ዓለም አቀፍ ፀረ ግርዘት መታሰቢያ ቀን | የጋዜጦች አምድ | DW | 04.02.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዓለም አቀፍ ፀረ ግርዘት መታሰቢያ ቀን

ፀረ ግርዘት ትግል

ዓለም ውስጥ በያመቱ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጉ ሕፃናት ሴቶችና ወጣት ልጃገረዶች የግርዘት ተግባር እየተፈፀመባቸው የአካልና የሥነ አዕምሯዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል። አንዳንዶቹም በዚሁ ወቅት ሕይወታቸውን ያጣሉ። ስለዚሁ ጎጂ ልማድ ዘግናኝነት ለዓለም ኅብረተ ሰብ ንቃተ ኅሊና ለማሳደግ ሲል የተመድ በያመቱ እአአ የካቲት ስድስት ቀን የፀረ ግርዘት ቀን ተብሎ እንዲታሰብ ወስኖዋል። በዚሁ መሠረትም፡ ዕለቱ የፊታችን ሰኞ ታስቦ ይውላል። ይህንኑ ልማድ ለማስቀረት የሚታገሉት ድርጅቶጭ በጠቅላላ የዚህኑ ልማድ አስከፊነት ለማጉላት እያሉ የሚጠቀሙበት አጠራር ግርዘት የሚለውን ሳይሆን የሴቶች ብልት የሚተለተልበት ተግባር የተሰኘው ነው።
በሀያ ስምንት የአፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ዛሬም በሴቶች ላይ ዘግናኙ የግርዘት ተግባር ይፈፀማል። ምንም እንኳን የዚህኑ ልማድ ጎጂነት ለማሳወቅ ካለፉት በርካታ ዓመታት ወዲህ ግዙፍ የገለፃና የማስተማሪያ ዘመቻ ቢካሄድም ባንዳንዶቹ ሀገሮች ውስጥ ልማዱ በመወገድ ወይም በመቀነስ ፈንታ ይበልጡን እየተስፋፋ መሄዱን ለሴቶች መብት የሚሟገተው ግብረ ሠናይ ድርጅት ቴር ዴ ፋም የሚያወጣቸው ጥናቶች ያመለክታሉ። በግርዘት ተግባር የሴቶች የብልት አካል በከፊል ይቆረጣል፤ ወይም በጠቅላላ ተተልትሎ ይነሣል። በምሥራቃዊ ኢትዮጵያ እና ሶማልያን በመሳሰሉ አንዳንድ ሀገሮች ውስጥ ደግሞ ልጃገረዶችና ሕፃናት ሴቶች ዕድሜአቸው ለጋብቻ እስኪደርስ ድረስ የወሲብ ፍላጎታቸውን ለመገደብና ከወንድ ጋር እንዳይገናኙ፡ እንዲሁም ድንግልናቸው እንዳይገሠሥ እየተባለ ብልታቸው ይሰፋል። ይኸው ስፌት የሚፈታላቸው ሲያገቡ ብቻ ነው። ይኸው አሰቃቂውንና ካለማደንዘዣ የሚደረገውን የግርዘት ተግባር የሚፈፅሙት ሴቶች ገራዦች ሲሆኑ፡ ለዚሁ ኢሰብዓዉ ተግባር የሚጠቀሙበት መሣሪያ ፅዳቱ በሚገባ ያልተጠበቀ መናኛ ምላጭ ወይም ቢላ ወይም ደግሞ የጠርሙስ ስባሪ ነው። ገንዘብ ያላቸው ቤተሰቦች የሴቶች ልጆቻቸውን ግርዘት በሐኪም ቤታ ያስደርጋሉ።

በአፍሪቃ፡ በእሥያ፡ በቅርብና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች ብዙ ሕፃናት ሴቶችና ወጣት ልጃገረዶች ዕድሜአቸውን ሙሉ ግርዘት በሚያስከትለው የአካል(ለምሳሌ መሀን የመሆን ዕጣ ይደርስባቸዋል።) እና የሥነ አዕምሯዊ ጉዳት ይሠቃያሉ። በተለይ በአፍሪቃ ለሴቶች ሞት ተጠያቂው ብዙ ጊዜ የግርዘት መዘዝ መሆኑ ቢታወቅም፡ ችግሩ ከሚመለከታቸው ሀገሮች መንግሥታት መካከል አንዱም እንኳን ገራዦች ሊቀጡ የሚችሉበትን ሕግ ማውጣት አልሆነለትም፤ ሕጉ አለባቸው በሚባሉት ሀገሮችም ለምሳሌ ግብፅ ውስጥ ሕጉን ማስፈፀም ያለባቸው ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ማድረግ እየተሳናቸው ነው የተገኙት። ከግርዘት ለማምለጥ የሚፈልጉ ሴቶች ወደ አውሮጳና ዩኤስ አሜሪካ ከመሸሽ የተሻለ ሌላ አማራጭ የላቸውም፤ በዚህም የተነሣ አሁን በአውሮጳና በዩኤስ ተገን የጠየቁት የአዳጊ ሀገሮች ሴቶች አሀዝ በጉልህ ጨምሮዋል። በጥናቶቹ መሠረት፡ ለምሳሌ ሱዳን ውስጥ የሴቶች ብልት የሚተለተልበትን ባህላዊ ልማድ ይከለክልና ይህንኑ ተግባር ሲፈፅሙ የሚገኙ ገራዦችንም ለፋቀር’ብ የነበረው ሕግ ከጥቂት ጊዜ በፊት ተሽሮዋል፤ ግርዘት የሚሰኘው ርዕስም በሀገሪቱ ኅብረተ ሰብ ውስጥ በጠቅላላ ችላ ተብሎ ተገኝቶዋል። ይሁን እንጂ፡ ይህ’ንኑ ልማድ ለማስወገድ በተጀመረው ጥረት መደዳ በሌሎች አፍሪቃውያት ሀገሮች ውስጥ አዎንታዊ ሂደት መታየቱን የቴር ዴ ፋም ባለሥልጣን ወይዘሮ ፍራንሲስካ ግሩበር ሲገልፁ እንዲህ ብለዋል። « ባለፈው ዓመት የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት አንድ ትልቅ ዝግጅት ላይ ራስዋን ከሴቶች ብልት ትልተላ ላማይ ነፃ ያደረገች ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሀገር ቤኒን እንደ አዎንታዊ ምሳሌ ትጠቀሳለች። በርካታ የሀገሪቱ ገራዦችም ከዚሁ ሥራቸው እንደሚላቀቁ በመግለፅ ምልክት ይሆን ዘንድ ቢላቸውንና ሌላ የመግረዣ ዕቃቸውን ሲጥሉ ታይተዋል። ሌላ በመልካም ምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር ደግሞ ቡርኪና ፋሶ ስትሆን፡ የዚች ሀገር መንግሥት በግርዘት ሥራ ላይ ተሠማርተው የሚገኙ ሴቶች በያሉበት ታድነው እየተፈለጉ ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሕግ አውጥቶዋል። የሀገሪቱ ሕዝብም ስለዚሁ መጥፎ ልማድ ይፋውን ክርክር ጀምሮዋል። » ብለዋል። አዎንታዊ ውጤት ከታየባቸው እጅግ ጥቂት ሀገሮች መካከል ሴኔጋልና በከፊል ኢትዮጵያም ይጠቀሳሉ።
ቴር ዴ ፋም በብልት ትልተላ አንፃር የተነቃቁ ፕሮዤዎችን ከሚደግፍባቸው ሀገሮች መካከል አንድዋ ቡርኪና ፋሶ ናት። ድርጅቱ በዚሁ ድጋፉ ላይ በሀገር ውስጥ ካሉ የሴቶች መብቶች ተሟጋቾች ጋር በቅርብ ታባብሮ ለመሣቱና ኃላፊነቱንም ለሀገሬው ሰው ለመስጠቱ አሠራር ትልቁን ክብደት ይሰጣል። ከዚሁ ድጋፉ ባሻገርም በሀገር ውስጥ ስለዚሁ አስከፊ ልማድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ልጃገረዶችና ሴቶች ጋር ብቻ ስሆን፡ ከጠቅላላቅ ኅብረተ ሰብ ቡድናት፡ ከወንዶች ጋር ጭምር ውይይት ማካሄዱ ጠቃሚ መሆኑን ያስተጋባል። ግሩበር አክለው እንደገለፁትም፡ « ወጣት ወንዶች ድንግልናቸው ያልተገሰሰ ሴቶችን ለማግባት ዝግጁ ሲሆኑ፡ አባቶችም እነዚህኑ ሴቶች ልጆቻቸውን እንደ ቤተሰብ ክብር አጉዳፊ መመልከታቸውን ሲያቆሙ፡ የሀይማኖት አባቶች ግርዘት ከክርስትና ወይም ከእሥልምና ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ሲያስተምሩ፡ የመንደር መሪዎችም በመንደሮቻቸው የግርዘት ተግባር እንዲፈፀም እንደማይፈልጉ ሲያስታውቁ፡ ወጣቶችና ሽማግሌዎች፡ ወንዶችና ሴቶች ሁሉም የኅብረተ ሰቡ ክፍል ስለዚሁ ልማድ ሲወያይና ጎጂነቱን አውቆ ሲያጣጥል፡ ችግሩም የሴቶች ብቻ አለመሆኑን፡ ይኸው ልማድም ለዘለቄታው መወገድ እንዳለበት አውቆ ሲቀበል ያኔ የፀረ ግርዘቱ ትግል ፍሬ ሊያስገኝ እንደሚችል ግሩበር አስረድተዋል። ይህ አስተሳሰብ ጀርመን ሀገር ውስጥ ሊሠራ እንደሚገባው ግሩበር ሳያሳስቡ አላለፉም፤ ምክንያቱም በፌዴራዊው የመዘርዝር አዘጋጅ መሥሪያ ቤት ዘገባ መሠረት፡ የሴቶጭ ብልት ትልተላ ከተስፋፋባቸው ሀገሮች የመጡ ወደ ሀምሳ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ሴቶች ይኖራሉ፤ ብዙዎቹም የዚሁ ልማድ ሰለባ የሆኑ ሲሆን፡ ተመሳሳይ ዕጣ የሚጠብቃቸው ሴቶች ልጆችም አሉዋቸውን፡ ቴር ዴ ፋኣም ይህንን ችግር ለማስወገድ በማሰብ የጀርመን ኅብረተ ሰብ ስለዚሁ አሰቃቂ ልማድ በቂ መረጃ እንዲያገኝና በአንፃሩ እንዲታገል ለመገፋፋት ቅስቀሳ ጀምሮዋል። በአፍሪቃ፡ በእሥያ፡ በቅርብና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖሩና የግርዘት ዕጣ የሚጠብቃቸው ብዙ ሴቶች ከከግርዘት ለማምለጥ የሚፈልጉ ሴቶች ወደ አውሮጳና ዩኤስ አሜሪካ ከመሸሽ የተሻለ ሌላ አማራጭ የላቸውም፤ በዚህም የተነሣ አሁን በአውሮጳና በዩኤስ ተገን የጠየቁት የአዳጊ ሀገሮች ሴቶች አሀዝ በጉልህ ጨምሮዋል።
የተ መ የሕፃናት መርጃ ድርጅት፡ ዩኒሴፍ፡ የተ መ የሕዝብ ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት እና የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ግርዘት በሴቶች ላይ የአካል እና የሥነ አዕምሮአዊ ጉዳት የሚያስከትል፡ እንዲሁም፡ መሠረታዊ የሴቶችን መብት የሚረግጥ አሰቃቂ ልማድ በመሆኑ በሕግ እንዲከለከል ባንድነት ጥረት አንቀሳቅሰው፤ ችግሩ የሚታይባቸው መንግሥታት፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፡ የፖለቲካና የሀይማኖት ቡድኖችና የርዳታ ድርጅቶች ጋር ስለጎጂው ግርዘት በመወያየት የኅብረተ ሰቡን ንቃተ ኅሊና ከፍ ለማድረግ ተነሣሡ። በዕቅዳቸው መሠረት፡ በአሥር ዓመት ውስጥ የግርዘት ሰለባዎችን አሀዝ በጉልህ ለመቀነስና ከተቻለም ግርዘትን ጨርሶ ለማስቆም ነው የታሰበው። ግን ባለፉት ዓመታት የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፡ አሀዙ በመቀነስ ፈንታ ባንዳንድ ሀገሮች ጭራሹን እየጨመረ ነው የሄደው።