1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት እና የማህበራዊ መድረኮች

ሐሙስ፣ ጥር 13 1996
https://p.dw.com/p/E0g1
በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረው እና በህንድ ከተማ በሙባይ ሲካሄድ የሰነበተው ዓለም አቀፍ መድረክ ትላንት ተጠናቀቀ ። ምንም ውሳኔዎችን ሳያስተላልፍ የተጠናቀቀው ይኸው መድረክ ድንበር የለሹን የኤኮኖሚ ስርዓት የሚቃወም ሲሆን ሰልፍም ተካሂዶበታል ። በሌላ በኩል ብልፅግና እና ፀጥታ በሚል መሪ መፈክር ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሃብት መድረክ በስዊዘርላንድ የመዝናኛ ደሴት በዳቮስ ትላንት ተጀምሯል ።

ድንበር የለሹ የኤኮኖሚ ስርዓት መኖር የለበትም የሰውን ልጅ ሰብአዊ መብት ይጻረራል በሚል ተቃውሞው እየተጋጋለ የመጣው እአአ በ1999 ዓ.ም ነበር ። የተዳቀሉ እና ሰው ሰራሽ ምግቦች በነጻው የገበያ ስም ወደ ታዳጊው ዓለም እንዳይሰራጭ እንዲሁም የስደተኞች መብትን ዋናው መነሻ አድርጎ ከሲያትል የተጀመረው ይህ ተቃውሞ ዛሬ የልዩ ልዩ መድረኮችን አጀንዳ ይጋራል ። እ.አ.አ በ2001 ዓም መካሄድ የጀመረው ዓለም አቀፉ የማህበራዊ መድረክም ከውልደቱ ጀምሮ ድንበር የለሹን የኤኮኖሚ ስርዓት እንደተቃወመ ነው ። አንድ መቶ ሺ ሰዎች ከአንድ መቶ ሃምሳ ሁለት ሃገራት የተካፈሉበት የሰሞኑ መድረክም ይህንኑ የድንበር የለሽ የንግድ ስርዓት ሲቃወም ሰንብቷል ። በተለይ ትላንት ጉባኤው ሲጠናቀቅ ጉባኤውን ያስተናገደችው እና ቀድሞ ቦንቤ በመባል ስትጠራ የነበረችው ሙባይ ከተማ በበርካታ ሺ ሰልፈኞች ተጣባ ነበር ። ሰልፈኞቹ የተቃወሙት ድንበር የለሹን የንግድ ስርዓት ብቻ አልነበረም ። የፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽን ምስል በትላልቅ ሰሌዳ ለጥፈው የወጡት ሰልፈኞች የኢራቅን ጦርነት መቃወማቸውን ይገልፁ ነበር ። ዩናይትድስቴትስ እና ብሪታንያ ከኢራቅ ምድር እንዲወጡ ጠይቀዋል ። ቶኒ ብሌርን እና ጆርጅ ቡሽን ሰው በላ ጨካኞች ብለዋቸዋል ።

ለስድስት ቀን የተካሄደው የማህበራዊ መድረክ ጉባኤ ዘንድሮ ሲካሄድ ለአራተኛ ጊዜ ነበር ። ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታት ጉባኤውን ያስተናገደችው የብራዚላዊቷ ከተማ ፖርቶ አልጌር ነበረች ። ዘንድሮ ወደ ህንዷ ከተማ ሙንባይ እንዲዛወር የተደረገበት ምክንያት የድንበር የለሹን ስርዓት ተቃውሞ በእስያ ውስጥ የበለጠ ለማጠናከር እንደሆነም ተነግሮለታል ። ጉባኤው ከኢራቅ ጉዳይ እስከ ግብርና ምርት ሲመክር እና ሲዘክር ቢሰነብትም የተጠናቀቀው የአቋም መግለጫ ወይም ውሳኔዎችን ሳያስተላልፍ ነው ። የማህበራዊው መድረክ በሙባይ ከተማ ሲጠናቀቅ ዓለም አቀፉ የምጣኔ ሃብት መድረክ ደግሞ በስዊዘርላንዷ የመዝናኛ ከተማ በዳቮስ በተመሳሳይ ቀን ተጀምሯል ። ይህኛው መድረክ ግን የዓለም የንግድ እና የምጣኔ ሃብት ምን ያህል አድጓል የሚለው ጥያቄ የሚያስደስታቸውን የዓለም ልዑካን አሳትፏል ። የመድረኩ መስራች እና ሊቀመንበር ክላውስ ሽዋብ እንደተናገሩት በዓለም ፀጥታ እና ሰላም ከሌለ ብልፅግና የለም ። ብልፅግና ከሌለም ሰላም የለም ። ስለሆነም ይላሉ ሊቀመንበሩ የዳቮስ ጉባኤ ቀመር ፀጥታ ሲደመር ብልፅግና ሲደመር ሰላም ነው ።

በዚህ ቀመር የተጀመረው ጉባኤ የዓለምን የኤኮኖሚ እድገት ይመረምራል ፤ የንግድ ስርዓቱ አካሄድን ይገመግማል ። የኤኮኖሚ ጠበብቶች እንደሚሉት ባለፈው የአውሮጳውያን ዓመት ብልፅግና የታየባቸው ሃገሮች ተብለው የሚወሰዱት ቻይና እና ዩናይትድስቴትስ ናቸው ። የእስያ ቁንጮ ለመሆን እየበቃች ያለችው ቻይና የስምንት ነጥብ አምስት በመቶ የኤኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች ። በአንጻሩ የዩናይትድስቴት ኤኮኖሚ የበለፀገ ነው ቢባልም የዋዠቀ ኤኮኖሚ በመሆኑ ከራሱ አልፎ በዓለም የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ ተፅዕኖ እያመጣ ነው ። በበገባችበት ጦርነት እና በምትከተለው የበጀት አጠቃቀምብክንተ የተነሳ የተረጋጋ ኤኮኖሚ አላት ማለት እንደማይቻል ባለሙያዎቹ ጨምረው ገልፀዋል ። በኤኮኖሚ ዕድገት በዓለም የሁለተኝነቱን ተርታ ይዛ የምትገኘው ጃፓንም ባለፈው ዓመት በሁለት በመቶ ዕድገት ማሳየቷ ሲገለፅ በዚህ ዓመትም ዕድገቱ ሊቀጥል ይችላል ተብሏል ። ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው ያለባትን የበጀት እጥረት ለማስወገድ ጥረት ካደረገች ብቻ ነው ። እንደ ምጣኔ ሃብት ጠበብቶቹ ትንተና የአውሮጳ ክፍለ ዓለም በአዝጋሚ የኤኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ትገኛለች ። ምክንያቱ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራትን ያስተሳሰረው የጋራ ገንዘብ የዩሮ ምንዛሬ ዋጋ ከሚገባው በላይ መጨመር ነው ። በሌላ በኩል የመስከረም አንዱን የአሸባሪዎች አደጋ ተከትሎ ወድቆ የነበረው የባንኮች ፣ የዋስትና ኩባንያዎች እና የበጀት ተቆጣጣሪ ድርጅቶች የተሻለ ሥራ እና ዕድገት እያሳዩ እንደመጡ ተነግሯል ። ዕድገቱ መኖሩ ጥሩ ነው የሚሉት እና በዳቮስ ጉባኤ የህዝብ ዓይን ሆነው የተቆጠሩት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች ግን ዕድገቱ የሰው ልጆችን ሰብአዊ መብትም ያከበረ እንዲሆን ይሻሉ ። የህዝብ ዓይንነታቸውን ለማሳየትም በጉባኤው ላይ ይህን ማንፀባረቃቸው ይጠበቃል