ዓመታዊው  የወባ በሽታ ዘገባ | ጤና እና አካባቢ | DW | 14.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ዓመታዊው  የወባ በሽታ ዘገባ

የዓለም ጤና ድርጅት፣ «WHO» ሰሞኑን ያወጣው ወባን የተመለከተው ዓመታዊ ዘገባ ተስፋ የሚሰጥ ነው። ይሁንና፣ በፀረ ወባ በሽታ ትግል አኳያ ገና ብዙ መሰራት ያለበት ነገር እንዳለ «WHO» አስጠንቅቋል።  ወባ አሁንም፣ በተለይ ፣ ከሰሀራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት ውስጥ አሳሳቢ የጤና ችግር እንደሆነ ይገኛል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:19
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:19 ደቂቃ

ፀረ ወባ ትግል

በዚህ ዓመት የወጣው ዘገባ አንድ አዎንታዊ መልዕክት ይዞዋል፣ ይኸውም አንዳንድ ሃገራት እንዳሳዩት ወባን ማጥፋት ይቻላል። አስር ሃገራት ውስጥ በ2015 ዓም በወባ ተይዘዋል ብለው  የመዘገቧቸው ሰዎች ቁጥር ከ150 ያነሰ፣ ሌሎች ዘጠኝ ደግሞ በ150 እና በ1,000 መካከል ነበሩ። በዚህም የተነሳ ወባን ቢያንስ በአስር ሃገራት ውስጥ እጎአ እስከ 2020 ዓም ድረስ ማጥፋት እንደሚቻል  የዓለም ጤና ድርጅት  እምነቱን ገልጿል። ይህን ዓላማ ለማሳካትም ለሕጻናት እና ለነፍሰ ጡሮች የሚደረገውን ክብካቤ ማሻሻል ወሳኝ ሚና እንደሚይዝ የዓለም ጤና ድርጅት  የወባ መከላከያ ጉዳይ ተመልካች ክፍል ኃላፊ ዶክተር ፔድሮ አሎንዞ ይናገራሉ።
« ይህም ፣ ሕጻናትና እና ነፍሰ ጡሮች በጤና ማዕከላት ውስጥ ትክክለኛውን ምርመራና አስፈላጊውን ህክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማሻሻልን ያካትታል። »


እንደ አሎንዞ አመለካከት፣  የዓለም ጤና ድርጅት በዚሁ ረገድ ውጤታማ ሆኗል፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ህክምና ያገኙት ሰዎች ቁጥር በ77% ጭማሪ አሳይቷል፣ በእርግዝና ወቅት ሦስት ጊዜ  ወባ መከላከያ ህክምና ያገኙት ቁጥር በአምስት እጥፍ፣ ፀረ ወባ ትንኝ መድሀኒት የተረጨባቸው አጎበሮች ያገኙትም ሰዎች ቁጥር በጉልህ ጨምሮዋል።  ይህንን በማዳረሱ ረገድ ግን ከሰሀራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት ውስጥ አሁንም ክፍተት እንደሚታይ፣ በሰበቡም ለወባ የሚጋለጡት ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ አዎንታዊዉ ውጤት ላይ ጥላ እንዳጠላበት አሎንዞ ገልጸዋል።  
« አሁንም በየዓመቱ 400,000 ሰዎች በወባ ሰበብ ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም 200 ሚልዮን ሰው በበሽታው ተይዟል።  ስለዚህ ጊዜው እፎይ ተብሎ የሚቀመጡበት አይደለም።  መሸፈን ያለብን ግዙፍ ክፍተቶች አሉ። »


እስከ 2020 በወባ የሚያዘውን ሰው ቁጥር በ40% የመቀነስ ስልት እንዲወጣ የዓለም ጤና ድርጅት የወባ መከላከያ ጉዳይ ተመልካች ክፍል ጥሪ አቅርቧል። ይሁንና፣ ብዙ ሃገራት ይህን ለማድረግ አቅሙ ጎድሏቸው ይገኛል። በዓለም ጤና ድርጅት መሠረት፣ ይላሉ ዶክተር ፔድሮ አሎንዞ፣ ወባ ከሚታይባቸው 91 ሃገራት እና አካባቢዎች መካከል ከግማሽ የማይበልጡት ናቸው ይህን ዓላማ በማሟላቱ መንገድ ላይ የሚገኙት።
«  ዓለም  ይህን ክፍተት ለመዝጋት  ገንዘብ ያስፈልገዋል፣ ሆኖም ለወባ የተመደበው ወጪ ባለፉት አምስት ዓመታት ጭማሪ አልታየበትም። ይህ ለጋሾች ለዓለም አቀፍ መርሃግብር  የሰጡትን እና በበሽታው የሚታይባቸው ሃገራትም የመደቡትን ወጪ ይመለከታል። »
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው፣ ፀረ ወባ ክትባት ሁኔታዎችን ሊቀይር ይችል ይሆናል። « ክትባቱ በዓለም በገዳይነቱ በሚታወቀው እና በአፍሪቃ በተስፋፋው የወባ ትንኝ አንፃር እንደሚሠራ ቢታመንም፣ ከፊል ከለላ ብቻ እንደሚሰጥ ነው ዶክተር አሎንዞ ያስረዱት። ለአሁኑ ግን አስተማማኞቹ የወባ መከላከያ ዘዴዎች አጎበሮች እና ተባይ ማጥፊያው መድሀኒት ብቻ ናቸው።  

ፋብያን ሽሚት/አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic