1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ
ማስታወቂያ
ማስታወቂያ

ዜና | 27.11.2021 | 23:00

ሱዳን፤ ስድስት ወታደሮች በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ተገደሉብኝ አለች

ሱዳን ስድስት ወታደሮቼ በኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ተገደሉብኝ ስትል ለሮፕተርስ ዜና ምንጭ ገለፀች። ወታደሮቹ የተገደሉት ቅዳሜ ዕለት በሁለቱ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ መሆኑም ተዘግቧል። የሱዳን ጦር ቀደም ብሎ በፌስቡክ ባወጣው መግለጫ የማቾችን ቁጥር ሳይገልፅ የኢትዮጵያ ጦር እና ታጣቂዎች በሠራዊቱ ላይ አል -ፋሻቃ እና አል -ሱቅራ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። ይህም ሞት አስከትሏል ...የእኛ ኃይሎች ጥቃቱን በጀግንነት በመመከት በአጥቂዎቹ ላይ ከፍተኛ የህይወት እና የንብረት ኪሳራ አድርሷል ብሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ በይፋ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ «ኢትዮጵያ ሱዳንን አጥቅታ አታውቅም።የምታጠቃበትም ምክንያት የለም። » ሲሉ ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ቅዳሜ ዕለት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ጀነራል ብርሃኑ ጁላ አክለውም «የድንበር ጭቅጭቅ አለ። ይህም በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል ፅኑ አቋም ኢትዮጵያ አላት።» ብለዋል።

ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን ከገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪነት ተሰናበቱ

ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን ከገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪነት መሠናበታቸውን የኢትዮጵያ መንግስት ፕላንና ልማት ሚኒስቴር ዛሬ አስታወቀ። ዕገዳው ከዛሬ ኅዳር 19፣ 2014 አንስቶ ተግባራዊ ይሆናል ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል። ዶክተር እሌኒ ከገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪነታቸው የተነሱት« በመንግስትና በህዝብ ታምነው የተጣለባቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምጹ ይሁንታ የሰጠውን መንግስት ቀይሮ የሽግግር መንግስት ስለማቋቋም በግልጽ ምክክር ሲያደርጉ በመገኘታቸው ነው» ብሏል። የአማካሪ ምክር ቤቱ ይህንን የወሰነው ኅዳር 18፣ 2014 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ መሆኑንም ገልጿል። ዶክተር እሌኒ ገብረ መድህን ታህሳስ 5 ቀን 2013 ዓ ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አማካኝነት ከተሰየሙ እና 16 አባላት ካሉት የገለልተኛ አማካሪዎች ምክር ቤት አንዷ ነበሩ። ዶክተር እሌኒ በቅርቡ በዓለም አቀፍ ሰላምና ልማት ማዕከል በተዘጋጀ እና በድብቅ ተካሂዷል በተባለ የበይነ መረብ ስብስባ ላይ የሰጡት አስተያየት በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በፍጥነት መሠራጨቱ ይታወሳል።

ሱዳን፤ አል ቡርሃን ቢያንስ 8 ጀነራሎችን አሰናበቱ

የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በትንሹ ስምንት ጀነራሎችን ከስራ አሰናብቱ፤ አዲስ የስለላ ኃላፊም ሾሙ ። አዲሱ ሹመት የተሰማው እጎአ ከጥቅምት 25 አንስቶ በሀገሪቱ ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በቁም እስር ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ከስምምነት ከተደረሰ አንድ ሳምንት በኋላ ነው። ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ በበኩላቸው ትናንት የሀገሪቱን የፖሊስ አዛዥ እና ምክትላቸውን አሰናብተው በሌሎች አዲስ ዋና እና ምክትል አዛዦች መተካታቸውን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።

በኦሚክሮን ልውጥ የኮሮና ተህዋሲ የተያዘው ሰው ቁጥር ጨመረ

በደቡብ አፍሪቃ የተገኘው ልውጡ የኮሮና ተህዋሲ ጀርመን ውስጥ ሁለት ሰዎች ላይ መገኘቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መረጋገጡን የባቫሪያን ግዛት መንግስት ይፋ አደረገ። ሰዎቹ ከአምስት ቀናት በፊት ከደቡብ አፍሪቃ ወደ ጀርመን ሙኒክ በአየር ተጓጉዘው የገቡ ናቸው። ከጀርመን በተጨማሪ ልውጡ የኮሮና ተህዋሲ ኦሚክሮን በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት መገኘቱ እየተረጋገጠ ይገኛል። እስካሁን ታላቋ ብሪታንያ፤ ጣሊያን ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ኔዘርላንድስ የደቡብ አፍሪቃውን ልውጥ የኮሮና ተህዋሲ እንዳገኙ ማረጋገጣቸውን ይፋ አድርገዋል። በጀርመን ሄሰን ግዛት ሌላ አንድ ሰው ላይ መገኘቱ ሲረጋገጥ በኔዘርላንድስ ከደቡብ አፍሪቃ ሰሞኑን የገቡ 13 ሰዎች ላይ ልውጡ ተህዋሲ ተረጋግጧል። የደቡብ አፍሪቃ የህክምና ማህበር እስካሁን በአዲሱ ልውጥ ተህዋሲ የተያዙ ህሙማን ላይ ከባድ የሚባል ህመም አለመስተዋሉን አስታውቋል። እንደዛም ሆኖ ደቡብ አፍሪቃ ልውጡን የኮሮና ተህዋሲ ይፋ ካደረገች በኋላ በርካታ ሀገራት ከደቡብ አፍሪቃ ጋር የነበራቸውን የአየር ጉዞ ማገዳቸውን ዛሬም ቀጥለዋል። ከአገዱ ሀገራት አንዷ የሆነችው ዮናይትድ ስቴትስ ደቡብ አፍሪቃን « ለግልፅነቷ» አወድሳለች። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከደቡብ አፍሪቃ ባልደረባቸው ናሌዲ ፓንዶር ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ሀገሪቱ ለሌሎች ሀገራት አርአያ የምትሆን ናት ብለዋል። እንደ የፖለቲካ ተንታኞች የብሊንከን ንግግር ሆን ተብሎ ቻይናን ለመተቸት የተደረገ ነው። ዋሽንግተን ቤጂንግ ለመጀመሪያ ጊዜ ውኃን ከተማ ላይ የተረጋገጠውን የኮቪድ 19 ተህዋሲ መረጃ ለረዥም ጊዜ ደብቃ አቆይታለች ስትል ትወነጅላታለች።

ግሪክ፤ ሁለት አዲስ የስደተኛ ጣሚያዎች ተከፈቱ

በግሪክ ደሴቶች ሌሮስ እና ኮስ ሁለት አዳዲስ የስደተኛ መጠለያ ጣሚያዎች ተከፈቱ። በመክፈቻ ስነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሀገሪቱ የስደተኞች ሚኒስትር ኖቲስ ሚታራቺ « የአዲስ ዘመን መባቻ» ሲሉ ተደምጠዋል። አዲሶቹ የስደተኛ መጠለያ ጣሚያዎች በሽቦ የታጠሩ ፣ ካሜራ የተተከሉባቸው እንዲሁም ለደህንነት ማረጋገጫ የሚሆኑ የኤክስሬ ማሽኖች የተገጠሙ ሲሆን ማታ ማታ በማግኔት የሚዘጉ በሮች ያሏቸው እንደሆኑ የፈረንሳይ ዜና ምንጭ አዣንስ ፍራንስ ዘግቧል። መንግስታዊ ያልሆኑ እና የእርዳታ ድርጅቶች አዲሶቹ የስደተኞች መጠለያ ጣሚያዎች ከከተማ ወጥተው የተሰሩ እና የነዋሪዎችን የመንቀሳቀስ ነፃነት የሚገድቡ ናቸው ሲሉ ከወዲሁ ይተቻሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ከፍተኛ የስደተኞች ባለስልጣናት ዛሬ እሁድ በፈረንሳይ የወደብ ከተማ ካሌ ህገ ወጥ የስደተኛ አዘዋዋሪዎችን ለመታገል የሚያስችል አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው እየመከሩ ነው። ሀገራቱ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት ረቡዕ ዕለት 27 ስደተኞች መሞታቸውን ተከትሎ ነው። ስደተኞቹ ህይወታቸው ያለፈው በጎማ ጀልባ ላይ ሆነው ፈረንሳይን ከእንግሊዝ ጋር በሚያገናኝ የውኃ መስመር ወደ ብሪታንያ ለመግባት ሲሞክሩ ጀልባዋ በመስመጧ ነው። በወቅቱ ከደረሰው አደጋ ሁለት ስደተኞች ተርፈዋል።LA/TD