ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴ መድረክ | ዓለም | DW | 25.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴ መድረክ

ባንጋላዴሺያዊዉ የጋዜጠኝነት መምሕር ራጂ «ብዙዉ ነገር አስደሳች፤ ጠቃሚ፤ አስተማሪ» ይለዋል።ሁሉም ግን የሁለቱን ርዕሶች ያክል አልሳቡትም።የመጀመሪያዉ «ከጦር ሜዳ ሥለ መዘገብ የተደረገዉ ክርክር ነዉ።» ይላል የ44 ዓመቱ የቺታጎንጎ ዩኒቨርስቲ መምሕር።ሁለተኛዉ ማሳሰቢያ ብጤ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:10
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:10 ደቂቃ

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴ መድረክ

ዶቸ ቬለ በየዓመቱ የሚያዘጋጀዉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ዘዴ መድረክ ወይም ጉባኤ የዘንድሮዉ ትናንት ተጠናቀቀ።ካለፈዉ ሰኞ ጀምሮ ሰወስት ቀን በዘለቀዉ ስብሰባ፤ ዉይይት፤ ክርክርና የሐሳብ ልዉዉጥ ላይ ከአንድ መቶ ሐገራት የተወከሉ 2000 ያሕል ጋዜጠኞችና የመገናኛ ዘዴ ባለሚያዎች ተካፍለዋል። እንግዶቹ በሰወስት ቀን ቆይታቸዉ ከሠላሳ በሚበልጡ አዉድ ጥናቶች ላይ ተካፍለዋል።ዶቸ ቬለ ለአምደ መረብ (ኢንተርኔት) ጋዜጠኞች ወይም ብሎገርስ እና ለፕረስ ነፃነት ለሚታገሉ በየዓመቱ የሚሸልመዉ «BOBS» የተሰኘዉ ሽልማትም ለዘንድሮ አሸናፊዎች ተሰጥቷል።

የሰወስት ቀን የቦን ቆይታዉን «ማራኪ» ይለዋል። ሑሴይን ዳዉድ።ኢራቃዊ ጋዜጠኛ ነዉ።የሠላሳ ዓመት ወጣት።እንደ ሁለት ሺሕ የሙያ ተጋሪዎቹ ሁሉ በተለያዩ ርዕሶች ላይ የተደረጉ ዉይይት ክክርክሮችን አድምጧል።ተንግሯል፤ ተካፍሏልም።የሚያዉቅ-የሚመስለዉን እንዳማያዉቅ አወቀ፤ ወይም በቅጡ ተረዳ።

«ሥለ ዉጪ መርሕ፤ ሥለ መገናኛ ዘዴዎች እና ሥለ ዲጅታል ዘመን የሚያወሱ ብዙ ጉዳዮችን አንብቤ ነበር።» አለ ሑሴይን በስተ ጉባኤዉ ማብቂያ ትናንት።«ይሕ ጉባኤ ግን»- ቀጠለ ኢራቃዊዉ ጋዜጠኛ« ሥለዚሕ ርዕሥ የተሻለ ሥዕል፤ የተሻለ ዳራ አግኝቼበታለሁ።»

የዘንድሮዉ መሪ ርዕስ «መገናኛ ዘዴ እና የዉጪ መርሕ-በዲጂታል ዘመን» የሚል ነበር።ይሕን ነዉ ሁሴይን በጣም አወቅሁ ያለዉ።ባንጋላዴሺያዊዉ የጋዜጠኝነት መምሕር ራጂ «ብዙዉ ነገር አስደሳች፤ ጠቃሚ፤ አስተማሪ» ይለዋል።ሁሉም ግን የሁለቱን ርዕሶች ያክል አልሳቡትም።የመጀመሪያዉ «ከጦር ሜዳ ሥለ መዘገብ የተደረገዉ ክርክር ነዉ።» ይላል የ44 ዓመቱ የቺታጎንጎ ዩኒቨርስቲ መምሕር።ሁለተኛዉ ማሳሰቢያ ብጤ ነዉ።-

«ሥለ ድሆች ተጨማሪ ዉይይት ያስፈልገናል።ዋና ዋናዎቹ መገናኛ ዘዴዎች፤ እንደ ዶቸ ቬለ እና ቢቢሲ የመሳሰሉት ለዓለም ድሆች ብዙም ትኩረት እየሰጡትም።የሚዘግቡት ሥለ ጦርነት ትግል ነዉ።ድሆች በየዕለቱ ስለሚያደርጉት ትግል አይዘግቡም።»

በየዓመቱ እንደሚሆነዉ በዘንድዉ ሥብሰባ መሐልም ዶቸ ቬለ ለአምደ መረብ አቀንቃኞች የሚሰጠዉ BOBs የተባለዉ ሽልማት ለአሸናፊዎች ተሸልሟል። ሽልማቱ እስከ ዘንድሮ ያልነበረዉ«የዶቸ ቬለ የመናገር ነፃነት ሽልማት» የሚል አዲስ የሽልማት መስክ አዉጥቷል። የሳዑዲ አረቢያ ፍርድ ቤት እስራትና ግርፋት የበየነበት ራዒፍ በደዊ-የአዲሱ መስክ የመጀመሪያዉ ተሸላሚ ሆኗል።

የአምደ መረብ ፀሐፊ ራፊዳ ቦኒያ አሕመድ ሌለኘዋ ተሸላሚ ናት።ባለቤትዋ አቪጂት ሮይ እንደስዋዉ ሁሉ የአምደ መረብ ፀሐፊ ነበር።ባለፈዉ የካቲት ባንግላዴሽ ዉስጥ በሰዉ እጅ ተገደለ።ግድያዉ በሐይማኖት ሐራጥቃ የተገፋ እንደሆነ ተነግሯል።

የጉባኤዉ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት እንግዳ የኦክስፎድ የምርምር ቡድን የተሰኘዉ ሥብስብ መሥራች ስሲላ ኢልዎርዚይ ናቸዉ።ዓለም ብዙ ችግሮች አሉባት።ሁለቱ ግን ያሰጋሉ።

«የከባቢ አየር፤ የአየር ንብረት ለዉጥ፤የተፈጥሮ ሐብት እጥረት እና የብዝሐ ሕይወትን መስጠበቅ የምዕተአመቱ ቁጥር አንድ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ።ሐብት ክፍፍል አለቅጥ መበላለጥና ሥራ አጥነት ሁለተኛዉ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ ።ሰወስት መቶ የሚሆኑ የዓለም ሐብታሞች ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ ከሚበልጠዉ ከሰወስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ካለዉ ገቢ በላይ ያገኛሉ።ይሕ ለአመፅ ትክክለኛ ምክንያት ሊሆን ችላል።»

የዶቸ ቬለ ዋና ስራ-አስኪያጅ ፔተር ሊምቡርግ የሰወስት ቀኑ ስብሰሰና ዉይይት የመገናኛ ዘዴዎች ነፃነትን ከማጉላት ባለፍ ነፃ መገኛ ዘዴ ለሠላም ያለዉን አስተዋዕ ማሳየቱን ገልፀዋል።

«ባለፉት ሰዎት ቀናት በተደረጉት በአብዛኞቹ ዉይይቶች፤ መገናኛ ዘዴዎች፤ ነፃነት እና እሴቶች በቅርብ በተሳሰረችዉ ዓለም በሠላም አብሮ ለመኖር እስፈላጊ መሆናቸዉን መረዳት ችለናል።» እና ስራ አስኪያጅ ሊምቡርግ አወጁ፤ ዓለም በሳላም አብሮ እንዲኖር የሚጠቅሙት ሰወስት እሳቤዎች የመጪዉ ዓመት የዶቸ ቬለ የመገናኛ ዘዴ መድረክ ርዕስ ናቸዉ።

«ሥለዚሕ የ2016 የዓለም መገናኛ ዘዴ መድረክ ጭብጥ መገናኛ ዘዴ፤ ነፃነት እና እሴቶች መሆኑን ሳስታዉቅ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል።»

እንግዶቹም ሔዱ።

ስቬን ፖይህለ/ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic