ዘርፈ ብዙው የፊዚክስ ምሁር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 03.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ዘርፈ ብዙው የፊዚክስ ምሁር

ባለፈው ሳምንት በድንገት ያረፉት ዶ/ር ለገሠ ወትሮ በበርካታ አስተዋጿቸዉ ይታወሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ብዙዎችን አስተምረው ለወግ ማዕረግ አብቅተዋል፡፡ በተጓዳኝ ያደርጓቸው የነበሩ ጥናቶች በምርምር ጆርናሎች ላይ ታትመውላቸዋል፡፡ በብዙሃኑ ዘንድ እንዲታወቁ ያደረጋቸው ግን ለዓመታት በሬድዮ ያስተላልፉት በነበረዉ ዝግጅት ነዉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:00

በተወዳጅ የሬድዮ ዝግጅታቸው ይታወቃሉ

ግንቦት 27 ቀን 1992 ዓ.ም ስርጭቱን አሃዱ ያለው ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 በኢትዮጵያ የሬድዮ ታሪክ አዳዲስ አቀራረቦችን እና ዝግጅቶችን ያስተዋወቀ ነበር፡፡ ያኔ በቀን ለ18 ሰዓታት አድማጭ ዘንድ ይደርስ የነበረው የጣቢያው ስርጭት በ125 ኪሎ ሜትር ርቀት ክልል ዉስጥ ላሉ የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ነዋሪዎች የታሰበ ነበር፡፡ ለጣቢያው ጋዜጠኞች ግርታ ይፈጥርባቸው የነበረው ግን ከሐረር እስከ ባሌ፣ ከአርሲ እስከ ደቡብ አካባቢዎች ይመጡ የነበሩ የስልክ አስተያየቶች ናቸው፤ “እንዴት ሊያዳምጡ ቻሉ?” በሚል፡፡

አድማጮቹ የጣቢያውን ዝግጅቶች ለማድመጥ ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ መላ ዘይደዋል፡፡ ዘዴው አንቴናዎችን ከጣሪያ በላይ መስቀልን ይጠይቃል፡፡ በትግራይ ክልል አዲግራት አቅራቢያ ተወልዶ ያደገው አቤል በላይ በዚህ ስልት የሬድዮ ስርጭቱን ከሚያደምጡት መካከል አንዱ ነበር፡፡ በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የነበረው አቤል ከዝግጅቶቹ መካከል ቀልቡን ያሸፍተው የነበረው በዶ/ር ለገሠ ወትሮ ተዘጋጅቶ ይቀርብ የነበረው የ“ህዋ ሳይንስ” የተሰኘው መሰናዶ ነበር፡፡ ለዝግጅቱ ከነበረው ውዴታ የተነሳ የሚነገረውን በቅጡ ለመረዳት ቤተሰቦቹን እና የአካባቢውን ሰዎች እስከማስቸገር ድረስ ይሄዳል፡፡ ስለ አዘጋጁ ዶ/ር ለገሠ ይህን ይላል፡፡  

“በሬድዮ ዝግጅታቸውን ሲያስተላልፉ ያንን እከታተል ነበር፡፡ ያ ቅዳሜ የነበረው ዝግጅት ካመለጠኝ ሰዎች እጠይቅ ነበር፡፡ ይነግሩኛል ምን ምን እንደተባለ፡፡ ብዙ አማርኛ አልችልም ነበር፡፡ መናገርም አልችልም፡፡ ነገር ግን የሚያወሩትን ነገር እሰማለሁ፡፡ እና አባታችንም የሚያወሩትን ነገር ይተረጉምልናል፡፡ ቀለል አድርገው ስለሚያስተላልፉ በጣም ተጽእኖ ፈጣሪ ነበሩ።“ ሲል በአዳጊነት ዕድሜው ያደምጠው የነበረው የሬድዮ ዝግጅት የፈጠረበትን ይተርካል፡፡ 

የዶ/ር ለገሠ ትንታኔታዎች ከልቡ የገባው አቤል ጥሩ ውጤት አስመዘግቦ በደብረማረቆስ ዩኒቨርስቲ ሲመደብ ያለምንም ማወላዳት ለማጥናት የመረጠው ፊዚክስን ነበር፡፡ ሁለተኛ ዲግሪውን ለመማር ለአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲያመለክትም ዶ/ር ለገሠ ትኩረት ያደረጉበትን አስትሮፊዚክስ የጥናት መስክ ተከትሎ ነው፡፡ ዶ/ር ለገሠ የህዋ ሳይንስ እና ፊዚክስን የሚያጣምረውን አስትሮፊዚክስ በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ በቀዳሚነት ከተማሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን አንዱ ነበሩ፡፡ እስከ ድንገተኛ ሞታቸው ድረስም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ሲያስተምሩ የቆዩትም ይህንኑ ነው፡፡ 

አሁንም ድረስ በአስተሮፊዚክስ ዘርፍ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አናሳ ነው፡፡ የሴቶቹ ቁጥርማ እዚህ ግባ አይባልም፡፡ ዶ/ር ለገሠ ከወራት በፊት ምክንያቱን ለዶይቸ ቨለ እንዲህ አስረድተው ነበር፡፡ 

“በኢትዮጵያ ውስጥ በአስትሮፊዚክስ የሴቶቹ ተሳትፎ ያን ያህል ጎልቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ግንባር ቀደም ሆነው የሰሩ በጣም ጥቂት ሴቶች ልጆች አሉ፡፡ በተረፈ ግን በአስትሮፊዚክስ የገፉ ሌሎች የሉም፡፡ ምክንያቱም አስትሮፊዚክስ ትንሽ ከበድ የሚል የትምህርት ክፍል ስለሆነ ነው፡፡”

ዶ/ር ለገሠ ግማሽ ክፍለ ዘመን ግድም በዚሁ የትምህርት መስክ ቢቆዩም ወደ ፊዚክስ ዓለም የመጡት ግን በአጋጣሚ ነው፡፡ በቀድሞ አጠራሩ አርሲ ክፍለ ሀገር ስሬ ወረዳ በ1942 ዓ.ም የተወለዱት ዶ/ር ለገሠ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአሰላ ከተማ ነበር፡፡ በወቅቱ በሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ቆይታቸው ጥሩ ውጤት ያስመዘግቡ የነበሩ ወጣቶች ከመላው ኢትዮጵያ የሚሰባሰቡበት የዩኒቨርስቲ መሰናጃ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ “ላብ ስኩል” በሚል መጠሪያ በሚታወቀው በዚህ ትምህርት ቤት የተማሩት ዶ/ር ለገሠ ለተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ውዴታ እንደነበራቸው በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ተናግረዋል፡፡ 

ለሂሳብ እና ተዛማጅ ትምህርቶች ልዩ ፍቅር የነበራቸው ዶ/ር ለገሠ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ በአራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መመደባቸው እምብዛም አላስገረመም፡፡ በዩኒቨርስቲው የመጀመሪያ ዓመት ቆይታቸው ወደፊት የሚያጠኑትን የትምህርት ዘርፍ ለመወሰን ሲዘጋጁ “ይበልጡኑ ይፈትነኛል” ያሉትን ፊዚክስን መረጡ፡፡ ከዓመታት በፊት ለ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ምክንያታቸውን አስረድተዉ ነበር፡፡    

“ፊዘክስን ማጥናት የሆነ አይነት ጀብድ አለው፡፡ አንድን የትምህርት ዘርፍ ከማጥናትም በላይ ነው፡፡ የትምህርት ክፍሉን ተቀላቅለው ነገር ግን መመረቅ ስላልቻሉ ተማሪዎች እንሰማ ነበር፡፡ ያ በጣም የሚስብ ነበር፡፡ ራሴን ከምርጥ እና በጣም ፈታኝ በሆነው የትምህርት መስክ መፈተን ፈለግኩ፡፡”

ዶ/ር ለገሠ የራሳቸውን ፈተና በአጥጋቢ ሁኔታ ተወጥተው በ1964 ዓ.ም ተመረቁ፡፡ ወዲያውኑ በአዲስ አበባ የንፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኑ፡፡ እምብዛም ሳይቆዩ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመልሰው አሁንም በፊዚክስ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያዙ፡፡ ከሁለት ዓመት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመምህርነት ቆይታ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ባህር ማዶ ተሻገሩ፡፡ በብሪታንያ ሼፌልድ ዩኒቨርስቲ በድጋሚ በፊዚክስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ጫኑ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በዚያው ዩኒቨርስቲ የመቀጠል ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ከአማካሪያቸው ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ሀሳባቸው ተጨናገፈ፡፡ 

በሌላ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ጥናታቸውን ለመሥራት ተቀባይነት ቢያገኙም የላካቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሼፌልድ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አሊያም ወደሀገራቸው እንዲመለሱ አዘዛቸው፡፡ ትዕዛዙን አሻፈረኝ ያሉት ዶ/ር ለገሠ ጓደኞቻቸው ካሉበት አሜሪካ ተጓዙ፡፡ በእዚያም በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ በአስትሮፊዚክስ ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ በአሜሪካ ቆይተው የጀመሩትን ምርምር መቀጠል ያልቻሉት ዶ/ር ለገሠ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ግድ አላቸው፡፡ 

በእናት ዩኒቨርስቲያቸው በማስተማር እና በጥናት ተጠምደው ባለበት ያላሰቡት ዕድል ከደጃፋቸው ከተፍ አለ፡፡ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ሲቋቋም ከጀመራቸው ፕሮግራሞች አንዱ የሆነው የ“ሳይንስና ቴክኖሎጂ” ዝግጅት አሰናጅ ጋዜጠኛ አስቻለው ሽፈራው ከአድማጮች የሚላኩለትን የህዋ ሳይንስን የተመለከቱ ጥያቄዎች እየያዘ ደጋግሞ ይጎበኛቸው ያዘ፡፡ ቀላል በሆነ የማስረዳት ዘዬ ለጥያቄዎቹ የሚሰጧቸው መልሶች ተጨማሪ ጥያቄዎችን ይወልዱ ጀመር፡፡ የአድማጮች በጎ ምላሽ ሌላ ውጥን ይዞ መጣ፡፡ አስቻለው ያስታውሳል፡፡  

“ይሄን ጉዳይ በተከታታይ እየተወያየንበት ስንሄድ የህዋን ሳይንስ ነገር እንዲህ አልፎ አልፎ በሚነሳ ዝግጅት ወይም በአጋጣሚ ከምናነሳው ለምን በመደበኛነት አንድ ዝግጅት አንሰጠውም የሚል መግባባት ላይ ደረስን፡፡ ከዚያ በኋላ ዝግጅቱ እንዴት ሊሆን ይችላል? አቀራረቡ ምን መምሰል አለበት? የሚለውን ጉዳይ ከእርሳቸው ጋር እዚያው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አራት ኪሎ በተከታታይ ተወያየን፡፡ አንዳንድ ለመነሻ የሚሆኑ ጥንቅሮችን እንዲሁ ከቋንቋው ጀምሮ እያነሳን አዳበርነው፡፡ ጥንቅሩን እርሳቸው ካዘጋጁት በኋላ እንዴት እያዳበርን፣ እያስተካክልን እንሂድ የሚለው ላይ መግባባት ላይ ደረስን፡፡ ከዚያ በኋላ የሬድዮ ዝግጅቱ ተጀመረ፡፡” 

እንዲህ አሃዱ ያለው ዝግጅት ለረጅም ጊዜ ቀረጻው የሚደረገው በአዲስ አበባ የኒቨርስቲ አራት ኪሎ በሚገኘው የዶ/ር ለገሠ ቢሮ ውስጥ ነበር፡፡ አስቻለው በመቅረጸ ድምጹ ያስቀረውን የዶ/ር ለገሠን ትንታኔ በፈርጅ ፈርጁ እያስተካከለ ለአድማጭ ያደርሳል፡፡ በአዘጋጅነት እና በምክትል አዘጋጅነት የቆየው የሁለቱ ጥምረት ለስድስት ዓመታት ያህል ዘልቋል፡፡ የአዲግራቱን አቤልን ጨምሮ ብዙ ተከታታዮች የነበሩት ዝግጅት በኢትዮጵያ ለህዋ ሳይንስ አስተዋፅኦዉ ከፍ ያለ እንደነበር አስቻለው ይናገራል፡፡ 

Hauptcampus der Universität Addis Abeba AAU

“ይሄ የሬድዮ ፕሮግራም ብዙ ተወዳጅ እና ብዙ አድማጭ የነበረው ነበረ፡፡ በመደበኛነት ለሳይንስ ፍላጎት ኖሮት ሬድዮ የሚያደምጠው ብቻ ሳይሆን በትላልቅ የመንግሥት ኃላፊዎች ጭምር ዝግጅቱ ተቀባይነት ነበረው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማኅበር እንዲመሰረት ውጥን በቀረበበት ወቅት ጭምር አንዱ መነሻ የነበረው ይሄ የህዋ ሳይንስ ዝግጅት ነበር፡፡”

በእርግጥም በወቅቱ በመንግሥት የኃላፊነት ደረጃ ከነበሩት ውስጥ አቶ ተፈራ ዋልዋ በሳይንሱ መሳብ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ሲሳተፉ ታይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የህዋ ሳይንስ ማኅበረሰብ የተሰኘው ማኅበር ሲመሰረት አቶ ተፈራ የበላይ ጠባቂ እና የቦርድ ሊቀመንበር ሆነዋል፡፡ ዶ/ር ለገሠ ለማህበሩ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን በላይ እንዲህ ያብራራሉ፡፡ 

“የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከእነተፈራ ጋራ ከጥቂት መስራቾች አንዱ ናቸው፡፡ በዚያ ሰዓት በ1996 ዓ.ም ላይ የቦርድ አባል ሆነው ለሶስት ዓመት ያህል በጸሐፊነት ሠርተዋል፡፡ ስለዚህ በዚያን ወቅት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡ አባል በሆኑበት ወቅት ደግሞ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እኔ ተማሪ ሆኜ አብረን ሀሳቦችን እናፈልቅ ነበር፡፡”

ዶ/ር ለገሠ በማህበሩ ቆይታቸው ኢትዮጵያን የህዋ ተመራማሪዎች መናኸሪያ የማድረግ ትልም ነበራቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የጠፈር መመልከቻ ቴሌስኮፖችን በመትከል ኢትዮጵያን በገንዘብም በምርምርም መጥቀም እንደሚቻል ያምኑ ነበር፡፡ ለዚህም ሁሌም በምሳሌነት የሚጠቅሷት የደቡበ አሜሪካዋን ሀገር ቺሊን ነው፡፡ በዓለም ላይ ለስነ-ፈለክ ጥናት ሁነኛ ቦታ ናት የምትባለው ቺሊ 15 የጠፈር ምርምር ጣቢያዎች አሏት፡፡ ኢትዮጵያም በእንጦጦ ተራራ አንድ ለእናቱ የሆነዉን ጣቢያ አቋቋማለች ፡፡ ዶ/ር ለገሠ ተመሳሳይ የምርምር ጣቢያ በላሊበላ አካባቢ ተመስርቶ የማየት ህልም ነበራቸው፡፡ 

አስትሮፊዚስቱ ህልማቸውን እውን ባያደርጉም ርዕያቸው ከተማሪዎቻቸው ዘንድ ቀርቷል፡፡ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ዶ/ር ለገሠን የሚያውቋቸው ዶ/ር ሰለሞን ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ሲሠሩ ተማሪያቸው ነበሩ፡፡ “ምን ዓይነት መምህር ነበሩ?” ለሚለው ምላሽ አላቸው፡፡ “መምህር ሆነው ሲያስተምሩ የድሮ በዕደ ማርያም ተማሪ ስለነበሩ መሰለኝ የትምህርት አቀራረባቸው፣ የማስተማር ስልታቸው፣ ዘዴያቸው ጥሩ ነው፡፡ ሳቢ ናቸው፡፡ ጥሩ አስተማሪ ነበሩ፡፡” 


በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአስትሮፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪ ጥናቱን እያካሄደ የሚገኘው አታክልቲ በላይ የዶ/ር ሰለሞንን ገለጻ ይጋራል፡፡ “ክፍል ውስጥ ሲያስተምሩን በጣም ጎበዝ አስተማሪ ነበሩ፡፡ አንድ ነገር ለመግለጽ ሲፈልጉ በቀላል ዘዴ ነው የሚያስረዱህ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የሂሳብ ችሎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በአጭሩ ነው የሚያስረዱህ ግን ለዚያ የሚጠቀሙበት ሂሳብ ደግሞ በጣም የተራቀቀ ነው፡፡ ከሌሎች መምህራን ለየት የሚያደርጋቸው ይህ ነው፡፡” 

ዶ/ር ለገሠ ከማስተማር ባሻገር የጥናት ሥራዎቻቸውን በታዋቂ የምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ “ጆርናል ኦፍ አስትሮ ፊዚክስ”፣ “ጆርናል ኦፍ አስትሮፊዚክስ ኤንድ ስፔስ ሳይንስ” እንደዚሁም “መንዝሊ ኖቲስ” ይጠቀሳሉ፡፡ የሬድዮ ዝግጅት አቅራቢው፣ መምህሩ፣ ተመራማሪው እና የማኅበር መሥራቹ ዶ/ር ለገሠ ሐሙስ ሚያዝያ 19 በቤታቸው ባሉበት ህይወታቸው አልፎ ተገኝተዋል፡፡ የሶስት ልጆች አባት የነበሩት የዶ/ር ለገሠ የቀብር ስነ ስርዓት በማግስቱ በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡  ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉትን እኚህን ምሁር አብሯቸው የሠራው ጋዜጠኛ አስቻለው እንዲህ ጠቅለል አድርጎ ይገልጻቸዋል፡፡  

“እኔ ከምንም በላይ ከዶ/ር ለገሠ የሚታየኝ ነገር ለሳይንስ የነበረው ፍቅሩና ይሄንንም ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስረጽ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስፋት የሞከረ ነው፡፡ እንደ ሀገርም ደግሞ ያኔ ትንሽ የሚያስገርሙና አስቂኝ የሚመስሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ እንደ ብርቅ ነበር የሚታየው፡፡ ስለ ህዋ ሳይንስ ማውራት እንዲሁ አንዳንዶችም ዋዘኝነት ይመስላቸው ነበር፡፡ ስለ ዳቦ እና ስለ ዕለት ጉርስ እርግጠኛ መሆን ባልተቻለበት ሀገር እንዴት ነው ስለ ህዋ ሳይንስ የሚወራው በሚል የህዋ ሳይንስ እስከ ምን ድረስ ደርሶ በሀገርና በህዝብ ደረጃ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ ያለመገንዘብ፤ እንዲሁ ከሰማይ እና ከምድር ርቆ ከመሄድ ጋር ብቻ የሚያገናኙት ሰዎች ነበሩ፡፡ ግን እዚህ ምድር ላይ በእያንዳንዱ ህይወት ውስጥ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ እና እመርታ ያለመረዳት ነገር ነበር፡፡ ዶ/ር ለገሠ ያንን ነበር ለማሳየት ይሞክር የነበረው፡፡ ይህንንም በታታሪነት፣ በፍቅር እና ባለመድከም አሳይቷል፡፡”      

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ
 
 

Audios and videos on the topic