ዙማ የገጠማቸው ተቃውሞ | አፍሪቃ | DW | 11.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዙማ የገጠማቸው ተቃውሞ

ለቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት እና ዋነኛው የፀረአፓርታይድ ታጋይ ለኔልሰን ማንዴላ ትናንት በጆሀንስበርግ በሶዌቶ በሚገኝ ስቴድዮም ይፋ ስንብት በተደረገበት ጊዜ ከመላው ደቡብ አፍሪቃ የመጣው ሕዝብ

በዚያ ለተገኙት ከሰባ የሚበልጡ የዓለም መሪዎች ደማቅ አቀባበል ሲያደርግ የራሱን ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ግን በማንጓጠጥ ጩኽት ነበር የተቀበለው። ሕዝቡ ፕሬዚደንቱን በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲህ ያሳፈረበት ርምጃው በሙስና የሚወቀሱት ዙማ እና የአፍሪቃውያን ብሔረተኞች ኮንግረስ፣ በምሕፃሩ የኤ ኤን ሲ አመራር የሚገኙበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ጠቋሚ መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።

የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ባለፈው ሀሙስ ከዚህ ዓለም በ95 ዓመታቸው በሞት ለተለዩት ለተወዳጁ መሪ እና ፀረ አፓርታይድ ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ ትናንት በጆሀንስበርግ የሶዌቶ ስቴድየም በተደረገው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ለማሰማት ወደ መድረክ በወጡበት ጊዜ የተሰበሰበው የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ በጩኸት የተቀበለበት ድርጊት የሥነ ሥርዓቱን መንፈሥ አበላሽቶዋል በሚል ብዙዎችን ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

ዙማ የማንዴላን ሕያው ስራ ለማወደስ እና ቤተሰቦቻቸውንም ለማፅናናት ገና ንግግራቸውን ሲጀምሩ ከተሰብሳቢዎቹ ደቡብ አፍሪቃውያን ከፍትኛ ጩኸት በመሰማቱ ንግግራቸውን ላጭር ጊዜ እንዲያቋርጡ በማስገደድ፣ ከዚያም አልፎ ዙማ መድረኩን ተተው እንዲወርዱም በእግር ኳስ ጨዋታ ጊዜ አንድ ተጫዋች ለመቀየር ሲፈለግ እንደሚደረገው በእጅ ምልክት በማሳየት ፕሬዚደንቱን አዋርደዋል። ብዙው የደቡብ አፍሪቃ ሕዝብ እና የማንዴላ ውርስ በተገቢው መንገድ ማሰፈፀም የሚገባው ኤ ኤን ሲን እና ፕሬዚደንት ዙማን በሙስና እና በአስተዳደር ብልሹነት አዘውትሮ ይወቅሳል። ይህን ርምጃው ያልጠበቁት እንደነበር እና በፓርቲው ውስጥ ያለው ሥነ ሥርዓት መእየተበላሸ መምጣቱን እንደሚያሳይ በጆሀንስበርግ የዊትዎተርስታንድ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ክፍል መሪ ፕሮፌሰር ዳርል ግሌዘር ገልጸዋል።

« በርምጃው እኔ ብቻ ሳልሆን የደቡብ አፍሪቃን ፖለቲካ የሚከታተል ሁሉ ተገርሞዋል።እርግጥ፣ ይህ በተለይ እአአ ከ2005 ዓም ወዲህ ኤ ኤን ሲ የአንጃ ፍትጊያውን የሚያካሂድበት አንዱ የተለመደ እና በግልጽ እና ይፋ መንገድ ነው። ግን፣ በጣም የሚያስገርመው ዙማን ማንጓጠጡ ለማንዴላ በታሰበው ስንብት ላይ መሆኑ እና ዓለም አቀፍ እንግዶች በተገኙበት መፈፀሙ ነው። »

ይህ የሕዝቡ ርምጃ የሕዝቡ ቅሬታ ምን ያህል ከፍተኛ መሆኑን ያሳየ እና በቀጣዩ ምርጫም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል የሚጠቁም ፕሮፌሰር ዳርል ግሌዘር ሀልጸዋል። ግሌዘር እንደሚሉት፣ የአፓርታይድ ሥርዓት ከተገረሰሰ ዛሬ ከሀያ ዓመታት በኋላም በሀገሪቱ ወንጀል እንደተስፋፋ እና የሕዝቡ መሠረታዊ ኤኮኖሚያዊ ፍላጎት ገና እንዳልተሟላ ነው ሕዝቡ በቅሬታ የሚናገረው።

« ቅሬታ መኖሩ ግልጽ ነው፣ ምንም እንኳን በስቴድየም የተደመጠው ማንጓጠጥ እንደጠቆመው የተጋነነ ባይሆንም። እንደሚታወቀው ኤ ኤን ሲ እአአ ከ1994 ዓም ወዲህ ምርጫዎችን በተከታታይ አሸንፎዋል። እአአ ሚያዝያ 2014 ዓም ይደረጋል በሚባለው ምርጫ ማሸነፉ አይቀርም። ጥያቄው አሁን በምክር ቤት ከያዘው መ,ቀመጫ ብዙውን ያጣል የሚሰኘው ነው። »

በአሁኑ ጊዜ በሀገሪቱ አንዳንድ የጥቁር ደቡብ አፍሪቃውያን ቡድኖችን የሚስቡ ከኤ ኤን ሲ ቀኝ እና ግራ የሆኑ ጥቁሮች መሪዎች ያሉዋቸው የሚታመኑ የተለያዩ ፓርቲዎች አሉ። በዚህም የተነሳ ኤኤንሲ ስጋት አድሮበታል። እና ይህ ሲታሰብ የትናንቱ ይፋ ማንጓጠጥ ትልቅ ትርጉም አለው። ግሌዘር እንዳስረዱትም፣ ዙማ በተለይ ጆሀንስበርግን በሚያጠቃልለው በጋውቴንግ ግዛት ከራሱ ከዜዜንሲ ሳይቀር ግዙፍ ተቃውሞ ገጥሞአቸዋል። ይህ በመሆኑም፣ የትናንቱ ይፋ ስንብት ሥነ ሥርዓት በሌላ ለምሳሌ በክዋዙሉ ናታል ቢሆን ኖሮ የተደረገው ተመሳሳይ ተቃውሞ ላይገጥማቸው ይችል እንደነበር ግሌዘር በማመልከት፣ መሠረታዊው ችግር የትናንቱን ሁኔታ ከአካባቢያዊ እና ብሔራዊ ፖለቲካ ነጥሎ ማየትእንደሚሆን አስታውቀዋል።

አርያም ተክሌ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic