደረገበት ወቅት አብሮት የተጓዘው ፈረንሳዊው ቀዶ ጥገና ሐኪም እና አትክልት አፍቃሪwwe አይሜ ቦንፕላን ተዋወቀ። በወርሃ ሚያዝያ 1799 ዓም አሌክሳንደር ሑምቦልት በዛክሰን ዲፕሎማት በኩል የስፔን ንጉሥ ዘንድ መቅረብ ቻለ። ወዲያም እሱና ጓደኛው አይሜ ቦንፕላ ደቡብ አሜሪካ ወደሚገኙ መላ የስፔን ቅኝ ግዛቶች መዘዋወር የሚያስችላቸውን የጉዞ ሠነድ ማግኘት ቻሉ። ቤርሊን የሚገኘው ሜንዴልሶን የተሰኘው ባንክ አሌክሳንደር ሑምቦልት የሚያስፈልገውን ብድር ለመስጠት አላቅማማም። እንዲህ ያለ አጋጣሚ በሕይወት አንዴ የሚገኝ ነውና አሌክሳንደር ዕድሉን ለመጠቀም አንዳችም አላመነታም።

በዘመኑ የነበሩ አብዛኛዎቹ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬያቸው እምብዛም መራቅ በማይሹበት ጊዜ አሌክሳንደር ሑምቦልት በበርካታ ሃገራት ተዟዙሮ ዛሬም ድረስ ጠቃሚ የኾኑ ምርምሮችን አከናውኗል። የእሳተ-ገሞራ ተመራማሪው ፓትሪኮ ራሞን ለዚያ የዘመኑ ምስክር ናቸው።

«በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች እሳተ-ገሞራ እጅግ ይፈሩ ነበር። እናም ወደ ተራራው ጫፍ መውጣት ያሰጋቸው ስለነበር ወደ እሳተ-ገሞራው ለመቅረብ ሙከራ የሚያደርግ ሰው መመልከት የምር ነበር የሚያስደንቃቸው። ሑምቦልት ግን ቀድሞም እሳተ-ገሞራ ያስደምመው ስለነበር፤ ወደ ተራራው ጫፍ ለመቅረብ አላመነታም። በእርግጥ ያን ለማድረግ መወሰኑ ለዚህች ሀገር እጅግ ጠቃሚ ኾኗል፤ ምክንያቱም ስለ እሳተ-ገሞራዎቻችን በዝርዝር ያሰፈራቸው ማብራሪያዎች አኹን አሉን። የእሱ ልምድ ለእኛ ጠቅሞናል።»

ጀርመናዊው ተመራማሪ፦ ከጀርመን ተነስቶ በርካታ የአውሮጳ ሃገራትን ማሰስ ችሎ ነበር። አምስት መጻሕፍትንም ለኅትመት አብቅቷል፤ አንዱን የጻፈው በላቲን ቋንቋ ነው። በ29 ዓመቱ ብዙ የማወቅ ጉጉቱን ለመተግበር ብርቱ ጽናት እና ኃይልም ነበረው። በስፔን የደቡብ አሜሪካ ቅኝ ግዛቶች በመዘዋወር በርካታ ተራሮችን፤ እሳተ-ገሞራዎችን፤ እጽዋትን እና እንስሳትን ብሎም በአማዞን ጥቅጥቅ ደን ነዋሪ የኾኑ አናሳ ማኅበረሰብ ነዋሪዎችን በጥልቀት አጥንቷል።

አሌክሳንደር ሑምቦልት በዘመኑ ካሜራ ወይንም መቅረጸ ድምጽ ባይኖርም የሚያያቸውን ነገሮች በመላ በዕለታዊ ክስተቶች ማስታወሻ ስብስብ መጽሐፉ በሚገባ ሰንዶ ለዘመናችን አሻግሯል። በርሊን የሚገኘው ግዙፉ ቤተ-መጸሐፍት የእጅ ጽሑፍ ክፍል ባልደረባ ዩታ ቬበር ሑምቦልት በእጅ ጽፎ ያስቀረውን ዝራዝ እያገላበጡ ምን ያኽል እያንዳንዱ ነገር በዝርዝር እንደሰፈረ ያብራራሉ።

«እዚህ ገጽ ላይ የሚጀምረው ወደ ኦሪኖኮ ያደረገው ጉዞ ዘገባ ነው። ኦሪኖኮ ምን እንደሚመስል በስዕላዊ ገለጣ አስፍሯል። እዚህ ጋር መመልከት እንደሚቻለው ሑምቦልት በጉዞው እጅግ ተመስጦ እንደነበር፤ እያንዳንዱን ነገርም እየመተረ ይለካ እንደነበር ነው። እናም እየመተረ በመለካት ሕይወት እንዴት ነው የጀመረው የሚለውን ለመረዳት ሙከራ አድርጓል። እዚህ ጋር መዘንጋት የሌለብን ይኼ ሙከራ የተደረገው ከዳርዊን በፊት ነው። ሑምቦልት በዚያን ጊዜ ካሜራ ኖሮት ቢኾን ኖሮ ምን አይነት ነገር ይሠራ ነበር የሚለውን ማሰብ ደስ ይለኛል።»

በእርግጥም አሌክሳንደር ሑምቦልት በዘመኑ ካሜራ ተፈልስሞ ቢኾን ኖሮ ደቡብ አሜሪካ ውስጥ የኦሪኖኮን ወንዝን ተከትሎ ግራና ቀኝ ጥቅጥቅ ብሎ ወደበቀለው ደን ይዞት በተጓዘ ነበር። ይሁንና ዘርፈ-ብዙው ተመራማሪ በዘመኑ ካሜራ ባይኖረም ዕይታዎቹን በሙሉ ግን ከላባ በተሠራ ብዕሩ ቀለም እየነከረ በዝርዝር አስፍሮልናል።

አሌክሳንደር ሑምቦልት ሰዎችን በመርዳትም ይታወቃል። ለ2800 የተለያዩ ሰዎች 30.000 ግድም ደብዳቤዎችን መጻፉ ይነገርለታል። እንዲያም ኾኖ ገና ብዙ ቀረኝ ይል ነበር። በ75 ዓመት የልደት ቀኑ ያሰፈረው ጽሑፍ፦ «በርካታ ነገሮችን ተመልክቻለሁ ግን ከምፈልገው በጣም ያነሰ ነው» ሲል ይነበባል።

አሌክሳንደር ምንም እንኳን ዝናው በዓለም እየናኘ ቢመጣም የእድሜ ማምሻው ሲቃረብ ግን ብቸንነት መርጧል። ሕይወቱ ሊያልፍ አቅራቢያም አብዛኛ ንብረቱን በሽምግልና ጊዜው ለተንከባከቡት ቤተሰቦች አስረክቧል። ለምርምር ላይ ታች ወጥቶ በመኳተን የጻፋቸው የመጽሓፍ ድጓዎቹን ግን ለወንድሙ ቤተሰቦች በማስረከብ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በግንቦት 6 ቀን፣ 1859 (ሚያዝያ 29 ቀን 1851 ዓም)ከዚህ ዓለም ተለይቷል። ከቬኔዙዌላ፤ ኩባ፤ ከኤኳዶር ፔሩ፤ ከሜክሲኮ አማዞን እየተመላለሰ በማጥናት ያሰፈረው ጥናታዊ ሥራዎቹ ዛሬ ከ250 ዓመታት በኋላም በታላቅ ተመራማሪነቱ እንዲዘከር አስችሎታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic