ዓለም በ2010 | ዓለም | DW | 27.12.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ዓለም በ2010

አምደ መረብ አገልግሎት ሃያኛ አመቱ ሲዘከረ ዊኪሊክስ የተሰኘዉ አምደ መረብ ያፍረጠረጠዉ ሚስጥር የአለምን አመለካከት ቀይሮ-ዘመን በዘመን ሊቀየር አራት ቀን ቀረዉ።

default

መካከለኛዉ ምሥራቅ -ሰዉ የጊዜን ዑደት ማስላት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እንዳረጀበት ሠላም ፍቅር፥ ዉይይት-ድርድር እየተሰበከ፥ እየተነገረበት ሞት መከራ እንደታፈሰበት ሁለት ሺሕ አስርም ተወልዶ-አድጎ አረጀበት።ኢራቅ የጦርነት ፍፃሜ፥ ምርጫ እየታወጀ-እየተደረገባት ቦምብ-ዉዝግብ እንዳዋከባት፥ አፍቃኒስታን ፓኪስታን የአሸባሪዎች ሽንፈት እየተነገረባቸዉ እንደተሸበሩ የዘመን ዘመን ሊተካ ነዉ።አምደ መረብ አገልግሎት ሃያኛ አመቱ ሲዘከረ ዊኪሊክስ የተሰኘዉ አምደ መረብ ያፍረጠረጠዉ ሚስጥር የአለምን አመለካከት ቀይሮ-ዘመን በዘመን ሊቀየር አራት ቀን ቀረዉ። የጎርጎሮሳዉያኑ ሁለት ሺሕ አስርን አበይት መታወሻዎች ላፍታ ዘክረን-እንሸዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።

አለም ለያኔዉ አዲስ አመት ቅበላ የተኮሰ-የለኮሰዉን የርችት-ችቦ አመድ-ክሳይ አፅድቶ ሳያበቃ የዱባይ ሰይማይ ከወገቡ የሚተፋዉ የርችት ብርሐን የፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሕዋን ሲያጥለቀለቅ አየ።የምሕንድስና እዉቀት፣ የሥነ-ሕንፃ ጥበብ ምጥቀት ፣የገንዘብ ጉልበት ዱባይ ላይ-ጉድ አሰኘ።ጥር አራት።ቡርጅ ኸሊፋ ሕንፃ ተመረቀ።ከአለም አንደኛ ነዉ።ስምንት መቶ ሃያ-ስምንት ሜትር ይረዝማል።አንድ መቶ ስልሳ ፎቆች አሉት።አንድ.ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ፈሶበታል።አረብ-አጃኢብ፣ አለም በየቋንቋዉ ጉድ ብሎ ሳያበቃ-ተፈጥሮ ሄይቲ ላይ በፍጡሯ ጨቀነች።

Symbolbild Ende 2010

«የሆነ ነገር ሕንጻዉን የመታዉ ነበር-የመሠለን።መሬት መንቀጥቀጥ መሆኑን ያወቅነዉ ሁሉም ከሆነ በሕዋላ ነዉ።»

የርዕሠ-ከተማ ፖርትኦፕረንሱ ነዋሪ።ጥር አስራ-ሁለት ከተማይቱ ሁሉም ተደፋባት።በቅፅበት ወደ አስከሬን፣ የአካል ቁርጥራጭ፣ የሕንፃ ፍርስራሽ፣ ክምርነት ተቀየረች።ደም ያቋረ ምድሯ፣ በቁስለኞች፣በቤት-የለሾች ተሞላ።ሁለት መቶ ሃያ ሺሕ ሕዝብ አለቀ።ከሞት የተረፈዉ የመከራዉን ልክ አሰላስሎ ሳያበቃ ከሌላ መከራ ገባ።ኮሌራ።ሁለት ሺሕ ሰዉ ገደለ።ጥቅምት የምርጫ ዉዝግብ ታከለበት።ጥቂት ሞቱ።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ እስራኤልና ፍልስጤሞች በየአመት ወሩ እንደሚያደርጉት ሁሉ ሽምግልና ድርድር ሲሉ በግዙፍ ሕንፃዋ አለምን ጉድ ያሰቸዉ ዱባይ ፍልስጤማዊ እንግዳዋ በጉደኛ ጠላቶቻቸዉ ጉድ-ሆነዉ-ጉድ ሆነች።

የአክራሪዉ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ የሐማስ የጦር መሪ ማሕሙድ አል-ማብሑሕ ሆቴላቸዉ ዉስጥ ተገደሉ።ጥር ሃያ።ገዳዮች የእስራኤል የስለላ ድርጅት የሞሳድ አባላት መሆናቸዉን ፍልስጤሞች በይፋ የተቀረዉ አለም በሹክሹክታ ይናገሩ ገቡ።እስራኤል አላመነችም።የሟች ደም፣ የፍልስጤሞች ቁጣ፣የአረብ ኤሚሬቶች ዉርደት የገዳዮቹ ማንነት ከየባለጉዳዮቹ ባለፍ ሐያሉን አለም የሚጎረብጥ አልነበረም።
ገዳዮቹ የአዉሮጳና የሌሎች ምዕራባዊ ሐገራትን ፓስፖርት ይዘዉ መሆኑ ግን የብራስልስ፣ የለንደን፣ የፓሪስ፣ የበርሊን፣ የካምቤራ፣ የኦታዋን ፖለቲከኞች ያንጨረጭር ያዘ።

Burj Dubai Eröffnung Flash-Galerie

ቡርጅ ኸሊፋ

«በግድያዉ የተካፈሉት ከአዉሮጳ ሕብረት ዜጎች የተሰረቀ የአዉሮጳ ሕብረትን መታወቂያና ክሬዲት ካርድ አጭበርብረዉ መጠቀማቸዉን አጥብቀን እናወግዛለን።»የአዉሮጳ ሕብረት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ካትሪን አሽተን።ብሪታንያና አዉስትሬሊያ የእስራኤል ዲፕሎማቶችን ከየሐገራቸዉ አባረዋል።

ኢራቅ የሰባት አመቱ የእልቂት ፍጅት ድግግሞሽ ቀዝቀዝ-ቀነስ ቢልባት ደም ለለመደ ቆሌዋ የቀድሞዉ ከፍተኛ ባለሥልጧናን ገበረችለት። በስልጣን ዘመናቸዉ ኩርዶችን በኬሚካል በማስገደል ወንጀል ሞት የተበየነባቸዉ አሊ ሐሰን አል-መጂድ ተሰቀሉ።

እንደ ፕሬዝዳትና እንደ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ባንድ አብረዉ የታሚል ታይገር ጠላቶቻቸዉን ድል ያደረጉት የሺሪላካ ባለሥልጣናት በእኩል ድል እኩል እንደፈነደቁ-በተቀበሉት አመት ትልቁን ስልጣን በምርጫ ለመያዝ ይሻሙ ገቡ።ተጣሉ።ጄኔራል ሳራታ ፎንሴካ እንደ ወታደር ያድርግ-አታድርግ መርሕን ሲቀምሩ ብልጣብልጡ ፖለቲከኛ ፕሬዝዳት ማሂንዳ ራጃፓካሳ ጄኔራሉን በወንጀል ሾኬ ጥለዉ በምርጫዉ ድል አድራጊነት አስጨፈሩ።

የበረዶዋ ሐገር ካናዳ የካናዳዋ ከተማ ቫንኩቨር የክረምት ኦሎምፒክን ለማስተናገድ በረዶ ቸግሯት ከሌላ ሥፍራ መለቃት፣በማቀዝቀዣ መስራት ግድ ነበረባት።እንዲያ ተጠባ-ተጨንቃ ያዘጋጀችዉ የበረዶ-ድግስ ፌስታዉን-በሐዘን ጭጋግ ጋረደባት።በጆርጂያዉ ስፖርተኛ ኖዳር ኩማሪታሺቪሊ ሲለማመድ ሞተ።ገደ ቢስ ድግስ።

በረዶ-የበረዶ ተጨዋች ሕይወትን የመቅጨቱ ሐዘን የበረዶ ስፖርተኞችን ልብ እንደሰበረዉ-ከአንታርክቲክ የበረዶ ግግር ላክሰምበርግን የሚያሕል የበረዶ ክምር ተደረሰመ።የሰሐራ በረሕይቱን አፍሪቃዊት ሐገር የኒጀርን ሙቀት ያጋማዉ ግን ፖለቲካዊ ሽኩቻ ነበር።የፕሬዝዳት ማማዱ ታንጃ መንግሥትን አሽቀንጥሮ ጣለዉ።

ታንጃ እንደ ወጣት የጦር መኮንን የተሳተፉበት መፈንቅለ መንግሥት አጉዞ አጉዞ ከኒያሚ ቤተ-መንግሥት በዶላቸዉ በአስራ-አንደኛ አመታቸዉ የጠሩት ምርጫ ዉጤት ጦራቸዉን አሳምፆ ከስልጣን አሽቀነጠሯቸዉ።የፕሮቶሪያ የሥልታዊ ጥናት ተቋም አስተንታኝ ኢሳይ ሱአሬ እንደሚሉት ታንጃ የእጃቸዉን ያገኙት።
«ታንጃ ሕገ-መንግሥቱን ለዉጠዋል።ምክር ቤቱን በትነዋል።የሕገ-መንግሥታዊዉ ፍርድ ቤት የተቃዋሚዎች ያቀረቡት ቅሬታ ተገቢ ነዉ ብሎ ሲበይን ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ፍርድ ቤቱን አገዱት።በመጨረሻ የምርጫ ኮሚሽኑ እቅዳቸዉን በመቃወሙ አገዱት።»

ትንሿ ወር ልትጠናቀቅ አንድ ቀን ቀራት።የካቲት።

ቺሌ በሃይለኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ተናወጠች።በሬክተር መመዘኛ ስምንት ነጥብ ስምንት የተለካዉ የመሬት መንቀጥቀጥና ጎርፍ ስምንት መቶ ሰዉ ገደለ።የቺሌ ሕዝብ ወገኑ ያለቀበትን ስድስተኛ ወር ሲዘክር ሰላሳ-ሰወስት የማዕደን ሠራተኞቹ በቁማቸዉ የመቀበራቸዉ መርዶ ደረሰዉ።ነሐሴ።
ጥቅምት አጋማሽ ግን የትም የማይሆነዉ ቺሌ ላይ ሆነ።ሰባት መቶ ሜትር ጥልቀት ጉርጓድ ዉስጥ ከሰባ-ቀን በላይ ከነሕወታቸዉ የተቀበሩት ማዕድን ቆፋሪዎች በሙሉ በሕወት ወጡ።ተአምር እና ፈንጠዝያ።

መጋቢት ዘጠኝ።ማዕከላዊ ናጄሪያ ጆስ በሚኖሩ ሙስሎሞችና ክርስቲያኖች መካካል በተነሳዉ ግጭት አራት መቶ ሰዉ ተገደለ።ግጭት ግድያዉ ዛሬም ቀጥሏል።

የኮሪያ ልሳነ-ምድር ላዲስ ፍጥጫ ንረት አዲስ ደም ፈሰሰለት።አንዲት የደቡብ ኮሪያ የጦር መርከብ ተመታ ሰጠመች።አርባ-ስድስት ባሕር ሐይሎች ተገደሉ።ለጥቃቱ ሰሜን ኮሪያን ተጠያቂ ያደረጉት ዩናይትድ ስቴትስና ደቡብ ኮሪያ ሲዝቱ ቆይተዉ ሐምሌ ላይ ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ ጀመሩ።ከአንድ መቶ በሚበልጡ ተዋጊ አዉሮፕላኖች እና በሃያ ተዋጊ መርከቦች የተጠናከረዉ የጠላቶችዋ-ስምንት ሺሕ ጦር አፍንጫዋ ስር የሚያደርገዉ ልምምድ ለሰሜን ኮሪያ-አንድ የሐገሪቱ ባለሥልጣን እንዳስጠነቀቁት ነገር ፈፍለጋ ነዉ።
«ይሕ የዲሞክራቲክ ሕዝባዊት ሪፐብሊክ ኮሪያ ጠላቶች ለሚከተሉት የጠብ ጫሪነት መርሕ ተጨማሪ ማረጋገጪያ ነዉ።የኛ አቋም ደግሞ ግልፅ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ደቡብ ኮሪያ ለሚደርጉት ወታደራዊ ልምምድ ተጨባጭ አፀፋ እንሰጣለን።»

የሰሜን ኮሪያዉ መሪ ኪም ጆንግ ኢል ምናልባትም የኑክሌር ቦምብ የሚጎርስ ሚሳዬላቸዉን በደቡብ ጠላቶቻቸዉ ላይ እንዳስደገኑ ለልጃቸዉ የባለ አራት ኮኮብ ጄኔራልነት ማዕራግ ሰጡ።መስከረም ማብቂያ።ለሃያ-ስምንት አመቱ ወጣት ለኪም ጆንግ ኡን የተሰጠዉን ሹመት ሽልማት ታዛቢዎች የአልጋወራሽነት ዝግጅት ብለዉታል።

የሶል-ዋሽንግተን ወታደሮች እያሰለሱ ጫካ፥ ጋራ-ባሕሩን በቦምብ-መትረየስ እየቀጠቀጡ-የአመቱን የጉዞ ፍፃሜ ሲያሰሉ የሰሜን ኮሪያ ጦር ሌላ ጠንካራ የመድፍ ዱላዉን ደቡቧ ደሴት-ዬኦንፕዮን ላይ አሳረፈ።ሁለት ወታደሮችና ሁለት ሠላማዊ ሰዎች ገደለ።

የዋሽንግተን፥ ሶል ፒዮንግዮንግ አየር በዳግም ዉግዘት ዛቻ፥ በፉከራ የጦር ልምምድ እንደቀረና ሁለት ሺሕ አስር ተሸበለለ።መጋቢት ሃያ ዘጠኝ። ሞስኮ።ሁለት ሴት አጥፍቶ ጠፊዎች ሞስኮ ባቡር ጣቢያ ባፈነዱት ቦምብ-ሰላሳ ሰባት ሰዎች አጥፍተዉ ጠፉ።ፕሬዝዳት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ሞስኮቫይቶችን አፅናንተዉ ለብቀላ በዛምቱ በሳምንቱ፥ የዩናይትድ ስቴትስ አቻቸዉን ለማነጋገር ወደ ፕራግ-ቼክ ሪፐብሊክ ወረዱ።ሚያዚያ ስምንት ሁለቱ መሪዎች አዲሱ የስልታዊ ጦር መሳሪያዎች ቅነሳ ዉልን ፈረሙ።

Aung San Suu Kyi fordert Meinungsfreiheit in Myanmar

አዉንግፈራሚ-አፈራራሚ ደጋፊዎቻቸዉ ደጋግመዉ እንዳሉት «ስታርት» የተሰኘዉ ዉል የኑክሌር ጦር ቦምብን ለመቀነስ በሃያ-አመት ዉስጥ ከተደረጉት ስምምነቶች ሁሉ እጅግ ጠቃሚ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትሱ ወግ አጥባቂ የሪፐብሊካን ፓርቲ ፖለቲከኞች ግን የዉሉን ጠቃሚነት ለመቀበል ከሚያዚያ እስከ ታህሳስ ማሰላሰል፥ የፈራሚዎቹን ማብራሪያ ማድመጥ-ማዉጣት ማዉረድ ነበረባቸዉ።

የኋላ ኃላ አፀደቁት።ታሕሳስ-ሃያ ሁለት።የዉሉ መፅደግ ለፕሬዝዳት ኦባማ የዉጪ መርሕ ታላቅ ድል-አንዳዶች እንዳሉት ደግሞ ለፕሬዝዳንቱ የጋና ሥጦታ ነበር።ኦባማም ደስታቸዉን አልሸሸጉም።

«በቅድሚያ በዚሕ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ልዩ ትኩረት የሚሰጠዉ የብሔራዊ ፀጥታ መርሔን-የስታርት ስምምነትን ለማፅደቅ ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች በጋራ በመስማማታቸዉ ተደስቻለሁ።ይሕ የጦር መሳሪያን ለመቆጣጠር ለሁለት አስርታት ከተደረጉት ጥረቶች ሁሉ በጣም ጠቃሚዉ ነዉ።ካደጋ ይጠብቀናል፥ ከሩሲያ ጋር የኑክሌር አረሮቻችን ያስቀንሰናል።»

ኦባማ-«ካደጋ ያድነናል» ያሉት ዉል ፕራግ ላይ በፈረሙ በሰባተኛዉ ወር ሊዝቦን-ፖርቱጋል ለተሰሰቡት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሐገራት አቻዎቻቸዉ አዲስ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል አብረን መስራት አለብን እያሉ ነበር።ሐያላኑ አሮጌዉን ለመቀነስም አዲሱን ለመስራትም በመስማማታቸዉ እንደተደሰቱ አመቱ ተገባደደ።

ሚያዚያ አስር የፖለንዱ ፕሬዝዳት ሌሕ ካቺይንስኪ-ባለቤታቸዉ እና ዘጠና ሰወስት ባለሥልጣኖቻቸዉ በአዉሮፕላን አደጋ አለቁ።ድፍን ፖላንድ ደነገጠ፥-አዘነም።

የኢይጃፊጃላላጆይኩል-አይስላንድ እሳተ ጎመራ የተተጎለቆለዉ ጥቅጥቅ ጢስ ጠለሰ የምዕራብና የሰሜን አዉሮጳን የአዉሮፕላን ጎዞ ቀጥ አደረገዉ።የትንሿ ደሴት-ጢስ የትልቁን አለም ትላልቅ መሪዎችን ጭምር ማስገበሩ እንዳስደነቀ የቻይናዋ ቂንጉሺይ ግዛት በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ሰወስት ሺሕ ዜጎችዋን ቀበረች።መቶ ሺሕ ተፈናቀሉባት።

ሚያዚም ለፍፃሜዉ አራት ፈሪ አለ።ምዕራቡ አለም በወንጀለኝነት የሚያወግዝ፥ አለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚያድናቸዉ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ዑመር ሐሰን አልበሽር ለተጨማሪ ዘመነ-ሥልጣን ተመረጡ።የደቡብ ሱዳኑ መሪ ሳልቫ ኪርም በድጋሚ ተመረጡ።

ሱዳን ምርጫ ሲደረግባት በሃያ-አራት አመት ታሪኳ የመጀመሪያዉ ነበር።ተቃዋሚዎች የምርጫዉን ሒደት ሲያወግዙ፥ የዉጪ ታዛቢዎችም አልረኩበት።የታይላንድ መንግሥት ለወራት የርዕሠ-ከተማ ባንኮኮን ማዕከል የተቆጣጠሩት ተቃዋሚዎቹን በጦር ሐይል በተነ።ግንቦት አስራ-ዘጠኝ።

በለበሱት ቀይ ሸሚዝ-ስም በሚጠሩት ሠልፈኞችና በፀጥታ አስከባሪዎች መካካል ለስልሳ ዘጠኝ ቀናት በተደረገዉ ግጭት ዘጠና-ሁለት ሰዉ ተገድሏል።ግንቦት ሃያ-ሁለት።ከዱባይ የተነሳዉ የሕንድ የመንገደኞች አዉሮፕላን ማንጋሎር ለማረፍ ሲሞክር ተፈጥፍጦ አንድ መቶ ሐምሳ ስምንት መንገደኞችን ገደለ።

አደጋዉ ለምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ ከሚዋከበዉ ኢትዮጵያዊዉ ጆሮ ቡዙም አልገባም ነበር።በሰወስተኛዉ ቀን መረጠ።ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ የሚመሩት ገዢ ፓርቲ-የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባርና ተባባሪዎቹ አንዳዶች እንዳሉት በቅርብ ዘመኑ የምርጫ ታሪክ የአለምን ክብረወሰን ሰበሩ።ዘጠና-ዘጠኝ ነጥብ-ስድስት በመቶ ድል።

