ዘመናዊው የመረጃ ቴክኖሎጂና ዕድገት | ኤኮኖሚ | DW | 09.12.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ዘመናዊው የመረጃ ቴክኖሎጂና ዕድገት

ዘመናዊው የመረጃ ቴክኖሎጂ IT ዛሬ በተለይም በበለጸገው ዓለም የተስፋፋው ዋነኛው የኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር ነው። ያለዚህ ጥበብ የዘመኑ ዕድገትም ሆነ የአካባቢ አየር ጥበቃ ችግሮች በቀላሉ መፍትሄ ማግኘታቸው ሊታሰብ አይችልም።

default

በዚህ በጀርመንም የመረጃው ቴክኖሎጂ ዘርፍ በአስቸጋሪው የኤኮኖሚ ቀውስ ሰዓት የወደፊት ዕርምጃ ተሥፋ ሆኖ ነው የሚታየው። ይሄው አመለካከት በአገሪቱ ደቡባዊት ከተማ በሽቱትጋርት ትናንት በተጠናቀቀው አራተኛ ብሄራዊ ጉባዔ ላይ ተንጸባርቆ ነበር። የጀርመን መንግሥት የመረጃውን ቴክኖሎጂ ዘርፍ አገሪቱን ከወቅቱ የኤኮኖሚ ቀውስ በተሻለ ሁኔታ የሚያላቅቅና ለአካባቢ አየር ጥበቃም የሚበጅ የተሥፋ ምንጭ አድርጎ ይመለከታል። የዚሁ ቴክኖሎጂ የውጭ ንግድ ወደፊት በአገር ውስጥ በርካታ አዳዲስ የሥራ ቦታዎችን ለመክፈትና የኢንዱስትሪ በካይ ጋዞችን ለመቀነስ የሚረዳ እንደሚሆንም የሚታመነው። በመሆኑም የጀርመን መንግሥት ይህንኑ የመረጃና መገናኛ ቴክኖሎጂ ይበልጥ ለማስፋፋት ሲነሣ በመንፈቅቅ ጊዜ ውስጥ አዲስ ስልታዊ መርህ እንደሚያቀርብ ነው በጉባዔው ላይ የተነገረው። አንዱ የዚሁ መርህ ቁልፍ ነጥብ ግን ከወዲሁ ግልጽ እንዲሆን መደረጉም አልቀረም። ይሄውም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ የኢንተርኔቱን መረብ ለተጠቃሚው ማስፋቱ ነው። ዕቅዱ ከተሳካ 75 በመቶው የአገሪቱ ሕዝብ በተፋጠነ የኢንተርኔት አገልግሎት ሊጠቀም ይችላል። ይህ ደግሞ ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ትናንት በጉባዔው ላይ እንዳስረዱት የገጠር አካባቢ ነዋሪዎችን ጭምር የሚጠቀልል ነው።

“ጀርመን ውስጥ እኩል የኑሮ ሁኔታ የማስፈኑ ጥያቄ በኢንተርኔቱ አጠቃቀም ላይ ጥገኛ እንደሚሆን በጣሙን እርግጠኛ ነኝ። በተለይም ለገጠር አካባቢዎች የወደፊት ዕጣ መሻሻል ወደዚያ የሚያደርሱ መንገዶች መዘርጋታቸውና አጠቃላይ አገልግሎት መሰጠቱ ብቻ አይበቃም። በእርሻ ልማት ወይም በቱሪዝሙ ዘርፍ የሚያተኩሩ መካከለኛ ኩባንያዎችም መቋቋም መቻል ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ በዛሬው ጊዜ የኢንተርኔት ግልጋሎትን የሚጠይቅ ነው”

መረቡን በማስፋፋት በሚቀጥሉት ዓመታት 400 ሺህ አዳዲስ የሥራ ቦታዎችን መክፈት እንደሚቻል ነው የሚታመነው። አንጌላ ሜርክል የመረጃ ቴክኖሎጂውን ዘርፍ በወቅቱ የቀውስ ሁኔታ ከፍተኛ ትርጉም ያገኘ የዕድገት ዘርፍ ነው ብለውታል። በጉባዔው ላይ 800 የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብትና የሣይንስ ዘርፍ ተጠሪዎች ሲሳተፉ ውይይታቸው መረቡ ከምዝበራ የሚጠበቅበትን ሁኔታም የጠቀለለ ነበር።

“እርግጥ ለነዚህ አዳዲስ የኢንተርኔት አጠቃቀሞች የሕዝቡን ተቀባይነት ማግኘት እንፈልጋለን። ስለዚህም ዘርፉ በአጠቃላይ፤ እንበል የመረቡን ዋስትና ወይም በመረቡ ውስጥ የተጠቃሚውን ደህንነት መጠበቁን ማዕከላዊ ነጥቦቹ ያደርጋል። እናም የተለያዩት የሥራ ቡድኖች በነዚህ ነጥቦች ላይ በማተኮራቸው ምስጋናዬ ጥልቅ ነው”

በሽቱትጋሪቱ የመረጃ ቴክኖሎጂ ጉባዔ ላይ ከመረቡ ዋስትናና መስፋፋት ባሻገር ስለ አረንጓዴ-IT ማለት በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ስለተመሰረተ የመረጃ ቴክኖሎጂም ውይይት ተደርጓል። የፌደራሉ የመረጃና የመገናኛ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ማሕበር ፕሬዚደንት አውጉስት-ቪልሄልም-ሺር በዚሁ አጋጣሚ በኮፐንሃገኑ የዓለም የአካባቢ ጉባዔ ላይ በማተኮር የጀርመን ቴክኖሎጂ ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሊያደርግ እንደሚችል ነው ያስገነዘቡት።

“ከዚህ ከሽቱትጋርት የ IT ስብሰባችን ለኮፐንሃገኑ የአካባቢ አየር ጉባዔ ሰላምታችንን ለማስተላለፍ እንወዳለን። በበኩላችን በደረስንበት የቴክኖሎጂ ብቃት የምድራችንን ዋስትና ለማረጋገጥና እያሰጋ የመጣውን ጥፋት ለመግታት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደምንችል ምሳሌዎቹ ቀደም ብለው ተጠቅሰዋል”

ከነዚሁ አንዱ በመረጃው ቴክኖሎጂ አማካይነት ኤነርጂን መቆጠብ መቻል ነው። እንደ ምሳሌ፤ የማመላለሻውን ዘርፍና የኤሌክትሪክ አመራረቱን ተሳማሚ አድርጎ ማጣጣሙ ተጠቅሷል። ሌላው የኩባንያዎችና የማሕበራት ተጠሪዎች ያተኮሩበት ጉዳይ የወጣት ሙያተኞች እጥረት ነበር። በዚሁ የተነሣ ዛሬ በመረጃ ቴክኖሎጂው ዘርፍ ሃያ ሺህ የሚሆኑ የሥራ ቦታዎች የሚሞላቸው አጥተው ባዷቸውን እንዳሉ ነው። ቻንስለር አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው እንዳሰነዘቡት በዚህ ሁኔታ የኩባንያ ተጠሪዎች ትምሕርት የጨረሱ ወጣት ሙያተኞችን ከመቅጠር ወደ ኋላ ሊሉ አይገባም።

“አሁን ወሣኙ ነገር ትምሕርታቸውን የጨረሱ ወጣቶች በዚህ የቀውስ ወቅት የሚቀስሙት ልምድ ከባድ ትምሕርት ለመማር ወስነው በኋላ የሚቀጥራቸው ማጣታቸው መሆን የለበትም። እናም ዘርፉን ከልብ የምለምነው ያሉንን ምሩቃንና የሰለጠኑ ሙያተኞች በአገር ይዘን እንድናቆይ ዘዴ እንዲያፈላልግ ነው”

አራተኛው የጀርመን የመረጃ ቴክኖሎጂ ጉባዔ የኢንተርኔቱን መረብ በማስፋፋትና ይበልጥ ዘመናዊ በማድረግ ሃሣብ ሲስማማ ጀርመን በተለይ በጤና ጥበቃና በኤሌክትሮኒክ የትምሕርት ዘዴም ወደፊት በዓለም ላይ ግንባር ቀደም ቦታ እንድትይዝ ለማድረግም ተወጥኗል።

የጀርመንና የቻይና የኤኮኖሚ ግንኙነት

China EU Handel Einkaufszentrum in Peking

ጀርመን በአንድ በኩል የመረጃ ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ግንባር ቀደም ቦታ ለመያዝ ስትነሣ በሌላ በኩልም የኤኮኖሚዋ ምሶሶ የሆነውን የውጭ ንግዷን ለማራመድም ትጥራለች። በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ የሆነው የጀርመን የውጭ ንግድ በወቅቱ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ ፈታኝ ሁኔታ ላይ መውደቁ አልቀረም። ምናልባት በሚቀጥለው ዓመት መለስተኛ ማገገም እንደሚታይ ነው የሚጠበቀው። በመሆኑም ዘርፉ በተለይም በእሢያ ከባድ የገበያ ትግል ይጠብቀዋል። ጀርመን ለምሳሌ ከአውሮፓ ሕብረት አገሮች ዋነኛዋ የቻይና የንግድ ተባባሪ ስትሆን ያለፈው ዓመት የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ መቶ ሚሊያርድ ኤውሮን ያለፈበት ነበር። እርግጥ ቻይና በዚሁ ለእድ ወገን ባደላው የንግድ ልውውጥ 25 ሚሊያርድ አትርፋለች። ይህም ሆኖ ግን የጀርመን ኩባንያዎች ቻይና ውስጥ ጥቅም ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ሁልጊዜ ቀላል ባይሆንም እንደቀጠለ ነው። የአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ራይነር ብሩደርለም በአዲሱ ሥልጣናቸው የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን ሰሞኑን በቻይና ነው ያደረጉት።

በሌላ በኩል የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ ስፋት ግዙፍ ከመሆኑ ሲነጻጸር ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ ወደ ቻይና ብቅ ያለ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር አልነበረም። ለዚህም ምክንያቱ በአንዳንድ ጉዳዮች የተከሰተ አለመግባባት ሲሆን በአጠቃላይ ቻይና ለጀርመን የንግድ ሰዎች ቀላል ቦታ አይደለችም ለማለት ይቻላል። እርግጥ ሁለቱም ወገን የራሱ የሆነ ችግር አለው። የአውሮፓ ሕብረት በቻይና የጫማ ምርቶች ላይ የጣለው የቀረጥ መረጮ እንዳይራዘም ድምጽ በሰጠበት ጊዜ ጀርመን በድምጸ-ተአቅቦ ብቻ መወሰኗ ቻይናን ማስከፋቱ አልቀረም። የአገሪቱ የምጣኔ-ሐብት ሚኒስትር ቼን ዴሚንግ ጉዳዩ አገራቸውን እንዳስከፋ በግልጽ ነው ያሳዩት። ጀርመን ደግሞ በአንጻሩ ርካሽ ብረት፣ ሲሚንቶና አሉሚኒየም አውሮፓን እንዳያጥለቀልቅ ትሰጋለች። የጀርመን ኤኮኖሚ የእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ኮሚቴ ፕሬዚደንት ዩርገን ሃምብሬሽት እንደሚሉት ቻይና ውስጥ የኤኮኖሚውን ቀውስ ለመታገል በተያዘው ጥረት እነዚህ ምርቶች ከመጠን በላይ ነው የተመረቱት።

“ቻይና በወቅቱ ያላት ትልቁ መነጋገሪያ ርዕስ ይህ ነው። በብራታ-ብረቱ ዘርፍ ከመጠን ያለፈ ምርት መኖሩ! ይህም በዓለም ገበያ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል። እንግዲህ የቻይና የዕድገት ሂደት ሲታሰብ ወደፊትም ለጉዳዩ ሃላፊነት መውሰዷ ግድ ነው። ማለት ለራሷ ብቻ ሣይሆን የሥራ ክፍፍል በመኖሩ ለዓለም ኤኮኖሚ ጭምር። ድንገት እንደፈለግሁ የምርት ይዞታ እገነባለሁ፤ ሌሎቹ እንዴት እንደሚሆኑ ራሳቸው ይወቁበት ማለት አይቻልም። የፋብሪካዎች ከመጠን በላይ መብዛት ለአካባቢ አየርና ለተፈጥሮ ጸጋ፤ እንዲሁም ለምርታማነትም የሚጠቅም አይደለም”

የሆነው ሆኖ በዓለም ላይ የዕድገት መንኮራኩር የሆነችው ቻይና ለጀርመን ኩባንያዎች ጠቃሚ ገበያ ሆና ትቀጥላለች። ሚኒስትር ብሩደርለም ቤይጂንግ ላይ ያንጸባረቁት ይህንኑ ተሥፋ ነው።

MM/DW