«ዓርብን ለወደፊት ዕጣ ፈንታችን» | ወጣቶች | DW | 05.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

«ዓርብን ለወደፊት ዕጣ ፈንታችን»

በመላው ዓለም በየሳምንቱ ዓርብ ለተሻለ ከባቢ አየር ለመታገል አደባባይ የሚወጡት ተማሪዎች ቁጥር ተበራክቷል። አላማቸው መንግሥታት ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ትኩረት ሰጥተው ርምጃ እንዲወስዱ ነው። የተማሪዎቹን አላማ የሚደግፉ ቢኖሩም፤ ዓርብ ዓርብ ከትምህርት ገበታቸው ለመቅረት ሲሉ ነው አደባባይ የሚወጡት በማለት የሚያጣጥሉባቸውም አልጠፉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00

«ዓርብን ለወደፊት ዕጣ ፈንታችን»

Fridays for future ወይም ዓርብን ለወደፊት ዕጣ ፈንታችን በሚል መሪ ቃል ብራስልስ ፣ በርሊን፣ ፓሪስ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች አደባባይ ወጥተዋል። አርያቸው  ደግሞ የ 16 ዓመቷ ሲውዲናዊት ግሬታ ቱንበርግ ነች። « ረዥም እና የተጎነጎነ ቡኒ ፀጉር አላት።»« ሲውዲን ውስጥ ይህንን ንቅናቄ የጀመረች ነች። ብቻዋን እንደዚህ አይነት ተቃውሞ መቀስቀስ መቻሏ የሚደነቅ ነው።» « ነገ ዓለማችን የምትወድም ከሆነ መማሩ ለምኑ ነው ትላለች።»ሲሉ የጀርመን ተማሪዎች ወጣቷን ይገልጿታል።

ግሬታ ቱንበርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰልፍ የወጣችው ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ሲሆን ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት ትምህርቷን ትታ የሲውዲን ምክር ቤት ፊት ለፊት መፈክር ይዛ ተቀምጣለች። ይህም ለከባቢ አየር ጥበቃ ስትል ከትምህርት ቤት መቅረቷን የሚገልፅ ነበር። የወጣቷ ዓላማ ሀገርዋ የፓሪሱ የከባቢ አየር ስምምነትን  ማለትም የሙቀት ልቀት ከ 2 ዲግሪ እንዳይበልጥ የሚለውን እንድታከብር ነው። ይህ ተግባራዊ እስከሚሆንም ወጣቷ አድማዋን እንደምትቀጥል በትዊተር መልዕክቷ አሰራጭታለች።  እዛም ላይ የተጠቀመችው መሪ ቃል #FridaysForFuture የሚል ነው። የወጣቷ አደባባይ መውጣትም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተማሪዎችን ትኩረት ስቧል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ወጣቶች በየሀገራቸው ተመሳሳይ ተቃውሞዎችን ዓርብ ዓርብ ማስተባበር እና ከትምህርት ቤት አድማ መትተው መቅረታቸውን ቀጥለዋል።

በጀርመን በመጋቢት ወር አጋማሽ በተደረጉ 230 ሰልፎች 300 000 የሚጠጉ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በመዲና በርሊን ብቻ ቁጥራቸው 25 000 ይደርስ እንደነበር ተገልጿል። የበርሊኑን ሰልፍ ለየት የሚያደርገው የሰልፉ አርአያ የሆነችው ግሬታ በእንግድነት የተገኘችበት መሆኑ ነው። ለሦስት ደቂቃዎች ያህል ንግግል ያደረገችው ግሪታ መልዕክት፣  « ልንደነግጥ ይገባል። መደንገጥ ስል መጩዋጩዋህ ሳይሆን ከተደላደለው ይዞታችን ወደሌላኛው ጎን ዞር ማለት መቻል ማለቴ ነው። ይህ ገና ጅማሬው ነው። እመኑኝ።»

ብዙዎች የግሬታን ሀሳብ ይጋራሉ። እንደ ጀርመን ሁሉ እኢአ መጋቢት 15 ቀን በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት፣ አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሩስያ ተማሪዎች ሰልፍ አካሂደዋል። ወጣቶቹ ሰልፍ የወጡበትን ምክንያትም እንዲህ ይገልፃሉ።

«በአድማው የምሳተፈው ለራሴ እና ለመጪው ትውልድ የተረጋገጠ የወዲፊት ዕጣ ፈንታ እንዲኖር ስለምፈልግ ነው።»

«በተማሪዎች የከባቢ ጥበቃ መሳተፍ የፈለጉት ተፈጥሮን ስለምወድ ነው። ሀገሬ ላይ የከባቢ ጥበቃ የለም። ስለዚህ ከማዘን ይልቅ ርምጃ መውሰድ ፈልጌ ነው።»

« ሆንግ ኮንግ በሕንፃዎች ተከባለች። 75 በመቶ ያህል ሕፃዎች ብቻ ናቸው ከፀሐይ የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ጣሪያቸው ላይ ያለው። ስለዚህ ከዚህም የበለጠ ለውጥ ለማድረግ ሆንግ ኮንግ አቅም አላት። እና መንግሥት ይህንን እንዲያደርግ ጫና ለማድረግ እፈልጋለሁ።»

አፍሪቃ ውስጥ የ Fridays for future ሰልፍ በተካሄደባት ደቡብ አፍሪቃ የሚኖረው አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት ከዚህ ቀደም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት እንደማያውቅ ነገር ግን አሁን ፋብሪካዎች በዙብን ብሎ ከማለት የበለጠ ማሰብ መጀመሩን ገልጾልናል።

ኢትዮጵያዊው መሀመድ ከሊል የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ባለሙያ ናቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ደቡብ ክልል አላባ ዞን ስለሚጨፈጨፈው ደን  መቃወም የጀመሩት ከ Fridays for future በፊት ነው። ግን እስካሁን ሰሚ አላገኘንም ይላሉ። « ደቡብ አሶሬ አላባ ላይ የሚገኝ ሰፊ እና ረዥም ደን ነበር። ያንን ባህርዛፍ በመመንጠራቸው ያንን በመቃወማችን ከስራ ተፈናቅለናል። ሰዎች ታስፈዋል። ከፍተኛ በደል ነው ወጣቱ ላይ የደረሰው» እስካሁን በፌስቡክ ተቃውሞ ያቀረቡት መሀመድ የጠፋው ጠፍቷል የተረፈውን እናድን ይላሉ።

ስውዲናዊቷ ወጣት ግሬታ ቱንበርግ በዓለም ዙሪያ ብዙ ወጣቶችን አነቃቅታለች። እንደ ዛሬ ዓርብ ዓርብ በሚካሄዱ ሰልፎች አዳጊ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ጎልማሶችም መሳተፍ ጀምረዋል። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርልክ የሰልፎቹን አስፈላጊነት ቢያምኑም የሚመሩት ፓርቲ ፖለቲከኞች ግን በተለይ የተማሪዎቹን መልዕክት ችላ ብለው አድማው ከትምህርት ገበታ ለመቅረት የሚያደርጉት ነው ሲሉ ይተቻሉ። ተማሪዎቹ ግን ትችቱን በዝምታ አያልፉም።

« ዓርብ ዕለት እዚህ ኮንስታንስ ውስጥ ትላልቅ በረዶ የቀላቀለ ዝናብ ዘንቧል። ኃይለኛም ንፋስ ነበር። ስለዚህ ከትምህርት ቤት መቅረት የፈለገ በርግጠኝነት አደባባይ ሳይሆን ሌላ ቦታ ይሄድ ነበር። »

« ራሱን የቻለ ትርፍ ጊዜ ሥራ ነው። በሳምንት ከ 10 እስከ 20 ሰዓት ለፍራይደይስ ፎር ፊውቸር አጠፋለሁ። ይህን ከትምህርት ቤት ለመቅረት ስል የማደርገው አይደለም። ዓለም አቀፍ የወጣቶች ንቅናቄን ከመደገፍ የቀለለ አማራጭ በርግጠኝነት አይጠፋም። »

«የምንሠራው አዲስ ነገር አይደለም። ላለፉት 40 ዓመታት ግልፅ የሆነውን ነገር ነው ማኅበረሰቡን ለማስገንዘብ እየሞክርን ነው። አስቸኳይ ባይሆን ኖሮ እና ባለፉት 40 ዓመታት ችላ ባይባል ኖሮ እንደዚህ አይነት ጠንካራ ርምጃ ባልወሰድን ነበር።»

በዚህም የአንድ ተማሪ አባት ይስማማሉ። « ልጆቻችንን እና የሚያቀርቡትን ጥያቄ እንደግፋለን። ከትምህርት ቤት አድማ መምታቱ ላይም ተወያይተንበታል። የማንቀበለው ነገር ቢኖር ሚኒስቴሮች ከትምህርት ቤት የሚቀሩ ተማሪዎች የቅጣት ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል የሚለውን ነው። ትምህርት ተቋማትም የተለያየ ርምጃ ነው በመውሰድ ላይ ያሉት። ይህን የሚሉ ፖለቲከኞች ተማሪዎቹ ትክክል እንደሆኑ ያውቃሉ። እውነታው እና ሳይንሱ ከተማሪዎቻችን ጎን ናቸው፣ ፖለቲከኞቹ ግን አድማው ከጉዳዩ በልጦባቸው ስለ ትምህርት ቤት መቅረት ያወራሉ።»

ምንም እንኳን የልጆቻቸውን ከትምህርት ገበታ የመቅረት አድማ የሚረዱና የሚደግፉ ወላጆች ባይጠፉም ወደፊት ወደውም ሆነ ተገደው ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሳይልኩ አይቀርም። ምክንያቱም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት የማይልኩ ወላጆች በገንዘብ ክፍያ እንዲቀጡ እየወሰኑ ነው። ከዚህ በፊት እንደዚህ አይነት ክፍያዎች የነበሩት ትምህርት ቤቶች ከመዘጋታቸው በፊት በቅናሽ ዋጋ ሽርሽር ለመሄድ ሲሉ አስቀድመው ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት የሚያስቀሩ ወላጆች ላይ ነበር። የጀርመን ወጣቶች በዚህ ሲደናገጡ የዚህ ንቅናቄ ቀስቃሽ ግሬታ ቱንበርግ ደግሞ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ አድማውን እንደምታቆም ጽፋ ተከታዮቿን በተጨማሪ አደናግጣ ነበር። በመጨረሻ ግን በአውሮጳውያኑ የሚያዚያ አንድ ቀን ቀልድ ማለትም አፕሪል ዘፉል እንደሆነ ገልፃ ትግሏን እንደምትቀጥል አስረድታለች። የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቿ ግሬታ በጀርመን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ የኖቤል ሽልማት ተሸላሚም ሆናለች።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

Audios and videos on the topic