ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ  | ዓለም | DW | 24.05.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ 

ከሰኞ ግንቦት 19 2011 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ረቡዕ ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ በየዓመቱ ዶይቼ ቬለ (DW) የሚያስተናግደው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ይካሄዳል። ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ በጀርመኗ ቦን ከተማ የሚካሄደው ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ «የኃይል ለውጦች» ላይ ይነጋገራል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:13

ለ12ኛ ጊዜ በቦን ከተማ ይካሄዳል

      
 ምክንያቱም ዲጂታላይዜሽን እያደገ በመጣባቸው በርካታ አካባቢዎች በመገናኛ ብዙሃን፣ ፖለቲካው እና ማኅበረሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት እየተለወጠ በመሄድ ላይ መሆኑ እየታየ ነውና። 
«በየአቅጣጫው የሚገኙት ሕዝበኛ ፖለቲከኞች ለተዋሐደችው አውሮጳ ስጋት» መሆናቸውን ያመለከቱት የዶይቼ ቬለ DW ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር ሊምቡርግ «የመረጃን ፍሰት መቆጣጠር የኃይል መሣሪያቸው» እየሆነ መምጣቱን ያመለክታሉ። በተመሳሳይ በርካታ ፖለቲከኞች የራሳቸውን የተዛቡ መረጃዎች መንግሥት በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሃን እና በማኅበራዊ መገናኛው ትስስር አማካኝነት ማስተላለፋቸውን በመጠቆምም፤ በዚህ መካከል ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ስጋት ላይ እንደሚወድቅ አሳስበዋል። 
ለመሆኑ በመገናኛ ብዙሃን እና በፖለቲካ መካከል «ጥላቻ እና ፍቅር»  እያደገ የሚገኘው እንዴት ይሆን? እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሁለት ቀናት የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ግንዛቤዎችን ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህን አስመልክተውም ፒተር ሊምቡርግ  «ከበርካታ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ደጋፊዎች እና ተጓዳኞች ጋር ድምጻችንን በማስተባበር ትኩረት እንስባለን» ነው ያሉት።  


መድረኩንም በቀጥታ የቴሌ ግንኙነት አማካኝነት የጀርመን ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ከዶይቼ ቬለ ሥራ አስኪያጅ ጋር በመሆን ይከፍታሉ። ከዚያም የመጀመሪያው የውይይት መድረክ የመገናኛ ብዙሃን ይዞታ እንዴት እየተለወጠ በመሄድ ላይ ነው፤ ያሉት አደጋዎች እና ዕድሎችስ የቱ ላይ ናቸው? በሚለው ነጥብ ላይ በመነጋገር ይጀምራል። በዚህ መድረክ ከሚወያዩት በተፅዕኖ ፈጣሪነቱ የሚታወቀው «ኢንዲያ ቱዴይ» የተሰኘው ቡድን ተባባሪ መሥራች አሩን ፑሪ እና የጎግሉ ማርክ ፒተርስ ይጠቀሳሉ። የአክስል ስፕሪንገር ማተሚያ ቤት ኃላፊ ማቲያስ ዲዩፍነር እንዲሁም በአሜሪካን የዲጂታል ቴክኒዎሎጂ ፈር ቀዳጁ ጃረን ላኒየርም ንግግር ያደርጋሉ። 
የመድረኩ ሁለተኛ ቀን በመገናኛ ብዙሃን እና በፖለቲካው መካከል ላለው «ጥላቻ እና ፍቅር» ትኩረት በመስጠት በሰፊው ይነጋገራል። «ቹምሁርያት» የተሰኘው የቱርክ ጋዜጣ የቀድሞው ዋና አዘጋጅ ካን ዲዩንዳር፤ NDR፣ WDR እና «ዚዩድ ዶይቼ» የተሰኘው የጀርመኑ ጋዜጣ የጋራ የምርምር ስብስብ ኃላፊ ከጊዮርግ ማስኮሎ ጋር በመሆኑ ግንኙነቱ ወዴት አቅጣጫ እያደገ በመሄድ ላይ ነው የሚለው ላይ በማተኮር  ይወያያሉ።

 
ከ140 ሃገራት የመጡ 2,000 ተሳታፊዎች በሚገኙበት በዚህ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ 70 የተለያዩ መርሃግብሮች እና የሀገር ውስጥ ጋዜጠኝነት ዕጣ ፈንታን የመሳሰሉ ሌሎችም መነጋገሪያ ነጥቦች ይኖራሉ። በዚህ አጋጣሚም በሀገር ውስጥ አዘጋገብ ላይ ካለው ቀውስ በተቃራኒ አዎንታዊ ማሳያዎች በአንደኛው የውይይት መድረክ ይቀርባሉ። 
ሰው ሠራሽ እውቀትን በተመለከተም ውይይት የሚካሄድ ሲሆን በተለይም በኮምፕዩተር ፕሮግራሞች አማካኝነት የሚሠሩ የሂሳብ ስሌቶች እና ትርጉሞች እንዲሁም የመወያያ መድረኮች የመገናኛ ብዙሃኑን ሥራ እንዴት እየቀየሩት ነው? በሚለው ላይ ውይይት ይኖራል። በዚህ መድረክም «ሶፊያ» የሚል ስያሜ የተሰጣት ሮቦት ለተሰብሳቢዎቹ አጭር ንግግር ታደርጋለች።  
በመድረኩ ተጓዳኝ አዘጋጆች አማካኝነትም ሕዝበኛ ፖለቲከኞች በበረከቱበት በዚህ ወቅት ስደተኞች ድምፃቸውን ማሰማት እንዴት ይችላሉ? ፖለቲከኞች እና የሕግ ባለሙያዎችስ የጥላቻ ንግግሮችን እንዴት መቆጣጠር ይችላሉ? የምርመራ ጋዜጠኝነትስ ምን ሚና ይኖረዋል? የሚሉት ነጥቦችም መነጋገሪያ ይሆናሉ። 

እንደቀደሙት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም የዶይቼ ቬለ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ሽልማት ይሰጣል። ከአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ጋር የተገናኙ ወንጀሎች እና ሙስናን፣ እንዲሁም ወንጀል ፈፅሞ ያለመቀጣትን በማጋለጧ በደረሰባት ስጋት ከሀገሯ የተሰደደችው ሜክሲኳዊት ጋዜጠኛ አናቤል ሄርናንዴዝ የዘንድሮ ተሸላሚ ናት። የአደንዛዥ ዕጽ ሕገወጥ ንግድን በሚመለከት የጻፈችው መጽሐፍ በመላው ዓለም በሺህዎች የሚገመት ቅጂ ተሸጧል። ይህን በማጋለጧ ከወንጀለኛ ቡድኖች ይልቅ ሊገድላት የሞከረው የሜክሲኮ መንግሥት መሆኑን የምትናገረው አናቤል ሄርናንዴዝ፣ ሽልማቱ ልዩ ትርጉም እንደሚሰጣት ተናግራለች።
«ይህ ሽልማት እጅግ ስሱነት በሚሰማኝ ወቅት ነው የመጣው፤ ምክንያቱም ከሜክሲኮ ውጪ በጣም ብቸኝነት ይሰማኛል። ሆኖም ግን ሽልማቱ ለእኔ ከሽልማት በላይ ነው። የመተባበር አይነት።»


መድረኩ ኪነጥበብንም ያካተተ ሲሆን 30 ዓለም አቀፍ ፎቶ አንሺዎች ከተለመደው የአፍሪቃ ገፅታ ወጣ ያሉ ሥራዎቻቸው የተካተቱበት «ኤቭሪዴይ አፍሪቃ/ አፍሪቃ በየዕለቱ» በተሰኘው ፕሮጀክት ሥር የፎቶ አውደርዕይ ያቀርባሉ። በዘንድሮው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን መድረክ የሚከናወነው አዲሱ መርሃ ግብር ከ200 የሚበልጡ ተሳታፊዎች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋባዥነት የሚያካሂዱት ልዩ  አውደጥናት ነው። መርሃግብሩ የሚከናወነውም ከመደበኛው ዝግጅት በኋላ ይሆናል።  ቦን ከተማ ድረስ መጥተው በጉባኤው የማይሳተፉ በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት በቀጥታ በሚኖረው ስርጭት አማካኝነት ሊከታተሉ ይችላሉ። 

ሸዋዬ ለገሠ/ ኢነስ አይዘል

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic