ዚምባቡዌ የሳዴክ ጉባኤና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ | አፍሪቃ | DW | 14.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዚምባቡዌ የሳዴክ ጉባኤና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ

Human Rights Watch ባወጣዉ መግለጫዉ እንዳለዉ የዚምባቡዌ መንግሥት በዜጎቹ ላይ የሚፈፅመዉ የሰብአዊ መብት ረገጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነዉ

ፕሬዝዳት ሙጋቤ

ፕሬዝዳት ሙጋቤ

ሰሞኑን ሉሳካ-ዛምቢያ የሚሰየመዉ የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ (SADC) አባል ሐገራት የመሪዎች ጉባኤ በዚምባቡዌ የሚታየዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲያስቆም አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጠየቀ።ርዕሠ-መንበሩን ኒዮርክ ያደረገዉ Human Rights Watch ባወጣዉ መግለጫዉ እንዳለዉ የዚምባቡዌ መንግሥት በዜጎቹ ላይ የሚፈፅመዉ የሰብአዊ መብት ረገጣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነዉ።ድርጅቱ እንደሚለዉ የSADC አባል ሐገራት መሪዎች በዚምባቡዌ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ ካላሳረፉ ችግሩ የአካባቢዉን ሐገራት በሙሉ ማስጋቱ አይቀርም።ነጋሽ መሐመድ ዝሩ ዝሩን አጠናቅሮታል።

ዚምባቡዌ በአባልነት የምትወከልበት የደቡባዊ አፍሪቃ የልማት ማሕበረሰብ የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ሐሙስና አርብ-ሉሳካ ዛምቢያ ዉስጥ ይደረጋል።ጉባኤዉ ከሚነጋገርባቸዉ አበይት ርዕሶች አንዱ የዚምባቡዌ ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚሆን የጉባኤዉ አስተናጋጆች አስታዉቀዋል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት Human Rights Watch የዚምባቡዌ ወቅታዊ ሁኔታ የሚለዉን ዲፕሎማሲያዊ ሐገረግ መጠቀሙን አይፈልግም።እንደ መብት ተሟጋች ድርጅት የዚምባቡዌ የሰብአዊ ድቀት ማለቱን ነዉ-የመረጠዉ።

ድርጅቱ የፕሬዝዳት ሮበርት ሙጋቤ መንግሥት ይፈፅመዋል የሚለዉን ይሕን የሰብአዊ መብት ረገጣ ወይም ድቀት ለማቃለል የሳዴክ አባል ሐገራት መሪዎች በሙጋቤ ላይ ተፅኖ ማሳራፍ አለባቸዉ ባይ ነዉ።የዚምባቡዌ መንግሥት በሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉን በደል እንዲያቆም የሳዳኬ መሪዎች ሁነኛ እርምጃ ካልወሰዱ የሑማን ራይትስ ወች ተወካይ ላንስ ላቲግ እንደሚሉት ሰብአዊ ድቀቱ ከዚምባቡዌ አልፎ የአካባቢዉን መረጋጋት ማወኩ አይቀርም።


«የተቃዋሚ ደጋፊዎች ተደርገዉ የሚታዩ ሰዎች እንዴት እንደሚንገላቱ፣ እንደሚታሰሩ፤ እንደሚገረፉ የሚያሳይ መረጃ አለን።ከዚሑ ጋር ከፍተኛ የሆነ የምጣኔ ሐብት ችግር አለ።በዚሕም ምክንያት ብዙ ወደ ሰወስት ሚሊዮን የሚገመት የዚምባቡዌ ዜጋ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ሸሽቷል።ይሕም በመሆኑ የዚምባቡዌዉ የሠብአዊ መብት ቀዉስ የአካባቢዉን መረጋጋት ለአደጋ እያጋለጠዉ ነዉ።»

ባለፈዉ መጋቢት ዳሬ ኤስ ሰላም-ታንዛኒያ ላይ ተሰይሞ የነበረዉ የሳዴክ አባል ሐገራት ልዩ የመሪዎች ጉባኤ የደቡብ አፍሪቃዉ ፕሬዝዳት ታቦ ኢምቤክ የዚምባቡዌ መንግሥትና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዲሸመግሉ መርጧቸዉ ነበር።ፕሬዝዳት ኢምቤኪ ሽምግልናቸዉ ያፈራዉን ዉጤት ሐሙስ ለሚጀመረዉ ጉባኤ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።ላቲግ እንደሚሉት ድርጅታቸዉ የሰብአዊ መብት መጠበቅ የድርድሩ አብይ ትኩረት መሆን አለበት ብሎ ያምናል።

«ድርድሩ ፖለቲካዊዉን ዉጥረት ከማርገቡ ደረጃ የደረሰ ይሆናል የሚል ተስፋ አለን።ይሑንና አስፈላጊ የሚሆነዉ የሰብአዊ መብት መጠበቅ ጉዳይ ነዉ።እኛም ኢምቤክንም እና ሌሎች መሪዎችን የምንጠይቀዉ በድርድሩ ሒደት ሠብአዊ መብት ማስከበርን ማዕከላዊ ርዕሳቸዉ እንዲያደርጉት ነዉ።»

አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የዚምባቡዌ መንግሥት በዜጎቹ ላይ ይፈፅመዋል ያለዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚከታተል ቡድን የሳዴክ አባል ሐገራት ወደ ዚምባቡዌ እንዲልኩም ጠይቋል።የሳዴክ አባል ሐገራት እስካሁን ድረስ በዚምባቡዌ መንሥት ላይ ሁነኛ እርምጃ አለመወስዳቸዉ ችግሩን እንዳባባሰዉም የድርጅቱ ባልደረባ ጠቅሰዋል።

«ባለፉት ጊዚያት የሳዴክ መሪዎች ዚምባቡዌ ሥላለዉ ቀዉስ የነበራቸዉ መርሕ በጣም ደካማ ነበር።አሁን ግን ችግሩ እየከፋ በመምጣቱ ጠንካራ እርምጃ መዉሰድ አለባቸዉ።»


የመብት ተሟጋቹ ድርጅት እንደሚያምነዉ የዚምባቡዌዉ ምጣኔ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ዉጥረት የሚቃለለዉ በሐገሪቱ የሚፈፀመዉ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሲቃለል ብቻ ነዉ።

ተዛማጅ ዘገባዎች