ዓመታዊው የኤሌክትሮኒክስ ዐውደ-ርእይ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 21.01.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ዓመታዊው የኤሌክትሮኒክስ ዐውደ-ርእይ

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት(WHO) ዘመናዊ ሥልጣኔ ያጎናጸፈው ምቾት እስከምን ድረስ ለቅሥፈት እንደሚዳርግ ሲያስጠነቅቅም ሆነ ሲያሳስብ፤ «የሥልጣኔ በሽታዎች» ባላቸው የበሽታ ዓይነቶች ሳቢያ በያመቱ ምን ያህል ሰዎች እንደሚሞቱ በሚያወጣው መዘርዝር ጥናት ላይ ያሳያል።

ከዓመት ዓመት፣ ቁጥሩ እየጨመረm መኼዱንም ለመገንዘብ አያዳግትም። ከ 2 ዓመት ገደማ በፊት 38 ሚሊዮን ሰዎች ናቸው በልብ ድካም፤ ወይም በስኳር በሻታ ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡት። ከእነዚህም መካከል ከሞላ ጎደል ገሚሱ ፤ ለምሳሌ ያህል 16 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት 70 ዓመት ሳይደፍኑ ነው ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉት። የሞቱትም፤ በካንሠር፤ በልብ ድካም፤ በሰውነት ውስጥ፤ የደም የዝውውር ሳንክ ፤ እና በስኳር በሽታ ነው። የ WHO ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ወ/ሮ ማርግሬት ቻን ፣ አብዛኛው አደጋ ሊገታ የሚችል በመሆኑ፤ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ፣ ቁርጠኛ የሆነ አቋም በመውሰድ ተግቶ ቢሠራ እንደሚበጀው ሳያሳስቡም ሆነ ሳያስጠነቀቁ አልቀሩም ።

ድርጅቱ እንደሚያስገነዝበው ከሆነ ፤ ከመደበኛ በሽታዎች ይልቅ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በቀላሉ ሊገቱ የሚችሉት ናቸው የጤና ጠንቆች የሆኑት። ይህ የሥልጣኔ በሽታ የተባለው ፤ በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት ሃገራት ባልተናነሰ፤ ምናልባትም በባሰ ሁኔታ በአዳጊ አገሮችና ከዚያም ትንሽ ላቅ ባለ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገሮች ሆኗል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው። ትምባሆ፤ የአልኮል መጠጥና አለመንቀሳቀስ ለተጠቀሰው የሥልጣኔ በሽታ ሰፊ ድርሻ አላቸው። በምግብ ላይ ጨው ማብዛትና የደም ጋፊት ማየልም፤ ዕድሜን እንደሚያሳጥሩ የሚያጠራጥር አልሆነም። እ ጎ አ እስከ 2025 በዚሁ የሥልጣኔ በሽታና ፍጻሜው ሳቢያ በሚያድጉ አገሮች የ 7 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሣራ ማስከተሉ የማይቀር ነው።

ታዲያ ፣ ተደጋጋሞ የሚሰጠው ምክርም ሆነ ማስጠንቀቂያ ችላ ስለሚባል ሊሆን ይችላል፣ የሥነ ቴክኒኩ ዓለም ተጨባጭ ያለውን ማስገንዘቢያ ይዞ ለመቅረብ የተገደደው። በያመቱ ፣ ከጥር እስከ ሚያዝያ በሚካኼዱ 3 ዓለም አቀፍ የኮምፒዩተርና መሰል የረቂቅ መሣሪያዎች ትርዒት የተጠቀሰው ማሳሰቢያ ፣ በተጨባጭ ሁኔታ እያጎላ በሚያሳይ ዐውደ ርእይ መታገዙ አልቀረም።

በዚህ በአውሮፓ ፣ ባርሴሎና ፤ እስፓኝ ውስጥ፤ ከየካቲት 23-26 Mobile World Congress ቀጥሎም በጀርመን ፤ ሓኖፈር ከተማ ውስጥ ከመጋቢት 7-11 ,2007 CEBIT በሚል ምሕጻረ ቃል የሚታወቀው ዓመታዊ ግዙፍ የኤልክትሮኒክስ ዐውደ ርእይ ከመቅረቡ በፊት ፣ በጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት የወር መባቻ ውስጥ ላስ ቬጋስ ፤ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚታየው ቀዳሚው Consumer Electronics Show (CES) ትርዒት፣ ዘንድሮም ፣ ከታኅሣሥ 28 እስk ጥር 1 ቀን 2007 ዓ ም አያሌ የኤሊክትሮኒክስ ውጤቶችን ለህዝብ እንዲታይ አድርጎ ነበር። በዚያ ፣የኤሌክትሮኒክስ ዐውደ ርእይ ላይ ከ 10 ያላነሱ በዋናነት የሚጠቀሱ ፣ የረቂቅ ኤልክትሮኒክስ ውጤቶች መቅረባቸውም ነው የተገለጠው። የረቂቅ ሥነ ቴክኒክ ውጤቶች ከሆኑት ትልልቅ መሣሪያዎች መካከል

1,በተለያየ ቅርጽ የተሠሩ አብራሪ የለሽ አይሮፕላኖች (Drones)

