ዘመናዊ የኃይል ምንጭ እና እድገት | አፍሪቃ | DW | 27.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ዘመናዊ የኃይል ምንጭ እና እድገት

በኤኮኖሚያቸዉ ያልበለፀጉ ሃገራት የእድገት ስኬት በኃይል አጠቃቀም ስርጭታቸዉ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ አንድ ጥናት አመለከተ። እንደጥናቱ ከሆነም የተመድ በጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2030 አሳካዋለሁ ያለዉን የልማት እድገት ከኃይል አቅርቦት አኳያ 47 ሃገራት ገና ብዙ ይቀራቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:14

በልማት ያላደጉ ሃገራት የኃይል አቅርቦታቸዉን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፤

የተመድ ዘገባ እንደሚለዉ በቤት ዉስጥ የመብራት ብርሃንን መጠቀሙ በራሱ 600 ሚሊየን የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት ለዉጦ ከድህነት ሊያወጣቸዉ ይችላል። አብዛኛዉ የዓለም ሕዝብ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ቀርቶ የኤሌክትሪክ መስመር ገና አላገኘም። ይህ የኃይል አቅርቦት እጥረትም በድሀዎቹ ሃገራት የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዉን  አዳክሞ የግብርናዉን እድገት ወደኋላ ይጎትታል። በማደግ ላይ ባሉት ሃገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ቢኖር እንኳን አብዛኛዉን ጊዜ አስተማማኝ አይደለም። ይህ ደግሞ ለተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ ይዳርጋል። በዚህ ምክንያትም ኩባንያዎች ጀነሬተሮችን በተጨማሪ ለመጠቀም ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ በተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ ባላቸዉ ከፍተኛ ወጪ ላይ ተደራቢ መሆኑ ነዉ። በሀኪም ቤቶች አካባቢ የኃይል አቅርቦት አለመኖር ማለት የብዙዎችን ሕይወት ለሞት አደጋ ማጋለጥ ማለት ሲሆን በዚሁ መዘዝ ማቀዝቀዣዎች ከሥራ ሲስተጓጎሉ በቀዝቃዛ ሥፍራ መከማቸት የሚገባቸዉ ክትባቶች እና መድኃኒቶች ከጥቅም ዉጭ ሆኑ ማለት ነዉ።  የተመድ የንግድ እና የልማት ጉባኤ በምህጻሩ አንክታድ ያወጣዉ ጥናት፤ በመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2030 የመንግሥታቱ ድርጅት ያለመዉን የልማት ግብ ለማሳካት ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ወጪ ዘመናዊ የኃይል ምንጭ ማቅረብ የመጀመሪያ ግብ መሆኑን ያመለክታል። ይህም ማለት በየሃገራቱ አሁን ያለዉ የኃይል አቅርቦት መጠን በ350 በመቶ ጭማሪ ማሳየት ይኖርበታል።

ከሰሞኑ በወጣዉ በዚሁ ጥናት መሠረትም 47 ሃገራት ለቤት አገልግሎትም ሆነ ለንግዱ ዘርፍ የሚሆን በቂ የዘመናዊ የኃይል አቅርቦትን ለማሳካት ብዙ እንደሚቀራቸዉ አመልክቷል። በዘገባዉ መሠረትም እነዚህ በኢንዱስትሪዉ ያልበለፀጉ ሃገራት የድህነቱን ወጥመድ ለመሻገር የግድ ዘመናዊ የኃይል አቅርቦታቸዉ መሻሻል ይኖርበታል። የጥናቱ አቅራቢ ቡድን አስተባባሪና በአንክታድ በልማት ያላደጉ ሃገራት ዘርፍ ጉዳይ ኃላፊ ሮልፍ ትሬገር ይህ ምን ማለት እንደሆነ ያብራራሉ፤

«እስከ 2030 ድህነትን ማስወገድ የተመድ በ2015 ዘላቂነት ያለዉ ልማት በሚል ያጸደቀዉ ግብ የመጀመሪያዉ ነጥብ ነዉ። ድህነትን ሙሉ በሙሉ እንዴት ማስወገድ ይቻላል? በአንክታድ እምነት በዘላቂነት ይህን ማድረግ የሚቻለዉ የሃገራትን የማምረት አቅም ማሳደግ እና የተሻለ ምርታማ የሚሆን የኤኮኖሚ፤ ዘመናዊ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እና ይበልጥ የተሻለ ዘመናዊ የኤኮኖሚ ዘርፍ ሽግግርን ተግባራዊ በማድረግ ነዉ። ይህ የኤኮኖሚ ወደዚህ አዲስ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲለወጥ ደግሞ ኤሌክትሪክ እና ሌሎች ዘመናዊ ማሽኖችን መጠቀም የሚያስችሉ ዘመናዊ የኃይል ምንጮች ያስፈልጉታል።»

Ägypten Äthiopien Damm am Nil

የሕዳሴዉ የኃይል ማመንጫ ግድብ በግንባታ ላይ፤

ይህም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብ፣ አስተማማኝ እና በቴክኒኩም የተረጋጋ መሆን እንዳለበትም ይገልጻሉ። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለአንድ ሀገር ኢንዱስትሪዋን ለማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ባልበለፀጉት ሃገራት የደን መራቆትን ለመቀነስ ለቤት ዉስጥ አገልግሎትም ወሳኝ ነዉ። በርካታ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በዘረጋችዉ ኢትዮጵያ ይዞታዉ ምን ይመስል ይሆን? አሁንም ሮልፍ ትሬገር፤

«ኢትዮጵያ ትኩረት የሚስብ ሁኔታ ያላት ናት። ምክንያቱም ከፍ ያለ መዋዕለ ንዋይ ለዘመናዊ የኃይል ምንጮች በተለይም ከሃይድሮ የኃይል ምንጭ፤ ኤሌክትሪክ ለማግኘት ብዙ ገንዘብ መድባለች፤ ሌሎች ታዳሽ የኃይል ምንጭ በተለይም ከንፋስ ኃይል የሚያስገኙ ፕሮጀክቶች ቢኖሯትም። እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያ የኃይል ፖሊሲ ከስልታዊ ኤኮኖሚዉ ጋር የተቀናጀ ሲሆን ሀገሪቱ በኢንዱስትሪዉ ዘርፍ በሙሉ ኃይል እየተንቀሳቀሰች ነዉ። እናም የዉጭ መዋዕለ ንዋይን ለመሳብ እና የራሷንም ኢንዱስትሪ ለማሳደግ የተረጋጋ፣  አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የሆነ የኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልጋትም ታዉቃለች። እናም ይህንን ነዉ ይህች ሀገር የምታደርገዉ።»

Äthiopien Gide III Staudamm

ግልገል ጊቤ ቁጥር ሦስት

ሮልፍ ትሬገር ከ47ቱ በኢንዱስትሪ ካላደጉት ሃገራት መካከል ቡታን እና ኔፓል አሁንበጀመሩት ጥረት ከቀጠሉ በ2030 በመንግሥታቱ ድርጅት የታሰበዉን የልማት ግብ ከዚህ አኳያ ያሳካሉ የሚል እምነት አላቸዉ። በተቃራኒዉ ለአብዛኞቹ ተመሳሳይ ሃገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ይህ የሚሳካ እንደማይመስልም አመልክተዋል። ይህም ማለት ኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ይበልጥ መጨመር ይኖርባታል። አሁን ያለዉ የኃይል አቅርቦት ስርጭትም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

«አሁንም በአንፃራዊነት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነዉ ያለዉ። ሆኖም ግን ተስፋዉ ጥሩ ነዉ፤ ምክንያቱም እንደጠቀስኩት ሀገሪቱ ከዘመናዊ የኃይል ምንጮች ኤሌክትሪክ ለማግኘት ከፍተኛ መዋዕለንዋይ እያፈሰሰች ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic