ዕድሜን ለማራዘም የሚደረገው ሳይንሳዊ ምርምር፤ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 20.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ዕድሜን ለማራዘም የሚደረገው ሳይንሳዊ ምርምር፤

ጤንነት ካለ ፣ ዕድሜ የሚጠገብ አይመስልም። ሰዎች ፤ በ 70 እና በ 80 ዓመታት ብቻ ሳይወሰኑ ከመቶ ዓመት በላይ የመኖር ዕድል ቢያጋጥማቸው ደስታውን አይችሉትም።

default

በኮሎኝ የሚገኘው፤ በሥነ-ህይወት ፣ በተለይም በእርጅና ላይ የላቀ ትኩረት በማድረግ ምርምር የሚካሄድበት የማክስ ፕላንክ ተቋም፣

የሳይንስ ተመራማሪዎችም በበኩላቸው ፤ በእርጅና ሳቢያ የሚከሠቱ በሽታዎች በተቻለ መጠን ተወግደው ፣ ሰዎች የዕድሜ ባለጸጎች ይሆኑ ዘንድ ከመጣር አልቦዘኑም። ምርምሩ፤ በቅድሚያ ያተኮረው በጥቃቅን ነፍሳት ላይ ነው።

ዕድሜን ለማራዘም የሚካሄደው ምርምር ፤ የዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብር ትኩረት ነው ፤ ለጥንቅሩ --ተክሌ የኋላ--

በተለያዩ ዘርፎች የተሳካ የምርምር ውጤት ለማስመዝገብ ሳይንስን የሙጥኝ ያሉ ጠበብት ካተኮሩባቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ፤ የሰው ልጅ ከመቶ ዓመት በላይ የዕድሜ ባለጸጋ ሆኖ መኖር የሚችልበትን ብልሃት ማግኘት ነው። ጉዳዩ እጅግ ከባድ ነው። ከመደበኛው የተፈጥሮ ሂደት ጋር መታገልም ይሆናል። በመሆኑም ምርምሩ እንደቀጠለ ነው። በዚህ ረገድ ምርምራቸውን ካጠናከሩት ተቋማት መካከል አንዱ ታዋቂው የጀርመኑ ማክስ ፕላንክ ማእከል ሲሆን ፣ በተለይ ከዕድሜና ዕድሜን ተከትሎ ከሚከሠቱ በሽታዎች ጋር በማያያዝ ዕድሜን መቀጠል ስለሚቻልበት ሁኔታ በሰፊው የሚመራመረው፤ በኮሎኝ የሚገኘው የተቋሙ ቅርንጫፍ ነው። በዚያም የእርጅና ምልክቶች በሆኑ የፊት ቆዳ መኮማተርንም ሆነ መሸብሸብን ፤ እንዲሁም የቆዳ ካንሠርን አስመልክተው የጎልማሳ ተመራማሪዎች ቡድን መሪ የ 35 ዓመቷ ፍንላንዳዊት Sara Wickström ወደሚሉት ከማምራታችን በፊት፤ ስለዕድሜ መራዘም በጥቃቅን ነፍሳት ላይ ስለተከናወነው ምርምር በዚያው በኮሎኙ ተቋም

ሌሎች ተመራማሪዎች ከዚህ ቀደም የነገሩንን እናስታውሳችሁ--ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ይቀጥላል።

ፍንላንዳዊቷ ተመራማሪና የተመራማሪዎች መሪ ሳራ ቪክሽትሮዖም፤ በሰው ቆዳ ላይ በሚደረግ ምርምር ሊቅ የመሆን ጽኑ ፍላጎት የላቸውም። ይሁን እንጂ በምርምሩ ዘርፍ መቆየት ይሻሉ። በሙያ የሠለጠኑ ሀኪም ናቸው። በሳይንስ ምርምር ረገድ ውጤት ሊያገኙ የሚችሉ፤ ታታሪ ሳይንቲስት ናቸው። በህክምና ላይ ቢሠማሩ ግን ፤ አሁን የሚያገኙትን እጥፍ ደመወዝ ለማግኘት በቻሉ ነበር። ለማንኛውም ራሳቸው ይህን ነው ያሉት።

«እርግጥ ነው ፤ በተቻለ መጠን የተሳካልኝ ተመራማሪ ለመሆን አልሜ ነው የምንቀሳቀሰው። በዚህ ምርምር የሚሠማራ ማንም ሰው እንደዚያው ማድረግ ይጠበቅበታል፤ ምክንያቱም የዘወትር ሙያህ ውጤት ግምገማ ነው ምርምሩ እንዲቀጥል የሚያበቃው። እዚህ ባከናወንኩት ተግባርና በተገኘውም ውጤት ደስተኛ ነኝ ብዬ አፌን ሞልቼ ለመናገር እቸገራለሁ። በሳይንስ ምንጊዜም ምርምር መቀጠል የተለመደ ተግባር ነው። ከጊዜ ወደ ጊዜ ፤ ራስን በሙያ ፣ በምርምር ማጎልመስ ተገቢ ነው።»

ሳራ ቪክስትሮዖም፤ ዓላማቸው በዕድሜ ከመግፋት ፤ ከእርጅና ጋር ተያይዘው የሚመጡ በሽታዎችን በተሻለ ሁኔታ መፍትኄ እንዲገኝላቸው ማብቃት ነው። ነገር ግን ፤ ሳራ ቪሽትሮዖም ፤ ሳይንስ ፤ ሽንጤን ወገቤን ፤ ጉልበቴን ለማያሰኝ፤ ዘወትር ጤናማ አድርጎ ለሚያቆይ፤ ከበሽታ ነጻ ለሚያደርግ ህይወት ዋስትና ይሰጣል የሚል አንዳች ግምትም ሆነ እምነት የላቸውም።

«ብዙዎቹን ባልቴቶችና ሽማግሌዎች ማከም እንችላለን። የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ፤ የሚያጋጥሙ የተለያዩ በሽታዎችን እንዲከላከሉ ማድረግ ላይሳነን ይችላል። ይሁን እንጂ፤ በመጨረሻ መሞታችን አይቀሬ ነው። በሆነ ምክንያት እንሞታለን።»

በዓለም ዙሪያ፤ በአንዳንድ ታሪኮች ፤ ሰዎች ረዘም ያለ ዕድሜ እንደነበራቸው ተጽፎ እናነባለን። ባለፉት ጥቂት ምዕተ ዓመታት በመዘርዝር ጥናት እንደሚታየው ከሆነ ፤ የሰው ዕድሜ ፤ በተረጋገጠ ሁኔታ ከ 122 ዓመት የበለጠ አይመስልም ። እስካሁን የልደት ቀናቸው በይፋ ከተመዘገባላቸው ሰዎች መካከል፤ በአንደኛ ደረጃ የዕድሜ ባለጸጋ ሆነው በ 122 ዓመት ከ 164 ቀን ዕድሜ ያረፉት ፈረንሳዊቷ ዣን ካልሞ ናቸው። እ ጎ አ በ 1875 ዓ ም ተወልደው በ 1997 ዓ ም ነው ያረፉት።

በአሁኑ ጊዜ፤ ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ ም፣ ብራዚላዊቷ የዕድሜ ባለጸጋ ማሪያ ጎሜሽ ቫለንቲም ካረፉ ወዲህ፤ በ 114 ዓመት የረጅም ዕድሜ ባለጸጋ በመሆን በአሁኑ ጊዜ ፤ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሱት አዛውንት አሜሪካዊው ቤስ ኩፐር ናቸው።

በአመዛኙ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ናቸው ረዘም ያለ ዕድሜ ያላቸው። የሥነ ህይወት ተመራማሪዎች እንደሚሉት ፤ በእንስሳት ፤ በተለይ በዝንጀሮዎችና ጦጣዎችም ዘንድ፣ አንስታይ ጾታዎቹ ናቸው የላቀ ዕድሜ ያላቸው።

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