ዳግም አደጋ የተጋረጠበት የፕሬስ ነፃነት | አፍሪቃ | DW | 18.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ዳግም አደጋ የተጋረጠበት የፕሬስ ነፃነት

የዶይቼ ቬለዉ ጋዜጠኛ ጄምስ ጄፍሪ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የተለያዩ ወገኖችን በማነጋገር ከለውጡ በኋላ በኢትዮጵያ የሚታየዉን የፕሬስ ነጻነት ይዞታ የዳሰሰበትን ይህን መጣጥፍ እንደሚከተለው ተተርጉሟል::

እንደ ጎርጎራውያኑ አቆጣጠር በ 2018 ዓ.ም ወደ ስልጣን የመጡት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ባደረጓቸው ግፊቶች እና በወሰዷቸው የማሻሻያ እርምጃዎች፤ በአፈና ስር ወድቆ የቆየው የአገሪቱ የመገኛ ብዙኃን ነጻነት መሻሻሎችን አሳይተው በመቆየታቸው ምስጋና ቢቸራቸውም ብዙም ሳይዘልቅ ዳግም የፕሬስ ነጻነት ችግሮች ተጋርጠውበታል ሲል ለአልጀዚራ እና ሌሎችም ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ እና በአፍሪቃ ቀንድ አገራት ዙሪያ ዘገባዎችን የሚያቀርበው የብሪታንያው የ«DW»ጋዜጠኛ ጄምስ ጄፍሪ ገልጿል::

ኃብታሙ መኮንን በትንሿ ቢሮው ውስጥ ተቀምጦ የነገውን የበረራ ጋዜጣ ዕትም ለማጠናቀቅ ላፕቶፑ ላይ የአርትዖት ስራውን በተመስጦ በማከናወን ላይ ይገኛል:: ጋዜጣው ባለፈው ጥቅምት ወር ዓለማቀፉ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊው ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የፖለቲካ ማሻሻያ ለውጡን ተከትሎ አዳዲስ የህትመት ስራ ከጀመሩት በርካታ የፕሬስ ውጤቶች መካከል አንዱ ነው::

እንደሚታወቀው የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለሽልማት ካበቋቸው መስፈርቶች አንዱ "አዲስ እና የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ በአገሪቱ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ተጥሎ የቆየውን የቅድመ ምርመራ ሳንሱር እንዲቆም ማድረጋቸው ነው" ሲል ገልፆ ነበር:: ይሁንና ከለውጡ በኋላ የተገኘውን የሚድያ ነጻነት ተከትሎ የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ቢበራከቱም አሁን የሚታየው የብሔር ግጭት ውጥረት አዲሱን የሚድያ ነፃነት የጥቃት ሰለባ እንዳደረገው ሙያተኞቹ እየገለፁ ነው:: በተለይም አንዳንድ ሚድያዎች ለተወሰኑ የማነት ፖለቲካ አቀንቃኝ ቡድኖችን ፍላጎት ወግነው ለብሔር ግጭቶት መባባስ እንዲሁም አገሪቱ እንዳትረጋጋ መንስኤ ሆነዋል የሚል ክስ እና ወቀሳ እየተሰነዘረባቸው መሆኑ ከፍተኛ ስጋትን አስከትሏል:: በአንጻሩ በተለይም መገናኛ ብዙኃንን በተመለከተ የቀደመውን ጨቋኝ እና የአፈና ሥርዓት የመድገም እንዲሁም የታየውን ነጻነት መልሶ የማዳፈን አዝማሚያ በመንግሥት በኩል እየተሞከረ ነው የሚሉ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው:: የበረራ ጋዜጣ ሪፖርተሮች የሙያ አማካሪና ጋዜጠኛ በሪሁን አዳነ "ይህ ጋዜጣ ዕውን ሊሆን የቻለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የለውጥ ጅማሮ ምክንያት ነው" ሲል ይገልፃል:: ይሁንና የመንግሥት አስተዳደር በተቀያየረ ቁጥር ተመሳሳይ ነገሮች እንደሚከሰቱ አሁን ላይ ማስተዋል ችለናል፤ ለውጥ ሲመጣ ብዙ አዳዲስ መጽሔቶች እና ጋዜጦች ብቅ ይላሉ፤ ጥቂት ቆይቶ ግን መንግሥት እነሱን ለማጥፋት ጥቃቱን ይጀምራል" በማለት የችግሩን ድግግሞሽ ለአብነት ጠቅሷል::

