ለዓመታት ከህመሙ የታገለው አንጋፋ ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሲታወስ
ሰኞ፣ ኅዳር 2 2017ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን የዜና አነባበብ ቅላጼው በብዙዎች ይወደዳል። እናት እና አባቶች በተለይ በቴሌቪዥን ቀርቦ ዜና ከማንበቡ አስቀድሞ በሚያቀርበው የአክብሮት ሰላምታው ትህትናውን እየገለጹ ልጆች ይመክሩበት ነበር።
አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ዜናነህ መኮንንበዶቼ ቬለም ለዓመታት ከኢየሩሳሌም ዘጋቢ ሆኖ በሙያው ቆይቷል። ጋዜጠኝነት ለዜናነህ ድንቅ ሙያ ሲሆን፤ በአንድ ወቅት እሱው እንዳጫወተኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂው ገጣሚ መንግሥቱ ለማ «ዜናን ዜናነህ አነበበው ማለት» ዘመዳዊ ተሳቢ ነው እያሉ ለተማሪዎቻቸው ያነሱ እንደነበር የሰማው ሁል ጊዜ ፈገግ ያስብለዋል። የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ቀልቡን ይስበዋል፤ በእስራኤላውያን ብሔርተኝነት ይደመማል፤ ኢትዮጵያውያን በየሀገሩ ተበትነው ስለሀገራቸው መቆርቆር አለማቆማቸውን ቢያደንቅም፤ የተሻለ ነገር ለመሥራት ብዙ ይቀረናል የሚል፤ ተቆርቋሪ ዓይነት ሰው ነበር። ዛሬ ስለዜናነህ ነበር እያልን ነው የምናወራው ትናንት ከዚህ ዓለም ድካም አርፏል። በህመም አልጋው ላይ ዓመታትን አሳልፏል። የኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችን ግለታሪክ የመሰነድ ጥረት በማድረግ ላይ ከሚገኘው ተወዳጅ ሚዲያ ባለቤት እንደተረዳነው በእራሱ በዜናነህ ትብብር የተዘጋጀው የሕይወት ታሪኩ አንጋፋው ጋዜጠኛ በ1945 ዓ.ም ጎንደር አዘዞ በምትባል ከተማ ውስጥ መስከረም ወር ላይ አደይ አበባና አዲስ ዓመቱን ተከትሎ መወለዱን ያመለክታል።
ዜናነህ የሦስት ሴት ልጆች አባት ነው፤ የልጅ ልጆችንም አይቷል። ሥርዓተ ቀብሩ ነገ ለረዥም ዓመታት በኖረባት እስራኤል ሀገር ቴልአቪቭ ከተማ ይፈጸማል። ለልጆቹ፤ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቹ፤ ጓደኞቹ እና አድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን። ነፍስ ይማር!
በሚያውቀው ርዕሰ ጉዳይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ቃለመጠይቅ ለመስጠት ወደኋላ የማይለው ዜናነህ መኮንን በየጊዜው ከሚቀርብባቸው አንዱ ኅብር ራዲዮ የተሰኘው የድረገጽ የዜና ምንጭ ነው። የኅብር ራዲዮ ዜና አቅራቢ ጋዜጠኛ ሀብታሙ አሰፋን በአጭሩ ስለዜናነን ትውስታውንና አስተያየቱን እንዲሰጠን ጋብዘን አነጋግረነዋል። የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