ዓለም በ2013 | ዓለም | DW | 30.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዓለም በ2013

ዋሽግተን-ብራስልሶች በጋራ ሶሪያ ላይ የመዘዙትን ሰይፍ ካፎቱ የዶሉበት፣ የግብፅ የዴሞክራሲ ጭላንጭል፣ በመፈንቅለ መንግሥት፣ በዜጎቿ ደም አጥንት የተመረገበት። ባሜሪካኖች የተሾሙት፣ አሜሪካኖችን ለዓመታት በታማኝነት ያገለገሉት ሐሚድ ካርዛይ የዋሽግተኖችን ትዕዛዝ እንቢኝ ያሉበት ዓመትም ነዉ

ከ1979 ጀምሮ በተዘዋዋሪ ተከታዮቻቸዉን የሚያጋድሉት፣ለቀጥታ ዉጊያ የሚዛዛቱ የቴሕራን እና የዋሽግተን፣ ፖለቲከኞች ያሽቀነጠሩትን ሠላም ከትቢያ ለማንሳት አንድ ሁለት አሉበት።ግን በተቃራኒዉ ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ የአሜሪካኖች፣ ወዳጅ፣ ሸሪክ አጋርነታቸዉ የደደረዉ የበርሊን፣ፓሪስ፣ የሮም ስጳኝ ፖለቲከኞች በዋሽግተኖች መሰለላቸዉ ተጋለጠበት። ሁለት ሺሕ አስራ ሰወስት። ደግሞ በተቃራኒዉ ዋሽግተን-ብራስልሶች በጋራ ሶሪያ ላይ የመዘዙትን ሰይፍ ካፎቱ የዶሉበት፣ የግብፅ የዴሞክራሲ ጭላንጭል፣ በመፈንቅለ መንግሥት፣ በዜጎቿ ደም አጥንት የተመረገበት። ባሜሪካኖች የተሾሙት፣ አሜሪካኖችን ለዓመታት በታማኝነት ያገለገሉት ሐሚድ ካርዛይ የዋሽግተኖችን ትዕዛዝ እንቢኝ ያሉበት ዓመትም ነዉ።

የጆርጅ ደብሊዉ ቡሽና የቶኒ ብሌር-የሁለት ሺሕ ሰወስት ወረራ የእብሪት፣ እብረታቸዉን ለመደበቅ የሰጡት ምክንያት ዉሸት፣ የገቡት ቃል፣ ቅጥፈት ባይሆን ኖሮ 2013 ኢራቆች ከሠላም፣ ዴሞክራሲ ከፍትሕ ብልፅግና ጎዳና የገቡበትን፣ ከዚያ ጎዳና ያስገቧቸዉን ዋሽግተን ለንደኖችን የሚያመሰግኑበት የፌስታ-ደስታ አስረኛ ዓመት በሆነ ነበር።

ሲጀመር እብሪት ነበር።ሲቀጥል ጥፋት።ጥንታዊቱ፣ ታሪካዊቱ ሐብታሚቱ፣ ሐገር የሐያላኑ ሐይል መሪዎች እብሪትን ለማስተንፈስ ከተወረረችበት ጊዜ ጀምሮ እንደተቆጠሩት ዘጠኝ ዓመታት ሁሉ አስረኛ ዓመቷን በዕልቂት ፍጅት ጀምረችዉ።

ጥር አምስት።የተለያዩ ከተሞችን ያሸበረዉ ተከታታይ የቦምብ ጥቃት ሰባ ስምንት ሰዎች ገደለ።በመቶ የሚቆጠሩ አቆሰለ።የካቲት የተለየ አልነበረም።መጋቢት አስራ-ዘጠኝ።ቡሽና ብሌር ያዘመቱት ጦር ባግዳድን ማንደድ የጀመረበት አስረኛ ዓመትን፣ ስትነድ የኖረችዉ ኢራቅ በቦምብ እየነደደች ተቀበለችዉ።ስልሳ አምስት ሰዉ ቀበረች።ቀጠለች። አሰለሰች።በሽብር እልቂት የጀመረችዉን ዓመት በእልቂት ሽብር ሸኝታ ሌላ ዓመት ልትቀበል ለሌላ እልቂት ሽብር ተሞሽራ ትጠብቃለች።አፍቃኒስታንም አስራ-ሁለት ዓመት እንደኖረችበት ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስትን በዉጊያ፣ በዜጎችዋ እልቂት፣በዘመተባት ጦር አባላት ግድያ ተቀብላ ነዉ-የሸኘችዉ።በአሮጌ እልቂት፣ ፍጅት፣ ግድያ ጥፋትዋ መሐል፣ በአሜሪካኖች የተሾሙት፣ አሜሪካኖችን ለአስራ-ሁለት አመታት በታማኝነት ያገለገሉት አሮጌ መሪዋ ሿሚ፣ አዛዦቻቸዉን በመቃወም አዲስ የያዙት አቋም ጉድ አጃኢብ ያሰኝ ገባ።

ሐያሉ ዓለም አሸናፊ ተሸናፊም ላለየበት ጦርነት ሁነኛ መፍትሔ ሳያበጅለት ጦሩን ከአፍቃኒስታን ለማስወጣት መዘጋጀቱ ያበሳጫቸዉ ፕሬዝዳንት ሐሚድ ካርዛይ በሁለት ሺሕ አስራ-ሁለት አሜሪካኖችን ከታሊባኖች ጋር አደራድሩኝ አሉ።ዋሽግተኖች ሰሟቸዉ፣ ላፍታ ደገፏቸዉም ወዲያዉ ግን ተዉአቸዉ።

ሰዉዬ በገኑ።እና ወደ ረዳቶቻቸዉ ዞር ብለዉ «አሜሪካኖች ያሰሯቸዉ ዜጎቼ ያሉበትን ሁኔታ አጣሩሉኝ» አሉ-አሉ።ጥር ሰባት።«የአሜሪካ ጦር ባሰራቸዉ ዜጎቼ ላይ የፈፀመዉን ግፍ እናወግዛለን» አሉ፥-አሁን ገዳዮች ለሚሏቸዉ ሲታዘዙ አስራ-ሁለት ዓመት ያስቆጠሩት ካርዛይ።

ግን ቀጠሉ።አሜሪካኖች አብዛኛ ጦራቸዉን ካስወጡ በሕዋላ-አፍቃኒስታን ሥለሚቆየዉ ጦሯቸዉ ተልዕኮ ያረቀቁትን ስምምነት አልፈርምም አሉ።ታሕሳስ ስምንት።የድፍረታቸዉ ድፍረት ቴሕራን ድረስ ሔደዉ ከአሜሪካኖች ቀንደኛ ጠላት ከኢራን ጋር የሠላምና የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።ካርዛይ፥- «የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም» እንዳሉ አመቱ አበቃ።አሜሪካኖች የሰጧቸዉ ሥልጣንም በቅርቡ ያበቃል።

ጥር ስምንት፣ ኢራን የዚያን ቀን ያደረገችዉን ስታስታዉቅ ኋላ ቴሕራን፣ ዋሽግተን፣ ኒዮርክ፣ ብራስልስ፣ ከሁሉም በላይ ዤኔቭ ላይ የሆነዉ ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም።ከምድር በታች በተከለችዉ የኑክሌር ፋብሪካ ዩራንየም ማንጠር መጀመሯን አስታወቀች።

የዋሽግተን ብራስልስ ፖለቲከኞች ቴሕራኖችን እንዳወገዙ፣ በማዕቀብ እንደቀጡ፣ እስራኤል ኢራንን ለመደብደብ እንደፎከረች፣ ኢራን ለአፀፋ እንደዛተች የኢራንና እና አምስት ሲደመር አንድ የሚባሉት ሐገራት ዲፕሎማቶች ያደረጉት ድርድር እንደተጠበቀዉ ያለዉጤት አበቃ።

ሰኔ አስራ-አምስት ግን ያልታሰበዉ ሆነ። ኢራን በተደረገዉ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለዘብተኛ የሚባሉት ፖለቲከኛ ሐሰን ሩሐኒ አሸነፉ።ቃል ገቡም።

«(በኢራን ላይ የተጣለዉን) ማዕቀብ ለማስወገድና ለመፍታት ሁለት ጉዳዮችን እንወስዳለን። የመጀመሪያዉ ሥለ ኑክሌር መርሐ-ግብራችን ግልፅ ጎዳናን መከተል ነዉ።መርሐ-ግብራችን በርግጥ ሙሉ በሙሉ የግልፅነት ባሕሪ አልተጓደለበትም።ይሁንና የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር የዓለም ሕግን የጠበቀ መሆኑን ለዓለም ይበልጥ በግልፅ ለማሳየት ዝግጁ ነን።ሁለተኛ፥ በኢራንና በሌሎች ሐገራት መካካል ያለዉ መተማመን አደጋ በገጠመዉ ሥፍራ ሁሉ መተማመንኑን ለማዳበር እንጥራለን።በኔ እምነት በኢራን ላይ የተጣለዉን ማዕቀብ ማስወገድ የሚቻለዉ በዓለም ሕግ መሠረት ግልፅንነትንና መተማመን በማዳበር ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ በዓለም ሠላም ለማስፈን ከገቡት ብዙ ቃል አንዱን እንኳ ገቢር ባለማድረጋቸዉ ከሚወርድባቸዉ ወቀሳ ትችት ለማምለጥ በሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ሲጣጣሩ፤ ፕሬዝዳት ሐሰን ሩሐኒ የሐገራቸዉን ምጣኔ ሐብት ያሽመደመደዉን ማዕቀብ ለማስነሳት ሲያማትሩ መንገድ ላይ ተገናኙ። መስከረም።በስልክ ተነጋገሩ።

የሁለቱ ሐገራት መሪዎች ሲነጋገሩ ከ1979 ወዲሕ የመጀመሪያ ነዉ።የአዮቶላሕ ሆሚንዋ «ታላቅ ሰይጣን» እና የጆር ቡሽዋ «የሰይጣን ዛቢያ» መሪዎች ለየጥቅማቸዉ መከበር «የጎበዝ መዉጪያ»ዉን እኩል አዉቀዉታል።ድርድር።አሮጌዉ ድርድር ባዲስ መንፈስ ተጀመረ። ጥቅምት።ቀጠለ።ተጣደፈም። ሕዳር ሐያ አራት።ዤኔቭ።

«ካላሰለሰ ድርድር በኋላ በጋራ የድርጊት መርሐ-ግብር ላይ ዛሬ ከስምምነት ደረስን።ስምምነቱ ለሁሉን አቀፍ ዘላቂ ሥምምነት መሠረት የሚጥልልን ነዉ።»

የአዉሮጳ ሕብረት የዉጪ ግንኙነት ሐላፊ ካትሪን አሽተን።ቴሕራንና ዋሽግተኖች በሰላሳ አራት አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ አግባቢ ሥምምነት ተፈራረሙ።ስምምነቱን ከፈረሙት አንዱ የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን’ ኬሪ ስምምነቱ ከማንም በላይ የእስራኤልን የደሕንነት ሥጋት እንደሚያስወግድ እርግጠኛ ነበሩ።

«ይሕ የመጀመሪያዉ እርምጃ (የኢራን) መርሐ-ግብርን አሁን ካለበት ወደ ኋላ እንደሚመልሰዉ በአፅንኦት መናገር እፈልጋለሁ።ይሕ ስምምነት ባይደረግ ኖሮ የማይኖረዉን (የማብላላት) ማቋረጫ ጊዜ ያሰፋዋል።የአካባቢዉ ወዳጆቻችንን ደሕንነት ያስጠብቃል።ተባባሪያችንን እስራኤልን ይበልጥ ከአደጋ ይከላከላል።»ስምምነቱን ድፍን ዓለም አወደሰ-አደነቀዉ።አንዲት ሐገር ግን «እንቢኝ አለች»።ያቺ ሐገር፥ ጆን ኬሪ እንደ መላዉ የዩናይትድ ስቴትስ፥ እንደ ሁሉም የምዕራብ ሐገራት ፖለቲከኞች ሁሉ ለፀጥታ፥ ደሕንነቷ መከበር ከሁሉም በላይ የሚጨነቁላት ናት።እስራኤል።ጠቅላይ ሚንስትሯ ቤንያሚን ኔታንያሁ ታላቁን ስምምነት «ታላቅ ስሕተት» አሉት።

«ትናት ማታ ዤኔቭ የተደረገዉ ታሪካዊ ሥምምነት አይደለም።ታሪካዊ ሥሕተት ነዉ።ዛሬ ዓለም እጅግ በጣም አደገኛ ሥፍራ ሆነ።ምክንያቱም ከዓለም እጅግ አደገኛዉ ሥርዓት፥ከዓለም እጅግ አደገኛዉን የጦር መሳሪያ ለመታጠቅ ታላቅ እርምጃ አድርጓልና።የዓለም ሐያላን እራሳቸዉ ያስፀደቁትን የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤትን ዉሳኔ ተቃርነዉ ኢራን ዩራኒየም ማንጠሯን እንድትቀጥል ለመጀመሪያ ጊዜ ተስማሙ።»

የትልቂቱ ሐገር ልዩ ወዳጅ ተቃዉሞ ለፕሬዳት ኦባማ በግል፣ ለመስተዳድራቸዉ በጥቅል ታላቅ ቅሬታን ነበር የፈጠረዉ።ይሁንና ኦባማ፣ ለልዩ ወዳጅነቱ ክብር፣ ብለዉ፣ የሰላም ዉል መብጠልጠሉን አልፈቀዱም።

«በዲፕሎማሲ ላይ በራችንን መዝጋት አንችልም።ለዓለም ችግሮች ሠላማዊ መፍትሔን «እንቢኝ» ማለት አንችልም።ማብቂያ ከሌለዉ የግጭት ዑደት መዳከር አንችልም።ጠንካራ ቃላትና ፉከራ ፖለቲካን ለማራመድ ቀላሉ ነገር ይሆን ይሆናል።ፀጥታችንን ለማስከበር ግን የሚፈይደዉ የለም።»

ጥር ሐያ፥ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ ከአፍቃኒስታን እስከ ሶማሊያ፣ ከየመን እስከ ሶሪያ፣ ከሊቢያ እስከ ፓኪስታን ሺዎችን የሚያረግፈዉን ጦርነት በቀጥታም በተዘዋዋሪም እየመሩ እንደ ሠላም አርበኛ የሠላም ኖቤል የመሸለማቸዉን ሰፊ ተቃርኖን ያፈጋዉን የመጀመረያ ዘመነ-ሥልጣናቸዉን አጠናቀቁ።

አዲሱን ጀመሩ።የቃለ መሐላዉ ሥርዓት መጠን፣ ሰብሰብ፣ ቀዝ፣ ቀዝ፣ ያለ ነበር።ያም ሆኖ ኋላ ከሶሪያ እስከ ኢራን፥ እስከ ሰሜን ኮሪያ እንደታየዉ ጦረኝነታቸዉን በሰላም አራማጅነታቸዉ ለማካካስ አንድ ሁለት ያሉበት ዘመን ነበር።

በሳልስቱ እስራኤል ዉስጥ በተደረገዉ አጠቃላይ ምርጫ አክራሪዉ የጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔትንያሁ ፓርቲ ሊኩድ አሸነፈ።ደቡብ ኮሪያዎች ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስትን የተቀበሉት አለምን ባስደደመዉ በድምፃዊ ፓርክ ጄ-ሳንግ አዲስ ሙዚቃ ዳንኪራ እየረገጡ ነበር።ጋጋም ስታይል።

የዓለም ወጣት በገፍ ሊያጅባቸዉ ሲታደም ግን ሶሎች፣ ከፒዮንግዮንግን የሚንቆረቆርላቸዉን የጦርነት ቀረርቶ ለማዳመት ተገደዱ።ጥርያ ሃያ-ሰወስት፣ ሰሜን ኮሪያ ሰወስተኛ የኑክሌር ቦምብ እንደምትሞክር አስጠነቀቀች።ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አዲስ ዘመነ ሥልጣን አዲስ ቀዉስ፣ ለአዲሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ለጆን ኬሪ የመጀመሪያዉ ፈተና ነበር።

ከሶል፣ ዋሽግተን፥ ከቶኪዮ፣ ከኒዮርክ፣ ብራስልስ ዉግዘት ማስጠንቀቂያዉ ቢጎርፍም የሰላሳ ዓመቱ ወጣት መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከቁብ አልቆጠሩትም።ቦምቡን አፈነዱት።-ለሙከራ።የካቲት12።ዉዝግቡ ማዕቀብ፣ ማዕቀቡ ፉከራ፣ ቀረርቶዉን አጋግሞ፣ የአሜሪካ የደቡብ ኮሪያ፣ የጃፓንን ጦርን በተጠንቀቅ አስቁሞ፣ የኋላ ኋላ በቻይናዎች አማላጅነት፣ ጥይት ሳይተኮስ ግን ጠቡም ሳይፈታ ዛቻ ፉከራዉ ከሰመ።ኪም ጆንግ ኡን ግን ደም ሳያፈሱ ሁለት ሺሕ አስራ ሰወስትን መሰናበት አልፈቀዱም።

ወጣቱ ኪም ምክትላቸዉንና አማቻቸዉን ዦዉግ ሶንግ ቴን ለኮሪያ ልሳነ-ምድር ቆሌ ጭዳ አደረጉ።ታሕሳስ አስራ-ሁለት።

ጥር ሃያ ሰባት። ደቡባዊ ብራዚል ዉስጥ አንድ የዳንካሪ ቤትን ያጋየ እሳት ሁለት መቶ ሰላሳ ሰዎችን ገደለ።የእግር ኳስ ጥበብ ቀንዲሊቱ ሐገር በቃጠሎ፥ ጢስ ጠለስ ያለቁ ዜጎችዋን በቀበረች ማግስት መንግሥት ኳስ ጨዋታ ለማስተናገድ ብዙ ገንዘብ ማዉጣቱን በሚቃወሙ ሠልፈኞችና እና በፀጥታ አስከባሪዎች ግጭት እንደተተራመሰች የዓለም እግር ኳስ ግጥሚያን ወደ ምታስተናግድበት ዓመት ተሸጋገረች።

ፕሬዝዳት ኦባማ በመጀመሪያ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ የመሩ የሚዘዉርትን ጦርነት ለመቀጠል ደግሞ በተቃራኒዉ የሰላም ኖቤል ያሸለማቸዉን የሰላም ቃል ተስፋ ገቢር ለማድረግ አንድ ሁለት ሲሉ ኔታንያሁ በመጀሪያ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ካቀዱ፣ ከጀመሩት አንዱን ቀጠሉ።ኔታንያሁ ያዘመቷቸዉ የእስራኤል የጦር አዉሮፕላኖች ሶሪያን ደበደቡ።ጥር ሰላሳ።

እርግጥ ነዉ ኦባማ እራሳቸዉ፣ የሚመሩና የሚያስተባብሯቸዉ የምዕራብ አዉሮጳ አቻዎቻቸዉ፣ የአረብ ቱጃሮች እና ቱርክ የሚያስታጥቁ፣ የሚያሰለጥኑ፣ የሚረዷቸዉ የሶሪያ አማፂዎችና በኢራን፣ በሩሲያና በሒዝቡላሕ የሚደገፈዉ የሶሪያ መንግሥት የገጠሙት ጦርነት ከእስራኤል ድብደባ በፊት በኋላም አላባራም።

እስራኤል ካንዴም ሁለቴ ሶሪያን መደብደቧ፣ አማፂያን ደማስቆን፣ አሌፖን፣ ዳራዕ፥ ሐማ፣ ሆምስን ወዘተ ማሸበራቸዉ፣ የተማረኩ ወታደሮችን ማረድ መተልተላቸዉ ለዋሽግተን፣ ብራስልስ፣ ለሪያድ፣ ዶሐ አንካራ ገዢዎች የሚወገዝ ወንጀል አልነበረም።

የሶሪያዉ ጦርነት የፈጀዉ ሕዝብ ከመቶ ሺሕ መብለጡ፣ ያሰደደ ያፈናቀለዉ አራት ሚሊዮን መድረሱ በሚዘገብበት መሐል የሶሪያ ጦር በተኮሰዉ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ የደማስቆ መዳረሻ መንደር ሕዝብ መንጨርጨሩ ተዘገበ።ነሐሴ ሃያ-አንድ።ሐያሉ ዓለም ተቆጣ።የዋሽግተን፥ ለንደን ፓሪስ፥ መሪዎች ሶሪያን ለመደብደብ ይዝት፥ይፎክር ገባ።የብሪታንያ ምክር ቤት የጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ የካሜሩንን የዉጊያ ዕቅድ ዉድቅ ሲያደርገዉ፥ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማም ከኢራን በፊት ሶሪያ ላይ «የጎበዝ መዉጪያ» ያፈላልጉ ያዙ።

የሩሲያ ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቲንን ጣለላቸዉ።የፑቲን ባንድ በኩል የሶሪያን መደብደብ በመቃወማቸዉ፥ በሌላ በኩል የደማስቆ ገዢዎች ኬሚካዊ ጦር መሳሪያቸዉን እንዲያስረክቡ በመገፋፋታቸዉ አስፈሪዉ ጦርነት ሳይቀጣጠል ከሰመ።ኦባማም የሶሪያ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ የሚወድምበት ጊዜ እንዲገደብ ከመጠየቅ ጋር ከጦርነት ተገላገሉ።

