ዘመን አይሽሬው ብዕረኛና ሥራዎቹ | ባህል | DW | 18.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ዘመን አይሽሬው ብዕረኛና ሥራዎቹ

በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ወደር የማይገኝለት የልቦለድ መጽሐፍ «ፍቅር እስከ መቃብር» ሰሞኑን ዳግም ከፍ ብሎ ደምቋል። ለዚህ ምክንያቱ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ ሐውልት ደብረማርቆስ ከተማ መመረቁ ነዉ። ሙዚቀኛ ቴዲ አፍሮም በዚህ ልብ ወለድ በፍቅር ወድቆ በዜማ ደራሲዉን «ማር እስከ ጧፍ» በሚለዉ ዜማዉ ሕያዉ ማድረጉ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:37

ደራሲ ዲፕሎማትና አርበኛ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ

«በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ብዙ ተራማጆችን ብዙ አስተሳሰብን የፈጠረዉ እስካሁን ድረስ መነጋገርያ ሆኖ የዘለቀዉ ፍቅር እስከመቃብር የተሰኘዉ 1948 ዓ.ም የፃፉት መጽሐፋቸዉ ነዉ። ይህ መጽሐፍ ፍቅርን በዉስጡ ይዞ ፊዉዳል ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ስርዓት እንደነበረና ወደፊት የምትመጣዋ ኢትዮጵያ ደግሞ እንዴት መገንባት እንዳለባትም የሚጠቁም መጽሐፍ ነዉ ተብሎ ነዉ በብዙ ምሑራን የሚዘረዘረዉ» 

 

ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ ስለ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ፤ የተናገርነዉን ነበር ።  በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ወደር የማይገኝለት የልቦለድ መጽሐፍ ፍቅር እስከ መቃብር ሰሞኑን ዳግም ከፍ ብሎ ደምቆ ወትዋል። ለዚህ ምክንያቱ የታላቁ ደራሲ፣ ዲፕሎማትና አርበኛ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ ሐውልት ደብረማርቆስ ከተማ ተሰርቶ መመረቁ ነዉ።  የፍቅር እስከ መቃብር ታሪክ ሲነበብ፣ አንባቢውን በፍቅር ወጀብ አላግቶ፣   የፍቅር እስረኛ የሚያደርግ ተአምረኛ መጽሐፍ ነው ይለዋል ጋዜጠኛ ጥበቡ። ሙዚቀና ቴዲ አፍሮም በዚህ ልብ ወለድ በፍቅር ወድቆ  በግሩም ዜማ ደራሲውን ብሎም ፍቅር እስከ መቃብርን በራድዮ የተረከዉን አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱን «ማር እስከ ጧፍ" በሚለዉ ዜማዉ  ሕያዉ ማድረጉ ሌላዉ የሰሞኑ ታላቅ ክስተት ነዉ። 

ከአስር ቀናት በፊት በደብረ ማርቆስ ዩንቨርስቲ 5ኛው አገር አቀፍ የሀዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ጉባዔ ላይ የክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ  «መልዕክት ለወዳጆቼ»  የተሰኘ የግጥም መድበልና በከተማዋ የቆመዉ የሀዲስ አለማየሁ መታሰቢያ ሀውልት ተመርቆአል። በደብረ ማርቆስ ዩንቨርስቲ ሀዲስ አለማየሁ የባህል ተቋም ዉስጥ የግዕዝ ቋንቋ አስተማሪ ሊቀ ህሩያን ተግባሩ አዳነ፤ እንደሚሉት፤ ተቋሙ በስማቸዉ 2004 ዓ.ም ሲመሰረት 2007 ዓ.ም  በተቋሙ 2007 ዓ,ም ተካሄደዉ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ሃዉልታቸዉን ለማቆም ተወስኖ ነዉ ዛሬ ለምርቃት የበቃዉ። ሐዉልቱን ያሰራዉም የደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ ነዉ።

 

በእንጊሊዘኛ የተተረጎመዉ የታላቁ ደራሲ የሀዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከ መቃብር አብዛኞችን በፍቅር የጣለ ልብ ወለድ መጽሐፍ ነው። ከዝያ በዘለለ በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማት በተለይ ደግሞ  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ ዲፓርትመንት ውስጥ ላለፉት 50 ዓመታት የጥናትና ምርምር ጽሁፎች ሲሰሩበት የኖረ መጽሐፍ ነው። የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የመመረቅያ ጽሑፋቸዉን ሰርተዉበታል፡ የሥነ/ጽሑፍ ተመራማሪዎች ፍቅር እስከ መቃብርን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተንተርሰዉ  ጥናት ሠርተዋል። ዘመን አይሽሬውን  ብዕረኛ ፤ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁን ለተከታታይ ዓመታት ለሦስት ጊዜ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸዉ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ሀዲስ አለማየሁ ለቃለ-ምልልስ ብዙም ክፍት እንዳልነበሩ ያስታዉሳል። ከብዙዎች ጥያቄ ቢቀርብላቸዉም እንቢታቸዉን ቀስ ብለዉ ነበር የሚናገሩት ሲል ይገልጻቸዋል። ነገር ግን ይላል ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ፤ የዲፕሎማቲክ ሕይወት እንዲሁም የአርበኝነት እና በፖለቲካ ሕይወት ዉስጥ በጣም ግዙፍ ቦታ የሚሰጣቸዉ ናቸዉ።

ምክንያቱም ይላል ጋዜጠኛ ጥበቡ በመቀጠል፤ «ምክንያቱም እኚህ ሰዉ በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ሕይወት ዉስጥ ብቅ ያሉት ከኢጣሊያ ወረራ በፊት ነዉ። ከ 1928 ዓ.ም በፊት ከተወለዱበትና ከአደጉበት ከደብረማርቆስ አካባቢ እንዶዳም ኪዳነምህረት፤ ዲማ ጊዮርጊስ አካባቢ ነዉ የተማሩት። ሀዲስ አለማየሁ የተወለዱበትን ዓመት መቼ እንደሆን እርግጠኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ነገር ግን  1902 ዓ.ም ወይም 1906 ዓ.ም ዓመተ ምህረት ይናገራሉ። ዲማ ጊዮርጊስ ቅኔን ቆጥረዋል፤ በኋላም ወደ አዲስ አበባ መጥተዉ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በዘመኑ የነበረዉን ትምህርት ማለትም እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረዉ ጨርሰዋል። እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርት ማለት በዘመኑ ትልቅ ትምህርት ማለት ነበር። ከዝያ በኋላም ወደ ዳንግላ ወደ ጎጃም መጥተዉ ሥራ የጀመሩበት ነበር ። እዝያም ትህርት ቤት እንዳቋቋሙ ነዉ ታሪካቸዉ የሚናገረዉ። በኋላም በኢጣልያ ወረራ ወቅት ከራስ እምሩ ጋር የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ለመዋጋት ወደ ዱር ወደ ጫካ የገቡ ደራሲ ናቸዉ። እንግዲህ ከዝያ በፊት በነበሩት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ስለ ኢጣልያ ወረራ በትያትር ሲያስተምሩ የነበሩ ናቸዉ ። ልዩ ልዩ ትያትሮችን ይጽፉ ነበር። ለምሳሌ የሀበሻና የወደኋላ ጋብቻ ፤ የኢትዮጵያና የኢጣልያ ጦርነት በዓድዋ፤  ሕዝብን መቀስቀሻ አድርገዉታል። ከዝያ በኋላ ወደ ጦርነቱ ነዉ የሚገቡት እኚህ ደራሲና የትያትር ሰዉ፤ በኢትዮጵያ ዉስጥ ትያትርን ከአስተዋወቁ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸዉ። ጦርነት ዉስጥ ከተሳተፉ በኋላ ተማርከዉ ወደ ኢጣሊያ አገር ነዉ ለእስራት የተወሰዱት። ኢጣልያ ዉስጥ ሊፐሪ በሚባል ደሴት ታስረዉ ለረጅም ዓመታት ቆይተዋል። 

