ዘመን የተሻገረው የቢያፍራ ጥያቄ | አፍሪቃ | DW | 04.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ዘመን የተሻገረው የቢያፍራ ጥያቄ

ባለፈው መስከረም ወር በስፔን የካታሎንያ እና በኢራቅ የኩርዲስታን ግዛቶች ለመገንጠል ያካሄዱት ህዝበ ውሳኔ እና በድምጽ ሰጪዎች ያገኙት ከፍ ያለ ድጋፍ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የሁለቱ ግዛቶች ርምጃ በሌሎች ሀገራት ያሉ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ህዝቦችን ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከል የናይጄሪያዊ ቢያፍራ አንዷናት፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 06:46
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
06:46 ደቂቃ

የቢያፍራ መገንጠል አቀንቃኞች ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ይሻሉ

በነዳጅ ሀብቷ፣ በእውቅ እግር ኳስ ተጫዋቾቿ፣ በዓለም ላይ ስሙ በሚነሳው የፊልም ኢንዱስትሪዋ እና ዝናን እያተረፉ በመጡ ዘፋኞቿ ይበልጥ የምትታወቀው ናይጄሪያ የ180 ሚሊዮን ህዝብ ሀገር ናት፡፡ በአፍሪካ በህዝብ ብዛት ቀዳሚ ቦታውን የምትይዘው ናይጄሪያ በውስጧ የያዘቻቸው 250 ጎሳዎች በአብዛኛው በሰላም ተዋህደው የሚኖሩባት ናት፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው ያልተመጣጠነ ዕድገት እና የመገፋት ስሜት ግን የመገንጠል ጥያቄዎች እዚህም እዚያም ብቅ እንዲሉ እያደረገ ነው፡፡ 

የናይጄሪያ መንግስት በነዳጅ በበለጸገው በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በኒጀር ዴልታ የሚታየውን የመገንጠል እንቅስቃሴ ለመግታት እየጣረ ባለበት ወቅት የተዳፈነ የመሰለው የቢያፍራ የነጻነት ጥያቄ እንደገና ግሟል፡፡ ቢያፍራ በደቡብ ምስራቅ ናይጄሪያ የምትገኝ የኢግቦ ብሔረሰብ መናኸሪያ ነች፡፡ ስሟ ይበልጥ የገነነው የዛሬ 50 ዓመት ግድም ከናይጀሪያ ተነጥላ “ራሴን የቻልኩ ሀገር ነኝ” ብላ በማወጇ ነው፡፡ የቢያፍራ አስተዳዳሪዎች ግዛቲቱን ለማስመለስ ጦርነት ካወጀው የናይጄሪያ ማዕከላዊ መንግስት ጋር ለሶስት ዓመታት ያህል ተዋግተዋል፡፡ ይህ አስከፊ ጦርነት በትንሹ የአንድ ሚሊዮን ህዝብ ህይወትን እንደቀጠፈ ይነገርለታል፡፡ 

የቢያፍራ የመገንጠል እንቅስቃሴ ለበርካታ ዓመታት ቀዝቀዞ ቢቆይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን መነቃቃቶች ታይተውበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁነኛው ምክንያት ናምዲ ካኑ ናቸው፡፡ ካኑ የቢያፍራ ነባር ህዝቦች የተሰኘው መገንጠልን የሚያቀነቅን የፖለቲካ ድርጅት መሪ ናቸው፡፡ ድርጅቱ ነጻ የሆነች የቢያፍራ ሀገርን ለመመስረት የሚያስችል ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ይሻል፡፡ ዓላማውን በህዝብ ለማስረጽ ተቀማጭነቱን በብሪታንያ ለንደን ያደረገ ራዲዮ ጣቢያ እስከ ማቋቋም ተጉዟል፡፡ 

ቢያፍራን የመገንጠል ፍላጎት በተለይ በወጣቱ ዘንድ እያደገ እንደመጣ የተረዳው የናይጄሪያ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ካኑ እና ሌሎች የድርጅት አጋሮቻቸውን ወደ ወህኒ ቤት መክተት ነበር፡፡ የሀገር ክህደት ለመፈጸም ማሴርን ጨምሮ ሌሎችም ክሶች የቀረቡባቸው የድርጅቱ መሪ “ከጤና ጋር በተያያዘ” በሚል ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ከእስር ተለቅቀዋል፡፡ ጉዳያቸው እየተመለከተ የሚገኘው የናይጄሪያ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ካኑን ከማንኛውም የፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቢያግዳቸውም እርሳቸው ግን “በጄ” አላሉም፡፡ 

በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ ነው እንግዲህ ባለፈው መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም መኖሪያ ቤታቸው በናይጄሪያ ወታደሮች መወረሩ የተነገረው፡፡ ካኑ ከዚያን ቀን ወዲህ በህይወት ይኑሩ፣ ይሙቱ እንደው አይታወቅም፡፡ በቤታቸው ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚያስተባብለው የናይጄሪያ መንግስት ካኑ “ተሰውረው ነው” ይላል፡፡ የቢያፍራ ነባር ህዝቦች ድርጅት አባል የሆኑት ኡቼኔ ኦቢዚኬ ግን የድርጅታቸው መሪ ተገድለዋል ብለው ያምናሉ፡፡ ኦቢዚኬ ከካኑ መኖሪያ ቤት መስኮት ፊት ቆመው ባሻገር ያለውን ስፍራ ለዶይቼ ቬለ ዘጋቢ እየጠቆሙ ተከታዩን ነግረውታል፡፡ “እዚያ ጋር ያለው የመንገድ ማካፈያ ይታያሃል፡፡ እዚያ ሆነው መተኮስ የጀመሩት፡፡ የመጡት ሰው ለመግደል ነበር፡፡”

የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ወረራውን ባደረጉበት ዕለት የካኑን መኖሪያ ቤት የሚጠብቁት እርሳቸው እንደነበር የሚናገሩት ኦቢዚኬ በዕለቱ 20 ሰዎች መገደላቸውን ይናገራሉ፡፡ በመኖሪያ ቤቱ ላይ የደረሰውን ጉዳትም ለዶይቼ ቬለ ዘጋቢ እያዟዟሩ አሳይተውታል፡፡ በመኖሪያ ቤቱ አንደኛው ክፍል ውስጥ ቆሞ የነበረ የካኑ አነስተኛ ሀውልት እጁ ተቆርጦ ከመሬት ወድቋል፡፡ በአንደኛው የመስታወት መስኮት ላይ ደግሞ የጥይት ቀዳዳ ይታያል፡፡ የቤት ቁሳቁሶች በወለሉ ላይ ተዝርክርከው ይታያሉ፡፡ የተገንጣይ ድርጅቱ አባላት “ወታደራዊ ዘመቻ” እያሉ በሚጠሩት በዚህ ወረራ ወቅት የተከናወነውን በሞባይላቸው ቀርጸው በማስረጃነት ያቀርባሉ፡፡ 

ከዚያን ዕለት በኋላ የድርጅታቸው መሪ ደብዛው መጥፋቱን ተከትሎ የካኑ ታናሽ ወንድም ራሱን ለመደበቅ ተገድዷል፡፡ የዶይቼ ቬለ ዘጋቢ ወንድምየውን ኢማኑኤል ካኑን ለማግኘት ያልተሳኩ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ካደረገ በኋላ በአንዱ ቀን ዕድል ሰመረለት፡፡ ኢማኑኤል ቃሉን ለመስጠት ተስማማ፡፡ የናይጄሪያ ጦር የወሰደው እርምጃ የቢያፍራ ነባር ህዝቦች ድርጅትን ይበልጥ ቁርጠኛ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ 

“ህዝበ ውሳኔን እንዲካሄድ መጠየቅ ጦርነትን መጋበዝ አይደለም፡፡ እኛ ነጻ ህዝብ መሆን እንፈልጋለን፡፡ ያንን ደግሞ ልናሳካ የምንችለው በህዝበ ውሳኔ ነው፡፡ የእኔ መሪ የሚሉትም ይህንን ነው፡፡ ሌሎችም የሚያምኑት ይህንኑ ነው” ይላል ኢማኑኤል፡፡  

የናይጄሪያ መንግስት የመገንጠል አቀንቃኞችን ፍላጎት አይቀበልም፡፡ በቢያፍራው የእርስ በእርስ ጦርነት ወቅት በመንግስት ወገን በወታደርነት የተሰለፉት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ሙሃሙዱ ቡሃሪ ሶስት ወር ለህክምና ከቆዩበት ብሪታንያ ባለፈው ነሐሴ ሲመለሱ መጀመሪያ ካደረጓቸው ነገሮች መካከል ወደ ቢያፍራ ጦር ማዝመት ነበር፡፡ መንግስታቸው እምብዛም ሳይቆይ የቢያፍራ ነባር ህዝቦች ድርጅትን አሸባሪ ድርጅት ብሎ በይፋ ሰይሟል፡፡ የናይጄሪያ መንግስት ድርጅቱ በተደጋጋሚ የሚጠይቀውን ለመገንጠል የሚደረግ ህዝበ ውሳኔ “ኢ-ሕገመንግስታዊ እና አደገኛ ነው” ባይ ነው፡፡ የሀገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር ኦጉባጎ አኒክዌ በክልሉ የሚገኙ ሁሉም አስተዳዳሪዎች “አቋማቸው ከዚህ ጋር የተስማማ ነው” ይላሉ፡፡ “ለህዝባቸው ያለባቸውን ኃላፊነት በሚገባ ያውቁታል፡፡ ህይወትን ወደማሳጣት የሚያመራ ቅስቀሳን ሊያበረታቱ አይችሉም” ብለዋል አኒክዌ ፡፡  

በህዝቡ ዘንድ ግን ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ፍርሃት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በደቡብ ምስራቅ የሚገኙ ናይጄሪያውያን ለረጅም ጊዜ የመገፋት እና የመገለል ስሜት ቢሰማቸውም በብዙዎች ዘንድ የመገንጠልን ሀሳብ ለሚያቀነቅኑት ድጋፍ የመስጠት አዝማሚያ እንደማይታይ የዶይቸ ቬለ ዘጋቢ ያን ፊልፕ ሾልስ ይናገራል፡፡ ይህ በተለይ የከዚህ ቀደሙን ጦርነትን በቀመሱ ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ 

ጃምቦ ኮሎምበስ የዛሬ ዓመት ገደማ በነበረው ጦርነት በተገንጣዮቹ ዘንድ ተሰልፈው ተዋግተዋል፡፡ አሁንም ቢሆን ከቀድሞ ጓዶቻቸው ጋር ሰብሰብ እያሉ ስለ ወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ ማውራታቸውን አልተውም፡፡ የቀድሞዎቹ ተዋጊዎች ህዝበ ውሳኔን ቸኮሎ ማካሄድ የሚፈጥረው አደጋ ያሳስባቸዋል፡፡ እንደ የስፔኗ ካታሎን ያሉ በሌላው የዓለም ክፍል ያሉ ህዝቦች የተገበሯቸውን ተመሳሳይ አካሄዶችንም ይከታተላሉ፡፡ “ናይጄሪያ ከስፔን ልትማረው የምትችለው ነገር ህዝበ ውሳኔ ሊቆም እንደሚችል ነው፡፡ የድምጽ መስጠቱ ሊቆም እና ሊሻር እንደሚችል ነው፡፡ እና ከዚያ በኋላ ማንኛውም ነገር ሊፈጠር ይችላል” ይላሉ ኮሎምበስ፡፡    

የቀድሞዎቹ ፋኖዎች ቢያፍራ ነጻ ሀገር ሆና የመመልከት ህልማቸው አሁንም አብሯቸው አለ፡፡ ነገር ግን  ያንን የሰው ህይወት ዋጋ ተከፍሎበት እንዲያዩት አይሹም፡፡ “የጦርነት መሳሪያዎች” ይላሉ ፋኖዎቹ “የጦርነት መሳሪያዎች መቀመጥ ባለባቸው ቦታ ነው መቆየት ያለባቸው- በሙዚየም ውስጥ፡፡”   

ተስፋለም ወልደየስ 

ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic