ዓይን ገላጭ ዐውደ-ርዕይ | ባህል | DW | 09.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ዓይን ገላጭ ዐውደ-ርዕይ

ብይ ተጫዋቾች፣ አርበኞች፣ ቀሳውስት፣ ጸሎተኞች፣ ጫማ አሳማሪ፣ አልቢኖ - እኒህን በሀሳብም፣ በድርጊትም፣ በይዘትም ከጫፍ ጫፍ የተራራቁ ነገሮች “ምን አንድ ቦታ ኮለኮላቸው?” ለሚል መልሱ “አዲስ ፎቶ ፌስት” ነው፡፡ አዲስ አበባን፣ ፎቶግራፍንና ፌስቲቫልን ያጣመረው ይህ ስያሜ በየሁለት ዓመቱ ብቅ ለሚል ዓውደ ርዕይ መለያነት የዋለ ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:58 ደቂቃ

በአዲስ ፎቶ ፌስት የ40 ሀገራት ፎቶ አንሺዎች ይሳተፋሉ

የኢትዮጵያን መዲና መናኸሪያ ያደረገው አዲስ ፎቶ ፌስት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ፎቶ አንሺዎች ስራቸውን የሚያሳዩበት ሁነኛ መድረክ ከሆነ ስድስት ዓመት አለፈ፡፡ ከዝግጅቱ ጀርባ የስመ ጥሩዋ ኢትዮጵያዊት ፎቶ አንሺ አይዳ ሙሉነህ አሻራ ጉልህ ነው፡፡ ከጥንሰሱ እስከ ምስረታው ብሎም አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ድረስ ያስጓዘችው እርሷ ናት፡፡ ትውልዷ ኢትዮጵያ፣ እድገቷ የመን እና ካናዳ፣ ትምህርቷ ደግሞ በአሜሪካ የሆነው አይዳ በሙያዋ በርካታ ሀገራት ረግጣለች፡፡ ስራዎቿ በዕውቅ ፌስቲቫሎች እና ጋለሪዎች ከመቅረባቸውም ባሻገር ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን እንድታሸንፍ ምክንያት ሆነዋታል፡፡ 

ዕውቅናዋ ባህር ቢሻገርም የመጣችበትን አህጉር የተወለደችበትን ቀዬ አልረሳችም፡፡ ለአፍሪካ ልዩ ቦታ የምትሰጠው አይዳ የፎቶን የማስተማር፣ የማስተዋወቅ እና ሚዛናዊ ምልከታን የማሰራጨት ሚና ተመርኮዛ የአህጉሪቱን ደብዛዛ እና አሉታዊ ምስል ለመቀየር ለፍታለች፡፡ አዲስ ፎቶ ፌስትን እና ተያያዥ ዝግጅቶችን የሚያሰናዳው ድርጅቷ እንኳ “ደስታ ለአፍሪካ” የሚል ትርጉም የያዘ መጠሪያ ነው ያለው፡፡ የእዚህ ዓመት ዝግጅቷ መሪ ቃልም “አፍሪካን እና ዓለምን በፎቶግራፍ ማስተሳሰር” የሚል ነው፡፡

በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የወጣቱ ቁጥር ከጠቅላላው ህዝብ ገሚሱን እንደመሸፈኑ የአይዳም ትኩረት በዚሁ የዕድሜ ክልል ባሉ ፎቶ አንሺዎች ላይ ያጠነጥናል፡፡ የምታዘጋጀው አውደርዕይም ሆነ በድርጅቷ  አማካኝነት የምታመቻቸው ስልጠናዎች እና ዕድሎች ህይወት ቀያሪ እንደሆኑ ከእርሷ ጋር የሰሩ ይመሰክራሉ፡፡ አነስተኛ ካሜራዎች እና የጥበብ ፍቅርን ብቻ የሰነቁ ወጣት ኢትዮጵያውያን ፎቶ አንሺዎች ለትርፍ ጊዜ መደሰቻ የጀመሩትን ወደ ሙያ እንዲያሳድጉት መንገድ አመላካች ሆናለች፡፡ 

የ26 ዓመቱ ዮናስ ታደሰ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ፎቶ ፌስት የተሳተፈው ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው ዝግጅት ላይ ነው፡፡ የግራፊክ ዲዛይን ባለሙያ የነበረው ዮናስ ፎቶ ማንሳት ሲጀመር ቀልቡ የታሰበው ወደ ፋሽኑ መንደር ነበር፡፡ በዓውደ ርዕዩ ያቀረባቸው ፎቶዎች ከሚያተኩርበት ዘርፍ ወጣ ያሉ እና የሴተኛ አዳሪዎችን ህይወት የሚያሳዩ ነበሩ፡፡ በዝግጅቱ መሳተፉ በዓለም አቀፉ ዕውቅ የፋሽን መጽሔት “ቮግ” ዓይን ውስጥ እንዲገባ እንዳደረገው እና ወደ ጣሊያን የመሄድ ዕድል እንዳመጣለት ይናገራል፡፡ 

“ቮግ ‘ተሰጥኦ’ የሚባል ድረ ገጽ አለው፡፡ የተለያዩ ሀገር እየሄዱ ተሰጥኦ [ያላቸውን] ይመለምላሉ፡፡ ለዚያ ድረገጽ አላቸው፡፡ ስራዎችህ እዚያ ላይ ይወጣሉ፡፡ ኢንስታግራም ገጻቸው ላይ ፖስት ያደርጉታል፡፡ [ጣሊያን] ጠርተውኝ የነበረው ዓውደ ጥናት ለመሳተፍ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የቮግ ፎቶ ፌስቲቫል ነበራቸው፡፡ እዚያ ፌስቲቫል ላይ ዓውደ ጥናቶች እንዳተፍ እና እንዳይ ነበር የተጋበዝኩት፡፡ ይህን ዕድል ያገኘሁት በአዲስ ፎቶ ፌስት መስራች እና ሀሳብ አፍላቂ በአይዳ ሙሉነህ በኩል ነው ያገኘሁት፡፡ ከእርሷ ጋር የተዋወቅነው አዲስ ፎቶ ፌስት ላይ ነው፡፡ እኔ ፋሽን ላይ በይበልጥ እንደምሰራ ስለምታውቅ ከእነርሱ ጋር አገናኘችኝ፡፡ ቮግ ኢትዮጵያ መጥተው ከኢጣሊያን ኢምባሲ ጋር በመሆን አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅተው ነበር፡፡ እርሱ ላይ ተሳትፌ ነበርና ከዚያ በኋላ ግንኙነቱ ተፈጠረ እና እዚህ ዕድል ላይ ደረስኩ” ይላል የዓውደ ርዕዩን ትሩፋት ሲያብራራ፡፡ 

የፎቶ ጋዜጠኛ የሆነው ሙሉጌታ አየነም እንደ ዩናስ ሁሉ በዓውደ ርዕዩ ከተሳተፈ በኋላ ወደ ሌሎች ሀገሮች የመጓዝ ዕድል ገጥሞታል፡፡ የፎቶ ጥበብ ይመስጠው የነበረው ሙሉጌታ ስለ ሙያው ቀረብ ብሎ ለመረዳት የቻለው ሰፈሩ ውስጥ ያለ ፎቶ ቤት ውስጥ በመላላክ ነበር፡፡ በ22 ዓመቱ ኮሌጅ ተማሪ እያለ የክረምት እረፍቱን ለፎቶ ቤቱ እና ለመሰረታዊ የፎቶ ትምህርት ከፋፍሎ ተጠቅሞበታል፡፡ የፎቶግራፍ ጥበብ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ አለመሰጠቱ የሙያው ፍቅር ላለቸው ለእንደእርሱ ዓይነቶቹ ወጣቶች ጉዳት እንደሆነ የሚናገረው ሙሉጌታ አዲስ ፎቶ ፌስት እና የአይዳ ሙሉነህ አስተዋጽኦ በትንሹም ቢሆን በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት ደፍኗል ብሎ ያምናል፡፡

“ይህ አይንህን የምትገልጽበት ነው፡፡ የሌላውን ዓለም የፎቶግራፍ ኢንዱስትሪ፣ ከባለሙያ ፎቶ አንሺዎች ጋር የመገናኘት ዕድልህን የሚያሰፋልህ እና ፎቶግራፍን እንደ ጥበብ ብዙ ግንዛቤ እንዲኖረህ የሚያደርገህ ነው፡፡ በጣም ትልቅ ዕድል ነው ለወጣቶች የሚሰጠው፡፡  ለትልልቅ ፎቶ አንሺዎች፤ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከአሜሪካ ለመጡ፤ ስራህን ታሳያለህ፡፡ ዕይታን፣ ወደ የት ማተኮር እንዳለብኝ ትልቅ ትምህርት የወሰድኩበት ነው፡፡ በ2012 [እንደ ጎርጎሳዊው] እንደውም ስፔን የመሄድ አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ በዚህ በአዲስ ፎቶ ፌስት ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮች የተመረጠን ወደ አምስት የምንሆን ፎቶ አንሺዎች ወደዚያ የሄድነው፡፡ በእኛ ዕይታ ምን ይመስላል የሚለውን ነገር ለማየት ነበር፡፡ በጣም  አስገራሚ የሆኑ ሙዩዚየሞችን የመጎብኘት እና ፎቶ አንሺዎችን የማግኘት ዕድል ነበር፡፡ እና ዘርፈ ብዙ [ጥቅሞች] ነው ያሉት አዲስ ፎቶ ፌስት፡፡ በጣም ትልቅ ዕድል ነው ለወጣቶች የሚሰጠው” ይላል፡፡

ባለፉት ተከታታይ ሶስት ዓውደ ርዕዮች ስራዎቹን ያቀረበው ሙሉጌታ ከፎቶ ጋዜጠኝነቱ ስራው ጎን የአዲስ አበባን የወቅቱን ሁለንተናዊ መልክ ለታሪክ የማስቀመጥ እንቅስቃሴ ተሳታፊም ነው፡፡ “እየፈረሰች የምትገነባ ከተማ” የሚል ቅጽል የተሰጣት አዲስ አበባ እንኳን አይደለም ለባዳ ለነዋሪዎቿም ግራ አጋቢ የምትሆንበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንን ፈጣን ለውጥ በካሜራ እየተከታተሉ ለታሪክ ማሸጋገር ሙሉጌታን የመሰሉ ወጣቶች ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡ አይዳ ይህን የወጣቶቹን ጥረት በድርጅቷ አማካኝነት ትደግፋለች፡፡ 

ፎቶን ለታሪክ ሰነድነት የማስቀመጥ ስራ በተቀያያሪው የአዲስ አበባ ገጽታ ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በነዋሪዎቿ እና በተወሰነ የማህብረሰብ ክፍሎች ዘንድ ላይ አተኩረውም የሚሰሩ አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የ21 ዓመቱ አሮን ስሜነህ ነው፡፡ በመጪው ሐሙስ ታህሳስ 6 በሚከፈተው የእዚህ ዓመቱ ዓውደ ርዕይ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈው አሮን ከሚያቀርባቸው ስራዎቹ መካከል በታሪክ ስነዳ መልክ ያነሳቸው እንደሚገኙበት ይናገራል፡፡ 

“የመጀመሪያው በአርበኞች ላይ የሰራሁት የፎቶ ስብስብ ነው፡፡ ይሄም የፎቶ ስብስብ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስሰራበት የቆየሁት ነው፡፡ የመጀመሪያው የሰራሁት ስብስብ ነበር፡፡ ከዚህ በፊትም በኒው ዮርክ፣ ለንደን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ባማኮ ታይቷል፡፡ ይሄኛው አዲስ አበባ ሲታይ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ መነሻ የሆነኝ ሀሳብ የነበረው አያቴ ለረጅም ጊዜ [የአጼ] ኃይለስላሴ ወታደር፣ ክቡር ዘበኛ ነበርና ሁሌ ይነግረኝ ነበር ታሪኮችን፡፡ ስለዚህ ሁሌም የማስበው የነበረው የእርሱን ታሪኮች እኔ አውቃቸዋለሁ ነገር ግን ማንም የሚያውቃቸው የለም ከእኛ ቤተሰብ ውጭ፡፡ ልክ እንደ እርሱ አይነት በእርግጠኝነት ሌሎችም ይኖራሉ ብዬ አምን ነበርና በዚያም የአርበኞችን ማህበር ሄጄ አገኘኋቸው፡፡ አድዋ ድል ማስታወሻ ስነስርዓት ላይ እና የአርበኞች ቀን ዝግጅት ላይ በመሄድ ከእነዚህን ሰዎች ጋር አጭር ቃለ ምልልስ እያደረግሁኝ በተጨማሪም ፎቷቸውን እያነሳሁ በቻልኩት መጠን እነዚህን ሰዎች በሰነድነት ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ” ይላል አሮን፡፡ 

የእንደዚህ አይነት ፎቶዎች ዋጋ እና ጥቅም ይበልጥ እየጎላ የሚመጣው ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ወጣቱ ፎቶ አንሺ ያስረዳል፡፡ ያገኛቸው አርበኞች ከ82 እስከ 95 ዓመት አማካይ ዕድሜ ላይ አንደነበሩ የሚናገረው አሮን ከእነርሱ ውስጥ ብዙዎቹ ባለፈው ሁለት ዓመት ውስጥ በሞት እንደተለዩ ይናገራል፡፡ ከጊዜ ጋር እሽቅድምድም የገባው አሮን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ መሰል አርበኞችን ታሪክ እና ማንነት ማስቀረት ባለመቻሉ ይቆጨዋል፡፡ 

ብዙም ትኩረት አልተሰጠውም ብሎ ለሚያምነው የወቅቱ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ራሱን በኃላፊነት ሾሞ የዘመኑን ሙዚቀኞች እና ዝግጅታቸውን በካሜራው እያስቀረ ይገኛል፡፡ የዚህ ስራው ውጤት የሆኑት እና “ኢትዮ ከለርስ” የተሰኘውን የባህል ቡድን ጭፈራዎች የሚያሳዩ ፎቶዎች በዚህኛው ዓውደ ርዕይ ይቀርባሉ፡፡ ላለፉት አራት አመታት ፎቶ ሲያነሳ የቆየው አሮን የሙሉ ጊዜ ፎቶ አንሺ የሆነው አይዳን ከተዋወቀ እና በአዲስ ፎቶ ፌስት በበጎ ፍቃደኝነት ከተሳተፈ በኋላ እንደሆነ ይናገራል፡፡ 

ከዓውደ ርዕዩ ጎን ለጎን የሚሰጠው የፎቶ ዓውደ ጥናት እና ከዕውቅ ባለሙያዎች ጋር የሚደረገው ውይይት ለሙያቸው ትልቅ እገዛ እንደሆነ ወጣቶቹ ይናገራሉ፡፡ አዲስ ፎቶ ፌስትን “ፈር ቀዳጅ” እና “በር ከፋች” ሲሉ ያሞግሱታል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ላይ የሚሳተፉ ፎቶ አንሺዎች ብዛት እና የመጡበትን ሀገር ለተመለከተ በእርግጥም ወጣቶቹ የሚመሰክሩትን እውነታነት ይረዳል፡፡ እስከ ታህሳስ 11 ለተመልካች ክፍት ሆነው በሚቆየው የዚህ ዓመት አውደ ርዕይ ላይ ከ40 ሀገራት የተውጣጡ 126 ፎቶ አንሺዎች ይሳተፋሉ፡፡ 

የእዚህን ዓመት ዝግጅት ከሌሎቹ ጊዜ ለየት የሚያደርገው ተሳታፊዎቹ የተመረጡት ለሁሉም ሰው ክፍት በተደረገ ጥሪ አማካኝነት መሆኑ ነው፡፡ በመራጭ ባለሙያዎች ግምገማ የተሻለ ፎቶዎች ያቀረቡ ስራዎቻቸውን እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡ ይህም የኢትዮጵያውያን ተሳታፊዎች ቁጥር ከቀደመው ጊዜ በላቀ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት አውደ ርዕዮች ኢትዮጵያውያን ፎቶ አንሺዎች ከሌሎች የአፍሪካ ሀገር ባለሙያዎች ጋር ተቀላቅለው ስራዎቻቸውን አንዲያቀርቡ ይደረግ የነበረ ሲሆን በዚህ ዓመት ግን ለብቻቸው ፎቶዎቻቸውን የሚሳዩበት መድረክ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ 

የዚህን ዓመት ዝግጅት ለየት የሚያደርገው ሌላ ጉዳይ ለምርጥ ፎቶዎች የሚሰጠው ሽልማት ነው፡፡ ፎቶዎቻቸውን ለውድድር የሚያቀርቡ በዳኞች ተመዝነው የካኖን ካሜራ እና የማተሚያ ማሽኖች ሽልማት ይበረክትላቸዋል፡፡ የካኖን ካሜራዎች አምራች ድርጅት ለምርቱ ተጠቃሚዎች ያዘጋጀው ዕድልም አለ፡፡ ይህ ዕድል ማንኛውም ካኖን ካሜራ ያለው ሰው ወደ ቦታው ወስዶ ማስመርመር የሚችልበት ነው፡፡  

ፎቶዎቹ ከሚታይባቸው ቦታዎች በአንዱ በሆነው የካንዛንቺሱ ፈንድቃ የምሽት ክበብ ደግሞ የሙዚቃ ዝግጅት በተጨማሪነት ይኖራል፡፡ የዓውደ ርዕዩ የተለያዩ ዝግጅቶች ከፈንደቃ ሌላ በሸራተን አዲስ እና ማሪዮት ኤክዘኪዩቲቭ አፓርትመንት ሆቴሎች፣ በዲኖ እና ሌላ የስዕል ጋለሪዎች እንደዚሁም በጣሊያን ባህል ማዕከል ይካሄዳሉ፡፡ ወጣቶችም ሆነ ሌሎች ተመልካቾች ይህን መሰል የፎቶ አውደ ርዕይ ቢመለከቱ ብዙ እንደሚያተርፉ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ 

ዮናስ ተመልካቾችን በሁለት ይከፍላቸዋል፡፡ 

“እንግዲህ ሁለት አይነት ተመልካች ነው የሚኖረን፡፡ አንደኛው በዚህ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያለው ነው፡፡ ፎቶ ማየት የሚፈልግ ሰው ነው፡፡ ለፎቶ ፍቅር ያለው ነው፡፡ እሱን ተመልካች ለምንድነው ነው የምመጣው? ብሎ አይጠይቅህም ግን ቢጠየቅህም ብዙ ነገር እንደሚማርበት [ያውቃል]፡፡ የጥበብ አፍቃሪ ነው፡፡ ማወቅ ለሚፈልገው ደግሞ አዲስ ፎቶ ፌስት ላይ 134 ፎቶ አንሺዎች ከተለያዩ 40 ሀገሮች ላይ ያላቸውን ዕይታ፣ የማህበራዊ ነገር፣ ኢኮኖሚ፣ ሙዚቃ፣ ባህል ሁሉኑም ነገር የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን ነገር መመልከት ግንዛቤን ለማሳደግ እና ለአእምሮ ለውጥ ራሱ ትልቅ ትምህርት ነው ብዬ ነው የማምነው” ሲል ተመልካቾች ሊያገኙት ስለሚችሉት ጥቅም ይዘረዝራል፡፡ 

ሙሉጌታም በዚህ ይስማማል፡፡ 

“ፎቶግራፎችን መጥተው ቢያዩ ለውጦችን፣ ዕይታዎችን ይመለከታሉ፡፡ ራስህን ዘና የምትደርግበትም ነው፡፡ ጥበብ ስታይ ትታደሳለህ፡፡ ነገሮችን የምታይበትን መንገድ ይቀይርልሃል፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ስትኖር እንደ ኢግዚቢሽኖች፣ ኮንሰርቶች አይነት ነገሮች ብዙ የሉም፡፡ ብዙ አማራጮች በሌሉበት መጥተህ እዚያ የተለየዩ ሰዎችን ዕይታ ታይበታለህ፡፡ ትልልቅ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ በተለይ በጥበብ ውስጥ ያሉ ልጆች ቢመጡ ለትስስር በጣም አሪፍ ነው፡፡ እዚህ መጥተው የምታገኛቸውን እነዚህን ባለሙያዎች ሌላ ቦታ ላግኛቸው ብትል እንኳ የማታገኛቸው ናቸው፡፡ በጣም ትልቅ ዕድል ነው ብዬ አስባለሁ” ይላል ሙሉጌታ፡፡ 

ወጣቶቹ ፎቶ አንሺዎች የጠቃቀሷቸውን አይቶ ለመመስከር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተዋል፡፡ አፍሪካን ከዓለም ጋር ለማስተሳሰር የሚያልመው አውደ ርዕይ ኢትዮጵያውያንን ከፎቶ ጥበብ ጋር የሚያስተሳስር እንዲሆን የብዙዎች ምኞት ነው፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ         

አርያም ተክሌ

  

Audios and videos on the topic