                  

በኢጣልያ ፋሺስት እስር ላይ የነበሩት ሀዲስ አለማየሁና ሌሎች ኢትዮጵያዉያን በኋላ በእንጊሊዝና በሌሎች የተባበሩት የአዉሮጳ ጦር ኃይላት አማካኝነት ከእስር ነጻ ሆነዉ ወደ ሃገራቸዉ ተመለሱ። ሀዲስ አለማየሁ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በ 1936 ዉይም 1937 ዓ.ም አካባቢ በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቀጥረዉ ማገልገል ይጀምራሉ። ከዝያም የኢትዮጵያ ዴፕሎማት ሆነዉ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተላኩ።

«አምባሳደር ሆነዉ ሲያገለግሉ በዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ በቆዩበት ወቅት፤ የዓለም አቀፍ ሕግ« ኢንተርናሽናል ሎዉ» ተምረዋል ነገር ግን አልጨረሱትም። ምክንያቱም በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመቀየራቸዉ ነዉ። እሳቸዉ እንደሚናገሩት ወረቀቱን ማለት ሰርተፊኬቱን ነዉ እንጂ ያላገኙት ትምህርቱን ተምረዉ ጨርሰዉታል። ይህ ማለት በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ ዉስጥ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እንዲሁም የቅኔ ትምህርትን የተማረ ሰዉ አሜሪካ ዉስጥ ሄዶ ዓለም አቀፍ ሕግ ትምርትን መከታተል መቻሉ የሚያሳየዉ፤ የጥንቱ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ተወዳዳሪ እንደነበር ነዉ። ሀዲስ አለማየሁ ከአሜሪካዉ ተልእኮዋቸዉ ተለዉጠዉ ወደ ሃገራቸዉ ከተመለሱ በኋላ በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነዉ አገልግለዋል። እንደገናም  በተመድ የኢትዮጵያ ዋና ተጠሪ ሆነዉ አገራቸዉን አገልግለዋል። እዝያ በነበሩበት ወቅት በተለይም ኒዮርክ ዉስጥ በነበሩበት ሰዓት ይህ አሁን አዲስ አበባ ዉስጥ የሚገኘዉን «ECA» ማለትም  «United Nations Economic Commission for Africa» የተባለዉን አዳራሽ እንዲሰራ አፍሪቃዉያን መሰብሰብያ ስለሌላቸዉ ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ የአፍሪቃ መዲና ናት በሚል፤ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ደብዳቤ በመጻፍ ስልክ በመደወል በመጨቅጨቅ ኢትዮጵያ ይህን አዳራሽ እንድትሰራ የአፍሪቃ መሰብሰብያ እንድትሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ዋናዉ ሰዉ ናቸዉ።» 

    

በመጭዉ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም 54ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የአፍሪቃ ኅብረት መቀመጫው ኢትዮጵያ እንደሆነ እስከ ዛሬ ዘልቆአል። እንደተጠቀሰዉ ብዕረኛዉ ክቡር ዶ/ር ሀዲስ አለማየሁ በኢትዮጵያ በሥነ-ጽሑፎቻቸዉ ይታወቁ እንጂ መተዳደርያቸዉ የመንግሥት ሥራ ነበር። ሀዲስ አለማየሁ መጀመርያ ከጻፉዋቸዉ መጽሐፍቶቻቸዉ መካከል በ 1948 ዓ.ም ለአንባቢ ያቀረቡት ተረት ተረት የመሰረት ይጠቀሳል።    