2, እጅግ ዘመናዊ የተሰኙ በስዕላቸው ጥራት የታወቁ ቴሌቭዥኖች፤ ለምሳሌ ያህል፣ «ሳምሱንግ» የተሰኘው የደቡብ ኮሪያው ታዋቂ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ፣ ጥራት ብቻ ሳይሆን 103 አጽቅ(ኢንች) ወርድ ያለው የሚታጠፍ ቴሌብዥን አቅርቦ አዳዲስ ውጤቶችን የሚያደንቁ ተመልካቾችን ማስደመሙ አልቀረም።

3, በግዙፉ ማለትም ፤ 204,386,688 ካሬሜትር ስፋት ባለው የዐውደ ርእይ ቦታ፣እጅግ ዘመናዊ የተሰኙ አውቶሞቢሎችም ቀርበዋል። የጀርመኑ ሜርሰደስ ቤንዝ ፤ በላስ ቬጋስ ጎዳና ያለ ዘዋሪ የሚሽከረከር አውቶሞቢል አቅርቦ ነበር። BMW i 3 ሙሉ አውቶማቲክ ተሽከርካሪ ያለአሽከርካሪ ተንቀሳቅሶ በአውቶሞቢሎች ማቆሚያ ሥፍራ ቦታ ፈልጎ ያላንዳች ሳንክ መቆም እንደሚችል አሳይቷል።በተመሳሳይ ሁኔታ አውዲ አውቶሞቢልም ይህን ማድረግ እንደሚችል በዐውደ ርእዩ ላይ ለመታዘብ ተችሏል።

እንዲሁም የደቡብ ኮሪያው ሂዩንዴይ፣ የተለያዩ የአውቶሞቢል ክፍሎች በልዩ የእጅ ሰዓት ትእዛዝ የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ አሳይቷል።

የስዊድኑ ቮልቮም ከኤሪክሰን ኩባንያና ከአንድ የእስፖርት ድርጅት ጋር በመተባበር፣ ከብስክሌተኞች የእጅ ስልክ አቅጫጫ አመላካች መሣሪያ አንዴት ማስጠንቀቂያ መልእክት መቀበል እንደሚቻል አሳይቷል። ከብስክሌተኞች ቆብ ብርሃን ይንጸባረቅና፤ ፊት ለፊት የሚመጣ ቮልቮ ተሽከርካሪ ካለ ስልኩ የመንቀጥቀጥም ሆነ የንዝረት ምልክት ይሰጣል። ሆኖም ፤ ገበያ ላይ ከመዋሉ በፊት ቆቡ አሁንም ተጨማሪ ፍተሻ እንደሚያሻው ቮልቮ አስታውቋል።

በዚያው CES የተጠቃሚዎች የኤልክትሮኒክስ ዐውደ ርእይ፤ የስፌት መኪናም፤ በካሜራ ርዳታ ፤ ቅድን ፣ ጥለትን እንደ መራጩ ፍላጎት አሳምሮ ራሱ መስፋትም መጥለፍም እንደሚችል ታይቷል።

4, ለአጭር ርቀት ፣ በአንድ፤ በሁለትና ሦስት ጎማዎች ሰዎች የሚጓዙባቸው ተሽከርካሪዎች

5, እንደ እጅ ሰዓትም ሆነ አምባር ጌጥ መስለው የተለያዩ ተግባራትን የሚፈጽሙ ንዑሳን መሣሪያዎች

በእንግሊዝኛ Wearables የሚሏቸውን ማለት ነው፣ እነዚህንና የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። እዚህ ላይ wearable computer የሚሰኘው፤ ለስፖርተኛ እንደ አሠልጣኝ፣ ለሕመምተኛ እንደ ነርስ በመሆን ፤ የልብ ትርታን ፣ የደም ግፊትን፤ የንፁህ የሚተነፈስ አየር ኦክስጂን መጠንን ይህንና የመሳሰለውን በመለካት አገልግሎት መስጠት የሚችል «ዲጂታል» መሣሪያ ነው።

የዓይን መንጽር ተንቀሳቃሽ ምስልና የመሳሰለው የሚታይበት ኢምንት የቴሌቭዥን ሣጥን ሆኖም ያገለግላል። ገላ ላይ የሚያርፍ ልብስም ኢምንት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ታክሎበት ተጨማሪ የተለያየ ተግባር ያከናውናል፤ የሙዚቃ ማድመጫም ሆኖ ያገለግላል።

በሥነ ቴክኒክ መራቀቁ ፤ አንዳንድ ሁኔታዎች ቅንጦት ይምሰሉ እንጂ በዘመኑ ለሚከሠቱ የተለያዩ ችግሮች መፍትኄ የማቅረቡ ፉክክርና ትብብር የሚደነቅ ነው። በባርሴሎና እስፓኝ ፣ ከዚያም በሃኖፈር ፤ ጀርመን ዘንድሮ ምን ተጨማሪ አዳዲስ የኤልክትሮኒክስ ውጤቶች ይቀርቡ ይሆን ፤ ጊዜው ሲደርስ የምንመለከተው ይሆናል።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic