ዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳይ ተመልካች ፍርድ ቤት እና የዩጋንዳ ዓማፅያን | የጋዜጦች አምድ | DW | 15.10.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳይ ተመልካች ፍርድ ቤት እና የዩጋንዳ ዓማፅያን

ከሦስት ዓመት በፊት የተቋቋመው ዓለም አቀፉ ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ የእሥራት ትዕዛዝ ማሳለፉ በኒው ዮርክ ተገለፀ።

የእሥራቱ ትዕዛዝ የተላለፈው የሎርድ ሬዚስተንስ ጦር በመባል የሚታወቀው የዩጋንዳ ዓማፅያን ቡድን አምስት ከፍተኛ አባላት ላይ ነው። በተጠርጣሪዎቹ ላይ የተሰነዘሩት ክሶች በቅርቡ ይፋ እንደሚወጡም በኮንጎ የተመድ ልዩ ተጠሪ ዊልያም ሌሲ ስዊንግ አስታውቀዋል። በእሥራት ከሚፈለጉት ተጠርጣሪዎች መካከል የሎርድ ሬዚስተንስ ጦር መሪ ዦሴፍ ኮኒ እና ምክትላቸው እንደሚገኙባቸው አላጠራጠረም። በኮንጎ የተመድ ልዩ ልዑክ ዊልያም ሌሲ ስዊን እንዳመለከቱት፡ በአምስት የሎርድ ሬዚስተንስ ጦር ከፍተኛ አባላት ላይ የተላለፈው የእሥራት ትዕዛዝ ተፈላጊዎቹ ተጠርጣሪዎች ይገኙባቸዋል ለሚባሉት የዩጋንዳ፡ የሱዳንና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ መንግሥታት ባለፈው ሣምንት መረጃ አቅርቦዋል። በዩኤስ አሜሪካ የሚገኙት የዩጋንዳ አምባሳደርም ይህንኑ ዘገባ በተዘዋዋሪ መንገድ አረጋግጠውታል። የሎርድ ሬዚዝተንስ ጦር ካለፉት ሀያ ዓመታት ወዲህ በዩጋንዳ መንግሥት አንፃር በሰሜናዊ የሀገሪቱ ከፊል ጭካኔ የተመላበት ውጊያ ያካሂዳል። ከአሥር ሺህ የሚበልጡ ሕፃናትን በውትድርና እንደመለመለ ይነገራል። ቡድኑ ወጣት ወንዶችን በነፍሰ ገዳይነት ያሠለጥናል፡ ወጣት ሴቶችን ደግሞ ካለፍላጎታቸው በወሲብ ተግባር ይበዘብዛል። ከዚህም ሌላ በሰሜን ዩጋንዳ የሚኖረውን ሕዝብ እንደሚያሸብር፡ እንደሚዘርፍ፡ እንደሚገድል፡ ክብረ ንፅሕናን እንደሚደፍርና ነዋሪዎችን በኃይል እያፈነ እንደሚያግት ነው የሚሰማው። በመሆኑም፡ ወደ ሁለት ሚልዮን የሚጠጉ የዩጋንዳ ዜጎችየሎርድ ሬዚዝተንስ ጦር አስከፊና ዘግናኝ የጭካኔ ተግባር እየሸሹ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው በገዛ ሀገራቸው በየስደተኞቹ ጣቢያዎች ውስጥ መኖር ተገደዋል። ግማሹን የዕድሜ ዘመኑን በሎርድ ሬዚስተንስ ጦር ውስጥ ያሳለፈው የሀያ ሰባት ዓመቱ ፒተር መጀመሪያ ላይ በኃይል ታፍኖ ከተወሰደ በኋላ በግዳጅ በውድትድርና ካገለገለ በኋላ ጠፍቶ መውጣቱን ሲናገር፡ « መመሪያው ለመኖር መግደል ይሰኛል ይላል። ባማፅያኑ ቡድን ውስጥ ለመኖር የፈለገ የገዛ ወንድም ወይም እህትህንም መግደል ይገደዳል። » ሕፃናት ታማኝነታቸውንና ታዛዥነታቸውን ለማረጋገጥም እኩዮቻቸውን በቆንጨራ መቆራረጥ እንደሚገደዱ ነው ፒተር ያስረዳው። ከሀዲዎች ጆሯቸውንና ከንፈሮቻቸውን ይቆረጣሉ። የሽብር አስፋፊው ያማፅያን ቡድን መሪ ዦሴፍ ኮኒ አንዳችም የፖለቲካ መመሪያ የሌላቸው ሲሆን፡ ከዩጋንዳ ሕዝብም አኳያ ድጋፍ የላቸውም። ኮኒ ዩጋንዳ ውስጥ አሠርቱ ትዕዛዛትን መሠረት የሚያደርግ መንግሥት መማቋቋም ይፈልጋሉ። የሎርድ ሬዚዝተንስ ጦር መሪው ተሸሸግው ከሚኖሩባት ከጎረቤት ሱዳን ይንቀሳቀሳል፤ ይሁንና፡ ራሳቸውን እንደ አንድ ነቢይ የሚቆጥሩት ኮኒ ሥልጣናቸው ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ እክል እንደገጠመው፡ እንዲሁም፡ ከሁለት ሣምንታት ገደማ በፊትም ምክትላቸው ቨንሴንት ኦቲ ወደ አራት መቶ የሚጠጉ ተዋጊዎችን ይዘው ወደ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ መሰሻቸውም ነው የተገለፀው። ይህ በዚህ እንዳለ፡ የዩጋንዳ ጦር ከደቡብ ሱዳን የሚንቀሳቀሱትን የሎርድ ሬዚስተንስ ጦር ዓማፅያንን ተከታትለው እንዲይዙ የሱዳን መንግሥት ከጥቂት ቀናት በፊት የአንድ ወር ፈቃድ መስጠቱን የዩጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ፌሊክስ ጉራይዤ አስታውቀዋል። ለዚህም ጦሩ በሱዳን የሚያካሂደውን የፍለጋ ተግባሩንከሱዳን መንግሥት ጦር ኃይላት ጋር ማስተባበር ቅድመ ግዴታ አርፎበታል። ሱዳን ይህንን ስምምነት ከዩጋንዳ ጋር የደረሰችው ዓለም አቀፉ የየወንጀል ጉዳይ ተመልካች ፍርድ ቤት በሎርድ ሬዚዝተንስ ጦር አምስት ከፍተኛ አባላት ላይ የእሥራቱን ትዕዛዝ ካስተላለፈና ያማፅያኑ ቡድንም በደቡባዊ ሱዳን በሊርያ አካባቢ አሥራ ስድስት የሱዳን ዜጎችን ከገደለ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው። የዩጋንዳ ጦር ከሦስት ዓመት በፊት ከሱዳን ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት፡ በደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ብቻ ዘልቆ በመግባት በዩጋንዳ ጦር አንፃር በሚዋጉት ዩጋንዳውያኑ ዓማፅያን ላይ ክትትል እንዲያደርግ ነበር የተፈቀደለት፤ ይሁንና፡ ዩጋንዳ ዓማፅያኑ ወደ ሰሜናዊ ሱዳን ዘልቀው በመግባት ተሸሽገዋል፡ እንዲሁም፡ ካንዳንድ የሱዳን ጦር ክፍላት ከለላ ያገኛሉ በሚል ስሞታ ካሰማች በኋላ ሱዳን የዩጋንዳ ጦር ፍለጋውን ለአንድ ወር እንዲያስፋፋ ተስማምታለች። በዩጋንዳ መንግሥትና በሎርድ ሬዚስተንስ ጦር መካከል ካለፉት ሀያ ዓመታት ወዲህ የቀጠለውን ውጊያ ለማብቃት ይቻል ዘንድ የተካሄዱት ድርድሮች ሁሉ ከሽፈዋል። የዩጋንዳ መንግሥት ለዓማፅያኑ ምሕረት ለማድረግ ያቀረበውን ሀሳብ ካንዳንድ የዓማፅያኑ ቡድን ዋና አዛዦች በስተቀር ብዙዎቹ አልተቀበሉትም፤ የቡድኑ መሪዎች፡ ዦሴፍ ኮኒ ጭምር ካለፉት ዓመታት ወዲህ የት እንዳሉም በውል አይታወቅም። በመሆኑም፡ አሁን ዓለም አቀፉ የወንጀል ጉዳይ ተመልካች ፍርድ ቤት በዓማፅያኑ ቡድን ከፍተኟ መሪዎች ላይ ያሳለፈው የእሥራት ትዕዛዝ፡ ከሌሎቹ የቡድኑ አባላት ጋር ዕርቀ ሰላም ማስገኘት መቻሉን የፖለቲካ አስተንታኝ እዝተው ተጠራጥረውታል፤ ምክንያቱም ሰማንያ ከመቶው የሚሆኑት የሎርድ ሬዚስተንስ አባላት ሕፃናት ወታደሮች ናቸውና።