ዓመታዊ ዐቢይ ሽልማት፣ በሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 17.12.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ዓመታዊ ዐቢይ ሽልማት፣ በሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ፣

በዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን፣ ከሳይንስ ጋር የሚገናኝ ዜና ካስቀደምን በኋላ ፣ በሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ ረገድ ከጀርመን ርእሰ ብሔር በሚሰጠው ዓመታዊ ዐቢይ ሽልማት ላይ ያተኮረ ዘገባ እናቀርባለን።

default

የጀርመን የሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ መፃዔ-ዕድል ሽልማት(Zukunftspreis 2008)አሸናፊዎች፣ የቦሽ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ባልደረቦች፣ ዶ/ር ኢንጂኔሮች፣--(ዪሪ ማሬክ፣ ሚሻኤል ኦፈንበርግና ፍራንክ ሜልትሰር)

አስደናቂው ተማሪ፣

አንድ አስደናቂ ኦስትሪያዊ ተማሪ፣ በ 16 ዓመቱ የባችልር ዲግሪ አገኘ።

የቪየና የሥነ-ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ትናንት እንዳስታወቀው፣ ማሪያን ኮግለር የተባለው የ 16 ዓመት ተማሪ፣ በዚህ ዕድሜው፣ የተጠቀሰውን የመጀመሪያ ዲግሪ ለማግኘት፣ በኦስትሪያ የከፍተኛ ትምህርት ማዕከላት ታሪክ ኮግለር የመጀመሪያው ነው።ኮግለር፣ ገና የ 13 ዓመት ልጅ ሳለ ዩኒቨርስቲ በመግባቱ፣ የክፍል ጓደኞቹ፤ ጉድ! እያሉ፣ በብሩኅ አአምሮው ይደነቁ እንደነበረ የጀርመን ዜና አገልግሎት ድርጅት DPA አመልክቷል። በ ኮምፒዩተር ሳይንስ፣ ባለፈው ወር የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው ለጋ ወጣቱ ማሪያን ኮግለር በመጪው የካቲት በይፋ በሚከናወን ሥነ-ሥርዓት እንደሚመረቅ ቢገለጽም፣ ወጣቱ በተያያዘው የትምህርት ዘርፍ ለመቀጠልና ሁለተኛ ዲግሪውን ከ 2 ዓመት በኋላ ለማግኘት መዘጋጀቱ ታውቋል።

የማሪያን ኮግለር ወላጆች፣ ልጃቸው ፣ ገና የ 2 ዓመት ህጻን ሳለ ማንበብ በመቻሉ ልዩ ተሰጥዖ እንዳለው ተገንዝበው ያበረታቱት እንደነበረ ታውቋል። ማሪያን ኮግለር፣ የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኘበትን የዩንቨርስቲ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ጎን ለጎን የ 2ኛ ደረጃ (ሃይ ስኩል) መደበኛ ትምህርቱን በተጨማሪ በመከታተል ላይ እያለ ነበረ። የኣንድ ዓመት ትምህርት ፈተና ለማለፍ የ 2 ቀናት ዝግጅትብቻ ያደረግ እንደነበረም ፣ አስገራሚው ተማሪ ገልጿል።

ለምርምር እንዲመጥቁ የተደረጉ ሰው ሠራሽ ሳቴላይቶች በቅርቡ እንደጠቆሙት ከሆነ፣ ፕላኔታችንን ከጠንቀኛ ጨረሮች የሚከላከለው የምድራችን መግነጢሳዊ ጋሻ፣ በሰፊው ተቦድሷል። ይህ መሆኑን የጠቆሙት የአሜሪካው የኅዋ ምርምር መሥሪያ ቤት ያሠማራቸው Themis በተሰኘው የ 5 ንዑሳን የምርምር ሳቴላይቶች አጀብ ነው። ምድራችንን፣ ከኅዋ በተለይም ከፀሐይ ከሚፈነጠቅ እጅግ አደገኛ ጨረርም ሆነ የፀሐይ ነፋስ የሚከላከለው መግነጢሳዊው ጋሻዋ ነው። አሁን በከባቢ አየር ያለው መገነጢሳዊ ጋሻዋ የመሸንቆሩ ሁኔታ እጅግ አንጸባራቂ ውጋገን እንዲከሠት ሊያደረግ ይችላል፣ ወይም፣ የሳቴላይትና የየብስ የመገናኛ አውታሮችን ተግባር ማሠነካከሉ አይቀሬ ነው። የ Themisሳቴላይቶች ሳይንቲስት የበርክሊ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ Marit Oieroset ትናንት በሳንፍራንሲስኮ ለአሜሪካ የመልክዓ-ምድራዊ ጥናት ማኅበር እንደገለጡት ፣ የምድራችን የአደገኛ ጨርረ መከላከያ መግነጢሳዊ ጋሻ የመቦደስ አደጋ በአፋጣኝ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው።

ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው፣ ከፍትፍቱ ፊቱ፣ እየተባለ ስልሚነገር፣ ጨፍጋጋነት፣ በኢትዮጵያውያንም ዘንድ እንደማይወደድ የታወቀ ነው። ፊቱን የሚያኮሳትር ወይም የሚጨፈግግ ሰው ራሱ «ሐምሌ ፊት!» እየተባለም ይተቻል። በዚህ በማዕከላዊም ሆን ሰሜናዊ አውሮፓ ቢሆን ሐምሌ ሳይሆን ታህሳስ ወይም ጥር ነው ሊባል የሚችለው። በወራቱ ቅዝቃዜ ሳቢያ ማለት ነው!

ሳቅም ሆን ፈግግታ ለራስም ለተመልካችም ደስ የሚያሰኝ ነው። ሲበዛ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ፣ ነው ፣ የሥነ-ልቡና ጠበብት የሚናገሩት።

ፊት ፈገግ፣ አፍ፣ ከንፈሮች ፈልቀቅ ብሎ ጥርስ ብልጭ ሲል አንጎል ደስታ የሚያስከትል ፈሳሽ (ሆርመን)ያመነጫል ። ይሁንና ረዘም ላለ ጊዜ ከልብ ያልመነጨ ፈገግታ ማሳየቲቱም ሆነ መገልፈጡ ጤና አይሆንም። ያለማቋረጥ መገልፈጥ እውነተኛ ስሜትን የሚያንጸባርቅ ካለመሆኑም ሌላ፣ በአንጎል ላይ ጫና በመፍጠር፣ በአካል ላይ ጤናማ ያልሆነ ስሜት ያስከትላል።

በይበልጥ ደግሞ፣ የደም ግፊትን ከመጨመርና ፣ በዑደተ-ደም ላይ ሳንክ ከመፍጠሩም ሌላ ፣ከባድ የሥነ-ልቡና መዘዝን ያስከትላል ሲሉ፣ በጃፓን የኦሳካ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ልቡና ሊቅ ማኮቶ ናትሱም ያስርዳሉ።

ራስን በማስገድድ፣ አዘውትሮ መገልፈጥ ፣ በጎ መንፈስንም ሆነ ስሜትን ያርቃል፣ አንዳንዴም ከዚያ በባሰ ሁኔታ፣ ከባድ የሥነ-ልቡና መታወክን ያስከትላል፤ ሊቁ እንዳሉት!

በተለይ ፣ በቀጥታ ከህዝብ ጋር በሚያገናኝ ሥራ (አገልግሎት)የተሰለፉ ሰዎች ፣ ለምሳሌ፣ በየብስም ሆነ በአየር እንግዶችን የሚያስተናግዱ ወይዛዝርት (ሆስተሶች)ወይም በመደብሮች ዕቃዎችን የሚሸጡ፣ ዘወትር ፈገግ ማለትም ሆነ መገልፈጥ፣ የሥራው ዓይነት የሚያስግድዳቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

ጃፓናውያን ፣ከትኅትና በመነጨ መንፈስ፣ ፈገግታ የሚያበዙ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣ ከህዝብ ጋር የሚያገናኝ ተግባር የሚያከናውኑ ዜጎቻቸው ፣ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ልዩ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። አዘውትሮ ፈገግ ማለት ተፈጥሮአዊ ሳላልሆነ ዘና ብሎ ደንበኞችን ማስተናገዱ በቂ ሊሆን ይችላል። መጠን ያለፈ ፈገግታ ግን ለአካልም ፣ ለመንፈስም ጤና የሚሰጥ አይደለም።

Smiling Faces-ፈገግታ የሚታይባቸው (ገጾች) ፊቶች አንዳንዴ እውነትን አያንጸባርቁም፣እውነትን አይናገሩም፣ ነው ያለው አቀንቃኙ!-----

