ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን | ዓለም | DW | 09.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ቀን

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን በነገዉ ዕለት ይታሰባል። ለሰብዓዊ መብቶች ያለዉ ክብር በበርካታ የዓለማችን ክፍል እየወረደ መምጣቱን ያመለከተዉ የተመድ ለዚህ ዓመት የመረጠዉ መሪ ቃል እያንዳንዱ ሰዉ ለሌላዉ መብት መከበር መቆም እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:30 ደቂቃ

አሳሳቢዉ የሰብዓዊ መብት አያያዝ

አብዛኞቻችን ዓለም ወዴት እየሄደች እንደሆነ ስናስተዉል እንፈራለን ይላል የተመድ በድረገፁ ዕለቱን አስመልክቶ ያወጣዉ መግለጫ። አያይዞም ሰብዓዊ መብቶችን ያለማክበሩ አዝማሚያ በአብዛኛዉ የዓለማችን ክፍል እየተስፋፋ መሆኑን ያመለከተዉ ይኸዉ መግለጫ፤ የጋራ ሰብዓዊነትን አጥብቆ መያዝ እንደሚገባም ያሳስባል። የጥላቻ መልዕክቶች እና አለመቻቻል ስጋቱን እንደሚያባብሱት በማመልከትም፤ ሰብዓዊ ዕሴቶች ጥቃት እየደረሰባቸዉ መሆኑንም የተመድ አመልክቷል። አምነስቲ ኢንተርናሽል በበኩሉ ዕለቱን አስመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ በበርካታ ሃገራት ዉስጥ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ሕይወታቸዉን እያጡ መሆኑን አስታዉቋል። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ብቻም በመላዉ ዓለም ከ150 የሚበልጡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተገድለዋል። አምነስቲ እንደሚለዉ በመላዉ ዓለም በአሁኑ ወቅት ጭቆናዉ ከፍ ብሏል። ሩሲያ ዉስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ ጫና እንደሚደረግባቸዉ ሩሲያዊዉ የመብት ተሟጋች ግሪጎሪ ኦኮቶኒ ይናገራሉ። «የጥሩ እና የትክክለኛ ነገሮች ተሟጋቾች በበርካታ ሃገራት ወደጎን እየተገፉ ነዉ። ይህንንም ዘር መሠረት ያደረገ ጥርጥርን ፈጥረዉ በከፋ ሁኔታ ላደጋ የተጋለጡት ወገኖችን ችላ ብለዉ ስልጣን ላይ መቆየት የሚፈልጉ አካላት ናቸዉ የሚያደርጉት።»

«ስማችንን ያጠፋሉ፤ የመንግሥት ጠላት ወይም የሽብር ደጋፊዎች ይሉናል» ይላሉ ኦኮቶኒ። የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን አሉታዊ ዘገባ እንደሚያቀርቡ፤ የተቃዉሞ ሰልፎችም በየቢሮዋቸዉ ደጃፍ እንደሚካሄዱም ይናገራሉ። እሳቸዉ እንደሚሉትም ሰልፈኞቹ ቁጣን ተላብሰዉ የተለያዩ ርምጃዎችን ሲወስዱም ፖሊስ ጣልቃ አይገባም። በሩሲያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሃገራትም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለጥቃት መጋለጣቸዉን አምነስቲ ኢንተርናሽና አመልክቷል። አንዳንዶቹም የዉጭ ሃገራት ወኪሎች በሚል ተፈርጀዉ ተዘግተዋል። ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑን የተመድ ተቋማት እና ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ICC መጠናከር እንደሚኖርባቸዉም ያሳስባል።

ራሱ አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በቀጣይ ዓመታት ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በቂ ከለላ ማድረግ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እንደሚሻም ገልጿል። በመላዉ ዓለም የሚገኘዉ ሲቪሉ ኅብረተሰብም የሰብዓዊ መብቶችን እና የመብት ተሟጋቾችን ከጥቃት እንዲከላከልም ጥሪ አቅርቧል። ባለፈዉ ዓመት የአምነስቲን ጥሪ በመቀበል 3,7 ሚሊየን ሕዝብ በጽሑት መንግሥታት ኢፍትሃዊነቱን እንዲያቆሞ ጠይቋል።

ይህን ዕለት በማስመልከት የጀርመን የሰብዓዊ መብት ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገሪቱ ስላለዉ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዘገባ አዉጥቷል። ተቋሙ ጀርመን ከሌሎች የአዉሮጳ ኅብረት ሃገራት በተለየ በሰብዓዊነት ቁጥራቸዉ ከፍተኛ የሆነ ስደተኞችን በመቀበል ግዴታዋን መወጣቷ አንድ ነገር መሆኑን ቢያመለክትም፤ ዘረኝነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች መድረሳቸዉን በአሉታዊነት በዘገባዉ ጠቅሷል። ዶክተር ፔትራ ፎልማር ኦቶ በርሊን የሚገኘዉ የጀርመን የሰብዓዊ መብቶች ተቋም የጀርመን እና አዉሮጳ ዘርፍ ኃላፊ ናቸዉ።

«ጀርመን የአዉሮፓ የጥገኝነት ስርዓት በተሽመደመደ ወቅት ወደእኛ የመጡ ሰዎችን ለማስጠጋት በመወሰን ሰብዓዊ ግዴታዋን ተወጥታለች። ነገር ግን እዚህ ላይ ጥላ ያጠላ አሉታዊ ተግባርም አለ፤ ለምሳሌ የዘረኝነት ጥቃቶች መጨመር ወይም ለተሰደዱ ሰዎች የመኖሪያ እና ክብካቤ እጥረት መኖሩን መጥቀስ ይቻላል።»

የተመድ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ሁሉም ጥብቅና መቆም እንዳለበት ባሳሰበበት በዚህ ዓመት የሰብዓዊ መብቶች ዕለት መልዕክቱ፤ ከየግል የሚጀምረዉ የሰብዓዊ መብቶችን የማስከበር እንቅስቃሴ፤ የስደተኞችን ወይም ጥገኝነት ፈላጊዎችን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን መብት ወደማስጠበቅ መሸጋገር እንደሚኖርበት አሳስቧል።  

ሸዋዬ ለገሠ/ ኒና ቬርክሆይዘር

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic