ዓርብ የሚካሄደው የጂቡቲው ምርጫ፣ | ኢትዮጵያ | DW | 06.04.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ዓርብ የሚካሄደው የጂቡቲው ምርጫ፣

ጂቡቲ፣ የፊታችን ዓርብ ምርጫ ታካሂዳለች። ፕሬዚዳንት እስማኤል ዖማር ጉሌህ ለሦስተኛ ጊዜ በእጩነት ሲቀርቡ፤ 3 የተቃውሞው ወገን መሪዎች ባለፈው የካቲት 11 ቀን 2003 ተይዘው በእሥር ላይ ይገኛሉ።

default

በተቃውሞው ወገን ላይ ወከባና እሥራት በማጠናከር ፣ ዓርብ ለ 3ኛ ጊዜ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው የሚቀርቡት የጂቡቲው ፕሬዚዳንት እስማኢል ዖማር ጉሌህ፣

ታዲያ ፣ ከወዲሁ፣ ምርጫው ፣ ነጻና ፍትኀዊ ሊሆን እንደማይችል፤ የአሠራሩ ደንብ ማመላከቱ አልቀረም። ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን ፤ ሂደቱን ሲከታተል የቆየው ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት(HRW)አስታውቋል። ተክሌ የኋላ፣ በለንደን የሚገኙትን የ HRW የአፍሪቃ ክፍል ተመራማሪ Mr.Ben Rawlence ን አነጋግሮ የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

በቀይ ባህር ደቡባዊ ጫፍ ፣በባብ ኤል መንደብ ( የዕንባ በር)ሠርጥ የምትገኘው ስልታዊ አቀማመጥ ያላት፣ ለፈረንሳይና ዩናይትድ እስቴትስ ወታደራዊ ጣቢያ የፈቀደችው ንዑሷ ምድረ በዳ ሀገር፣ ጂቡቲ ፣ የፊታችን ዓርብ ምርጫ የምታካሂድ ሲሆን፣ መንግሥቷ በተቃውሞ ወገኖች ላይ የሚወስደውን የማዋከብና ይዞ የማሠር ተግባር አቁሞ፣ ምርጫው፣ የምርጫ ደንብን ይከተል ዘንድ፣ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት (HRW) ጥሪውን አሰምቷል። በለንደን የ HRW የአፍሪቃው ክፍል የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተመራማሪ Ben Rawlence ---

«የጂቡቲ መንግሥት ፣ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲፈቅድ ጠይቀናል። ምክንያቱም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ተከልክሎ ነበረና! ባለፈው የካቲት 11 ቀን ፣ ምንድን ነበረ የሆነው፤ የተቃውሞ ሰልፈኞች ከሚያመሩበት ቦታ ታግደው ተከለከሉ፤ ብዙዎች ተይዘው ታሠሩ ፤ የተቃውሞው ወገን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ታሥረዋል። በሥልጣን ላይ ያለውመንግሥት ህጋዊ ምርመራ እንዲደረግ ቢያዝም በይፋ አልከሰሳቸውም።»

የጂቡቲ ህገ-መንግሥት፣ ሐሳብ የመግለጽና የመሰብሰብ ነጻነትን ይፈቅዳል እንጂ አይከለክልም። ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ በዓርቡ ምርጫ፣ የተቃውሞው ወገን ስለማይሳተፍ፣ ምርጫው ትክክለኛና ፍትኀዊ ሊሆን አይችልም። HRW ፤

«የጂቡቲ መንግሥት፤ የተቃውሞ ወገኖችን መብት መግታት ሳይሆን ፣ የመተማመን መንፈስ ሠፍኖ ፤ ተቃዋሚዎች የሚሳተፉበትን ሁኔታ ቢያመቻች ማለፊያና ገንቢ ተግባር በሆነም ነበር »፤ ይላል። ታዲያ ዓርብ የሚካሄደውን ምርጫ ነው ማለት ይቻላል፤ ወይስ ሌላ ሥያሜ የሚሠጠው ነው?

«አሁን እንደሚታየው ከሆነ፣ ምርጫ ብሎ ቋንቋ የለም። ፕሬዚዳንቱ አሁንም፤ በአጩ ተወዳዳሪነት ይቀርባሉ የአገልግሎት ዘመን እንዳይገደብ ለማድረግ፣ የህገ-መንግሥቱን አንቀጽ አስለውጠዋል። የአንድ ወቅት የአገልግሎት ዘመን 6 ዓመት መሆኑ ቀርቶ፣ 5 ቢሆንም ፣ በየጊዜው እየተመረጡ ከሥልጣኑ መንበር ንቅንቅ ሳይሉ ለመኖር ነው የቀየሱት። የተቃውሞው ወገን ራሱን ከምርጫው አርቋል። ብቸኛው ነጻ የተቃዋሚ እጩ ተወዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲ የሌላቸው፣ የቀድሞው የህገ-መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ከፍተኛ ዳኛ የነበሩ ናቸው። ስለዚህ ከሞላ ጎደል፤ እንዲሁ የይስሙላ ምርጫ ነው ማለት ነው የሚቻለው፣ እንደምናየው። በአገሪቱ ነጻ የመገናኛ ብዙኀን የለም። ዋናው የሰብአዊ መብት ድርጅት፣ የምርጫውን አያያዝ በከፍተኛ ደረጃ ነው የሚቃወም። ጂቡቲ ይህን ፈለግ መከተሏ፣ የተቃውሞው ወገን እንዳይሳተፍ ፣ መሠረታዊ ህግን አለማክበሯያሳፍራል።»

በአፍሪቃ ነጻና ፍትኀዊ ምርጫ እንዲካሄድና ዴሞክራሲ እንዲገነባ ለማድረግ፣ የይስሙላ ምርጫን ለማስቀረት ምን ዓይነት መፍትኄ ይኖር ይሆን?!

«አዎ የጂቡቲውን ምሳሌ ብንመለከት DI የተሰኘው የአሜሪካው የምርጫ ታዛቢ ድርጅት በጂቡቲ ዴሞካራሲን መነጽ ይቻል ዘንድ ገንቢ ሐሳቦችን ቢያቀርብም፣ መንግሥት ችላ ከማለትም አልፎ፣ DI አገር ለቆ እንዲወጣ አድርጓል። ለነገሩ እኮ የተወሳሰበ አይደለም። የዴሞክራሲ መሠረታዊ መርኆዎች ነጻና ፍትኀዊ ምርጫዎች ፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በማኅበር የመደራጀት መብት፤ የፓርቲዎች ተሳትፎ--ቀላል አካሄድ ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ፣ ምን ዓይነት እርምጃም እንደሚወሰድ ማንም ያውቀዋል። ማንም መንግሥት ሊያከናውነው ይችላል። ካልተቻለ፣ ህዝብ ይቃወማል፣ ለለውጥ ግፊት ያደረጋል ሙከራውን ይቀጥላል። ይሁንና በብዙ የአፍሪቃ አገሮች፣ እንደታየው መንግሥታቱ፣ ይህን አይፈቅዱም። የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። ጂቡቲ፤ በዚህ ረገድ የሆነ ዓይነት የመሪነት ሥፍራ ለመያዝ የሚያስችላትን ወደ ጎን በመግፋት ለሥልጣን ዘመን ገደብ በማድረግ ፣ ባላት ጥሩ ህገ-መንግሥት በመጠቀም ፤ አርአያ መሆን በቻለች ነበር።»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