ዚምባብዌ ምዕራባውያን ታዛቢዎችን ላለማስገባት መወሰኗ | አፍሪቃ | DW | 10.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዚምባብዌ ምዕራባውያን ታዛቢዎችን ላለማስገባት መወሰኗ

በዚምባብዌ ሕገ መንግሥት ላይ በሚቀጥለው ሣምንት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል። ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የሚመሩት የዚምባብዌ መንግሥት ምዕራባውያን ታዛቢ ቡድኖች በአውሮጳውያኑ ዓመታት 2013 አጋማሽ ገደማ የሚደረገውን

default

አጠቃላይ ምርጫ ቀድሞ የሚደረገውን ሕዝበ ውሳኔውን በታዛቢነት እንዲከታተሉ እንደማይፈቅድ አስታውቋል። ለምርጫው የገንዘብ ርዳታ እንዲሰጡት ተስፋ የጣለባቸው ሀገራት ታዛቢዎችን ወደ ሀገሩ እንደማያስገባ ነው መንግሥት ያስታወቀው።

የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሲምባራሼ ሙምቤንጌግዊ ለዶይቸ ቬለ እንዳረጋገጡት፡ ወሳኝ የሚባለውን የሕገ መንግሥታዊውን ሕዝበ ውሳኔ እና አጠቃላዩን ምርጫ ከአፍሪቃ ሀገራት የተውጣጡ ታዛቢዎች እንጂ የአውሮጳ ህብረት እና ምዕራባውያት ሀገራት ሊታዘቡ አይችሉም።
« በዚምባብዌ ላይ ጥላቻ የሌላቸው ሀገራት በምርጫው ወቅት ዚምባብዌ ሊገቡ ይችላሉ። በዚምባብዌ ምርጫ ላይ ከሚሳተፉት ቡድኖች መካከል በአንዱ ላይ ማዕቀብ የጣሉ ወገኖች ገለልተኛ ሊባሉ አይችሉም። በአንዱ ፓርቲ ላይ ማዕቀብ ከጣልክ ገለልተኛነትን ያከትምለታል። ገለልተኛ ካልሆንክ ደግሞ ምርጫ እንድትታዘብ አይፈቀድልህም። »
ምዕራባውያት ሀገራት፡ የአውሮጳ ህብረት እና ዩኤስ አሜሪካን ጨምሮ እአአ በ 2002 ዓም በፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ፡ የሰብዓዊ መብት ረግጠዋል፡ ምርጫም አጭበርብረዋል በሚል ምክንያት፡ ማዕቀብ መጣላቸው ይታወሳል። የምዕራባውያት ሀገራት ታዛቢዎችን ወደሀገሯ እንዲይገቡ እንዳማትፈቅድ ካስታወቀች በኋላ በመዲናይቱ ሀራሬ የሚገኙት የብሪታንያ አምባሳደር ወይዘሮ ዴቦራ ብሮነርት በሰጡት አስተያየት የትኞቹን ታዛቢዎች የመጋበዙ ድርጊት የዚምባብዌ መንግሥት ውሳኔ ብቻ ነው።
« አንድ ሀገር ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን የምትጋብዝበት አሰራር በዓለም የተለመደ ነው። ምርጫውን እንዲታዘቡ የመወሰኑ ድርጊት ምርጫውን የምታካሂደው ሀገር መንግሥትን ብቻ የሚመለከት ነው። የዚምባብዌ መንግሥት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎችን ቢጋብዝ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። የአውሮጳ ህብረት በሚገባ የሠለጠኑ ታዛቢዎችን በመላክ ጥሩ ስም አትርፎዋል። »

Simbabwe: Robert Mugabe und Morgan Tsvangirai Flash-Galerie


ማክዶናልድ ሌዋኒካ በዚምባብዌ የቀውስ ጉዳዮች ተመልካች ጥምረት ኃላፊ ናቸው። ይኸው መፍቀሬ ዴሞክራሲ ቡድን በዚምባብዌ የሰብዓዊ መብት ረገጣን መርምሮ ሰነድ አዘጋጅቶዋል። ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ ወደ ዚምባብዌ የሚገቡትን የምርጫ ታዛቢዎች ራሳቸው ለመምረጥ ስለወሰኑበት ድርጊት ቀጣዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
« ምርጫዎች ተዓማኒነት ሊያገኙ የሚችሉት ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ ታዛቢዎች ምርጫዎቹ በነፃና በትክክለኛ መንገድ መካሄዳቸውን ሲያረጋግጡ ነው። ስለዚህ የዚምባብዌ መንግሥት ባለሥልጣናት አሁን የውጭ ታዛቢዎች አንፈልግም ብለው ሲናገሩ መስማታችን አሳሳቢ ሆኖ አግኝተነዋል። እና ይህ ዓይነቱ አሰራር የውጭ ታዛቢዎች እንዲያጋልጡበት የማይፈልገውን ጉዳይ ለመደባበቅ የሚሻ መንግሥት የሚከተለው የተለመደ አሰራር ነው። »

እአአ በ2002 ዓም ዚምባብዌ የአውሮጳ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ፒየር ሾሪን ቪዛ ከከለከለች በኋላ፡ የአውሮጷ ህብረት እና ሌሎች በርካታ ምዕራባውያት ሀገራት በዚምባብዌ ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ እና በተመረጡ ታማኝ ባለሥልጣኖቻቸው ላይ ማዕቀብ መጣላቸው የሚታወስ ነው። እርግጥ፡ ህብረቱ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ማዕቀቡን ቀስ በቀስ አላልቶዋል። እንዲያውም፡ በምባብዌ የሚካሄደው ምርጫ ተዓማኒነት ከተረጋገጠ ህብረቱ በፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤና በባለሥልጣኖቻቸው ላይ የጣለውን የጉዞ እና የንብረት ዝውውር ዕገዳን በጠቅላላ ሊሰርዝ እንደሚችል ህብረቱ ከአንድ ወር በፊት አስታውቋል። ከጥቂት ጊዜ በፊት ዚምባብዌን የጎበኙት የስዊድን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ሚንስትር ጉኒላ ካርልሶን የአውሮጳ ህብረት ስለዚምባብዌ የወደፊት የፖለቲካ ሂደት ብሩሕ አመለካከት እንዳለው ገልጸዋል።
« የዚምባብዌ ዜጎች ድምፃቸውን በሚሰጡበት ሕገ መንግሥት ረቂቅ ላይ ሀሳብ ማቅረብ በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን። በሀገሪቱ ምርጫ የሚደረግበትን መንገድ የሚያመቻች የራሳቸው ሕገ መንግሥት ነው። የብሔራዊ አንድነቱ መንግሥት ዓላማም ይኸው ነበር። እርግጥ፡ ይህ ሂደት ጥቂት ዓመታት ወስዶዋል። ዋናው ግን፡ እምንፈልገው ደረጃ ላይ መድረሳችን ነው። እና አሁን ምርጫው ካላንዳች ሁከት ዓለም አቀፉን መለኪያ በተከተለ መንገድ እንዲካሄድ በጉጉት እየጠበቅን እንገኛለን። ነፃ እና ትክክለኛ ምርጫ እንዲካሄድ ነው ፍላጎታችን። »

አርያም ተክሌ

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic