ዚምባብዌ ከምርጫው በኋላ | አፍሪቃ | DW | 01.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዚምባብዌ ከምርጫው በኋላ

የዛኑ ፒኤፍ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምርጫውን አሸንፈናል ፣ ተቀናቃኛችን የዲሞክራሲያዊ ለውጦች ንቅናቄ MDC አልቋለታል ተቀብሯል እያሉ ነው ። ስማቸውን ያልጠቀሱ አንድ ነፃ የዚምባብዌ የምርጫ ታዛቢም የድምፅ ቆጠራ የመጀመሪያው ውጤት ለቻንጋራይ ታላቅ ውድቀት እንደሚመስል ለሮይተርስ አታውቀዋል ።

የዚምባብዌ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሰላማዊ እንደነበረ የምርጫ ታዛቢዎች አስታወቁ ። የአፍሪቃ ህብረት የታዛቢዎች ቡድን ምርጫው ሰላማዊና ነፃ ነበር ሲል ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ምርጫው ነፃ ነበር ፣ አይደለም ለማለት ጊዜው ገና ነው ብላለች ። በዛሬው እለት የፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ፓርቲ ዛኑ ፒኤፍ በሰፊ ልዩነት ማሸነፉን ሲያሳውቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞርገን ቻንጋራይ ደግሞ ምርጫውን ዋጋ ቢስ ብለውታል ። ፓርቲያቸው MDC ከፍተኛ ማጭበር ተፈፅሟል እያለ ነው ።
የትናንቱ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደተፈራው ግጭት ያልተከሰተበት ሰላማዊና ነፃ ምርጫ እንደነበረ ምርጫውን የተከታተሉ ታዛቢዎች እየተናገሩ ነው ። ሮይተር የጠቀሳቸው የአፍሪቃ ህብረት ታዛቢዎች ቡድን መሪ በመጀመሪያው ቅኝታቸው የድምፅ አሰጣጡ ሰላማዊና በስርዓት የተካሄደ ነፃና ትክክለኛ እንደነበረ አስታውቀዋል ።
ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ የምርጫው አካሄድ ሰላማዊ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶች ከመነሻው መታየታቸውን አስታውቃ ምርጫው ትክክለኛ ነበር ለማለት ግን ጊዜው ገና ነው ብላለች ። የዚምባብዌ የምርጫ ታዛቢዎች ደግሞ ምርጫው ነፃና ትክክለኛ ነው ብለው ያምናሉ ። ከነዚህ አንዱ ሪታ ማካራው ናቸው ።


«አዎ ምርጫው ነፃና ትክክለኛ ነው ብዮ አምናለሁ።በተጨማሪም ወደፊት የሚወጡት ዘገባዎች ምናልባትም ነፃና ትክክለኛ ነው የሚለውን የኔን አመለካከት ይጠቁሙይሆናል ። »
ስለ ምርጫው ሂደት ታዛቢዎች ይህን መሰል አስተያየቶች ሲሰጡ በዛሬው እለት የፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ፓርቲ የዛኑ ፒኤፍ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምርጫውን አሸንፈናል ፣ ተቀናቃኛችን የዲሞክራሲያዊ ለውጦች ንቅናቄ MDC አልቋለታል ተቀብሯል እያሉ ነው ። ስማቸውን ያልጠቀሱ አንድ ነፃ የዚምባብዌ የምርጫ ታዛቢም የድምፅ ቆጠራ የመጀመሪያው ውጤት ለቻንጋራይ ታላቅ ውድቀት እንደሚመስል ለሮይተርስ አታውቀዋል ። አንዳንድ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ዋና ዋና የMDC አባላት ፣ ብዙ ደጋፊዎች እንዳላቸው በሚገመትበት በዋና ከተማይቱ በሃራሪ ሳይቀር የምክር ቤት መቀመጫዎችን አላገኙም ። የቻንጋራይ ፓርቲ በበኩሉ የተባለውን ውጤት እንደማይቀበል አስታውቆ እጅግ ከፈተኛ ማጭበርበር ተፈፅሟል የሚል ክስ አቅርቧል ። ሞርገን ቻንጋራይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ምርጫውን ባዶና ዋጋ ቢስ ሲሉ ውድቅ አድርገውታል ። አድማ በታኝ ፖሊስ ሃራሬ የሚገኘውን የMDC ፅህፈት ቤት መክበቡ ተዘግቧል ። የድምፅ አሰጣጡ በሰላም ቢጠናቀቅም ፣ አንዳንድ ታዛቢዎችም ምርጫው ነፃ ነበር ቢሉም ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ ከወዲሁ አሸንፌያለሁ ማለቱና ተቀናቃኙ MDC የሚያሰማው ክስ ከዛሬ 5 ዓመቱ ምርጫ በኋላ የተከሰተውን ዓይነት ግጭት እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት አለ ። የጀርመኑ የኮናርድ አደናወር የጥናት ተቋም ባልደረባ ዩርገን ላንገ ካለፈው ምርጫ ልምድ በመነሳት ውጤቱ ሲታወቅ ችግሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል ።


« ከምርጫ ጋር የተያያዙ ችግሮች ብዙውን ጊዜ መውጣት የሚጀምሩት ከምርጫ በኋላ በተለይም የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ነው ። ባለፈው የ2008 ቱ ምርጫ ፣ ውጤቱ እስኪገለፅ ድረስ ብዙም ወከባና ደም አፋሳሹ ግጭት አልነበረም ። »
በአሁኑ የዚምባብዌ ምርጫ ከበፊቱ የበለጠ መራጭ ነው ድምፅ የሰጠው ። ህዝቡ የሰጠው ድምፅ በትክክል መቆጠሩ ከምርጫ በኋላ ሊከሰት ይችላል ተብሎ የሚፈራውን ግጭትና ብጥብጥ ሊያስቀር እንደሚችል ይታመናል ። ሆኖም ካለፈው ልምድ በመነሳት ይህ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑ ህዝቡን አሁንም እንደሚያሳስብ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ ኢሪን ፔትሩስ ያስረዳሉ ።
« በአንዳንድ የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ና በአንዳንድ ክፍላተ ሃገር የተጀመረው የድምፅ ቆጠራ ሂደት ግልፅነት በጣም ወሳኝ ጉዳይ ነው ። የምርጫው ውጤት በተቻለ ፍጥነት ይፋ ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን ። ይህ ህዝብን የሚያስጨንቅና የሚያሳስብ ጉዳይ ይመስለኛል ምክንያቱም ህዝቡ በምርጫ ላይ ብዙም እምነት የለውም ። ምክንያቱም በምርጫ ሰበብ ግጭቶች ተከስተዋልና ። »
የዚምባዌ ምርጫ የመጀመሪያው ውጤት ዛሬ ወይንም ነገ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ። ቢዘገይ ደግሞ እስከ ሰኞ ሊቆይ ይችላል ። ከዚያ በኋላ የ89 ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ ለሰባተኛ የሥልጣን ዘመን በፕሬዝዳንት መቀጠል አለመቀጠላቸው አለያም የ61 ዓመቱ ሞርገን ቻንጋራይ ሥልጣኑን መረከባቸው ይለይለታል ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic