ዘግናኝ የጅምላ ግድያ በአንድ የጀርመን ትምህርት ቤት | ዓለም | DW | 12.03.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዘግናኝ የጅምላ ግድያ በአንድ የጀርመን ትምህርት ቤት

በአንድ የደቡብ ምዕራብ ጀርመን ትንሽ ከተማ ትናንት የተፈጸመው አሰቃቂው ደም የተንጣለለበት ተግባር መላ ጀርመንን እንደገና አስደንግጦዋል።

default

አንድ የአስራ ሰባት ዓመት ተማሪ በሽቱትጋርት ከተማ አቅራቢያ ባለችው የቪኔንደን ከተማ ዘጠኝ ተማሪዎች፡ ሶስት ሴቶች መምህራንና ሌሎች ሶስት ሰዎችን፡ ባጠቃላይ አስራ አምስት ሰዎችን ገድሎ በመጨረሻ የራሱን ህይወት አጥፍቶዋል።

በፖሊስና በዓቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ባወጣው ዘገባ መሰረት፡ ጥቁር በጥቁር የለበሰው ታጣቂው ቲም ክሬችሜር ትናንት በሀገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ ሶስት ሰዓት ተኩል ወደ ሰላሳ ሺህ ህዝብ በሚኖርባት በቪኔንደን ከተማ ወደሚገኘው የአልበርትቪል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከሄደ በኋላ ወደ ሁለት መማሪያ ክፍሎች በመግባት ተኩስ ከፍቶ በአስራ አራት እና አስራ አምስት ዓመት መካከል የነበሩ ስምንት ሴቶችና አንድ ወንድ ተማሪዎችን፡ እንዲሁም፡ ሶስት ሴቶች መምህራንን ገድሎዋል። ሶስት ሰዓት ገደማ በዘለቀው የሽሽት ሙከራው ታጣቂው በመንገዱ ያጋጠሙትን ሌሎች ሶስት ሰዎችንንም ህይወት ከማጥፋቱ ሌላ በበርካታ ተማሪዎችንና መንገደኞች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ አድርሶዋል። ከቪኔንደን ከተማ አርባ ኪሎሜትር ርቆ በምትገኘው የቬንድሊንገን ከተማ ሲደርስ፦ ቀደም ሲል እንደተሰማው በፖሊስ ጥይት ሳይሆን፦ ራሱ ህይወቱን ማጥፋቱን የፖሊስ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አስታውቃለች።

የጅምላው ርሸና ተግባር ካበቃ ከብዙ ሰዓታትም በኋላም ወላጆች እና ቤተ ዘመዶች ልጆቻቸው እና ዘመዶቻቸው ከሟቾቹ መካከል ይሁኑ አይሁኑ እንዳላወቁ ነው የተገለጸው። እስከ ትናንት ማታ ድረስ የሽቱትጋርት ፖሊስ ጽህፈት ቤት ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ጥያቄዎች እንደቀረቡለት አስታውቋል። እርግጥ አሁን የግድያው ሰላባዎች ማንንነት ቢታወቅም፡ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡት በተለይ ግድያው ከተፈጸመበት ቦታ ርቀው ከሚኖሩ ቤተ ዘመዶች ነው፤ በፖሊስ ዘገባ መሰረት። ያካባቢው መስተዳድር የባህል ሚንስቴር ሄልሙት ራው ግድያውን በአንድ ትምህርት ቤት የደረሰ ትልቅ መቅሰፍት ነው ብለውታል። የባድን ቭርትምበርግ ጠቅኣል ሚንስትር ጊውንተር ኧቲንገር ደግሞ ከግድያው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በግድያው የተሰማቸውን ቁጣ እንዲህ ነበር የገለጹት።

« ባድን ቭርትምበርግ በዚህ ምክንያቱን ለማወቅ በማይቻለው ዘግናኝ ተግባር እጅግ ተነክቶዋል። በቪኔንደንና በቬንድሊንገን የተፈጸመው የጅምላ ግድያ፡ እኔ እስካሁን በሀገራችን አይቼው የማላውቀው ዓይነት፡ በኤርፉርት ከተፈጸመው ግድያ ጋር ብቻ ሊወዳደር የሚችል ተግባር ነው። »

እንደሚታወሰው፡ ከሰባት ዓመታት በፊት በኤርፉርት በተካሄደው የጅምላ ግድያ አስራ ሰባት ሰዎች ነበር የተገደሉት። ኧቲንገር በመላ ባድንቭርትምበርግ ባንዴራው ዝቅ ብሎ በግማሽ ሰንደቅ ላይ እንዲውለብለብ አዘዋል። የጀርመን ርዕሰ ብሄር ለግድያው ሰለባዎች ቤተሰቦ ሀዘናቸውን በመግለጽ ገልጸዋል። በአውሮጳ ምክር ቤትም እንደራሴዎቹ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት አድርገዋል። ድርጊቱ እጅግ ያሳዘናቸው መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ደግሞ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ያን ያህል ተማሪና መምህራን የተገደሉበትን ድርጊት ለመረዳት በጣም የሚያዳግት መሆኑን በማስታወቅ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

« ዕለቱ ለመላ ጀመርመን የሀዘን ቀን ነው። ሀሳባችን ከሰለባዎቹ ቤተሰቦቹ ጋር ነው፡ በሀሳብ ከነርሱ ጋር ነን። በጸሎታችንም እናስባቸዋለን። »

የአስራ ስድስት ሰዎች ህይወታ ያጠፋው የጅምላው ግድያ ያስከተለው ጉዳት በጠቅላላ እስካሁን ገና በውል አልታወቀም። ታጣቂው ግድያውን በፈጸመበት ጊዜ በጎረቤት መማሪያ ክፍል ትገኝ የነበረችው ተማሪ ሳራ ስለሁኔታው ስትናገር፡

« መጀመሪያ ስሉኔታው የሰማሁት ከአንዲት የትምህርት ቤቱ ጸሀፊ ነበር፤ ከዚያ ጥቂት ቆይቶ ሁሉም ተማሪዎች ሰሙ። ትልቁ የዕረፍ ት ጊዜ ሲደርስ ከክፍላችን ከወጣን በኋላ ሁላችንን በመዋኛው ቦታ ሰበሰቡን። ከዚያ ቀስ በቀስ ስለተፈጸመው ግድያ እና ማን እንደሞተ ሰማን። »

ታጣቂው ዘጠኙን ተማሪዎችና ሶስት ሴቶች መምህራንን፡ እንዲሁም ሲሸሽ በነበረበት ጊዜ ሌሎች ሰዎችን የገደለበት ዘግናኙ ተግባሩ ከማብቃቱ በፊት ከፖሊስ ጋር የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የባድን ቭርትምበርግ ሀገር አስተዳደር ሚንስት ሀርበርት ሬኽ ገልጸዋል።

« በተኩስ ልውውጡ ወቅት ሁለት ፖሊሶች በጠና ሲቆስሉ፡ ሁለት ባካባቢው የነበሩ ሰዎች ተገድለዋል። በዚሁ ጊዜም ታጣቂው ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ተመቶ ከቆሰለ በኋላ ህይወቱን አጥቶዋል። »

ብለው ነበር። አሁን ግን ፖሊስ ይህንኑ የሀገር አስተዳደሩን ንግግር በማስተካከል ታጣቂው ራሱን እንደገደለ አስታውቋል። የፖሊስ ዘገባ እንዳመለከተው፡ የታጣቂው ወላጅ አባት የአንድ ዒላማ ተኳሾች ማህበር አባል ስለሆኑ በህግ ፈቃድ ያላቸው የጦር መሳሪያ በቤታቸው አላቸው። የባህል ሚንስትር ሄልሙት ራው እንዳስረዱት፡ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ የነበረው ታጣቂ እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ተግባር ይፈጽማል የሚያሰኝ አካሄድ በፍጹም አልታየበትም ነበር።

« የትምህርት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ እንዳረጋገጡልኝ፡ ታጣቂው ተማሪ የተለየ ባህርይ ያልታየበት ተማሪ ነበር። ባለፈው ዓመት የአስርኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን አጣናቆ የሙያ ስልጣና ትምህርት ጀምሮ ነበር። »

የትናንቱን የአስራ አምስት ሰዎችና የራሱን ህይወት ያጠፋበትን ደም ያንጣለለ ተግባሩን እንዲያካሂድ የገፋፋው ምክንያት እስካሁን በውል አልታወቀም።

Heineken, Ralf/Abraha, Aryam

Negash Mohammed