የጀርመን ርእሰ-ብሔር ሆርስት ከኧለር፣ በሥነ ቴክኒክ ምርምር አሥምስጋኝ ውጤት ላስመዘገቡ 3 ግለሰቦች ሽልማት ሰጡ። እ ጎ አ ከ 1997 ዓ ም አንስቶ በጀርመን ሀገር በሥነ-ቴክኒክ ረገድ ላቅ ያለ ውጤት ላስመዘገቡ የሚሰጠው ሽልማት ፣ በኣዲስ የፈጠራ ውጤት ወይም አንድ የተፈለሰፈን ነገር ፣ይበልጥ በማሻሻልና ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ፣ በባለሙያዎች ላቅ ያለ እውቅና ያገኘ መሆን ይኖርበታል። የፈጠራው ውጤት አንዳንዴ ከጀርመን አልፎ በዓለም ዙሪያ ተፈላጊነት ያለው ፣ የአገሪቱን ኤኮኖሚም የሚጠቅም መሆን እንዳለበት ይታመንበታል።

250,000 ዩውሮ የተመደበለትን የዘንድሮውን ሽልማት የተቀበሉት፣ በምርምርና ሥነ-ቴክኒክ፣ በመሃንዲስነትና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ላይ ያተኮሩ ግለሰቦች ናቸው። ዘንድሮ፣ 3 ፕሮጀክቶች ነበሩ፣ ሽልማቱን ለማግኘት የመጨረሻ ውድድር ያደረጉት፣ «ዲጂታል ማይክሮፎን»፣ በሞቃት አገሮች በፀሐይ ኃይልየኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ አውታሮችን ጥረት ከፍ ማድረግ የሚቻልበት ዘዴ፣ እንዲሁም ፣ የሞባይሎች ፤ ኮምፒዩተር ወይም የአቅጣጫ መንገድ መሪ መሣሪያዎች መለኪያ ነበሩ። ታዲያ ከአነዚህ ከ 3 ቱ ላቅ ያለውን ሽልማት አሸናፊ የሆነው የሥነ-ቴክኒክና የፈጠራ ሥራ ዘርፍ ሆኖ ሦስት ሰዎች ከሥነ-ቴክኒክና ፈጠራ የ 2008 የመጪው ዘመን ሽልማት (Zukunftspreis) የተሰኘውን በያመቱ ከርእሰ-ብሔሩ የሚሰጨውን ሽልማት ተቀብለዋል። የመጪው ዘመን ሽልማት ሲባል መጪው ዘመን በአዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች የተሻለ በሩኅ መጻዔ-ዕድል ያለው መሆኑን ለማመላከት ነው። ይህ ስያሜ የተሰጠው ለ 3 ቱ ኢንጂኔሮችና ተመራማሪዎች ፣ ፕሬዚዳንት ሆርስት ከኧለር፣ ራሳቸው በማድነቅ ነበረ ሽልማቱን ያበረከቱላቸው። የጀርመኑ ርእሰ-ብሔር ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክለኤኮኖሚ ዋልታ መሆን ይገባቸዋል ብለው በጥብቅ የሚያምኑ ናቸው።

«የጀርመንን የመጪ ዘመን ሽልማት፣ በርእሰ-ብሔሩ የሚበረከተውን የ 2008 ን የሥነ-ቴክኒክና ፈጠራ ውጤት ሽልማት ለመስጠት፣ የእኔም ልብ ተሠቅሏል። አሸናፊዎቹ፣ ዶ/ር ዪሪ ማሬክ፣ ዶ/ር ሚሻኤል ዖፈንበርግና ዶ/ር ፍራንትዝ ሜልትሰር ናቸው።» (ጭብጨባ)

ኢንጅኒየር ዪሪ ማሬክና ባልደረቦቻቸው የ Bosch ኢንዱስትሪ ኩባንያ ባልደረቦች ሲሆኑ፣ ሽልማቱ የተሰጣቸው በመለስተኛ አውቶሞቢሎች ጭምር የኤሌክትሪክ ግልጋሎትን በማሻሻል ረገድ ባስመዘገቡት ውጤት ነው። ዪሪ ማሬክ እንዲህ ይላሉ---

«የኤሌክትሮኒክ ተቆጣጣሪ ፣ በኤሌክትሮኒኩ ዓለም ፣ የስሜት ተቆጣጣሪ አካል ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በተሽከርካሪዎች ፣ ፍጥነትን እንደሁኔታው ይቆጣጠራል። አደጋ ቢያጋጥሞት፣ ከመ-ቅጽበት የኤሌክትሮኒኩ አካል ፤ አደጋ መከላከያው Airbag ተፈናጥሮ ተገቢውን ህይወት የመታደግ ተግባር ይፈጽማል። »

የቦሽ ኢንዱስትሪ ኩባንያ ባልደረቦች የሠሩት ኢምንት የኤሌክትሪክ ተግባር መቆጣጠሪያ መሣሪያ ፣ ህዝብ በሰፊው ሊገለገልበት የሚችል መሆኑን ዪሪ ማሬክ ይናገራሉ።--

«ሞባይል ስልኮች፣ «ላፕቶፕ» ኮምፒዩተሮች፣ በጣትም ሆነ (ማውስ በምትባለው መሣሪያ የሚፈልጉትን ለማግኘት መነካካት ይኖርቦታል። በዚህ ዓይነት መገልገሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባድ እየሆነ ነው የተገኘው። ስልሆነም የፍለጋ እንቅሥቃሴን ለማሻሻልና አጠቃቀሙን ለማቃለል እንሻለን። በንግግር ላይ እያለሁ፣ ሞባይል ስልኬ ቢደውል፣ «የሚረብሸኝ አልፈልግም» በማለት ሞባይሉን ፊቱን ገልብጬ አስቀምጠዋለሁ። እናም መደወሉን፣ ማቃጨሉን ያቆማል። ይጠፋል ማለት ነው። ወይም ፣ ወደፊት--ከሩቅ፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራም መጀመሪያ ፣ ማጥፊያና መለዋወጫ መሣሪያ በመነካካት ሳይሆን በአካል እንቅሥቃሴ በመራመድ እንዲጠፋ ወይም የድምፁ መጠን እንዲቀነስ ፣ ይህንና የመሳሰለውን ማድረግ ይቻላል ማለት ነው። »

ቀደም ሲል እንደገለጽነው፣የቦሽ ፋብሪካ አባላት የሽልማቱ አሸናፊ ለመሆን የበቁት ከሌሎች 2 የፈጠራ ውጤት ካቀረቡ ወገኖች ጋር ተወዳድረው ነው። የሳይንስና ኤኮኖሚ ጉዳይ የምርምር ውጤቶች ታዛቢዎች ሊቀ-መንበር ፣ የበርሊን ብርንደንቡርኽ የሳይንስ አካዳሚ ፕሬዚዳንት Guenter Stock ሁሉም ፣ ሦስቱም የውድድር ተካፋዮች አሥመስጋኝ ተግባር ማከናወናቸውን ሆኖም ሽልማቱን ለአንድ አሸናፊ ብቻ መሰጠት ግድ መሆኑን ነበረ የገለጹት።--

«እንደሚመሰልኝ ጠቃሚው ውሳኔ፣ የፈጠራ ውጤት ሰፋ ያለ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ፣ ከፊል ችሎታ ብቻ ነው፣ ውጤት እያሳዬ ያለው። በህክምናው ዓለም፣ ገና የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አልተቻለም። 2ኛ፣ በሥነ-ቴክኒክ ፈጠራ፣ ጥረቱ መቀጠል ያለበት ነው። 3ኛ፣ በጀርመን ሀገር የሠራተኞች ክፍት የሥራ ቦታ የሚፈጠርበት ሁኔታ ሊታሰብበት የሚገባ ነው።»

ተሸላሚዎቹን የሚመርጠው አካል በኢንዱስትሪ ኩባንያዎች ተጽዕኖ ይኖረው ይሆናል ስልሚባለው ጥርጣሬ፣ ጉዑንተር እሽቶክ ፣ ተሸላሚዎችን የሚመርጠው አካል ፍጹም ነጻ ነው በማለት አንዳች ጥያቄ ሊኖር አይገባም ማለታቸውም ተጠቅሷል።

በመጨረሻ፣ ፕሬዚዳንት ሆርስት ከኧለር ፣ አሁን ዓለምም ጀርመንም ከተደቀነባቸው የኤኮኖሚ ቀውስ አንጻር ፣ ለትምህርትና ምርምር ጠንከር ያለ ድጋፍ እንዲሰጥ አሳስበዋል። መጪውን አዲሱን 2009 ዓ ,ም, አስታከውም፣ አንዲህ ብለዋል---

«ቀውስ ላይ ነው ያለነው። መጪው ዓመት ከባድ ነው ፣ ነገር ግን አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ይከሠታሉ። ሐሳቦች ይፈልቃሉ የህዝቡ ተስፋ ያንሠራራል። እናም ጀርመን አትወድቅም።»