የዋነኛዉ ተቃሚ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲምራሲያዊ መድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንዳሉት የምርጫዉ ሒደት-ዉጤት የተጭበረበረ ነበር።«መንግሥት ካላጭበረበረ በስተቀር በሌላ መንገድ ሊያሸንፍ አይችልም።»

የአዉሮጳ ሕብረት የታዛቢዎች ቡድንም የምርጫዉን ሒደት «የገዢዉ ፓርቲ ተፅኖ ያየለበት» እና «አለም አቀፍ የምርጫ መመዘኛን የማያሟላ ብሎታል።»

ሕንድ ለአዉሮፕላን አደጋ ሙታኗ ያፈሰሰችዉ እንባዋ ሳይደርቅ-እንባ ወለደባት።ምዕራባዊ ግዛትዋን ቤንጋልን እና ባንግላዴሽን የመታዉ አዉሎ-ንፋስ ሰወስት መቶ-ሰላሳ ሰዉ ገደለ።አንድ ሚሊዮን አፈናቀለ።

ግንቦት ሰላሳ አንድ።የእስራኤል ጦር ለጋዛ ፍልስጤማዉያን እርዳታ የጫነች አንዲት መርከብን ወርሮ-ዘጠኝ-እርዳታ አቀባዮችን ገደለ።ስምንቱ የቱርክ አንዱ አሜሪካዊ ነበሩ።እርምጃዉ ለርዳታ ሰራተኞች በሙሉ አስደንጋጭ፥ ለቱርክ ደግሞ አስቆጪ ነበር።ከሙስሊም ሐገራት ሁሉ ከእስራኤል ጋር ጥሩ ግንኙነት የነበራት የቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር ጠይብ ኤርዶገን ከእንግዲሕ በቃን አይነት አሉ።

«የዛሬዉ ዕለት የመሠረታዊ ለዉጥ ዕለት ነዉ።ከዛሬ በሕዋላ ምንም ነገር እንደ የእስካዛሬዉ እንደማይሆን ግልፅ ነዉ።በዓለም ፊት፥ በአለም አቀፍ ባሕር ላይ ሰዎችን የሚገድል እብሪተኛ መንግሥት ጥፋቱን ተቀብሎ ይቅርታ ሳይጠይቅ አለም አቀፉን ማሕበረሰብ በሙሉ አይኑ ለማየት ማፈር አለበት።»

ኪርጊስታን ሁለት ሺሕ ሕይወት ያጠፋዉ የጎሳ ግጭት ተቀጣጠለባት።ሰኔ-አስር።በማግስቱ የአብዛኛዉ አለም አይን-ጆሮ ወደና ደቡብ አፍሪቃ ላይ ተቀሰረ።የአለም እግር ኳስ ግጥሚያ። አፍሪቃ-ደቡብ አፍሪቃ ወር የፈጀዉን ግጥሚያ ለመጀመሪያ ጊዜ አስተናገደች።ዋንጫዉን ግን ለመጀመሪያ ማድሪድ ገባ።ስጳኝ ፈነጠዘ።

ስጳኞችን ያስቦረቀዉን-ግጥሚያ በቴሌቪዥን ለመመልከት የዩጋንዳ-ርዕሠ ከተማ ካምፓላ በሚገኙ ምግብ ቤቶች የታደሙ ሰባ-ዘጠኝ ሰዎች በአጥፍቶ ጠፊዎች በቦምብ አለቁ።ለጥቃቱ የሶማሊያዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ ሐላፊነቱን ወስዷል።

ሐምሌ-ሃያ ስምንት።አንድ የፓኪስታን የመንገደኞች አዉሮፕላን ኢስላማባድ አጠገብ ተከሰከሰ።አንድ መቶ አርባ-ስድስት መንገደኞቹ ሞቱ።ፓኪስታኖች የአዉሮፕላኑ አደጋ ዜና በቅጡ ሳይሰሙ አንድ አምስተኛ ግዛታቸዉ በዉሐ ተዋጠ።ሁለት ሺሕ ያሕል ሕዝብ አለቀ።ሁለት ሚሊዮን ተፈናቀለ።

ፓኪስታን ዉሐ ተግታ ዉሐ ሲለብቃት ሩሲያን ሙቀት አግሟት እሳት ያስተፋት ገባ።ከባዱ ቃጠሎዉና ጢሱ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገደለ።

ኢራቅ ከቦምብ ፍንዳታዉ ሽብሩ ፋታ መጋቢት መግቢያ ላይ የምክር ቤት ምርጫ ተደርጎባት ነበር።በሕጋዊ መንግሥት ሳይመሰረትባት ሰባት አመት ከተቆጣጠራት የአሜሪካ ጦር አብዛኛዉ ተሰናበታት።ነሐሴ- አስራ ዘጠኝ።ዩናይትድ ስቴትስ ያወጀችዉ ዉጊያም በይፋ አበቃ።
ድምፅ
«ማክሰኞ፣-ከሰባት አመታት በሕዋላ፥ ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ላይ የከፈተችዉ ዉጊያ ያበቃል።እና የኢራቁን ጦርነት ለማጠናቀቅ ሐላፊነት የተሞላበት እርምጃ ትወስዳለች።»

በስድስተኛዉ ቀን ኢራቅ በሐያ-ሥፍራ በተጣሉ ቦምቦች ተሸበረች።ስላሳ-አራት ሰዉ ተገደለ።ሞቃዲሾም እንደ ባግዳድ ተሸበረች።ስድስት የምክር ቤት እንደራሴዎች ተገደሉ።

የእስራኤልና የፍልስጤም መሪዎች የዩናይትድ ስቴትሱን ፕሬዝዳት መሐል አቁመዉ ዋሽንግተን ዉስጥ ሠላም ለማዉረድ ቃል ገቡ።ተጨባበጡም።መስከረም ሁለት።ግን ቃል-መጨባበጡ እንደ ልጆች የእቃ እቃ ጨዋታ በወር እድሜ ፈረሰ።

አፍቃኒስታን ታሊባን የተወገደበትን አስረኛ አመት ለማክበር ዕለታት ሲቀራት ሁለተኛዉን የምክር ቤት ምርጫ አስተናገደች።መስከረም-አስራ ስምንት።የድሮዋ ሐገር በዉጊያ፥ ሽብር ትንቅንቁ መሐል የሙስናዉ ቅሌት፥ የምርጫ ዉዝግብ፥ ደግሞ ለወጉ የድርድር ሐሳብ እንደ ወዘወዛት ሁለት ሺሕ አስርን ድሮ ልትል-አራት ቀን ቀራት።የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ የአመቱን የሠላም ሽልማት ለታሠረዉ ለቻይናዊ የመብት ታጋይ ለሊዩ ዢያኦቦ ሰጥተ።

Jahresrückblick 2010 International Norwegen China Friedensnobelpreis Verleihung an Liu Xiaobo in Oslo Thorbjörn Jagland Flash-Galerie«የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ የሁለት ሺሕ አስሩን ኖቤል የሠላም ሽልማትን ለረጅም ጊዜ አመፅ-የሌለበት ትግል ላደረጉት ለሊዩ ዢያኦቦ እንዲሰጥ ወስኗል።»

ዉሳኔዉ የቻይናን ሐይል ቁጣ ቀስቅሶ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጡንጯንዋን አስዘረጋት።ቿይና በኖሮዌ ላይ ማዕቀብ ስትጥል ሕዳር በተከናወነዉ በሽልማቱ ድግስ ላይ የአስራ-ሰባት ሐገራት ተወካዮች እንዳይገኙ አሳደመች።በሠላም የኖቤል ሽልማት ታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ ተሽላሚ ወይም ተወካዮቹ በሌሉበት ተደገሠ።

የዘንድሮዉ የኖቤል ሽልማት ለእስረኛዉ ቻይናዊ የመንግሥት ተቃዋሚ መሰጠቱ ከመታወጁ ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ኢትዮጵያዊቷ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ከእስር-ቤት ተለቀቁ።ለቤተሰብ-ደጋፊዎቻቸዉ ደስታ፥ ፌስታም ነበር።የኖቤል-ሽልማት ድግሱ-የዲፕሎማሲ ብቀላዉ ዘመቻ በጋመበት መሐል ሌላዋ ኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ፥ የበርማ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አዉን ሳንሱቺ ከቁም እስረኝነት ተለቀቁ።ሕዳር-አስራ ሰወስት።ራንጉን ወይም ያንጉን በጭፍራ ቀለጠች።

የያንጉን ጄኔራሎች በምርጫ ድል ማግስት ያደረጉትን ማድረጋቸዉ-«ከአዲስ አበቦች ተምረዉ ይሆን?» የጠየቀ አይጠፋም ግን እንደ ብርቱካን የወደፊት የፖለቲካ አቋም ሁሉ እስካሁን አልተሰማም።

አዉስትሬሊያዊዉ የኮምፒዉተር አዋቂ ጁሊያ አሳዥ የመሠረቱት ዊኪሊክስ የተሰኘዉ አምደ መረብ በኢራቅና አፍቃኒስታን ዉስጥ የተገደሉትን ሰዎች ብዛት፥ የጦርነቱን እና ያገዳደላቸዉን ሚስጥር ሲዘከዝከዉ ጉድ አሰኝቶ ነበር።የአለም በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኛና ዲፕሎማቶች በአደባባይ የሚሉትን በሚስጥር የማፍረሳቸዉን የተቃርኖ ሚስጥር ሕዳር ላይ ሲያፍረጠርጠዉ ግን ጉዱን-ጉድ ዘለቀዉ ከማለት ሌላ ሌላ ቃል ለጊዜዉ አልተገኘም።አለም ሥለ መሪዎቹ ያለዉን አመመለካከት በሰአታት እድሜ የለወጠዉ ሚስጥር መፍጋቱ ለአለም ዘዋሪዎች በርግጥ አሳፋሪ-አናዳጅም ነበር።

«ይሕ (ሚስጥርን) ማዉጣቱ በአሜሪካ የዉጪ ጥቅም ላይ የተፈፀመ ጥቃት ብቻ አይደለም።በአለም አቀፉ ማሕበረሰብ፥ በወዳጅነትና ትብብር፥ በድርድርና ዉይይት፥ በአለም ደሕንነት እና ምጣኔ ሐብት ትብብር ላይም የተሰሰነዘረ ጥቃት ነዉ።»

የመረጃ ቴክኖሎጂ ጉድን በዘለቀ ጉድ አለምን ጉድ እንዳሰኘ-የአምደ መረቡ መስራች በአስገድዶ መድፈር ተከሰዉ ብሪታንያ ፍርድ ቤት ቀረቡ።እስራኤል በታሪኳ አጋጥሟት በማያዉቀዉ እሳት ሥትጋይ-አዉሮጳ ከሰላሳ አመት ወዲሕ በመታዉቀዉ በረዶ ስትቀዘቅዝ-ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሐገር ኮትዲቯር በምርጫ ዉጤት ዉዝግብ ትታበጥ ገባች።በትንሹ መቶ ሰባ ሰዉ ተገድሏል።

በምርጫዉ አሸንፌያለሁ የሚሉት ፕሬዝዳት ሎራ ግባግቦ ከተቃዋሚዎቻቸዉ ይልቅ ሠላም አስከባሪ ጦር ያሰፈረዉን የዉጪዎቹን ነበር-ያወገዙ-የረገሙት።

«ከኛ ፍላጎት ዉጪ እነዚሕን ወታደሮች እንዳሠፈራችሁ ለመቀጠል ከፈለጋችሁ፥ ከናንተ ጋር መስራት አንፈልግም።»

የካካዎዋ-እመቤት ምርጫ ደም ሲፈስባት የጋና ባሕር ጠረፍ ነዳጅ ይዛቅበት ያዘ።ታሕሳስ አስራ-አምስት።በሳምንቱ በጎርጎሮሱ ቀመር የሚያሰላዉ ዓለም ገናን አከበረ።አዜብና መሳይን አመሰግናለሁ፥ ነጋሽ መሐመድ ነኝ በዘመኑ ለምትቆጥሩ መልካም ገና መልካም አዲስ አመት።
ነጋሸ መሐመድ