ዚምባብዌ የኤኮኖሚ ውድቀቷና የወደፊት ዕጣዋ | ኤኮኖሚ | DW | 26.03.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዚምባብዌ የኤኮኖሚ ውድቀቷና የወደፊት ዕጣዋ

የዚምባብዌ የኤኮኖሚ ውድቀት በዓለም ላይ አቻ ተፈልጎ አይገኝለትም። አገሪቱ በ 80 ኛዎቹ ዓመታት መግቢያ ነጻነቷን ስትጎናጸፍ ዛሬ ከዚህ አዘቅት ውስጥ ወድቃ ትገኛለች ብሎ ለመተንበይ የደፈረ አልነበረም።

ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ

ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ

ሆኖም በፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ከሁለት አሠርተ ዓመት በላይ ስትገዛ የቆየችው የደቡባዊው አፍሪቃ አገር በተለይ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በከፋ ቀውስ ላይ ነው የምትገኘው። የኑሮ ውድነት በማይታሰብ መጠን ወደ ላይ ተተኩሷል። ብዙሃኑ የአገሪቱ ዜጎች የሚቀመስ ያጡበት፣ ለስደት የተዳረጉበት ሁኔታ ነው የወቅቱ የአገሪቱ መለያ ሆኖ የሚገኘው። በፊታችን ቅዳሜ ዚምባብዌ ውስጥ ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል። ታዲያ ሙጋቤን ከሥልጣን አሰናብቶ የአገሪቱን የኤኮኖሚ ዕድል ለማቃናት የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆን?

ዚምባብዌ ዛሬ ዜጎቿ በከፋ የኑሮ ውድነት የተጠመዱባት፣ ሥራ አጥነት ከመጠን በላይ የተስፋፋባትና በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ወደ ጎረቤትና ወደ ምዕራቡ ዓለም መሰደድ የተገደደባት አገር ናት። ከአምሥት አራቱ ዜጋ ሥራ አጥ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን በየቀኑ ሶሥት ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገሮች መሄድ የተገደዱበት ጊዜ አለ። በአጠቃላይ ብዙዎች የአገሪቱ ተወላጆች መጠለያ ጎጆና የሚቀመስ ምግብ እንዳያጡ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ዘመዶች የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኞች ናችው።

በዚምባብዌ የሰፈነው የኑሮ ውድነት ሲበዛ አስደንጋጭ ነው። ምንም እንኳ የኑሮ ውድነት በሌሎች የአፍሪቃ አገሮችም ያለ ጉዳይ ይሁን እንጂ የዚምባብዌ የኤኮኖሚ ክስረት መጠን ተወዳዳሪ የለውም። ዓመታዊው የኑሮ ውድነት አምሥት ሺህ ከመቶ ገደማ እንደሚጠጋ በሚነገርላት የደቡባዊው አፍሪቃ አገር ሁኔታው ብዙዎችን የሚላስ-የሚቀመስ ያሳጣ ጉዳይ ነው። የዳቦ ዋጋ ዛሬ ከዓመት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር ሃምሣ ጊዜ ያህል ጨምሯል። መጨመርም የቀጥለ ነገር ነው። በሌላ በኩል የሠርቶ አደሩ ደሞዝ ሁኔታውን ተከትሎ ሊያድግ ቀርቶ ጥቂት እንኳ ከፍ አላለም።

ይህ እርግጥ የዚምባብዌን ያህል አይሁን እንጂ የብዙ የአፍሪቃ አገሮች ሃቅ ነው። የምግብ ምርቶችና የነዳጅ ዋጋ በዓለምአቀፍ ደረጃ እጅግ እየናረ በሄደበት በዛሬው ጊዜ አፍሪቃን የተናነቀው የኑሮ ውድነት በተለይ በዝቅተኛ ገቢ ኑሮውን ለሚገፋው ዜጋ ሲበዛ ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳይ ነው። የኑሮ ውድነትን ተከትሎ የሠርቶ አደሩን ደሞዝ በማሳደግ ከሁኔታው ማጣጣም በማይታወቅባት ክፍለ-ዓለም የብዙዎች ዕጣ-ፈንታ መራብ፤ መልሶ በዕርዳታ ላይ ጥገኛ መሆን ነው። ያሳዝናል አፍሪቃ ዛሬም የሕዝቦቿን መሠረታዊ የምግብ ፍላጎት ልታሟላ በምትችልበት ሁኔታ ላይ አይደለችም። ዞሮ ዞሮ በጎ አስተዳደር መጓደሉ፤ አግባብና ቀጣይነት ያለው የልማት ራዕይ አለመኖሩ ነው ጎልቶ የሚታየው።

እነዚህ ሃቆች ዚምባብዌም ቀውስ ላይ ጎልተው የሚታዩ ናቸው። ለብዙ የአገሪቱ ተወላጆች የችግሩ መሠረታዊ መንስዔ የመንግሥቱ የመሬት ስሪት ይዞታ ነው። አገሪቱ ነጻነቷን ከተጎናጸፈች በኋላም በነጮች ዕጅ የቆየው የእርሻ መሬት በዘጠናኛዎቹ ዓመታት መጨረሻ ያላንዳች ካሣ እንዲወረስ መንግሥት ያወጣው ዕቅድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሳያመዝን አልቀረም። የመንግሥቱ ፖሊሲ ዚምባብዌን በተለይ ከምዕራቡ ዓለም ያገለለ ብቻ አልነበረም። በርካታ እርሻዎች ከተወረሱ በኋላ የአገሪቱ የእህል ምርትና የትምባሆ የውጭ ንግድ ተንኮታኩቶ ይወድቃል። ይህና አገሪቱ በዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ ውዝግብ ውስጥ በመነከር ብዙ ገንዘብ ማፍሰሷ የመቅሰፍትን ያህል ነው የሆነው።

ውጤቱ የምግብ እጥረት ቀውስ ነበር። በእርሻና በቱሪዝም ዘርፎች የውጭ ገቢው ማቆልቆልም በኤኮኖሚው ላይ ብርቱ ፈተናን ያስከትላል። የዚምባብዌ መንግሥት ለችግሩ መባባስ የራሱ ፖሊሲ ያለውን ድርሻ ለመቀበልም ሆነ ለመፈተሽ አልከጀለም። ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ለአገሪቱ ኤኮኖሚ ውድቀት የራሳችውን የመሬት ይዞታ ለውጥ ሣይሆን ሤረኛ ያሉትን ማዕቀብ የጣለባችውን የምዕራቡን ዓለም፤ በተለይም የቀድሞይቱን ቅኝ-ገዥ ብሪታኒያን ነው ተጠያቂ ያደረጉት። ያም ሆነ ይህ በአፍሪቃ በተለያዩ አገሮች እንደተለመደው ለኤኮኖሚው አጠቃላይ ቀውስ ከውጭው ይልቅ ቤት-ሰራሹ ችግር ያመዝናል።

ይህም ሆኖ ፕሬዚደንት ሙጋቤ ሃቁን አስተውለው በውዴታቸው ገሸሽ የሚሉ አይመስሉም። የአገሪቱ የፖለቲካ ሣይንስ ምሁር ጆን ማኩምቤ እንደሚሉት “ሙጋቤ ወንበራችን የሙጥኝ ብለው ከዚህ ንቅንቅ አልልም እንደሚሉ ይታየናል። ታዲያ እንደ አገሪቱ ማቆልቆል ሁሉ መቀመጫቸውም አልጠራጥርም” ፕሬዚደንት ሙጋቤ በእርግጥም አንዳች የስንብት ሃሣብ የላቸውም። ሕዝብ እንደገና እንዲመርጣቸው ለመሳብ ባለፉት ጊዜያት ያላደረጉት ሙከራም የለም። የዚምባብዌ መንግሥት በፊታችን ቅዳሜ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ የአገሪቱን የኤኮኖሚ ቀውስ ለመቋቋም ይበጃሉ ያላችውን በርካታ ዕርምጃዎች ወስዷል። ከነዚሁ መካከል በውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ የማስፈን፣ የዚምባብዌን ዶላር ዋጋ ከፍ የማድረግና የዋጋ ቁጥጥርን የማጥበቅ ዕርምጃዎች ይገኙበታል።

መንግሥት ከዚሁ በተጨማሪ በውጭ ይዞታ በሚገኙ ኩባንያዎች ውስጥ የአገሪቱ ዜጎች የብዙሃን ቁጥጥር እንዲኖራቸው ለማድረግ እያቀደም ነው። ሆኖም የንግዱ ዘርፍ ሰዎች ለውጡን ጠቃሚ አድርገው አይመለከቱትም። እንዲያውም የአገሪቱን ኤኮኖሚ ከለየለት የባስ ውድቀት ላይ እንዳይጥል ነው የሚሰጉት። ዚምባብዌ ከፊታችን ቅዳሜ ምርጫ በኋላ ምናልባት አዲስ ፕሬዚደንት ልታገኝ ትችላለች። ጥያቄው አገሪቱን ከወደቀችበት የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ኑሮ አዘቅት ሊያወጣ የሚችል መንግሥት ይቋቋማል ወይ ነው። ለወቅቱ ቀውስ ተጠያቂ የሆኑት ሙጋቤ በውዴታ ሥልጣን መልቀቃቸውን የሚያምን ማንም የለም። በመሆኑም አንድ ነጋዴ የዘርፋችውን ሁኔታ አስመልክተው እንዳስረዱት ብዙዎች መጪውን ጊዜ የሚጠብቁት በፍርሃቻና በጥርጣሬ መንፈስ ነው።