የኢትዮጵያ መንግሥት ካለፈው ዓመት ወዲህ የሚድያ ነጻነትን ለማረጋገጥ ከወሰዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች አንዱ በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን ከእስር መፍታት ነበር:: ከዚህም ጎን ለጎን ማሻሻያው በቀደመው የመንግስት አስተዳደር ሃገር ውስጥ እንዳይተላለፉ ወይም እንዳይሰራጩ እገዳ ተጥሎባቸው የቆዩትን 260 ያህል በስደት እንዲሰሩ የተገደዱ የመገናኛ ብዙኃንን ድህረ ገጾች እገዳ ማንሳትንም ያጠቃልላል:: በዚህም ምክንያት ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ባወጣው ዓለም አቀፍ "የሚድያ ነፃነት" መለኪያ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ 180 አገራት ቀድሞ ትገኝበት ከነበረው 150 ኛ ደረጃ ወደ 110 ኛ በመውረድ ከሌሎች አገራት በተለይ ከፍተኛ መሻሻል አሳይታለች ማለቱ የሚጠቀስ ነው::በጋዜጠኝነት የሙያ ተግባሩ "ሽብርትርኝነትን" በማነሳሳት ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ከ 3 ወራት የእስር ቆይታ በኋላ የተፈታው በሪሁን ተሞክሮ ግን ከዚህ የተለየ ነው::በሪሁን ከአሁን ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላደረጉት ቃለ መጠይቅ ሲናገር "ለመገናኛ ብዙኃን ተስማሚ ሰው ናቸው የሚል ግምቱ ነበረኝ፤  አሁን ግን ሚድያዎችን የጥላቻ እና የብሔር ተኮር ወይም መሳሪያዎች አድርጎ የመፈረጅ ዕይታ ያላቸው ይመስላል። ሆኖም የሚድያ አሰራሮች መገምገም ያለባቸው በባለሙያ ተቋማት መሆን አለበት" ይላል:: በመሰረቱ ኢትዮጵያ ረዘም ላለ ጊዜ ከገጠማት ተከታታይ ሁከት እና ብጥብጥ አንጻር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥጋት ቢያድርባቸው አይፈርድባቸውም:: የብሔር ግጭቶች በሚልዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከመኖሪያ ቀያቸው ሲያፈናቅል ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይም 86 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል:: በአዲስ አበባ የሚታተመው ሌላው የአዲስ ዘይቤ ጋዜጣ ዋና አርታኢ አቤል ዋበላም "ብዙ ግለሰቦች አንድ ላይ አብረው ሊሄዱ የማይችሉትን የአክቲቪስትነትን እና የመገናኛ ብዙኃንን ሚናዎች ይቀላቅላሉ" ሲል ትዝብቱን ገልጿል:: "ሕዝባዊ ተቃውሞን የሚቀሰቅሱ ሚድያን የሚመሩ ሰዎች ሳይቀሩ አሉ፤ በመሰረቱ ይህ ፈፅሞ ያልተለመደ ጉዳይ ነው" ይላል አቤል::

ዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምኒስቲ ኢንተርናሽናል መንግሥት ካለፈው ሰኔ ወር ጀምሮ የፀረ-ሽብርትርኝነት አዋጁን በመጠቀም ክስ የመሰረተባቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩን በመግለፅ ድርጊቱን አውግዟል:: "የፀረ-ሽብር ሕጉ ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥቅም ላይ መዋሉ በአገሪቱ ከታዩት የተሃድሶ ለውጥ እርምጃዎች ውጭ ነው" ሲሉም የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ አፍሪቃ ቀንድ ምክትል ዳይሬክተር ሲፍ ማጋንጎ ተናግረዋል:: ሕጉ ከዓለማቀፍ ስምምነቶች ጋር ተስማሚ በሆነ መልኩ መከለስ እንዳለበት እና ዳግም ጋዜጠኞችን ለማጥቃት ሊያገለግል እንደማይገባውም ማጋንጎ ጠቅሰዋል:: "በአሁኑ ወቅት እየተለወጥ እና እየጠነከረ የመጣው የሚድያው እንቅስቃሴ አጠቃላይ ገፅታ ጋዜጠኞችን ራስ በራሳቸው ሳንሱር ለማድረግ አስገድዷቸዋል" በማለት በሪሁንም ስጋቱን ይገልጻል:: ለምሳሌ በሱ ላይ ተመስርቶ የነበረው ክስ አሁንም እልባት ባለማግኘቱ ለጥንቃቄ ከፅሁፍ ስራዎቹ ይልቅ ለሌሎች ጋዜጠኞች ድጋፍ እና እገዛ ማድረጉ ላይ ማተኮሩን ይናገራል:: በቲውተር ገፅ የሚለጥፋቸው መልዕክቶችም ተጨማሪ ችግሮች ያመጡብኛል ከሚል ስጋት ማስወገዱን መርጧል:: በሪሁን እና ሌሎችም ልምድ ያካበቱ ጋዜጠኞች "ለአስርተ ዓመታት በጭቆና /በኃይል/ ጥቃት ስር ወድቆ የቆየው የሚድያው ዘርፍ በተቋማዊ አደረጃጀቱ አሁንም ደካማ ሆኖ መቀጠሉ ለአዲሱ የሚዲያ ነጻነት የለውጥ ሂደት እንቅፋት ሆኗል" የሚለውን ኃሳብ ይጋራሉ:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አምና የጀመሩትን የለውጥ ማሻሻያ ተከትሎ ከእስር የተፈታው እውቁ ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ ግን "መንግሥት እኛን መደገፍ ወይም በተቃራኒው መሰለፍ/መቃወም ነው" በሚልበት በአሁኑ ሁኔታ የጋዜጠኝነት ሙያ አስቸጋሪ ነው ሲል ተናግሯል::

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአገሪቱን ፓርላማ ሳይቀር ሚድያ በአገሪቱ የሚታየውን " አለመረጋጋት በማባባስ" በሚያስከትለውን ችግር በተለይም በኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች ሚና ዙሪያ ትኩረት የሰጠ ውይይት እንዲካሄድ ሞክረዋል:: "ሁለተኛ ዜግነታቸውን እና የውጭ አገር ፓስፖርታቸውን በመጠቀም እነዚህ የሚዲያ ባለቤቶች ግጭቶችን በማነሳሳት አገሪቱን ወደ ቀውስ ውስጥ ካስገባች በኋላ ሰላም እና ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት አገር ሸሽተው ይሄዳሉ " ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረው ነበር፡፡ የፖለቲካ አክቲቪስትና የኦሮምያ ሚድያ ኔትወርክ መስራች ጃዋር መሃመድም አከራካሪ ሃሳቦችን በማህበራዊ ሚድያዎች በመሰንዘር ጠንካራ ትችት ደርሶበታል:: ለምሳሌ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በአገሪቱ የተከሰተው ግጭት አንዱ መንስኤ ጃዋር በመንግሥት የተመደቡለትን የፀጥታ አስከባሪዎች በድንገት ለማንሳት ሙከራ ተደርጓል ብሎ ያቀረበውን ውንጀላና ጥሪ ተከትሎ ነበር ብሏል ዘገባው:: የሱ ደጋፊዎች ግን "ህይወቱ አደጋ ላይ በመጣል ላይ ላለው መንግስት ችግሩን ለማስገንዘብ እና መልስ ለመስጠት በቅፅበት የተደረገ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ነበር እንጂ፤ ጃዋር በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ አልነበረውም" ሲሉ ይከራከራሉ:: ሌላው የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶቹ ችግር የገንዘብ እጥረት በስራቸው ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ነው ይላል የጄፍሪ ዘገባ:: በወር የ 6ሺህ ብር ወይም 181 ዩሮ ደመወዝተኛው የ 22 ዓመቱ ወጣት የበረራ ጋዜጣ አዘጋጅ ረቂቅ ተሰራ " ምንም ትርፍ የለንም፤ ከማስታወቂያ ምንም ገቢ ማግኘት አልቻልንም" ሲል ችግሩን ያስረዳል:: ለዚህም አንዱ ምክንያት "ድርጅቶች እና የንግድ ተቋማት ፤ ሚድያዎች ብሔር ተኮር እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩበት የተዛባ አመለካከት ስላለ ምናልባት በመንግሥት በኩል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችል ይሆናል ከሚል ፍራቻ ከማስተዋወቅ ይቆጠባሉ፤ እኛ እንደ አማራ ክልል የሚድያ ልሳን ተደርገን የምንታይበት ሁኔታ ቢኖርም መላ አገሪቱን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ነው የምንሸፍነው" በማለትም ያብራራል:: አንባብያኑም በተመለከተ ደግሞ በሪሁን እንደገለፀው "የፖለቲካው ሁኔታ መረጋጋት ሲያሳይ የአንባቢያኑ ቁጥር የማሽቆልቆል ወይም የመቀነስ አዝማሚያ እንደሚታይበት፤ በአሁኑ ጊዜ ግን በርካታ አንባብያን እንዳሏቸው" በዘገባው ተጠቅሷል:: ለምሳሌ የበረራ አንባቢያን ቁጥር በኢትዮጵያ በተከሰተው ግጭት ሳቢያ በወር ከ 2ሺህ 500 ገደማ ወደ 5 ሺህ እንዴት ሊያድግ እንደቻለ መታዘቡንም ነው በሪሁን የሚናገረው::

በርካታ ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና መሰረታቸውን ውጭ ሃገራት ያደረጉ መገናኛ ብዙኃንን በዜና ምንጭነት መጠቀማቸው ለተዛቡ እና ሃሰተኛ መረጃዎች የመጋለጥ ዕድላቸውን ከፍ ማድረጉም ሌላው በዘገባው የተጠቀሰ ጉዳይ ነው ::ይህንን እና አጠቃልይ ችግሮቹን ለመፍታት መንግሥት የአገሪቱን ሚዲያዎች አቅም ለማጎልበት እንዲሁም የሚመሩባቸውን ደንቦችን ለማውጣት ጥረት እያደረኩ ነው ብሏል ፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም "የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እንዲ ዓይነቱን ችግር ለማስተካከል/ለመቆጣጠር ተቋማዊ የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ ሂደት ላይ ይገኛል " ነው ያሉት:: ለእንደዚህ ዓይነቶቹ ተቋማት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን መሾም ቀደም ሲል በተቋማቱ ይታይ የነበረውን ጨቋኝ ዝንባሌን ለመቀልበስ የተወሰደ የመንግሥት ቁርጠኝነት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም በመንግስት አዲስ የሚዲያ እና የፀረ-ጥላቻ ንግግር ህግጋት መዘጋጀታቸውን ነው ቢልለኔ ያስረዱት፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የሚድያ ኢንዱስትሪ ተቋማት እንደነዚህ ያሉ ህጎች አሁን ጥቃት እና ፈተና የተጋረጠበትን አዲሱን የሚድያ ነጻነታቸውን ይበልጥ ለማደናቀፍ ወይም ለማፈን ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል ሲል ለአልጀዚራ እና ሌሎችም ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ እና በአፍሪቃ ቀንድ አገራት ዙሪያ ዘገባዎችን የሚያቀርበው የብሪታንያው ጋዜጠኛ ጄምስ ጄፍሪ ዘገባውን ቋጭቷል::

ጄምስ ጄፍሪ / እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