« በተረት ብዙ ፍልስፍናዎችን ብዙ ትልልቅ ነገሮችን የተናገሩበት ያስተማሩበት  1948 ዓ.ም የጻፉት ተረት ተረት የመሰረት በሚለዉ መጽሐፋቸዉ ነዉ። ከዚያ በመለጠቅ 1948 ዓ.ም የትምህርትና የተማሪ ቤት ትርጉም በሚል ስለትምህርት የጻፉ የመጀመርያዉ ሰዉ ናቸዉ። ሌላዉ ላለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዉስጥ ትልቅ ማስተማርያ የሆነና የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረገ መጽሐፋቸዉ «ፍቅር እስከ መቃብር» የተሰኘዉ ልብወለድ 1958 ዓ.ም የታተመ ነዉ። በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዉስጥ አዲስ ክስተት አዲስ አስተሳሰብ ያመጣ ትዉልድን ያነቃነቀ፤ ለለዉጥ በብዙ ፍልስፍናዎች ብዙ ጥያቄዎችን ያነሳሳ መጽሐፍ ነዉ። ሌላዉ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል በሚል በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት ተጽፎ የቆየ ነዉ። ሀዲስ አለማየሁ ይህንኑ ጽሑፋቸዉን ለጃንሆይም አሳይተዋቸዉ ይታተማል ብለዋቸዉ ግን እሳቸዉም ያላሳተሙላቸዉ፤ በኋላም የደርግ አስተዳደር 1966 ዓ.ም ላይ ከመጣ በኋላ ለደርግ ሰጥተዉት አይታተምም ብሎ ያልታተመ መጽሐፋቸዉ ነዉ። ሌላዉ  በኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ዉስጥ እንደዚሁ ተጠቃሽ የሆነዉ  1974 ዓ.ም ያሳተሙት ወንጀለኛዉ ዳኛ የተሰኘዉ መጽሐፋቸዉ ነዉ። የጥንታዊዉን የኢትዮጵያ የጋብቻ ሁኔታ ያሳዩበት 1980 ዓ.ም ያሳተሙት የልምዣት የተሰኘዉ ትልቁ መጽሐፋቸዉም ይጠቀሳል። ወደ መጨረሻ ላይ የጻፉትና የሳቸዉንም ሆነ በሳቸዉ የዕድሜ ዘመንተኛ የሆኑ የሌሎችን ኢትዮጵያዉያን የሕይወት ታሪክ እና የኢትዮጵያን ታሪክ የዳሰሱበት ትዝታ የተሰኘዉ መጽሐፋቸዉ 1985 ዓ.ም  ያሳተሙትና ያስነበቡት ግሩም መጽሐፍም በቀዳሚነት ቦታን የሚይዝ ነዉ።  

ፍቅር እስከ መቃብር በንጉሱ ጊዜ የቡርዧዉን ዘመነ ስልጣን የሚደግፍ ሆኖ መታየቱን ብዕረኛዉ ሀዲስ አለማየሁ፤ ለጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ አጫዉተዉታል። ንጉሱም ከስልጣን ወርደዉ አብዮት ከፈነዳ ወዲህ የቡርዥዋዉን ስርዓት የሚያጥላላ፤ የአሮጎዉ ስርዓት ማክተሚያና የአዲስ ስርዓት መምጫን የሚያሳይ መሆኑንም ተነግሮለት ነበር።    

« ደራሲ ሀዲስ አለማየሁን 1994 ዓ.ም እንደዚሁ «አዲስ ዜና ለተሰኘዉ ጋዜጣ ቃለ-መጠይቅ አድርጌላቸዉ ነበር። የዝያን ጊዜ እንደነገሩኝ ፍቅር እስከ መቃብር መጽሐፍ እንደታተመ  ሰዎች መጽሐፉን ይዘዉ ለጃንሆይ አሳይዋቸዉ። ይኸዉ አዲስ አለማየሁ ከኛ ጋር እየኖረ በኛ ተሹሞ የዚሁ የኛዉ መንግሥት ባለሥልጣን ሆኖ እንዲህ ዓይነት መፅሐፍ አዘጋጅቶ መንግሥታችንን አዋረደ ብለዉ ለጃንሆይ ሰጥዋቸዉ። ጃንሆይም ተቀብለዉ መጽሐፉን ሲያዩ ርዕሱ ፍቅር እስከ መቃብር ይላል ከስሩ ልብ ወለድ ታሪክ እና ወድያዉ ሳያነቡ መለሱላቸዉ።ምንድን ነዉ የምትሉት እናንተ ሰዎች ፤ ይሄ ሰዉ ፍቅር እስከ መቃብር ልብ ወለድ ታሪክ ብሎ ነዉ የጻፈዉ ፤ ልቡ የወለደዉን ነዉ የጻፈዉ ምን አድርግ ነዉ የምትሉት? ብለዉ ጃንሆይ መለሱት ስለዚህ ያ መጽሐፍ ተጽኖም አልፈጠረብኝም በጃንሆይ በኩል እንደዉን ከሚወድዋቸዉ መጽሐፎች አንዱና ዋናዉ እሱ ነበር። ምክንያቱም እሳቸዉ የሚያስቡት እኔ የጻፍኩበትን ሥርዓተ ማኅበር እሳቸዉ ካሉበት በፊት የነበረ ብለዉ ነዉ ያሰቡት ። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ 1923  ዓ.ም  ወደ ስልጣን ሲመጡ ብዙዎቹን አሻሽለዋል ተብሎ ይታሰባል።  ስለዚህ ጃንሆይ ዘመናዊነትን አዲስ አስተሳሰብን ያመጡ ናቸዉ ፤ ሀዲስ አለማየሁ በዚህ ልቦለድ የጻፉት ግን ከሳቸዉ በፊት የነበረዉን ሥርዓተ ማኅበር ነዉ፤ የሚል አስተሳሰብ ጸርሶ ስለነበር፤ ያንን መጽሐፍ በአዎንታዊ መልኩ ነበር የተቀበሉት። በኋላ ደርግ ሲመጣ እንቅስቃሴዎች ማለት እንደ መሬት ላራሹ ሲከሰት ፍቅር እስከመቃብር አብዮት አስነስቶአል ብለዉ እንቅስቃሴ አራማጅ ነዉ ተራማጅ ነዉ የሚል አስተሳሰብ ስለነበር ብዙ ወጣቶች እዛ ዉስጥ የነበረዉን የፍቅር ታሪክ ወደ ፖለቲካ በማዞር አሮጌዉን ስርዓት ማክተምያና አዲስ ስርዓት መምጫን ያሳየ ነዉ ፤ ነዉ የሚሉት።  

በ 1974 አርቲስት ወጋየሁ ንጋቱ ፍቅር እስከመቃብርን በኢትዮጵያ ራድዮ ግሩም አርጎ ከተረከዉ ወዲህ መጽሐፉ በኢትዮጵያዉያን ልብ ዉስጥ ተቀመጠ ወጋየሁንም ከጫፍ እስቀጫፍ አስተዋወቀ ለዚህ ብዕረኛዉ ሀዲስ አለማየሁ መጽሐፉን እኔ ጻፍኩት እንጂ መጽሐፉ ያንተ ነዉ ብለዉ መጽሐፋቸዉ ላይ ጽፈዉና ፈርመዉ እንደሰጡት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ተናግሮአል።  በ1992 ዓ.ም የክብር ዶክትሪት መአረግን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የተቀበሉት ሀዲስ አለማየሁ በጤንነት ምክንያት ዩንቨርስቲዉ ተገኝተዉ መቀበል አልቻሉም ።» በደብረማርቆስ የቆመዉ የሀዲስ አለማየሁ ሀዉልት ለኢትዮጵያዉያን ደራሲዎች ማስታወሻ ነዉ ሲሉም በደብረማርቆስ ዩንቨርስቲ ሀዲስ አለማየሁ የባህል ተቋም ዉስጥ የግዕዝ ቋንቋ አስተማሪ ሊቀ ህሩያን ተግባሩ አዳነ ተናግረዋል። ሀዲስ አለማየሁ የትዳር አጋራቸዉ በትዳር ብዙም ሳይዘልቁ በሞት ከተለዩዋቸዉ በኋላ ሳያገቡ ነዉ የኖሩት። ለምን? ልጆችስ አላቸዉ? ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ

 

 

 

 

  

 

 

Audios and videos on the topic