በሽር አል-አሰድም ቢያንስ ለጊዜዉ ከመጥፋት-ዳኑ።መስከረም ሃያ ሰወስት-የእፎይታ ቃል።

«በዚሕ ጉዳይ የሚያሳስበን ነገር የለም።ሶሪያ ነፃነትዋን ከተቀዳጀችበት ጊዜ ጀምሮ ለተቀበለቻቸዉ ዉሎች ትገዛለች።የገባነዉን ቃል እናከብራለን።ቻይና እና ሩሲያ ለተጫወቱት ገንቢ ሚና ምስጋና ይግባዉና ሶሪያን ለመዉጋት የሚቀርብ ምክንያት አይኖርም።ማለት የምፈልገዉ ዩናይትድ ስቴትስ፥ ፈረንሳይና ታላቅዋ ብሪታንያ፥ ሶሪያ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያዋን የምታጠፋበትን ቀነ-ገደብ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንዲቆርጥ የዉሳኔ ሐሳብ ማቅረባቸዉ እና ከሩሲያ ጋር ለመስማማት የሚጥሩት ከሶሪያ ጋር በገጠሙት ምናባዊዉ ጦርነት አሸናፊ መስለዉ ለመቅረብ ነዉ።ሥለዚሕ ብዙም ከቁብ የምንቆጥረዉ፥የሚያሳስበንም ጉዳይ አይደለም።

የሶሪያ ሕዝብ እልቂት፥ ስደት አላባራም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሟች፥ ስደተኞችን ይቆጥራል።ሕዳር፥-ከመቶ ሥልሳ ሺሕ በላይ ሕዝብ መገደሉ፥ከአራት ሚሊዮን በላይ መሰደድ መፈናቀሉ ተዘገበ።ጦርነቱ ግን ሊባኖስም እየለበለበ-ዛሬም ቀጥሏል።

ግብፅ-የሠላሳ ዘመን አምባገነን ገዢዋ በሕዝባዊ አመፅ የተወገዱበትን ሁለተኛ ዓመት ባከበረች ማግስት ሐገር ጎብኚዎች ሞቱባት።የካቲት ሃያ-ስድስት በተንሳፋፊ የላስቲክ ፊኛ ይጓዙ የነበሩ ሐገር ጎብኚዎች ፊኛቸዉ አየር’ ላይ ነዶ-ሞቱ።አስራ-ዘጠኝ ነበሩ።

አደጋዉ ፕሬዝዳት መሐመድ ሙርሲን የሚቃወሙ ግብፆችን ከሠልፍ ተቃዉሟቸዉ አላናጠባቸዉም ነበር።ሐምሌ ሰወስት፥ ሞቅ-ቀዝቀዝ የሚለዉን ተቃዉሞ አድፍጠዉ ሲጠባበቁ የነበሩት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ሲሲ የልባቸዉን አደረሱ።መፈንቅለ መንግሥት።

የግብፅ የዴሞክራሲ ተስፋ ሳያባብ ተቀጠፈ።መፈንቅለ መንግሥቱን የተቃወመዉን ሰልፈኛ የጄኔራል አል ሲሲ ጦር ከሰማይ በሔሊኮብተር፥ ከምድር በመትረየስ ያጭደዉ ገባ ሺዎች ረገፉ፥ ብዙ ሺዎች አካላቸዉ ጎደለ፥ በጣም ብዙ ሺዎች ወሕኒ ተወረወሩ።በሕዝብ የተመረጡት ፕሬዝዳት ሙርሲ ሲወነጀሉ፥ የሰላሳ-ዘመኑ ወታደራዊ መሪ ሆስኒ ሙባራክ ወደ በቁም እረኝነት እንዲጠበቁ ከወሕኒ ቤት ተፈቱ።የግብፅ ፖለቲካ በጭፍጨፋ እንዳደፈ ቀጠለ።

የካቲት ሃያ-ስምት።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛ ሥልጣን ለቀቁ።ቤኔዲክት አስራ-ስድስተኛ ሥልጣን ሲለቁ በቤተ-ክርስቲያኒቱ የስድስት መቶ ዓመት ታሪክ የመጀሪያዉ ናቸዉ።መጋቢት ላይ የመጀመሪያዉ ደቡብ አሜሪካዊ ቄስ የርዕሠ-ሊቃነ ጳጳስነቱን ሥልጣን ያዙ።ዮርገ ቤርጎጂሊዮ።ፍራንሲስም ሆኑ።

መጋቢት አምስት፥-እዉቁ የቬኑዙዌላ ፕሬዝዳት ሁጎ ሻቬዝ ሞቱ።ሐምሳ ዘጠኝ አመታቸዉ ነበር።ሻቬዝ ዩናይትድ ስቴትስን በመቃወም፥ በተለይ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደቡሊዉ ቡሽ እንደ ሰይጣን በመቁጠር የቆሙበትን ሥፍራ «ድኝ ድኝ» ይሸታል በሚል ተረባቸዉ እዉቅናን አትርፈዉ ነበር።

በወሩ የቀድሞዋ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ባሮነስ ማርጋሬት ታቸር ተከተሉ።ሚያዚያ ስምንት። ሰማንያ ስምንት አመታቸዉ ነበር።ወግ አጥባቂዋ ፖለቲከኛ የመጀመሪያዋ የብሪታኒያ ሴት ጠቅላይ ሚንስትር ግን አወዛጋቢ ፖለቲከኛ ነበሩ።

ሚያዚያ ሃያ አራት፥ ባንግላዴሽ ዉስጥ አንድ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ሕንፃ ተንዶ-አንድ ሺሕ አንድ መቶ ሃያ-ሰባት ሠራተኞችን ፈጀ።

ሐምሌ-ዘጠኝ። የሃያ-ዘጠኝ ዓመቱ የዩናይትድ ስቴትስ ሰላይ ሐገሩን ከድቶ ሆንግ ኮንግ መግባቱ ተነገረ።ኤድወርድ ስኖደን።በሆንግ ኮንግ አድርጎ ሞስኮ የገባዉ ስኖደን የትልቂቱ ሐገር የስለላ ቅሌትን ይዘረግፈዉ ገባ።ዩናይትድ ስቴትስ የቅርብ ወዳጅዋን የጀርመን መራሒተ-መንግሥት የአንጌላ ሜርክልን የስልክ ንግግር ሳይቀር የመጠለፏ ቅሌት የዓለም መሪዋን ሐገር፥ በዓለም ሕዝብ ዘንድ እንዳቀለላት-ዓለም ሌላ ጉድ ግን አሳዛኝ ጉድ ከወደ ላምፔዱዛ-ኢጣሊያ ሰማ።ጥቅምት ሰወስት፥ በአብዛኛዉ የኤርትራ ስደተኞችን ያሳፈረች አንዲት ጀልባ ሰጥማ ከሰወስት መቶ በላይ ስደተኞች አለቁ።ሕዳር አራት።በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ ሳዑዲ አረቢያ ሕገ-ወጥ የዉጪ ስደተኞችን ወደየሐገራቸዉ ማጋዝ ጀመረች።በርካታ የዉጪ ዜጎች ወደየሐገራቸዉ በርካታ ገንዘብ በመላክ ከዓለም ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥሎ ሁለተኛዉን ስፍራ የያዘችዉ ሳዑዲ አረቢያ እስከ ዓመቱ ማብቂያ ወደ አንድ ሚሊዮን ተኩል የሚደርሱ የዉጪ ዜጎችን ማባረሯን አስታዉቃለች።

መቶ አርባ ሺዉ ኢትዮጵያዉያን ናቸዉ።የማባረሩ ዘመቻ ዱላ፥ ግድያ፥ ግፍ ግርግር አላጣዉም።
ታሕሳስ አምስት።ዓለም ምናልባት የምዕተ-ዓመቱን ታላቅ የሠላም አርበኛ አጣች።ኔልሰን ሆሊሻሻ ማንዴላ።

ዘጠና አምስት ዓመታቸዉ ነበር።እና እስራኤል ፍልስጤሞሽ ለሰባ-ዘመናት ያሕል እንደኖሩበት ድርድር እያሉ እንደተጋደሉ፥ ሕንድ በሴቶቿ መደፈር እንዳፈረች፥ እንዳዘነች፥ ፊሊፒንስ በከባድ ወዠቦ ያለቁ ዜጎችዋን እንደዘከረች፥ሩሲያ በቦምብ ጥቃት እንደተጎነጫጨፈች፥ ብራዚል ኳስ እንዳለች ሁለት ሺሕ አስራ-ሰወስት አዲዮስ-አሚጎስ። በዘመኑ ለምታሰሉ። መልካም አዲስ ዓመት።


ነጋሽ መሐመድ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic